Tuesday, November 27, 2018

መታነቂያ ገመድ የምገዛበት 60 ብር ብቻ..!

መታነቂያ ገመድ የምገዛበት 60 ብር ብቻ..!

" በቦሌም ብለህ በባሌ" እንደሚባል ተሳክቶላቸው ወደምዕራባውያኑ ምድር የመጡ ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል የቤተሰቦቻቸውን አልያም የጓደኞቻቸውን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ብርቱ ጥረት የሚያደርጉት በድሃ አገር ያለውን ችግር ስለሚረዱ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ነው። ስለዚህም  ሁለትና ሶስት ስራ መስራት ለብዙዎች አዲስ ነገር አይደለም።

ክርስትና በቅጡ የገባቸው ወገኖች ደግሞ  ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብና ምድራዊ ቁስ ከመስጠት የላቀ ምኞትና ጥማት አላቸው። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ውጭ አገር ለመኖር የመጣች የአንድ ክርስቲያን እናት ታሪክ ቀጥሎ ቀርቧል። እናኒ ሰሞኑን እንደውም  ለወገኖች ከሚላከው የቫይበር ላይ የምስክርነት ጽሁፍ ተነሳስታ ለዓመታት የሱስ እስረኛ ለሆነ፣ ህይወት አሰልቺ ለሆነበት የልጇ ባል ወንጌል መስክራ ወደ ቸርች አምጥታው  ኦክቶበር 21,2018 ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ አድርጎ ተቀብሏል። ለሦስት ትናንሽ ልጆቹም ተጸልዩዋል።  በብዙ የህይወት ትግል ውስጥ ያለፈ፣ ዓለም የተጫወተችበት ሰው ነው፤ በወንጌል አምኖ ንስሐ ከገባ በኋላ  ደስታችን ወደር አልነበረውም። ሃሌ ሉያ!!  እናኒ ለቀሩትም ቤተስቦቿ ይህን  የሕይወት ዘመን ትልቅ ውሳኔ እንዲወስኑ የተቻላትን ሁሉ በማድረግ ላይ ነች። ቤተሰቦቿን እንኳን በራሷ የጸሎት ዝርዝር ውስጥ ቀርቶ እኛን እንኳ ስንት ጊዜ አደራ ብላ አሳስባናለች። ይህም ሰው እንዲጸና በያላችሁበት ጸልዩለት!

  እናኒ የሕይወት ውሳኔ አድርጋ ክርስቶስን ልትከተል የቻለችበት አስደናቂ ታሪክም አላት እነሆ፡-....
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል የጀመረችው ህዳር 12,2000 ዓ.ም. ነው። ወደ ክርስቶስ እንድትመጣ ምክንያት የሆነው ነገር ደግሞ በተከታታይ ያጋጠማት ሐዘን ነበር። የልጅነት ባሏ በ1999 ዓ.ም. በመኪና አደጋ በድንገት ህይወቱን አጣ። ያን ጊዜ በድንጋጤ ወድቃ ግንባሯ አበጠ፤ ምልክቱ እስከዛሬ ድረስ ይታያል። በጣም ነበር የምንዋደደው፤የኑሯችን ብዙ ነገር እርሱ ላይ የተንጠለጠለ ስለ ነበር.. ጉዳቴን አከፋው ትላለች። የባለቤቴ ሃዘን ሳይለቀኝ ከ1ዓመት 4ወር በኋላ የምወዳት ሴት ልጄ ከቤሩት ወደ ቱርክ አገር እሻገራለሁ ብላ ከሌሎች ሰዎች ጋር በጀልባ በባህር ጉዞ ላይ እንዳሉ ሙሉ ለሙሉ ሰጥመው ውሃ በላቸው፤ የልጄ አስክሬንም ተፈልጎ ተላከልኝ፤ በጥቂት ጊዜ ልዩነት ውስጥ የምትወደውን ባል እና የደረሰች ሴት ልጇን ያጣች ምስኪን እናት ሆንኩኝ። ከዚያ በኋላ እዕምሮው እንደተነካበት ሰው ባዶ እግሬን ገዳም ለገዳም እየዞርኩ በባህላችንና- በዕምነታችን መሠረት የሙታን ተዝካር /ሙት ዓመት እያወጣሁ ገንዘቤን ቀስ በቀስ ጨረስኩ። በተለይ የልጄን 12 ካወጣሁ  በኋላ መሞት እንዳለብኝ ወሰንኩ! ..ሰይጣን አጠገቤ ቆሞ ብዙ ጊዜ የሚያዋራኝ ያህል ይሰማኝም ነበር ። አንቺ አሁን ሰው ነሽ?! እንዴት ቆመሽ ትሄጃለሽ? ሰው ምን ይልሻል? ...ለምን አትሞቺም?! ...እያለ ደጋግሞ ይወተውተኛል። ባሏንና ልጇን የምትወድ ብትሆን ኖሮ እንዴት እንደዚህ ቆማ ልትሄድ ቻለች? እያሉ ጎረቤቶች የሚያሙኝ ያስመስልብኝ ነበር። ጥቁር ልብሴም አልወለቀ! ሞራሌም ተሰባበረ፣ የልቤም ሆነ የኑሮዬ አቅም ወደቀ! ብቸኝነት ተሰማኝ፤ በተለይ ዓመታዊ በዐላት ሲመጡ ድሮ የለመድኩት በግና-ዶሮ ቀረ! ገና ያልጠነከሩ አንድ ወንድና ሌላ ሴት ልጄ ይከፉቸዋል ብዬ እጨነቃለሁ ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደራርበው ...መሞት እንዳለብኝ ወሰንኩ።

ባለቤቴ ሲሞት 300 ሺህ ብር ያህል ባንክ ውስጥ ተቀማጭ ነበረን፤ አሁን 60 ብር ብቻ ቀርቷል፤ እርሱ ደግሞ ገመድ መግዣ ይሆነኛል ብዬ ሌሊትና ቀን ከራሴ ጋር ሟውራት ጀምሬያለሁ። አንድ ቀን ልጄን ከቀበርኩ 12ኛው ቀን በኋላ በጠዋት 12 ሰዓት / 6AM/ ላይ ተነሳሁና ለልጆቼ እንጀራ ጋገርኩ፣ ወጥ ሰራሁ ፣ ልብሳቸውን አጣጠብኩና መታወቂያዬን፣ የእነርሱንም ፎቶ ይዤ ከእንቅልፍ ሳይነሱ የምታነቅበትን ገመድ ይዤ ከቤት ወጣሁ፤ መካኒሳ ሰፈር አካባቢ <አቦ ቤ/ክ> ጫካ ውስጥ ለመታነቅ ወስኛለሁ፤ አንድ ወፍራም የወይራ ግንድ ላይ ገመዱን ሸምቀቆ ሰርቼ፣ አስሬና አስተካክዬ ፡ ባሌና ልጄ ወደተቀበሩበት  ቦታ  መጣሁ (እዚያው አቅራቢያ ነበር)፤ ለሁለቱም ሟቾች ሻማ ለኩሼ ለደቂቃዎች አለቀስኩ ፤ "ልመጣላችሁ ነው!" እያልኩ ነበር የማለቅሰው፤ ውስጤ በኃይል ሲነድ ይሰማኛል፤ አስተኝቻቸው የመጣኋቸው ህጻናትም በአዕምሮዬ ይታወሱኛል፤ በሌላ አንጻር የሰይጣን ክስ   አለብኝ። እሞትና... መታወቂያዬንና የልጆቼን ፎቶ ያዩ እሬሳዬን አፈላልገው ለቤተሰቤ ይሰጡልኛል፤ በዚህ ላይ አባቴና ሌሎች ዘመዶቼ ለልጄ ለቅሶ ከጎንደር መጥተው አቅራቢያዬ ነው ያሉት፤ ለቀብሩም ሳይቸገሩ በዚሁ ይገላገላሉ!  እያልኩ ውሳኔዬን በአዕምሮዬ እያጠናከርኩ ነበር የማለቅሰው፤ ከዚያም ጨርሼ፡ ለመታነቅ ወዳዘጋጀሁት ስፍራ ስወርድ፤ መንገድ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ተገናኘሁ፤ የቀብር ጉድጓድ በመቆፈር የታወቀ "መ??ይ" የሚባል የአካባቢዬ ሰው ነው። አንቺ ሴትዮ...! በሚል  ከፍ ባለ ድምጽ ንግግሩን ጀመረ፤...እንዚህን ህጻናት ትተሽ ጫካ ለጫካ ለምን ድነው የምትዞሪው? ለልጆሽ መኖር አይሻልሽም? ወይም ብትሞቺ ይሻልሻል!! ቀጠለ ንግግሩን...ወይም መፍትሄ የምትፈልጊ ከሆነ ደግሞ አሩሲ... አንድ አዋቂ ቤት አለ እዚያ ልውሰድሽ/ጥንቆላ ቤት መሆኑ ነው/፤ እዚያ ለሦስት ወር ቀጥ ብለሽ ካገለገልሻቸው ልጅሽንና ባለቤትሽን እንድታናግሪ በሙታን ጠሪ መንፈስ ያገናኙሻል...ወዘተረፈ አለ። እኔ ደግሞ በልጅነታችን ጠንቋይ ቤት እንዳንሄድ! ከቤተሰባችን መሃል የሚሄድ ካለ ርጉም ይሁን  ተብሎ ከተወሰነበት ቤተሰብ ነው ያደኩት! መሄድ አልወድም! ...በብዙ ሌላ ቃላት አባበለኝ፤..እስቲ ተመልከች! በቀደም ዕለት 15 ጉድጓድ እንድቆፍር ትዕዛዝ የሰጠኝ የኡሩሲው ጠንቋይ... ፤ ገና አንድም ሰው ሳይሞት 15 የቀብር ጉድጓዶች አስቆፈርኩ በዚያን ቀን 5ቱ ሞቱና ተቀበሩ፤ በተቀሩትም ጥቂት ቀናት 10ሩም ጉድጓዶች ውስጥ ሰው ተቀብሮበታል። ይታይሽ! አለኝ፤ ...ሰውየው የከብት እርባታ ያለው፣ መኪና  ያለው ሃብታም ቢጤ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ያን ሁሉ ንብረት ያፈራው  በጠንቋዩ እየተመራ ፣ጉድጓድ እየቆፈረ፤ ለ40ና 80 ተዝካር ለሟች ቤተሰቦች በሬ እየሸጠላቸው ነው።... ይህን ሁሉ ዝባዝንኬ ሲያወራ ቆሜ ሰማሁት፤ ነገር ግን አሁን እርሱ እያለ ታንቄ መሞት የለብኝም! ትንሽ ደቂቃ ወደ አስፋልቱ ልውጣና ሰውየውን ላሳልፈው፤ ብዬ ከጫካው ውስጥ ወጥቼ ወደ አስፋልቱ መንገድ ሄድኩ።

   እዚያ እንደ ደረስኩ ወዲህና ወዲህ ስል የባስ ፌርማታ አጠገብ ደረስኩ፤ አጠገቡ የቆመ ስልክ እንጨት አለ፡፡ እንጨቱ ላይ ደግሞ የተለጠፈ አንድ ጽሁፍ አየሁ፤ "ፖስተር"- የኮንፈረንስ ማስታወቂያ ነው። <<መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ፤ ..እመን እንጂ አትፍራ!  ይላል >> እነዚህ መናፍቃን ናቸው! ብዬ ማሾፍ ጀመርኩ! ግን ጽሁፉ ውስጤ ቀረ! በአፌ" እነዚህ አታላዮች፣ ሌቦች... እላለሁ፤....ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ ፕሮቴስታንቶች ያለኝ ስዕል የተበላሸ ነው፡፡ "ጨለማ ክፍል ውስጥ ገንዘብ በኮርኒስ ውስጥ የሚበትኑ..፤ የድመት ስጋ የሚያቆርቡ፣ በሰው 50 ብር እየተቀበሉ አዳዲስ ሰው የሚሰብኩ!"....."ድሮ ድሮ እንደውም የእናቴ ታላቅ ወንድም አማኝ ነበረ፤ እኛን ለመጠየቅ እቤታችን ሲመጣ እንኳ በእጁ አንጠልጥሎ የሚመጣውን ፍራፍሬ... ዘፍዝፈን፣ በብዙ ውሃ አጥበን ነበር የምንበላው ጴንጤ ስለሆነ ተጸይፈነው..። ስልክ እንጨቱን ይዤ እንዲህ አልኩ። <<እውነተኛው የድንግል ማርያም ልጅ ከሆንክ፣ አስቲ  ካዘጋጀሁት ከዚያ ገመድ አስጥለህ ለልጆቼ አኑረኝ! በዚህ እፈትንሃለሁ! አልኩት። ድንገት ሳላውቅ ፖስተሩ የተለጠፈበትን ስልክ እንጨት ተጠምጥሜ ይዣለሁ፤ አውሎ ነፋስ ከፊት ለፊቴ በኩል ሲነሳ አየዋለሁ..ብዙ ግሳንግስ ሰብስቦ ወደ እኔ ተጠጋ፤ አንዲት ድንቢጥ ወፍ ውስጡ ትታየኛለች፤ አይኔን ለታጠፋው ይመስላል እና እጄን እያወራጨሁ ተከላከልኳት፤ መሬት ላይ ወደቅኩ! ከደቂቃዎች በኋላ ስነሳ፡ በርካታ ሰዎች ከበውኝ ከንፈራቸውን ይመጣሉ። የተለኮሰ ክብሪት አጠገቤ አለ። የሚጥል በሽታ ነው ብለው አስበው ይህን እንዳደረጉ ገባኝ! የእኔን ትግል ማን አየ?!

ተነሳሁና ከበባውን ሰንጥቄ በመሄድ ፌርማታው ጋር የተቀመጠ አንድ ተለቅ ያለ  ሰው ጋር ተጠጋሁ፤ ይህ ማስታወቂያ ያለበትን ቤ/ክ ጠቁመኝ! አልኩት። ምነው አናቴ? አለኝ! መናፍቃን እኮ ናቸው፤ እዚያማ በፍጹም እንዳትሄጂ ! ይልቅስ  እዚህ ጋር ኪዳነብረት አለልሽ! እዚያ ጋርም ገብርኤል ቤ/ክ አለልሽ አለኝ በእጁ ምልክት እያሳየ! አአይ ለቅሶ ልደርስ ፈልጌ ነው ፤ ቦታው ደግሞ ቸርቹ ፊት ለፊት ነው፡ ስለው፤ ሰሞኑን አንድ ለቅሶ የነበረባት፥ ሴት ልጇ አረብ አገር የሞተችባት እና ባሏንም በሞት ያጣች ..ብሎ የእኔን ታሪክ ለራሴው ሳይጨርስ ተወው! እርሷን አውቃታለሁ፤ እርስዋ ሳትሆን ሌላ ሰው ነች! አልኩት። አደራ እንዳትጠጊያቸው! ብሎ ቦታውን በርቀት ጠቆመኝ። ወደዚያ አመራሁ FBI ቸርች ገና አዳራሹ እየተሰራ ዕቃዎች ብትንትን ብለው ይታያሉ፤ ተጠጋሁ ግን  በታች በኩል ነበር የሄድኩት፤ ዘበኛውን በአጥር ላይ አናገርኩት! ምን ፈልገሽ ነው? አለ ዘበኛው። " ወደ ወንዝ ልትገባ ያለችን ነፍስ የሚያድን! አልኩት" በደንብ ስላልገባውና እንደ ጤነኛም ስላልቆጠረኝ በላይኛው በር ዞሬ እንድመጣ ጠቆመኝ። ዞሬ መጣሁ፤ በዋናው በር ገብቼ የቅድሙን ቃል ደገምኩለት " ወደ ወንዝ ልትገባ ያለችን ነፍስ የሚታደግ ሰው ፈልጌ ነው! የመጣሁት፡፡" ወዲያው አንድ ወንጌላዊ ተጠራ፤ ወ/ዊ መንግስቴ ይባላል፤ አናገረኝና ይዞኝ ወደ ጸሎት ቤት አመራን ፤ እርሱ ከፊት ለፊት እየመራኝ እኔ እየተከተልኩት ነበር። ድንገት መሃል መንገድ ላይ ግን እኔ ቆምኩ በእውነት መንቀሳቀስ አልቻልኩም! የተከተልኩት መስሎት ነበር ፤ ሲያጣኝ ተመልሶ መጣ፤ ቆሜያለሁ። ምነው አለ? አልቻልኩም አልኩት! ገባውና መጸለይ ጀመረ፤ ሌሎች ሶስት አገልጋዮች መጡ.. እስኪያልባቸው ድረስ ጸለዩ ገሰጹ። ያ ቅድም ያየሁት አውሎ ነፋስ ያቺን ድንቢጥ ይዞ ዳግመኛ ሲመጣ ይታየኛል፤ እንደ ቅድሙ ግን አጠገቤ ሳይደርስ ተበትኖ ጠፋ! እግሬንም ለቀቀኝ ጸሎት ቤት ገብቼ ወንጌልን መሰከሩልኝ ክርስቶስን አዳኜና ጌታዬ አድርጌ ተቀበልኩ።

ወደ-ጫካው ተመልሰን ሄደን ገመዱን ፈታነው ፎቶዎቹንና ሌሎች እቃዎችን ይዘን መጣን። ከዚህ በፊት እዚያ ቦታ ቢያንስ አምስት ሰው ታንቆ እንደሞተ እስታውሳለሁ። በተለይ እኔ ገመድ ያንጠለጠልኩበት የወይራ ዛፍ ደግሞ አንድ ጎረቤቴ ታንቃ የሞተችበት ዛፍ ነው፤ ባሏንና ሁለት ልጆቿን በከባድ የመኪና አደጋ ካጣችበት ጊዜ ጀምሮ ባጋጠማት ሃዘን ምክንያት ነው፡ ይህን መጥፎ ውሳኔ የወሰነችው በህይወት የለችም። እኔን ግን ዛሬ  ኢየሱስ  ከሞት አድኖኛል። የሞቴን ገመድ በጥሶታል!!  ለ3 ቀናት ተመላልሼ የዳንኩበት ቤ/ክ ውስጥ የድነት ትምህርት ተማርኩ። በኋላም ጌታን መቀበሌን የሰሙ ክርስቲያን ጎረቤቶቼ ቀረቡኝ  አቅራቢያዬ ወደሚገኝ ቸርች አስፈቅጄ አብሬያቸው እንድመጣ ነገሩኝ፤ እኔም ለመጋቢዎች ነገርኳቸው ... የቀረኝን የድነት ትምህርት በሙሉ ወንጌል ቤ/ክ ውስጥ ተምሬ የውሐ ጥምቀት ወሰድኩ። የጥምቀት ስነስርዓቴ የሰርግ ያህል የደመቀ ነበር የእኔ ብትሉ የህዝቡ ደስታ ወደር አልነበረውም። ሃሌ ሉያ!!!
   እናኒ ከዚያም በኋላ መከራው በቅቷል አላለችኝም፤ ያው አንዳንድ ነገር አይጠፋም ፤ ለምሳሌ ድሮ ያውቋት የነበሩ ጎረቤቶች ከቸርች ስትመለስ ቆሻሻ ውሃ እየደፉባት  ቢያንስ 3ት ነጠላ ቀይሬያለሁ አለች! ልጆቿን እያሳደሙባትም የተወሰነ ጊዜ መከራ ቀምሳለች፤ ...እየመጡ እናታችን አዋረድሽን፣ አሸማቀቅሽን ይሏታል፤  ይህ አይነት መከራ ግን ስለ ስሙ ነው፤ ለኛ ክብር ነው! ጌታም በብዙ ሁኔታ አጽናናኝ አለች፤ በቀበሌያችን ውስጥ ከሚገኝ <ራሴድ >በሚባል ማህበር ውስጥ ታቅፌ፣ ስልጠና ወስጄ በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ውስጥ ለመሰማራት 500 ብር ብድር ተሰጠኝ ፤ እየነገድኩ በወር 50 ብር አጠራቅም ነበር። ልጆቼን በግል ከፍዬ እስተማርኩ ዛሬ ሁለቱም ኮሌጅ ተመርቀዋል፤ ወንዱ ንግድ ላይ ተሰማርቷል፣ ሴቷ የማስተርስ ዲግሪ ቀጥላ እየተማረች ትገኛለች፤ እናኒ ወደ አሜሪካ ስትመጣ ከዚያች 500 ብር ተነስታ በአካውንቷ ውስጥ 60ሺህ ብር ተቀማጭ ነበራት፤ ዛሬ አብራን ጌታን እያከበረች ትገኛለች፤ መከራዋን ሁሉ ታሪክ አድርጎላታል፡፡

እናኒ ጌታ አብዝቶ ይባርክሽ! ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን! እስከ ፍጻሜ ድረስም በቤቱ አጽንቶ ያቁምሽ! አሜን!

ወገኖች አሁንስ ቢሆን በየአካባቢያችን ስንት እናቶችና እህቶቻችን ገመድ ይዘው ለመሰቀል እየተንከራተቱ ይሆን?<< ወደ ወንዝ እየገባች ያለችን ነፍስ የሚታደግ ሰው አለ?>> ማንን ልላክ? ማንስ ይሄድልኛል? ይላል ዛሬም፤ ጌታ ሆይ እኔ አለሁልህ! እኔን ላከኝ! እንበል፤ ሌላ ታሪክ ይቀጥላል...

<<LET US BE WITNESSES FOR CHRIST>>

ከ 32 ዓመታት በኋላ ይፀፅትሃል??

ከ 32 ዓመታት በኋላ ይፀፅትሃል??

በቅርብ ጊዜ የአንድ ወዳጃችን 20ኛ  የሚንስትሪ
ዓመቱን ክብረ በዓል አስመልክቶ በተዘጋጀ እራት ላይ እንድንገኝ ተጠርተን ስለነበር ወደዚያው አቀናን፤ እኔም አንዱ ተካፋይ ነበርኩ። ይህ ሰው በአብዛ ኛው ዓለም ላይ ወንጌልን አስተምሯል፤ ምናልባት ከ195 በላይ የዓለም ከተሞች ላይ ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ 60 ያህል ከተሞች ውስጥ  ተዘዋውሮ ወንጌልን ስብኳል፤ በ30 ዓመት የአገልግሎት ጊዜው በርካታ መንፈሳዊ ስራዎችን እንደሰራ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩትን በየሳምንቱ በሚድያ በኩል እንዳገኛቸው፤ ሺዎች በእርሱ አገልግሎት ወደ እግዚእብሔር መንግስት እንደተጨመሩ ምስክርነት ቀረበ! አቤት ደስ ሲል! የሆነ ሆኖ ይኽው አይደል የሚፈለገው? ቀሪ ዘመኑንም ሲያገለግል ይለቅ ብዬ በውስጤ መረቅኩት። በዚህ ሁሉ እየተደነቅን..  ይህን ሰው ግን ማን ወደ ክርስቶስ አመጣው? እንዴትስ ጌታን አገኘ? የሚል ጥያቄ ሰው ውስጥ ያለ ይመስለኛል፤ ዝግጅቱ ከመጠናቀቁ በፊት  ለ7 ደቂቃ ንግግር እንዲያደርግ  የፕሮግራሙን  መርሃ ግብር በሚመራው ሰው ተጋብዞ ወደ መድረክ መጣ፤.. ..ከአገልግሎቱ  ጋር የተያያዘ ጥቂት ነገር ተናገረ፤ በህይወቱ ውስጥ  ጠቃሚ ሚና  የነበራቸውን ሰዎችም እልረሳቸውም ፤ ከድሮ እስከ አሁን አመሰገናቸው!...። በተለይ የእኔን ቀልብ የሳበው ደግሞ የአንድ ሰው ሁኔታ ነበር፤ ያ ሰው የዛሬ 32 ዓመት ለዚህ አንጋፋ ወንጌላዊ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌል የመሰከረ ፣ እምብዛም የማይታወቅ ሰው ነበር። በእርግጥ ወ/ዊ ያሬድ ጌታን እንደ ግል አዳኝ አድርጎ ወስኖ የተቀበለው ጅቡቲ ውስጥ ነው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ጥቂት ስለህይወቱ እንዲነግረኝ  ጠይቄው ነበር፤ ተከታዩን ምላሽ ሰጥቶኛል እነሆ:-

1.ጌታን ሳታውቅ በፊት ምን አይነት ሰው ነበርክ?
ወ/ዊ ያሬድ:-  በልጅነት ማለት እስከ 13 ዓመት
አጥባቂ የሃይማኖት ሰው ነበርኩ፤ በጊዜው ከአቡነ ኤልሳዕ (ጳጳስ የነበሩ) እጅም ድቁንናን ተቀብያለሁ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ በኪነ ጥበብ ውስጥ ማዘጋጃ ቤትና ብሔራዊ ቲያትር ውስጥ ትወናና የተወሰነ ግጥም ድርሰት ላይም ተሳትፌያለሁ። 

2.ጌታን የመሰከርልህ ሰው ምን ብሎ መሰከረልህ? ከዚያስ በኋላስ ምን ተፈጠረ?
ወ/ዊ ያሬድ:-በስደት ውስጥ ሆኜ በጣም ተስፋ ከመቁረጤ የተነሳ ራሴን ማጥፋት አስብ ነበር ፤
በዚህ መሀል በምኖርበት በር ላይ ዘውትር የሚያልፍ አንድ በህይወቱ ደስታ የሚነበብበት አማኝ ዘውትር ሳየው እቀናበት ስለነበረ እባክህን የዚህን ደስታ ሚስጥሩን ትነግረኝ? ብዬ ጠየኩት፤ የሰላሙንና የደስታውን ምስጢር ነገረኝ፤... ከዚያማ ያ ደስታ እኔም ውስጥ ገባ፤ "ሚስጥሩ" እኔ የጎደለኝ "ኢየሱስ ክርስቶስ" ነበረ። ኢየሱስ ክርስቶስን የህይወቴ ጌታ አደረኩት!

3.ህይወትህን የለወጡ ዋና ዋና ነገሮችን እስቲ ንገረኝ ?
ወ/ዊ ያሬድ:-በተለይ በቅዱሳን ህብረት ውስጥ ያገኘሁት ጥቅም እጅግ ነው፤ ሌላው የእግዚአብሔርን ቃል (መጽሐፍ ቅዱስን) አጠና ነበር፣..ለጸሎትም ጊዜ ነበረኝ፤ እነዚህ ነገሮች ህይወቴ የበለጠ ከጌታ ጋር እንዲጣበቅ እረድተውኛል።

4. በዳንክ ሰሞን የውስጥና የውጪ ተግዳሮቶችህ ምን ነበሩ?
ወ/ዊ ያሬድ:-እንዳልኩህ ስደት አገር ነው እኖር የነበረው፤ የአገሩ ሕዝብ ባብዛኛው እስልምናን የሚከተል በመሆኑ የማምለክ ነጻነት እምብዛም አልነበረም! በዚህ ምክንያት እስር ቤት ታስሬም አውቃለሁ...በስደት ውስጥ ነገ ምን ይፈጠር ይሆን ? የሚሉ ስጋቶች አሉ፤ እኔም ውስጥ በተወሰነ መልክ  የነበረ  ነው።

5. ከ32 ዓመት በፊት ወስነህ ጌታን በመከተልህ ዛሬ ላይ ሆነህ ይቆጭሃል? ወይስ..?
ወ/ዊ ያሬድ፡-የግርምት ሳቅ...! እንዴት ሆኖ? ዘላለሜን ስለዚያች ዕለት ስባርከው እኖራለሁ እንጂ! ሃሌ ሉያ!

6.በመጨረሻ ይህን መልዕክት ለሚያነቡ ሁሉ ምን ልታስተላልፍ ትወዳለህ?
ወ/ዊ ያሬድ፡-ሰው የሆነ ሁሉ ይህችን ምድር ነክቶ ሲያልፍ አንድ ትልቅ ውሳኔ ወስኖ እንዲያልፍ እፈልጋለሁ፤ ይህም ኢየሱስ ክርስቶስን የህይወቱ ጌታና አዳኝ እንዲያደርግ! እና በቀሪ ዘመኑ ሁሉ ክርስቶስን መስሎ እንዲኖር እመክራለሁ። ብልጫ ያለው... <<የሰው ትልቁ ውሳኔ ይህ ነው።>>
አመስግናለሁ! ጌታ ይባርክህ!
እባክዎ ወንጌልን ላልሰሙ ሰዎች ይመስክሩ! የሌሎች ወንጌል አርበኞች ታሪክ ይቀጥላል...

<<LET US BE WITNESSES FOR CHRIST>>

ኢየሱስ ..ተገለጠልኝ!

ኢየሱስ ..ተገለጠልኝ!
/የኢራንአዊው አህመድ ታሪክ/

ዕለቱ ማክሰኞ ኦክቶበር 24, 2018 ከሰዓት በኋላ፤ አንድ ቤተሰብ ለመጎብኘት በቨርጂንያ ተገኝተን ነበር፤ ደስ ብሎን ተጫወትን ፣ጸለይን፣ ቃል ተከፋፈልን...ከተጫወትናቸው ቁም ነገሮች መካከል አንዱ  ሰሞኑን እግዚአብሔር እየሰራቸው ያሉ አስገራሚ ነገሮችን ነበር ። ለምሳሌ ባለፈው ሳምንት ፡ሐሙስ ዕለት አንድ ሰው ሲጎድል ፣ሙሉ ቤተሰብ ሴትና ወንድ አያቶችን ጨምሮ አራት ያህል ስዎች በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው ንስሐ የገቡበት ታሪክ አስገርሞናል! ነገሩ  እንዲህ ነው በዚያ ቤተሰብ ውስጥ የ2ኛ ዓመት የኮሌጅ ተማሪ የሆነች ልጃቸው መንፈስ እያሰቃያት መታመም ከጀመረች ሰነባብታለች ፤ አንዳንድ ጊዜ እናቷን እንኳ እንደ "አውሬ" እስከ ማየት ጭምር ያደረሳት ነው ...ያም ነገር ቤተሰቡን ማወክ ጀመረ፤ መፍትሔ ጠፋ! ድንገት ከጎረቤት ያለች አንድ  ክርስቲያን እህት በነገሩ ላይ እንዲጸለይ ሃሳብ ታቀርብና ይስማማሉ፤ እርሷም ከቤተክርስቲያን ሁለት አገልጋዮችን ወስዳ ጉዞ ተጀመረ፤ እቤት እንደደረሱ ታማሚዋ ወጣት ከቤት ወጥታ ሄዳለች ፤ ቢሆንም ለተቀረው ቤተሰብ ጸሎት መጸለይ ተጀመረ። ነገሩ በዚህ ሁኔታ ቀጥሎ ሳለ አንደኛው ወንድም ድንገት ሴት አያታቸው ላይ እጅ ጭኖ መጸለይ ይሰማውና.. ሲጸልይ ከእርሳቸው ሳይሆን ከልጃቸው ላይ፡ ማለትም ከወጣቷ እናት ላይ መንፈስ ጮሆ ራሱን ገልጦ ይወጣል! በነገሩ ቤተሰቡ ድንጋጤ ውስጥ ገባ፤  ግራ መጋባትም፣ መገረምም ይዟቸው ባሉበት ሰዓት አገልጋይ ወንድማችን ጌታን እንዲቀበሉ ቆሞ በብዙ ቃል ከተናገራቸው በኋላ የነበሩት ሰዎች ሁሉ ክርስቶስን ጌታና አዳኝ አድርገው ተቀብለዋል። ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን!!

ይህንንና የመሳሰሉትን እያወራን ሳለ ጋባዥ ወንድማችን በዚህ 15 ቀናት ውስጥ በመስሪያ ቤቱ የገጠመውን ታላቅ ነገር አጫወተን። ነገሩ እንደዚህ ነው የስራ ባልደረባው የ70 ዓመት ኢራናዊ ሰው ናቸው፤ ክርስቲያን ነህ አይደል? ብለው ጠየቁኝ አዎን! አልኳቸው ፤ ቀጥለውም ኢየሱስን አውቀዋለሁ! አሉ፤ እርሱም <ኢሳ> ማለትዎት ነው? አይደለም! አሉ ሰውየው ፣ "ኢየሱስን" ነው፤ በተደጋጋሚ በህልሜ መጥቶ አናግሮኛል። 12ቱ ሐዋርያትን፣ሙሴና አብርሃምን እያሳየኝ የአንተ ዕድል ፈንታ እነዚህ መሐል ነው አለኝ። በተለይ ጴጥሮስ የሚለው ስም ሲጠራ ትዝ ይለኛል ። እሺ አሁን ለማንኛውም ኢየሱስን ይቀበላሉ ? ሲል ጠየቀ፤ "I already recieved Jesus Christ as a personal Savior" አሉ ! እንዴት ? ብሎ አለ፤  ይህን እርሱ ራሱ ኢየሱስ ነግሮኝ ነው ያደረኩት አሉ። ለማንኛውም አሁን ከእኔ ጋር ንስሐ ለመግባት ፍቃደኛ ነዎት? አላቸው። አዎን! አሉ "ሙስሊሙ" ኢራናዊው አህመድ... እየመራኋቸው ንስሐ ገቡ ፤ጌታንም በእኔ እጅ እንደ ገና ተቀበሉ አለ። አሁን ተከታታይ ትምህርት ልንጀምርላቸው ቀጠሮ ይዘናል።  እንደዚህ ያሉትን ሰዎች ማስተማርማ ዕድል ነው። ኢየሱስ በታላቅ ስራ ላይ ነው ! ራሱ ተገልጦ ሰዎችን እያዳነ ነው። እኛም የታዘዝነውን እንፈጽም ዘንድ እንበርታ!

"ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ።" /ማር.16:15 /ወንጌልን መመስከር ከዕድለኝነትም በላይ ነው!!!
(የአሌክሳንደሪያው ኤልያስ፣መጋቢ ኤልያስ፣ መሲና ትንሱ የእግዚአብሔር ስራ ይብዛላችሁ !)

<<LET US BE WITNESSES FOR CHRIST>>

ወንጌል ያልደረሰው የኢትዮጵያ ክልል!

ወንጌል ያልደረሰው የኢትዮጵያ ክልል!
♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦♦
ከአርባ ጊዜ በላይ ስሟ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰች፣ የሦስት ሺህ ዓመት ታሪክ እንዳላት የሚወራላት አገራችን ኢትዮጵያ ፤ ወንጌልን በተመለከት ምን ደረጃ ላይ እንዳለች የሚከተለው ዘገባ ያሳያል:-
የውጭ ዜግነት ያላቸው(አሜሪካኖች፣ አረቦች፣ ሱዳኖች፣የመኖች፣ አርመኖች፣ ብሪቲሾች፣ ቻይናውያን፣ ፍሬንቾች፣ ግሪኮች፣ ጣልያኖች፣ አይሁዶች፣ ፓኪስታናውያን፣ ራሺያውያን የሱማሌ) ነዋሪዎችን ጨምሮ፡-      
    ♥113 ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ.
    ጠቅላላ የሕዝብ ብዛቷ በአሁን ሰዓት 108 ሚሊዮን ይጠጋል ፤ 
    ♥ካቶሊክ፣ኦርቶዶክስ እና ወንጌላውያንን ጨምሮ 59.7% ክርስትና ሃይማኖት አለ፤
    ♥የወንጌል አማኞች ቁጥር 17.03% ደርሷል
    ♥22 ሚሊዮን 33ሺህ ህዝብ ገደማ በወንጌል ያልተደረሰ ህዝብ አላት።/ 20.5% ማለት ነው/
     ♥ወደ 35 ያህል ብሔር ብሔረሰቦች የወንጌል መልዕክት አልደረሳቸውም፤ ይህም በመቶኛ ሲሰላ 31.0 % ይሆናል። ከእነዚህ መካከል በተለይ የእኛ ጸሎትና እገዛ የሚያስፈልጋቸውን ቀጥዬ እዘረዝራለሁ፤ አማኞች ሁላችን በየጸሎት ህብረቱ ላይ፣ በቤተሰብ ጸሎት ጊዜ፣ በቤት ህብረቶች ላይ በግልና በጉባኤ እንድትጸልዩላቸው በጌታ ፍቅር አሳስባለሁ!!!
1.የአፋር ህዝብ = 1,914,000 ብዛት
2.ለአርጎባ ህዝብ= 211,000     >>
3.ለቤንሻንጉል ህዝብ= 313,000
4.ለዳሳናች ብሔር= 72,000
5.ለአላባ ብሔረሰብ = 349,000
6.ለሐመር ህዝብ = 110,000
7.ለአደሬዎች = 48,000
8.ለቀበና ብሔረሰብ = 79,000
9.ለመስቃን ብሔረሰብ = 217,000
10.ለሐረርጌ ኦሮሞ ህዝብ= 5,938,000
11.ለጅማ ህዝብ = 3,350,000
12.ለከረዩ ሕዝብ = 315,000
13.ለወሎ ህዝብ = 345,000
14.ለየጁ ብሔረሰብ = 108,000
15.ለስልጤ ህዝብ = 1,402,000
16.ለሱማሌ ህዝብ= 6,877,000
17.ለሱርማ ብሔረሰብ= 42,000
18.ለጸማይ ማህበረሰብ= 30,000
19.ለቱርካናዎች = 42,000
20.ለዎላን ብሔረሰብ= 130,000 ያህል ናቸው።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት ወንጌላውያን አማኞች በኢትዮጵያ ውስጥ በየ ዓመቱ የ4.3% ዕድገት ቢያሳዩም ወንጌል በቋንቋው ካልደረሰው በሚሊዮን የሚቆጠር ህዝብ ጋር ሲነጻጸር ገና ብዙ እንደሚቀረን ያሳያል፤

  ፨ ሁላችን የክርስቶስ ኢየሱስ ምስክሮች እንሁን! በጸሎት፣ በገንዘብና በተለያየ መልክ ወንጌል እንዲሮጥ የበኩላችንን እናድርግ! በእውነት ዋጋችን በሰማይ ታላቅ ይሆናል! ይቀጥላል.....
(ምንጭ:- joshua project .net)

<< LET US BE WITNESSES FOR CHRIST! >>

Sunday, November 18, 2018

ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ- ልጅ ነውን?


ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ- ልጅ ነውን?



ክርስትና እምነት ዋነኛ መሰረቱ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ማመንና  ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ማንነት ጠንቅቆ ማወቅ ነው፡: ስለክርስትና እምነት የሚነሱ የስህተት ትምህርቶች በአብዛኛው የሚመነጩት፣ ክርስቶስ ማንንት ላይ ተመርኩዘው በመሆኑ ስለክርስቶስ ማወቃችን የምንሰማቸው መልእክቶች ሁሉ እንዳያስቱን የበለጠ እንድንጠነቀቅ ያደርገናል፡፡ አንዳንድ የስህተት እምነቶች የተመሠረቱት ‹‹ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ አይደለም ፣አምላክ አይደለም ፣ ፍጡር ነው›› በሚሉ አደገኛ የሆኑ አስተምህሮ ላይ ተመrekuzew ሲሆን፤ ሌሎችም በኢየሱስ  አምላክነትና ጌትነት ቢያምኑም፣ ቅሉ ‹‹ክርስቶስ አልሞተም›› ወይም ደግሞ ‹‹አልተነሳም›› በሚል ኑፋቄ ይደመድማሉ፡፡ በሌሎች የክርስትና ጉዳዮች ላይ ተመርኩዞ የተፈለሰፈ ስህተት የለም ማለት አይደለም፡፡ ይሁንና አንዳንዱ ስህተት ድነትን የማይከለክል ሊሆን ይችላል፡፡ የክርስቶስ ማንነት ላይ ተመርኩዞ የሚነሳ ስህተት ግን ድነትን እንኳ እስከማሳጣት ሊያደርስ ይችላልና መጠንቀቁ ጥሩ ነው፡፡ ሐሳውያኑ ስለ ክርስቶስ ማንነት ወይም ለድነታችን ስለ ተፈጸመው ነገር ጥቂት እውነታ ያለው ነገር ቢኖራቸውም የክርስትና ዋና ስለሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ግን  መሠረታዊ ነገር አጉድለው ነው የሚያስተምሩት፡፡  ብዙ ስህተቶች ከክርስትና ውጪ ሆነው፣ በስም ተሰይመው ስለሚኖሩ እነርሱን ለይቶ ማወቅ ብዙ ጊዜ አያስቸግር ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የዮሕዋ ምስክሮች፣ ሞርሞኖች…ወዘተ ግልጽ ስህተት አንግበው የሚጓዙ እምነቶች ናቸው፡፡ የራሳችን በሆኑና በማንጠራጠራቸው ወንድሞች የሚነሱ ስህተቶች ግን ይልቁን አደገኛ ናቸው፡፡ እንደኛው የሚዘምሩ ፣እንደኛው ልሳን የሚናገሩ፣ ተመሳሳይ መጽሐፍ ቅዱስ እየተጠቀሙ ግን በተለየ አተረጓጎም፣ በተለየ አስተምህሮ የተገለጡ ናቸው፡፡ ስለዚህ ነው እንግዲህ ነገሩን የበለጠ አሳሳቢ የሚያደርገው፡፡  



  በዚህ ርዕስ ላይ እንድጽፍ ምክንያት የሆነኝ ሰሞኑን በአንድ ማኅበራዊ ገፅ (ሶሻል ሚዲያ) ላይ የተመለከትኩት መልዕክት  ነው፡፡   በማህበራዊው መገናኛ ፊት ለፊት ገጽ ላይ ‘’No more  Begotten Son” በሚል ርእስ ጽሐፍ ተጽፏል፡፡ ወደ አማርኛ ስንመልሰው ‹‹አንድያ ልጅ የሚባል ነገር ከእንግዲህ የለም›› የሚለውን አቻ ትርገም ይይዛል፡፡   ለመሆኑ ወዴት ወዴት እየሔድን ነው? ሀይ ባይ የለም? ይህንን መልእክት አንብቤ ዝም ከምል ወይም ሌላ ሰው ምልሽ እንዲሰጥ ከምጠብቅ እኔም ሐላፊነቱ ስለተሰማኝ የድርሻየን ምላሽ ለመጻፍ ተገደድኩኝ: ይህ አጭር ጽሑፍ፣ በተመሳሳይ የስህተት መንገድ  ላይ ያለውን ብዥታ ለማጥራት፣ በጣም ርቀው የሔዱትንና ርቀው ለመሄድ ዝግጅት ላይ ያሉትን ለመመለስ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡

ኢየሱስ የምድር አገልግሎቱን ጨርሶ ወደመስቀል ሞት ከመሔዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ ሲጸልይ ‹‹እውነተኛ አምላክ የሆንክ አንተን የላከኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት፡፡›› (ዮሐ.17፡ 3) ነበር ያለው፡፡ ስለዚህም ስለክርስቶስ ማንነት ማወቅ እና ከስህተት መጠበቅ የእውቀት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ለዘላለም ሕይወት መብቃት ወይም መጉደል ያለበት ወሳኝ አቋም ነው፡፡

ስለ ክርስቶስ ማንነት ማወቅ ወይም ራሱን ክርስቶስን ማወቅ ከዕውቀት የዘለለ ትርጉም አለውየዘላለም ሕይወትም ጭምር ነው፡፡ ለዚህም ነው ጌታ  ደቀ መዛሙርቱን ‹‹የሰውን ልጅ ማን ይሉታል?›› ብሎ  ጥያቄ የጠየቃቸው፡፡ በጊዜው የነበሩት የሕብረተሰብ ክፍሎች   ስለክርስቶስ የነበራቸው መረዳት ሙሉ ስላልነበረ፣ ደቀመዛሙርቱም  ‹‹ኤርሜያስ ፣ኤልያስ፣ ከነብያት አንዱ›› የሚል መልስ ነበር የሰጡት ፡፡ ጌታም ደቀመዛሙርቱን ‹‹እናንተስ እኔ ማን እንደሆንኩ ትላላችሁ?›› ብሎ ጠየቃቸው፡፡ ጴጥሮስ ሲመልስ ‹‹ አንተ ክርስቶስ የሕያው የእግዚአብሔር ልጅ ነህ›› አለ፡፡››  ክርስቶስ የሚለው የግሪኩ ስሙ ትርጉም  በዕብራይስጥ መሲህ ማለት ሲሆን ትርጉሙም   ‹‹የተቀባ›› የሚለውን በእግዚአብሔር የተመረጠና የተላከ መሆኑን ያመለክታል ፡፡ ኢየሱስ በጴጥሮስ መልስ ከመደነቅ ይልቅ ይህንን ታላቅ እውነት የገለጠለት ላይ ነው ያተኮረው፡፡ ‹‹አባቴ እንጂ ስጋና ደም አልገለጠልህምና ብጹህ ነህ››  አለው፡፡ (ማቴ.16 ቁ.24)፡፡ ይህ ማለት የክርስቶስን ማንነት ሰው በራሱ ዕውቀት ሊደርስበት አንደማይችል ያሳያል፡፡ እግዚአብሔር ግን ስለ ራሱ ልጅ መሰከረ፡፡ እግዚአብሔር አብ እንዲህ ያለ ተመሳሳይ ምስክርነቶች በተለያየ ቦታ ስለ ልጁ መስክሯል፡፡ ለምሳሌ መጥምቁ ዮሐንስ በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ ኢየሱስን ባጠመቀው ወቅት ‹‹የምወደው ልጄ ይህ ነው›› ብሎ መስክሯል፡፡ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ በመሆነ መልኩ፣  ከሦስት ዓመታት በኋላም በደብረዘይት ተራራ ከገናናው ክብሩ ድምጽ ወጥቶ ‹‹የምወደው ልጄ እርሱ ነውና እርሱን ስሙት›› እንዳለ ሐዋርያቱ መስክረዋል፡፡(ማቴ.17፡1-8 እና 2ጴጥ.1፡17)፡፡

 ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ /Begotten-Son/

ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ነው ስንል ምን ማለታችን ነው? ‹አንድያ-ልጅ› የሚለው ቃል በእንግሊዝኛ ‹‹Only-Begotten›› በግሪኩ ደግሞ ‹‹monogeneis›› የሚባል ትርጉም አለው፡፡ ቃሉ ግን  ዳግመኛ ለተወለዱ አማኞች ሁሉ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው ተብሎ የተገለጸው ዓይነት ተመሳሳይ ትርጉም የያዘ ሳይሆን  የእግዚአብሔር የባህሪ ልጁ አንድ ብቻ በመሆኑ  የተለየ ማንነት ላለው የሚሰየም የተለየ መግለጫ ነው፡፡ ለምሳሌ ዮሐ.1፡14 ፣ 4፡18 ፣ 3፡16 እና 18 it would litrally mean the <only generated one.> This is the key Expression for the doctrine of <the eternal generation of the Son,> ማለትም እርሱ ክርስቶስ ሰው ሆኖ ሳይወለድ በፊትም የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደነበረ የሚያሳይ ትርጉም ነው፡፡ ቃሉ በፍጹም ሰው ሆኖ ሲወለድ ወይም ሲጠመቅ ስላገኘው የእግዚአብሔር ልጅነት የሚያሳይ አይደለም( አንዳንዶች ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው በተጠመቀ ጊዜ ነው ስለሚሉ ነው፡፡) ይልቁንም ክርስቶስ ከዘላለም ዘመናትም በፊትም የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ እንደሆነ ያሳያል፡፡ <beget> የሚለው ቃል <make> እና <create> ከሚባሉ ቃላት ትርጉሞች በተለየ የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለቱ ቃላት ባህርይን ስለማካፈል የሚጠቀሱ አይደሉም you can only beget a child has the same nature as you have-a son or a daughter .There is nothing else you can beget (unless you were speaking very figuratively). ወንድ ልጅ ወይም ሴት ልጅ ከወላጆቻቸው ስለሚወርሱት ዘረ-መል‹Gene› ስናስብ አጠቃላ ሂደቱን <create> or <make> የሚል ቃል ልንጠቀም እንችላለን፡፡ But when you use <beget> it only means you produce a child that has your nature. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው ስንል ሙሉ ለሙሉ የመለኮትን ባህሪ ከአባቱ ተካፍሏል! ስለሆነም ኢየሱስ የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ስለሆነ መለኮት ነው፡፡ ዘለዓለማዊ አምላክ ነው፡፡ ሊቃውንቱ ‹የተፈጠረ ያይደል የተወለደ› Jesus was ‹begotten› not ‹made› የሚሉት ስለዚህ ነው፡፡ ከአብ ጋር አንድ ነው፡፡ (ዮሐ.10፡30).

አማኞችም የእግዚአብሔር ልጆች ተብለን ተጠርተናል፡፡ ይሁንና የእግዚአብሔር አንድያ ልጅ ግን አይደለንም፡፡ Jesus is the <Only-Begotten Son> but we are the <children of God.> ልጅነታችንንም ያገኘነው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ባመንን ጊዜ በጸጋው የተሰጠን ችሮታ ነው፡፡(ዮሐ.1፡12-13)፡፡ በእርግጥ ከመለኮታዊ ብህሪውም ተካፍለናል ይህም በጸጋው ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የስላሴ አካል ልንሆን፣ ምንም የማይሳነን አምላክና ፈጣሪ ተደርገናል ማለት አይደለም፡፡‹‹ ወይም ሰማዩን አርሱ ይዞ ምድር ደግሞ ያለ እኛ ፍቃድ አንድዬ ቢሆን ፍቃድ ካላገኘ መስራት አይችልም ብለው ለእግዚአብሔር ፍቃድ ሊሰጡና ሊነሱ እየፎከሩ እንዳሉ ምስኪኖችም አይደለም፡፡›› The Attributes of God ተብለው ከሚታወቁት እግዚአብሔርን ልዩ የሚያደርጉት ባህርያት He is Omniscience /ሁሉን ነገር ማወቁ/,He is Omnipresent /በሁሉም ስፍራ በአንድ ጊዜ መገኘቱ/,He is Omnipotent/ ሁሉን መቻሉ/ God. ብታስቡትስ ከቶ ሰው ይህን መሆን ይችላልን? ይህንንስ ባህሪ ከመለኮት ተካፍያለው ብሎ መናገር የሚችል ሰው አለን? ትዕቢትና ድፍረት ካልሆነ በቀር መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አያስተምርም፡፡ እግዚአብሔር ጋር የሚገኙ የፍቅር፣የርህራሔ፣የሰላም ፣የቸርነት …ወዘተ ተቋዳሾች ግን ሆነናል፡፡ የእርሱ የጸጋው ልጆች ከተደረግን ቀን ጀምሮ ውስጣችን፣አስተሳሰባችን ተቀይሯል፡፡ ያለ ባህሪያችን ጸድቅ መባሉስ! ቅዱስ መባሉስ…ከቅድስናው በመካፈላችንም አይደል? ሌሎችን ታረቁ ማለት፣ መታገስ ፣ርህራሄ ከመለኮት ወርሰናል፡፡ብህሪውን በክርስቶስ ያካፈለን ዘላለማዊ አባታችን፣ፈጣሪያችን፣ ጌታችን ሆኖ ለዘላለም ይኖራል፡፡ እኛም እርሱን እናመልካለን ፣ እንገዛለታለን፣ እንሰግድለታለንም፡፡ ልጆች ስለተደረግን ስግደት አንተውም! አምልኮ አንተውም! እኛ ፍጡር ነን! እርሱ ፈጣሪያችን ነው፡፡ እርሱ መለኮት ነው እኛ ሰዎች ነን! ከዚህ በላይ አልፎ መንጠራራት ምንጩ ሌላ ነው! ምናልባትም ከአሳቹ ከዲያቢሎስ ነው እርሱ ቀድሞ ሕይዋንን ከዚህ ፍሬ እንዳትበሉ እግዚአብሔር የከለከላችሁ እንደ እርሱ መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንዳትሆኑ ፈልጎ ነው ብሎ በተንኮል እንዳሳታት ተጽፏል፤ ስለዚህም እግዚአብሔር በምጸታዊ ‹‹ አዳም መልካምንና ክፉን ለማወቅ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ›› ብሎ ተናግሯል፡፡( ዘፍ.3፡5፣ ቁ.22)፡ ከተጻፈው ባንልፍ መልካም ነው!

መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች ስለ ዘለዓለማዊ ልጅነቱ

 ከላይ እንደተብራራው ኢየሱስ በመለኮትነቱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ በሰውነቱም ደግሞ በጸጋው ልጅነትን ለተቀበልን አማኞች በኩር በመሆን ልጅ ተብሎ ተጠርቷል፡፡ በሁለቱም ባሕርይው የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በርካታ ቦታ ተጠቅሷል፡፡

ለምሳሌ ዮሐ.5፡20 የእግዚአብሔር ልጅ በስጋ መጣ ይላል እንጂ የእግዚአብሔር ልጅ ሆነ አይልም፡፡ የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊም ይህንኑ ሲያረጋግጥ በመጨረሻ ‹ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ ለእኛ ተናገረን፡፡› (ዕብ.1፡1-3)፡፡ ልጅነቱ ዓለማት በተፈጠሩበት ጊዜም እንደነበረ ያሳያል፡፡ ምናልባት የምሳሌ ምዕራፍ 8 አሳብና ቆላ.1፡15-18 ስለ ክርስቶስ የተነገረና አስቀድሞ ከአብ በመወለድ ፍጥረታትን ሁሉ ከአባቱ ጋር ሆኖ የፈጠረ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

ወልድ ቅድመ ዓለም የአብ ልጅ ነው፡፡ በሰው ስርዓትና አስተሳሰብ እንዴት ወለደው? መቼ ወለደው? ለሚለው መልስ ልናገኝ አንችልም፡፡ በዚህች ትንሽ አዕምሮ የሚገባን ነገርም አይመስለኝም፡፡ የምሳሌና የቆላስያሱ ጥቅሶች ግን ምንም ነገር ከመፈጠሩ በፊት እንደተወለደ እና ዓለማትን በሙሉ በእርሱ እንደፈጠረ ፍንጭ ይሰጣል፡፡(ምሳ.8፡25)፡፡ የዮሐንስ ወንጌል ም.1፡1-3 ደግሞ ‹ቃል› (ወልድ) በእግዚአብሔር ዘንድ እንደነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር እነደነበረ ይገልጻል፡፡›› ስለዚህ ሳይወለድ እግዚአብሔር ዘንድ የነበረ ወይም እግዚአብሔር ውስጥ የነበረ ነው፡፡ እግዚአብሔር የማታይ አምላክ ስለሆነ‹ መንፈስ ስለሆነ ‹ዓለም ሳይፈጠር በፊት እኔ ተወለድሁ› የሚለውን ቃል ይዘን እንዴት አድርጎ ወለደው; ብለን መጠየቅ የለብንም፡፡ሰማያዊ ፣መለኮታዊ ድርጊት ነው፡፡ ዋናው ነገር ወልድ ከአብ እኩል የነበረ‹ያለ እና የሚኖር አልፋና ኦሜጋ ነው /ራዕ.22፡13/ የሚለውን እውነት መረዳት ብቻ ያስፈልጋል፡፡ ቅድመ ዓለም ከአብ የተወለደ እንጂ የተፈጠረ አይደለምና፡፡ ጳውሎስ ለፊሊስዩስ አማኞች እንደጻፈው ክርስቶስ በእግዚአብሔር መልክ ይኖር ነበር፡፡(ፊሊ.2፡7)፡፡

አይሁድ ኢየሱስን ሊገድሉት ከሚፈልጉበት ምክንያት ዋናው ደፍሮ ‹እግዚአብሔር አባቴ ነው! ››(ዮሐ.5፡18) ስላለ ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ኤሁድ እራሳቸው ራሳቸውን የእግዚአብሐሔር ልጅ አድርገው የመቁጠር ልማድ እንዳላቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሷል፡፡ በዮሐ.8 ቁ.41 ላይ ‹‹..አንድ አባት አለን እርሱም እግዚአብሄር ነው››ብለው ተናግረዋል፡፡ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሲል ግን ይቆጡ ነበረ፡፡ ለምነ; ምክንያቱም እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ሚልበት መንፈስ ገብቷቸዋል፡፡ ልጅ ነኝ ሲል መለኮት ነኝ! ፣ ፈጣሪ ነኝ! ከሁሉም በፊት ነበርኩ ራሴ እግዚአብሔር ነኝ ማለቱ ነበረ፡፡ የክርስቶስ የመከራው ሳምንት ተብሎ በሚታወቀውም ጊዜ አካባቢ ሊቀ ካህኑ ‹‹የብሩክ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህን?›› ብሎ ሲጠይቀው አዎ እኔ ነኝ ብሎ መልስ ሰጥቷል፡፡/ማር.14፡61/በዚያን ጊዜም ምክንያት እየፈለጉ ለነበሩ አይሁዶች እንደ አንድ ትልቅ የምስክርነት ግብዐት እንዲሆናቸው ተጠቅመውበታል፡፡ አይሁዶች በብሉይ ኪዳንም ቢሆን እግዚአብሄር አባታችን ነው ብሎ የመጥራት ችግር አልነበረባቸውም (ዘፀ.4፡22-23)፡፡ በተጨማሪ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሞተበት ሰዐት ከስድስት ሰዐት ጀምሮ እስከ ዘጠኝ ሰአት ድረስ በምድር ላይ ጨልሞ ነበር፡፡ ወዲያውም የመቶ አለቃው ስለ ክርስቶስ ‹‹በእውነትም የእግዚአብሔር ልጅ ነበር ››(ማር.15፡39) ብሎ መስክሯል፡፡



   እግዚእብሔር አንድያ ልጁን ነው የላከልን፡፡ ልጁ አንድ ብቻ እንደሆነ ሲገልጥ ‹አንድ ልጅ በአባቱ ዘንድ እንዳለው …ክብሩን አየን› (ዮሐ.1 ቁ.14)፡፡ ቃሉ ‹‹ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለሁላችን አሳልፎ የሰጠው (ሮሜ.8፡32) የሚለው ቀድሞውንም ልጁን እንጂ የላከልን ለዚህ ዓላማ ሲል ቆይቶ ልጅ የተደረገ  አይደለም- የሞተልን፡፡ ይህንን በሌላ በብዙ ማስረጃ ማስረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ እግዚአብሔር ወደ ዓለም ብዙ ባርያዎቹን(አገልጋዮቹን) ልኮ ሁሉንም ስለገደሏቸው በመጨረሻ ልጄንስ ያፍሩታል ብሎ /ልጄ የሚለው አንድ ልጁ ክርስቶስን ነው/ እንደሰደደው (ማቴ…..) ተገልጧል፡፡ ዕብራውያን ምዕራፍ አንድም እግዚአብሔር ከጥንት ጀምሮ ለአባቶቻችን ሲናገር የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሞ እንደነበረ በመጨረሻ ግን ዓለማት በፈጠረበት በልጁ እንደተናገረን ያሳያል፡፡
May God bless you!
benjabef@gmail.com

Wednesday, August 8, 2018

እኛ ግን የተሰቀለውን...!

እኛ ግን የተሰቀለውን.....

በሆነ አንድ ወቅት በአንድ ቤተክርስቲያን የማምለኪያ አዳራሽ ፊት ተሰቅሎ የነበረ አንድ የጨርቅ ባነር ነበር በአቡጀዴው ጨርቅ ላይ ተጽፎ የነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ "እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!" የሚል ነበር። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከጨርቁ ላይ ፊደሎች  መጥፋት ጀምረው ነበር። በመጀመሪያ < እኛ ግን> የሚለው ቃል ቀለም በመጥፋቱ ምክንያት አረፍተ ነገሩ<<.. የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን" የሚል ጽሁፍ ሆነና ስብከቱን በውል ማን እንደሚሰብክ የማይታወቅ ሆነ። ቀጥሎም <የተሰቀለውን> የሚለው ስለለቀቀ <..ክርስቶስን እንሰብካለን> የሚለው ቀረ። ይህም የበለጠ የተለያየ ትርጉም ወደሚሰጠው ደረጃ ደረሰ። ምክንያቱም ብዙ ክርስቶስ ስላለ የትኛውን ክርስቶስ? የሚል ጥያቄ ያመጣልና። ክርስቶስ ራሱ በስሜ ብዙዎች ይመጣሉና ...ማቴ.24 &25 
በመጨረሻም <ክርስቶስን'> የሚለው ጠፍቶ .."..እንሰብካለን!" የሚለው ብቻ ቀረ።
ዋናው መስበካችን ሳይሆን ምን እንደምንሰብክ ፣ ማንን እንደምንስብክም ሌላው ዋና ነገር ነው። የስብከታችንና የአገልግሎታችን ማዕከላዊ አሳብ የተሰቀለው ክርስቶስ መሆን አለበት። ወንጌል ሙሉ የሚሆነው ክርስቶስ በስጋ መምጣቱ (መወለዱ)፣ መሰቀሉ ፣ መሞቱና መነሳቱ ነው። ቤተክርስቲያን በምድር ላይ የቆየችበት ምክንያት ይህንን እውነት እንድትመሰክር ነው። ወንጌል ሙሉ ነው ይዘቱም ይኽው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት ስለሚሰብከው ነገር ለዋኖች ለማስታወቅና ለማስመርመር በመንፈስ መገለጥ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር። ገላ.2፡ 1-10...እነርሱም የሚሰብከው ምን እንደሆነ ከመረመሩ በኋላ ለእርሱና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጥተዋቸዋል። ሃሌ ሉያ! ከተሰቀለው ክርስቶስ ውጪ ለመስበክ ብቻ ሳይሆን ሌላ ነገር ላለማወቅም ቆርጦ እንደነበር ተናግሯል።.....
ዝም ብሎ እንሰብካለን ብለን እንደቤተክርስቲያን መናገር አንችልም። የክርስቶስ አብያተክርስቲያናት መስበክና ማወጅ ያለባቸው የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው። ዋናው መልዕክት እርሱ ነውና።
 የምትወዱንና የምትጸልዩልን ወዳጆቻችን ሁሉ ይህንን የወንጌል መልዕክት ለሌሎች ሁሉ ለማድረስ አብራችሁን እንድትሆኑ በፍቅር እንጋብዛችኋለን። መልዕክታችን ሁለት ነገር ነው ጠቅለል አርጎ ለማስቀመጥ:-
1ኛ እኛ ነን መስበክ ያለብን!
ይህ ቃል ሌሎች እንዲሰብኩ፣ ሌሎች ወንጌል እንዲንገሩ የሚጠቁም ሳይሆን  እኛ ራሳችን  ሃላፊነቱን ወስደን ወንጌል እንድንሰብክ የሚያሳስብ ቃል ነው።

2ኛ. የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው መስበክ ያለብን!
ያልተሰቀለልን፣ ያልሞተልን ሌላ ክርስቶስ ስላለ ነው። ዘንድሮ ብዙ የሚሰብኩ /preachers and teachers/ ቢኖሩም መልዕክታቸው ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን ማሳየቱን፣ማላቁን ልብ ብለን ማየት አለብን። ክርስቶስ እስኪመጣ የቤ/ክ ስብከት ገንዘብ መሆን የለበትም፣ ስለ ሰው መሆን የለበትም፣ ሌላ ወንጌል መሆን የለበትም(ገላ 1 :6-9)   ስብከታችን የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ነው!!!

Sunday, January 1, 2017

በጥልቀት መታደስ !



በጥልቀት መታደስ….!
አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ራሳችንን በጥልቀት ፈትሸን እንታደስ ዘንድ በማሰብ ይህ ጽሑፍ ለመላው አብያተክርስቲያናት አገልጋዮችና ምዕመናን ተዘጋጅቷል፡፡
ይሁዳ 11
“ ..ወዮላቸው በቃየል መንገድ ሄደዋልና፣ ስለ ደመወዝም  ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፣ በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል፡፡ 
ይሁዳ በመልዕክቱ ውስጥ የጠቀሳቸው እነዚህ ሦስቱ ሰዎች/ቃየል፣ በለዓምና ቆሬ/ በብሉይ ኪዳን በተለያየ ዘመን የኖሩ ሲሆኑ ፡ጸሐፊው በዘመኑ ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኮ ስለገባው የስህተት ትምህርትና አስተማሪዎቹ/ሐሳውያን/ ባህሪና ምግባር በስፋት ያነሳው ቤተክርስቲያንን ከጥፋት ለመታደግ እንደሆነ ከመልዕክቱ እንረዳለን፡፡ ይሁንና  የዛሬይቱም ቤተክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ትልቅ ትምህርት የሚወስዱበት ሁኔታ አለና ከቀጣዩ መልዕክት እያንዳንዱ ለህይወቱ የሚጠቅመውን ቁም ነገር እንዲያስቀር ይሁን ፡፡
ፀሐፊው ከጠቀሳቸው፡- 1.የቃየል መንገድ
                                 2.የበለዓም ስሕተት
                                 3.የቆሬ መቃወም  ምን ማለት ነው? መቼ ነው የሆነው? እንዴት ነው የሆነው? የሚለውን ቀጥለን እንመልከት
ቃየል፡-የፍጥረት የመጀመሪያው  ሰው አዳም ልጅና የአቤል ወንድም ነበረ፡፡ የዘፍጥረት 4፡3 ማብራሪያ እንደሚነግረን  በቅንዐትና በጥላቻ ተነሳስቶ ወንድሙን አቤልን የገደለ ነፍሰ ገዳይም ነው፡፡ ወደ ግድያ ያደረሰው ጉዳይ ጥላቻ ፤ስግብግብነት፣ ምቀኝነት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡/NIV/  የእናት አባቱ ልጅ አቤል አብሮት እየኖረ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ለራሱና ለመስዋዕቱ ሞገስና ተቀባይነትን እንዳገኘ ትምህርት ከመውሰድ ይልቅ ጥላቻ አደረበት፤ የቃየል ስሕተት ይህ ብቻ አልነበረም፡ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እያዘገመ እንደሆነና ከክፉ መንገዱም እንዲመለስ እግዚአብሔር ቢያስጠነቅቀውም እንኳ መመለስ አልቻለም፡፡ ስለዚህ የቃየን መንገድ ማለት አጠገቡ ካለው ወንድሙ ትምህርት ከመውሰድ ይልቅ በተሳካላቸው ሰዎች መቅናት፣ እንዴት እንደሚወድቁ ሴራ ማሴር ፣ በሌላ በኩል ሐጢያት እንዳይነግስበት ሊጠቁመው የመጣውን ድምጽ / ምክር/ መናቅ ፤ ችላ ማለት! የሚሉት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? ወገኖች ወንድምን  መግደል የመጨረሻው የክፋት ደረጃ ቢሆንም፤ ትንንሽ ወንድሞችና መገለጫዎችም አሉት፡፡ አሁን አሁን በስፋት እየተለመዱ ያሉ ነገሮች አሉ! ለምሳሌ አንዳንድ  መጋቢዎችና ሽማግሌዎች ትውልድ እንዳይተካ  በር በመዝጋት፣ ትንሽ የጸጋ ስጦታ የሚታይበትን ሰው ድራሹን በማጥፋት፣ እንዲማረር በማድረግ ፤ አሰሪዎች ከሆኑ ከሥራቸው ያሉ ቅጥረኞችን ሁልጊዜ የበታችነት እየተሰማቸው ከስራቸው ብቻ እንዲሆኑ፣ በተለያየ ዘርፍ ሰዎች ከስር ተነስተው ልቀው እንዳይወጡ የሚደረግበት ሥጋዊ አሰራር ሁሉ የቃየል መንገድ መገለጫ ነው፡፡  በሌላ መልክ ሲነገራቸው የማይሰሙ፣ መንፈሳቸውን የማያደምጡ፣ ምክርና ተግሳጽን የሚንቁ፣ ነጋቸው/ዘላለማቸው/ የማይታያቸው ሁሉ በዚህ መንገድ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ መጨረሻቸውም አሳዛኝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ስለ አቤል ደም እግዚአብሔር ዝም አላለምና! ልክ እንደ ደሙም በር የተዘጋባቸው ፣ ያለ አግባብ መብታቸውን የተቀሙ፣ እንዳያድጉ የሚኮረኮሙ፣ ያለ በቂ ምክንያት ዕድገት/ሹመት/ የተነፈጉ፣ ዘራቸው ፣ቋንቋቸው ተፈትሾ የማለፊያ መንገድ የተከለከሉ፣ አድሎ የተፈጸመባቸው፣ግፍ የተሰራባቸው የበርካቶች ወንድሞችና እህቶቻችን እንባና ጩኽት እየተሰማ ነው፡፡
  በለዓም ፡-ምንም እንኳ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተለያየ ሥፍራ ላይ የተጠቀሰ ቢሆን / ራዕይ 2፡14፣ 2ጴጥ.2፡15..ወ.ዘ.ተ./  በዋናነት ግን ታሪኩን በዘኁ.ም.22-25 ድረስ እናገኛለን፡፡ በተለይ በራዕይ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው በአንድ ወቅት ለእስራኤላውያን እልቂት ምክንያት  የሆነውን የጥፋት ድግስ ያስደገሰ ዋነኛ ጠላት እርሱ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል  ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፡፡››ይላል፡፡ በለዓም ባላቅን  ያስተማረው ምንድን ነው? መቼስ  ነው ያስተማረው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ በቅድሚያ ስለ ግንኙነታቸው እናንሳ፡፡ ባላቅ በአንድ ወቅት የሞዐብ ንጉስ የነበረ ሲሆን፤ በለዓም ግን ከሞዐብ ትንሽ  ራቅ ያለ ሥፍራ ላይ ተቀምጦ በረጋሚነት የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ከነአን ጉዞ መጀመራቸውን ተከትሎ  በምድሩ እንዳያልፉ፡ በተለይም ከሰማው ዝናቸው አንጻር ሰግቶ በለዓምን አስመጥቶ በሙዋርት ሊያስረግማቸውና መንገድ ሊያስቀራቸው ሽቶ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ነው እንግዲህ በለዓምን የሚያግባቡ ተለቅ ተለቅ ያሉ ሰዎች ተልከው ከቀናት በኋላ ተክተልትለው አብረው የደረሱት፡፡ ቢሆንም እቅዳቸው ሳይሰምር ቀረ፡፡ ለሦስት እና ለአራት ጊዜ ፈጽሞ መባረክ ብቻ እንጂ መርገም ከቶ አልተቻለም ነበረና፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በስውር ለሕዝቡ እየተሟገተ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ሁለቱ ሰዎች በዚህ መልክ እንደተለያዩ ቢገልጽም፤አዲስ ኪዳንን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች ላይ በለዓም የሰራው ተንኮል ቁልጭ ብሎ ወጥቷል፡፡
 በለዓም ሁለት መልክ ያለው፣ ሁለት ምላስ ያለው፣ከባድ ሰው ነበር፡፡ ፊት ለፊት እስራኤልን ይመርቃል፣ ያደንቃል ፣እግዚአብሔር በመካከላቸው ያለ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን ይናገራል፣ከአንበሳ ደቦል ጋር ያመሳስላቸዋል፣ ሞታቸውን እንኳ እኔ ልሙት ብሎ እስኪመኝ ደርሶ ይታያል/ዘኁ.23፡10……../፤ ዞር ብሎ ደግሞ የሚጠፉበትን፣ተሰነካክለው የሚወድቁበትን ጉድጓዳቸውን ይቆፍራል፡፡ ያወቀውን ድካማቸውን አጋልጦ ሰጠ! ድካማቸውን ፈጽመው እንዲወድቁበት ተጠቀመበት፤ ከፊት ጥሩ ስለሚናገር ማንም እርሱን ጠላት ነው ብሎ ሊፈርጀው አይደፍርም ከጀርባ ግን ሐሜት አለ! እየሳቀ የሚገድል ቀን ጠብቆ አሳልፎ የሚሠጥ ከባድ ሰው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መተት ያላጠፋው ሕዝብ፣ ሙዋርት ያልገደለው ሕዝብ፣ ከቶ እርግማን ሊሰራበት ያልቻለ፣ ሊረገምም ያለተቻለ የእግዚአብሔር ሕዝብ በድካሙ ምክንያት መንገድ ቀረ‹! በአንድ ቀን ብቻ ሃያ አራት ሺህ ሰዎች ሞቱ! ይለናል / ዘኁ.25ቁ.9/፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?  እየሳቁ የሚገድሉ፣ ፊት ለፊት ጥሩ ነገር ያወሩና ከጀርባ ጉድጓድ የሚቆፍሩ …በተለይ እግዚአብሔር ቤት ውስጥ በርካቶች እንዳሉ ሲሰማ አያምም ወይ? ዞረው የሚያሙ፣ ድካሙን እንዲያስተካክል ለወንድማቸው ከመናገር ይልቅ ለሌላው /ለገዳይ/ አሳልፈው የሚሰጡ፣ በለዓም ለደሞዝ ተታሎ ይህን እንዳደረገ ተጠቅሷል፡፡ እንዲህ ባለ ምድራዊ ጥቅማ ጥቅም የሚታለሉ፣ እውነትን የሚሸቃቅጡ፣ ለሆዳቸው ያደሩ፣ እውነትን መጋፈጥ አንድ ቀን እንኳ የተሳናቸው፣ ዘላለማዊውን ነገር የረሱትን ይመስላል፡፡ የበለዓም ስህተት በሐዋርያት ዘመንም ነበረ፣ ዘንድሮም በየ አጥቢያው አይጠፋም …ይህን መንገድ እየተከተላችሁ ያላችሁ ወንድሞች፣ ቄሶች፣መጋቢዎች፣ዲያቆናት፣ሽማግሌዎች፣ልዩ ልዩ ባለስልጣናት…ራሳችሁን ከዚህ ክፉ መንገድ አውጥታችሁ በመጪው አዲስ ዓመት ሰው መንገዱ የሚቀናለትን ሁኔታ በበጎ ሕሊና እንድታስቡ፣ በተግባር ሰው መንገዱ እንዲቀናለት አድርጋችሁ እንድታመቻቹ ትለመናላችሁ! ዞሮ ጉድጓድ መቆፈር  ይብቃ! ሌላው መንገድ ላይ የሚቀርበትን ሸር መስራት ይብቃ! ……
ቆሬ፡- ይህ ደግሞ  ታሪኩ በዘኁ.16  ላይ ተጠቅሶ እንደሚገኘው  የትዕቢትና የንቀት ምሳሌ ነው፡፡ በተለይ ሁሉን ማድረግ እኛም እንችላለን! እነሱ ማናቸውና! እያሉ እውነተኛ  አገልጋዮች ላይ በድፍረት የሚናገሩ፣ በንቀት ለተሞሉ፣ ሳይችሉ እችላለሁ! ለሚሉ፣ ድምጽ-ተሰጦ ሳይኖራቸው በእልኸኝነት መዘምራን መካከል ገብተው ለሚረብሹ፣ አንዳችም ነገር ሳይሰማቸው የሰውን ስነ ልቦና እያነበቡ ከልባቸው እያወጡ ለሚተነብዩ፣ ሳይሾሙ ራሳቸውን ለሾሙ፣መሪነት ሳይሰጣቸው መምራት እችላለሁ! ለሚሉ ደፋሮች፣ ቀን ተቀን ለእግዚአብሔር ቤት የማነቆ ገመድ ለሆኑ እልኸኞች፣ የቆሬ ሰዎች ሕይወት ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጥቂት ነበሩ፤ ነገር ግን አድማ ሰርተው አለቆችን አሳምነው እኛም እንደነርሱ ካህናት መሆን እንችላለን! ማጠን እንችላለን! በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ተሰበሰቡ /ቁ.6-10/፡፡ አሳዛኙ ነገር እንዲህ በትዕቢት ተወጥረው ማድረግ የሌለባቸውን እናደርጋለን ብለው የተነሱቱ ወገኖች መጨረሻቸው አለማማሩ ነው/ቁ.31-33/፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? ካህን ተደርገው ሳይመረጡ የራሳቸውን ጥና የያዙ፣ ጥሪ ሳይፈተሸ/ሳይረጋገጥ/ ቤተክርስቲያን እንመራለን ብለው ግርግር የሚፈጥሩ፣ በተቀቡ ሰዎች ላይ አድማ የሚያሳድሙ፣ ለመልካም ሳይሆን-ለክፉ፣ ለማቅናት ሳይሆን-ለማፍረስ፣ የሚሰበሰቡ፣ የማይመለከታቸውን ጉዳይ እየፈተፈቱ ቤታቸው ቁጭ ብለው ቤተክርስቲያን የሚያፈርሱ፣ ካልቻሉ አሳባቸውን በሰው ምላስ ላይ እያኖሩ ሰላም እንዳይገኝ ምክንያት የሚሆኑ ሁሉ ቆሬና ሰዎቹ ሞቱ እንጂ መንፈሱ አልሞተምና በተለያየ ተዋረድ በእጅ አዙር እየተጠቀመባቸው እንዳይሆን መፍራት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁሉን አውቃለሁ የሚልን ሰው መምከር ከባድ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ጥልቅ አሰራር መርምሮ ሊደርስበት የሚችል የለምና እስኪ በትጋትና በደስታ ራዕያቸውን ይፈጽሙ ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አገልጋዮቹ ላይ ዞር ትሉ ዘንድ በአዲሱ ዓመት ጌታ እንዲረዳችሁ ጸልዩ! ደግሞ በተቃራኒው ሥራውን መደገፍ ፣መጸለይ፣ የፈረሰ ጎን አይቶ መቆም….ምንም ነገር ከተቃውሞ ሳይሆን ከፍቅር እንዲመነጭ ማድረግ ብስለት ነው፡፡
 እንዲያው ባጠቃላይ ቅንነትን ተላብሰን የቀረችን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነች አትታወቅምና እግዚአብሔር በረዳን መጠን ጥሩና ደግ ሰዎች፣ የሰላም ሰዎች፣ ራሳቸውን የካዱ ለሌላው የሚኖሩ ሰዎች ፣ ለትውልድ መንገድ ከፋቾች ፣ የማደጊያ አቅጣጫ ጠቋሚዎች ያድርገን ! በክርስቶስ ኢየሱስ ስም! አሜን!
                                                                             ብንያም በፍቃዱ /መጋቢ/
                                                                               benjabef@gmail.com