Friday, April 10, 2020

passion for z harvest



                ‹‹   እንዴት ልመስክር  ? ››    
/ ወንጌልን በግለት (passion ) ስለማገልገል /

                      ምዕራፍ አንድ
  ወይቤሎሙ፡ ሑሩ፡ ውስተኩሉ፡ ዓለም፡ ወሰብኩ፡ ወንጌል፡ ለኩሉ፡ ፍጥረት፡፡
/ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል ያላመነ ግን ይፈረድበታል፡፡/ ማርቆስ 16፡15
ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክ ትዕዛዝ የሰጠን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወንጌል መስበክ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም፡፡ እኛ ወደ ጌታ እስከምንሔድ ወይም ጌታ በዳግም ምፅዓት እስኪመለስ ድረስ የምንከውነው ታላቅ የሆነ ሰዎችን የማዳን ተገግባር ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ይኸው ወንጌልን የማሰራጨት ተልዕኮ ለጥቂቶች ብቻ የተተወ  ይመስላል፡፡ ሌሎቹ  ምንም የማይመለከታቸው ነውን? አንዳንድ ጊዜም በዘመቻ ይጀመርና በዘመቻ ሲተውም ይታያል፡፡ በእኔ እምነት አንድ ቤተክርስቲያን ወንጌል መስበኩዋን ማቆም ያለባት በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ድነው ካበቁ እና የዓለም ፍጻሜ ደርሶ ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ወንጌልን መስበክ ማቆምና እንደፈለግን አጀንዳውን መቀያየር የምንችል አይመስለኝም ፡፡ ቤተክርስቲያንን የመሰረታት እና ራስ የሆነላት ጌታ እስኪመለስ ድረስ አድርጉ ብሎ ያዘዘውን ተልዕኮ መፈጸም ይኖርብናል፡፡ ተቋሙ የእርሱ ነውና፤ በቤቱ የእርሱ ትዕዛዝ ሊተገበር እንደሚገባ አስባለሁ ፡፡

 መሰረታዊው  ነገር ይህ ሆኖ ሳለ፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌልን በግድ ፣በፍርሀትና በመጨነቅ እንዳንሰብክ ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ እንዴት እንስበክ ?... ከውስጥ በሆነ ፍቅር! በጋለ ስሜት! ነፍሳት እንዲድኑ ባለ እውነተኛ ቅንዐት  / passion / 
በወንጌል ስለ መቅናት ስናነሳ አስቀድመን ከትርጉሙ ብንጀምር ጥሩ ነው፡፡ ስለ ወንጌል መቅናት /ፓሽን-Passion/ በላቲንኛው ቋንቋ ለሆነ ዓላማ ዋጋ መክፈልን / to suffer for/ የሚያመለክት ሲሆን በ MC Clung እንደተብራራውም Passion is what you hunger for so intensely that you will sacrifice any thing to have it. ወደ አማርኛው ስንመልሰው በጣም በጋለ ስሜት ውስጥ ሆነህ የምትራበውና ለዓላማህ ያለህን ነገር ሁሉ የምትሰዋበት ነው፡፡
 በነገራችን ላይ ለወንጌል ብቻ ሳይሆን፡ ሰለ ሌላውም  ስለምናደርገው ነገር አስቀድሞ ፍቅርና መነሳሳት ቢኖረን ጥሩ ነው፡፡ ቶዘር የሚባል አንድ መንፈሳዊ ሰው እንደተነናገረው '' አንድን ነገር ከመስራት በፊት ለዚያ ነገር ፍቅርና መነሳሳት ያሻል፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ትልቁ ነገር፡ ከሌሎች ነገሮች ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ የውስጥ መነሳሳት፣ ለነፍሳት የሚኖረን ፍቅር ተልዕኮና አገልግሎት ሁሉ የሚገኘው ወይም የሚገነባው ለክርስቶስ ኢየሱስ ባለን ጥልቅ ፍቅር ላይ ተመስርቶ ነው '' ብሎአል፡፡
           ከውስጥ የሆነ ቅናት /passion/ እንዴት ይመጣል ?
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለምሳሌ የነህምያን ታሪክ ብንመለከት፡ ከጦቢያና ሰንበላጥ  የመጣበትን ዛቻ ማስፈራሪያ ሳይበግረው ህዝቡን አስተባብሮ የኢየሩሳሌምን ቅጥር 52 ቀናት  ሰርቶ የጨረሰ ታላቅ ባለ ራዕይ ነው፡፡ የትልቅ ነገር ባለ ራዕይና ባለ ገድል ከመሆኑ በፊት ግን፡ እስራኤላውያን፡ ተግዘው በሄዱበት በስደት ምድር - በባቢሎን ቤተመንግስት ውስጥ በጠጅ አሳላፊነት ሙያ ተቀጥሮ ኑሮውን ሲገፋ የነበረ ሰው ነው፡፡አንድ ቀን ግን አናኒ የሚባል ወንድሙ ስለ ኢየሩሳሌም ጉዳይ ወሬ ይዞ መጣ፡፡ ያንን ወሬ ሌሎችም  የእስራኤል ሰዎች ሳይሰሙ አይቀርም፡፡ ከሰማው ነገር ተነስቶ አንድ ነገር ለማድረግ የወሰነ ግን አናይም፡፡ ነህምያ ግን የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስና ፣የአባቶቹ መቃብር ያለበት ከተማ በር መቃጠሉን ሲሰማ  ልቡ ተነካ፤ አያሌ ቀን ተቀመምጦ  አለቀሰ፡፡/ነህ.13-4/፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡ በሰማይ አምላክ ፊት እያዘነ ይጾምና ይጸልይ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ውስጡ ሲነካ ነው ፡ወደ ቀጣዩ እንቅስቃሴ የተራመደው፡፡ ከሞቀ ስራው አስፈቅዶ ወጥቶ የሄደው፤ ሌሎችን ሁሉ አስተባብሮ ቅጥሩን ሰርቶ የጨረሰው፡፡
ልክ እንደዚህ የሆነ ነገር ስንሰማ፣ ስንሰበክ፣ ስንማር ወይም  ስናነብ፣ ቅዱስ ቅንዓት ውስጣችን ሊገባ ይችላል፡፡ የወንጌል ቅንዓትም ወይ በዚህ መልኩ አልያም በሌላ መንገድ ውስጣችን ይመጣል፡፡ ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል 15 ላይ የምናገኘውና ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት፡፡ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ነበሩት ፤ከመቶዎቹ መካከል አንደኛው በግ ወደ በረሀ ኮበለለ፡፡ ወዲያውም ሰውዬው የነበሩትን ዘጠና ዘጠኙን በመተው የጠፋውን አንዱን ሊፈልግ እንደሄደ ይገልጻል፡፡ያሉትን ዘጠና ዘጠኙን ይባርክልኝ ብሎ እንደ መቀመጥ ፡እንዴት ስለ አንድ በግ  ብሎ ፍለጋ ወጣ  ? ብንል፤ መልሱ ሊሆን የሚችለው ስለ አንድ ግድ የሚያሰኝ ጥልቅ ፍቅር ገብቶበት ነው! በጉ ጠፍቶ መተኛት አይችልም፡፡ ቀጥሎም ነገሩን ከልቡ ሆኖ እንደሚያደርገው የሚያሳየን  '' እስኪያገኘው ድረስ  አጥብቆ መፈለጉ ነው፡፡'' .4 ፡፡ ካገኘው በሁዋላ ደግሞ፡ ደስታውን የገለጠበት መንገድ በተጨማሪ ልቡንና ቅንዐቱን ያሳየናል፡፡ በጫንቃው ተሸክሞ ወደ ቤት አምጥቶ፣ ጎረቤቶቹን ጠርቶ፣ ደስታውን ገለጸ ይላል፡፡ ካደረጉስ ማድረግ እንዲህ ነው፤ እስኪያገኙ ድረስ አጥብቆ መፈለግ !
     ዛሬ በኛ ዘመን ስንት በግ  ጠፍቶብን  ነው  የተቀመጥነው ?
... ሚያዚያ ወር 2012  ላይ ስለ ዓለም ህዝብ ቁጥር  አንድ አለም አቀፍ ሪፖርት ወጥቶ ነበር ፡፡ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ሰዐት የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን ገደማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ ውስጥ 750 ሚሊዮን ወይም 11% የሚሆነው ህዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት  የሚያምን፣ 2.6 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ወይም  38%  ገደማ የሚሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሰማ ነገር ግን ያልተቀበለ  / ሌሎች አዳኞች አሉ! ብለው የሚያምኑ/ የተቀረውና ሰፊው ህዝብ ማለትም 3.5 ቢሊዮን ወይም  50% ገደማ የሚሆነው ምንም የወንጌል መልዕክት ያልሰማና የክርስቶስን አዳኝነት ያልተቀበለ ነው፡፡
   ከነበሩት መቶ  በጎች  አንዱ ቢጠፋ አክንፎ ያስኬደው ፍቅር ተጽፎልን: ከሶስት  ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ጠፍቶ ምንም ሳይመስለን ተረጋግተን መቀመጣችን  ምን ያህል አዚም ቢደረግብን ነው? ማን ነው ይህን ታላቅ ቅንዐት ከውስጣችን የዘረፈብን? እርግጥ ነው በዚህ የተቀደሰ ተግባር ላይ የተሰለፉ ተግዳሮቶች በርካታ ናቸው፡፡ ውስብስብም ናቸው፡፡ ነገር ግን ጌታ ተልዕኮውን በሰጠበት ጊዜ "አይዞአችሁ እኔ  እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎናል '' ማቴ.2820
ነፍሳትን ከሲኦል የመታደግ አገልግሎት በእግዚአብሔር መንግስት ካሉት አገልግሎቶች ሁሉ ላቅ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ትልቅ ውጊያ ያለበት አገልግሎት ነው፡፡ በስጦታ ካልሆነ በቀር ብዙዎች በምርጫ ደረጃ ላይመርጡት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ታላቅ የነፍስ እርካታ የሚገኘውም የነፍስ ማዳን ርብርቦሽ ውስጥ እንደሆነስ  ያውቃሉ? ሰው  ከሲኦል ሲያመልጥ ያለ እርካታ!
 ወንጌልን መመስከር ከልባችን ተነክተን እንድናደርገው፡ ነፍሳትን የመታደግ ቅንዓት እንዲጨምርብን አስቀድመን ብንጸልይ መልካም ነው፡፡ ፍሬያማ ውጤታማ እንድንሆን ያግዛልና፡፡ ብንጸልይ ሊሰጠን እንደሚችል ከተጻፈልን ተስፋ ቃሎች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት፡-
1- ማቴዎስ ወንጌል 77-8 በእንግሊዝናው ምዕጻረ ቃል /አብሪቬሽን/ A .S .K. ይባላል፡፡
     A  S  K
     S  E  E  K
     K  N  O  C  k
 '' ለምኑ ይሰጣችኋል  ፤ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ  ይከፈትላችኋል፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል፡፡'' እንደሚል፤ ከልባችን እየፈለግን እንለምን፡፡ በሩን እስኪከፍትና እስኪሰጠን  ድረስ  ደጋግመን በሩን እንቆርቁር፡፡ በተስፋ ቃሉ መሰረት በሩን ይከፍትልናል፡፡ ሌሎችን የምናተርፍበት የወንጌል ቅንዐትም ከብዙ ጥበብ ጋር ወደ ልባችን ይገባል፡
2-  ሁለተኛው የያዕቆብ መልዕክት 117 ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ይላል፡-'' በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው ፤መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡''  ለወንጌል  የመቅናት ስጦታ በጎም ፍጹምም ነው፡፡ ይህን በረከት ከጌታ ልንቀበል እንደምንችል ቃሉ ያሳያል፡፡
ፀሎት፡- ጌታ ሆይ  የወንጌልን ቅናት እንድትሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምንሀለሁ፡፡  
               አሁን ለኛ ቀን ነው ሌሊት?
'' ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ላደርግ ይገባኛል፡፡ማንም ሊሰራ   የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡'' ዮሐ.94፡፡
    በሰው ህይወት ውስጥ ቀንም ሌሊትም አለ፡፡ ይህ ሁሉን ሰው ሲያጋጥም የኖረ፣ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡የምንሰራበት ምቹ ጊዜና ሁኔታ ይሰጠናል ፤ደግሞ ሌላ ጊዜ መስራት ብንፈልግና ጊዜ ቢኖረን እንኩዋ የወደድነውን ማድረግ የማንችልበት ሌሊት ደግሞ ይመጣል፡፡የተመቻቸው ቀን ላይ ያልሰራ፣ያልተጋ ሰው የማይሰራበት ሌሊት ሲመጣበት ይቆጨዋል፡፡
     ከወንጌል መስበክ አኩዋያ እነዚህን ሁለት ሁነቶች በምድራችን ላይ እንኩዋ ማሰብ ይቻላል፡፡ አንዱ  ወንጌልን በነጻነት መስበክና ማስተማር የማይቻልበት  ጊዜ ነበር፡፡ ምናልባት ደግሞ አሁን በአንጻራዊ  ሁኔታ ቤተክርስቲያን በድብብቆሽ  ከምትሰበሰብበትና ከምትሰራበት ሁኔታ ወጥታ ወንጌልን በትልልቅ  አዳራሾች በአደባባይ መስበክ ችላለች፡፡ ይህ ሲባል ግን መቼም ዘመን ቢሆን ወንጌልን ከመስበክ ጎን ለጎን ከሚገጥሙ ትንሽም፣ ትልቅም  ተግዳሮቶች ጋር ማለት ነው፡፡
  ይሁንና ይህንን ነጻነት ተጠቅመን የማንሰብክበት፣ የማንመሰክርበት ከሆነ ነገ ደግሞ ሌሊት ሊመጣብን ይችላል፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚከሰት አይታወቅም፤ የወንጌል ተቃዋሚዎች በዓለም ላይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አይለው ተነስተዋል ጌታም ለጊዜው ስለ ፈቀደላቸው ይመስለኛል፡ አንዳንድ በጸሎት መከልከል የማንችላቸውን ድርጊቶች ሁሉ እያደረጉ ያሉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ነገ በእኛ አካባቢ ምን ሊከሰት ይችላልከህግ ፣ከዲሞክራሲ አንጻር የሰው መብት አትንካ ፣የራስህን አመለካከት ሰው ላይ መጫን አትችልም፤ የስብከት ፍቃድ፣ የአገልጋይነት ፍቃድ....ወዘተ የሚሉ ነገሮች ከአሁኑ በራችንን እያነኩዋኩ ነው፡፡ ለምሳሌ  የኤርትራ ወንድሞችና በዚያም ያለች ቤተክርስቲያን ሌሊት ውስጥ ናቸው ያሉት፡፡ እንደሚሰማው መስበክ መናገር አይቻልም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር ምናልባት በቅርብ ጊዜ ምቹ ቀን ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ ሀዘናቸውም ይጽናናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሁንና እኛ ግን ከእንደነዚህ  አይነት ሁኔታዎች መማር አለብን እላለሁ፡፡
            ወንጌልን  በራሳችን  ዘመን ...!
" ዳዊት በራሱ  ዘመን  የእግዚአብሔርን  ሐሳብ  ካገለገለ  በሁዋላ  አንቀላፋ፡፡" ሥራ.1335
 ዳዊት በተሰጠው በራሱ ዘመን እንዲሰራው የተቀመጠለትን ነገር አድርጎ ማለፉን ነው ቅዱስ ሉቃስ የዘገበልን፡፡አሁን እኛ በእኛ ዘመን እንድንሰራው የሚፈለግ ታላቅ የእግዚአብሔር ዓላማ፡ በዋነኛነት ምን ሊሆን ይችላልይህንን ጥያቄ  ለመመለስ  በሚደረጉ ጥረቶች ብዙ ሰዎች የተለያየ በጎም የሚመስሉ፣  በጎም ያልሆኑ አመለካከቶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፊት ለፊት የተቀመጠላቸውን የእግዚአብሔርን አጀንዳ ችላ ብለው ሲመራመሩ ፡አላስፈላጊ ወደ  ሆኑና ከእግዚአብሔር የልብ ትርታ ጋር ግንኙነት ወደሌላቸው ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን፣ ከትህትና ይልቅ ትዕቢትን ፣ለሌላው ከማሰብ ይልቅ ለራስ ብቻ በሚያደላ አፍቅሮ ነዋይ እየተሳቡ ገብተው ሲለፉና ሲሰቃዩ ማየት የተለመደ ነገር  ሆኑዋል፡፡ሁሉም ድርጊቶች የሚፈጸሙት በእግዚአብሔር የዘመኑ አሳብ ራዕይ ጥሪ ስም ነው፡፡ በተለይም  ቤተክርስቲያን  ዋና ነገሩዋን ስትስት ከማየት በላይ የሚያም ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር ግን በዚህ ዘመን ማድረግ የፈለገውን አሳቡን በግልጽ ተናግሯል '' በክርስቶስ ለማድረግ እንደ ወደደ እንደ አሳቡ የፍቃዱን ሚስጥር አስታውቆናልና፡፡'' በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው''  ኤፌ.110፡፡ ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንዲሆንና ለእርሱም እንዲሆን ባለ የመለኮት አጀንዳ ውስጥ ተሳታፊ መሆን  ምን ያህል ታላቅ ዕድል ነው?! ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ  የምናደርግበት መንገዱ ደግሞ ወንጌልና ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ለሰው  የሞኝነት መንገድ የሚመስል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን አስቀድሞ የታሰበ ዘዴ ፣ጥበብ ብልሀት ነው፡፡ '' ....ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ፣ ካልሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ''----የተባለበት ሚስጥር፡፡
          ነፍሴም ወደ አምላኳ
        ስጋም ወደ አፈሩ ሳይመለስ
        ቶሎ ቶሎ ብዬ ስራዬን ልጨርስ
        /መዝሙረኛው መጋቤ ተስፋዬ ጋቢሶ/
             ቤተክርስቲያን ሆይ ንቂ !
  ጾምና ጸሎት ይዘን በወንጌል ሳይሆን በተለያዩ ዘመነኛ ሃጢያቶች ሱሶች ቀስ በቀስ እየተወረሰ  ያለውን ህብረተሰብና አካባቢ እንዲሰጠን መጸለይ ብንጀምርስ ? ክፉ በብዙ እየተጋ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያን በሰበብ አስባብ የጸሎት ቀናት ፣ሰዐታት እያስቀነሰ ፣የማለዳ  ጸሎቶች አዳር ጸሎቶችን እያስተወ፡ ያለምንም ውጊያ እየሰራ ያለ ይመስላል፡፡ መሳሪያዎቹዋን ቀስ በቀስ የተዘረፈችዋ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዐት መንቃት ይጠበቅባታል፡፡ ሙሽራው ሊመጣ በደጅ ነው እያልን ሙሽሪት ተገቢውን ልብስ  ሳታደርግ ፣ ሳትዘጋጅ እንዴት ይሆናል?
  ቤተክርስቲያን ትውልዱን እየተናጠቀች  ካልጸለየች ሌላ የተጋ ይወስዳቸዋል፡፡ ዲያቢሎስ ለራሱ አጀንዳ እንደሚጸልይ  የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ሰይጣን እንደ  ስንዴ  ሊያበጠጥራችሁ ለመነ" ሉቃ.2231 ፡፡ የሰይጣን ልመና ትውልድን የማበጠር፣ የማድከምና የመበተን ሲሆን : ጌታ ግን ስለ ጴጥሮስ '' እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ '' ይላል፡፡ምንም እንኩዋ ጴጥሮስ በፈተናው ተሸንፎ ክዶ ሄዶ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ በንስሀ ተመልሱዋል፡፡ ለመመለሱ ምክንያት የነበረው ግን ጌታ ስለ እርሱ ስለ ማለደለት ነው፡፡/.32/
     ቤተክርስቲያን ዕቅድ ያላወጣችበትን ህዝብ እና ስፍራ ጠላት እያቀደበት ነው ፡፡ ሰሞኑን አይ ኤስ የተባለው እስላማዊ ድርጅት ምን እየደረገ እንደሆነ ለማንም ጆሮ ባዳ አይደለም፡፡ የደከሙ መንግስታትን እያሰሰ ይቆጣጠራል ይደራጃል፤ ለምሳሌ ጋዳፊ የወደቁበት ሊቢያ፣ ሳዳም ሁሴን የወደቁበት ኢራቅ፣ በብዙ ጦርነት የደቀቀችውን ሶሪያ....እንደ የመን ያሉ ሌሎችንም አገሮች፡፡ በትንሽ ተዋረድ ደግሞ ወንጌል ለመስበክ ያላሰብንባቸው አካባቢዎች ጠንካራ ጸሎት የማይደረግባቸው ልል ቦታዎች ልክ ጠንካራ መንግስት እንደሌለባቸው አገሮች ለክፉው ስራ የተጋለጡ  ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ምን ምን ያልነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች  እንደ ወረርሽኝ የጫትና የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች ማከፋፈያ እና መጠቀሚያ ሆነው ሲታዩ ፤የዝሙት ማስፋፊያ፣ የመጠጥ ንግድ ቤቶች ፣ዳንኪራ ቤቶች እንደ ሰደድ እሳት በየቦታው በፍጥነት ሲስፋፉ፡ ከሁዋላ  ደጀን የሆናቸው ዕቅድ አውጪው  ማን ነውበዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያን የት ነች? ለትውልዱ ምን እያሰበች ነው?
በዚህና  በዚያ ተወጥሮ  ያለውን  ወጣት ትውልድ  ከጠላት  መንጋጋ  ለማላቀቅ  ተግቶ  እየጸለየ ያለ ማን ነው? የትውልድ  ሸክም ያለበት የዘመኑ  የወንጌል ሰው ማን ነው? ቀድማ አይታ  የተነሳች እንደ ሰራዊት  እየጸለየች ያለች  የዘመንዋ  ቤተክርስቲያን  የቱዋ ነችለሚከፈቱ  አጥቢያዎች አጀንዳ  ያላት፣ ለወንጌል በጀት ያላለቀባት፣ የጌታ  ዋነኛ  አሳብ  የገባት  አጥቢያ  የት ናት? ሲመስለኝ ሰይጣን የቤት ስራ ሰጥቶን ፡እርሱ የራሱን ስራ እየሰራ ነው፡፡ አንገብጋቢና ዋና  ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ እንድንፈጅ እርስ በርስ እንድንለያይ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲጠላ ፣ቤተክርስቲያን  ከቤተክርስቲያን ፣መሪዎች ከመሪዎች  እንዲራራቁና እንዳይግባቡ ተደርገናል፡፡ እንደ ጥንቱዋ ቤተክርስቲያን መሪዎች ስለ ተሐድሶ ወይም ስለ ሪቫይቫል ሊያስቡ በሚገባበት ጊዜ ላይ '' የማርያም አይን ጥቁር ነው ቡናማ ?'' '' በአንድ መርፌ ላይ ስንት መላዕክት ይቆማሉ?'' '' ቅዱስ ቁርባን ውስጥ ዝንብ ብትገባ ዝንቡዋ ትቀደሳለች ወይስ ቁርባኑ ይረክሳል ? '' በሚሉ ጭቅጭቆች ተወጥረው፣  በሐሳብ ተለያይተው፡ ውድ ጊዜያቸውን እንዳቃጠሉ ሰይጣንም ኑፋቄዎችን በቤተክርስቲያን አሾልኮ ለማስገባት ዕድል እንዳገኘ፡ ዘንድሮም ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ብናስተውል መልካም ነው፡፡
   ሩቅ የመሰሉን ነውሮች ቤተክርስቲያን ደጅ ላይ፣ ብቻ አይደለም ምስባኩ ላይ ከወጡ ቆዩ፤ የጺዮንን በር የተዳፈሩ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች  እየሆኑ ነው ፡፡ እኛስ እንደ ዳነ ሰው እንደ ቤተክርስቲያን  ምን እያሰብን ነው?

-------------------------------------------------------------------
     
           የሰው ዕድሜ

‹‹ የዘመኖቻችን ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፡፡ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፡፡ ከእኛ ቶሎ ያልፋና እኛም እንገሰጻለንና ›› መዝ.90፡10
  በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በርካታ ክፍሎች ላይ ስለ ዕድሜያችን የተጠቀሰው እምብዛም የሚያደላድል ና የሚያስፋፋ ነገር እንዳልሆነ ነው፡፡በጣም ጥቂት ጊዜ የሆነ አንድ ዓላማን ፈጽመን እንድናልፍበት የተሰጠን እንጂ፡፡በዚህ ጉዳይ የተጠቀሱ የተወሰኑ ጥቅሶችን ቀጥለን እንመልከት፡-
. ዘመኖቻችን እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ፡፡ መዝ.90፡9
. በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፡፡ መዝ.39፡6
. የህይወቴ ዘመኖች ጥቂት ክፉም ሆኑብኝ፡፡ ዘፍ.47፡9
. ህይወታችሁ ምንድን ነው ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፍ እንፏሎት ናችሁና፡፡ ያዕ.4፡14
. በሌሎች ስፍራዎችም ሰው ህይወት /ዘመን/ እንደ ሸማኔ  መጠቅለያ ፣ እንደ ተን ….ወዘተ ተመስሏል፡፡
  እነዚህ ከላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች አበክረው የሚያስረዱን ዕድሜዎቻችንን በቁም ነገር ጉዳዮች ላይ ካላዋልነው እና አንድ የተቀደሰ ዓላማን ካልፈጸምንበት ዝም ብሎ በዋል ፈሰስ ሊያልፍ እንደሚችልም ጭምር ነው፡፡እግዚአብሔር አምላክ ዕድሜን የሰጠንና የወሰነልን በአቅማችን እኛው ሰርተን ማለፍ ካለብን ዓላማ ጋር ነው፡፡በተለይም ወንጌልን ከመስበክ ጋር የተያያዘ ዓላማ ደግሞ እጅግ የላቀው ነው፡፡
በአንድ አገር ውስጥ የሰዎች ዕድሜ ላይ የሚያጠና አንድ ምሁር  የምድር ቆይታቸው ሰባ /70/ ዓመት የሆኑ ሰዎች የኖሩበትን ዘመን ምን ምን አድርገውበት እንደሚያልፉ ካሰፈረው ጥናት እንመልከት
    ለእንቅልፍ 23 ዓመት / 32%
   ለስራ 6 ዓመት / 22.8 %
  የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመመልከት 8ዓመት /11.4 %
  በመመገብ 6ዓመት / 8.6 %
  በመጓጓዝ 6ዓመት / 8.6 %
  በመዝናናት 4.5 ዓመት / 6.5 %
  በተለያየ ህመም 4ዓመት / 5.7 %
  በመልበስ 2ዓመት / 2.8 %
  የኣመልኮ ስርዓት በመፈጸም 0.5 ዓመት 0.9 %
    በእርግጥ አጠቃላይ ነገሮችን ስንዳስስ አልፎ አልፎ እንደየአካባቢው ሁኔታ ሊለያይ የሚችል ነገር አይጠፋው ይሆናል ፤ ለምሳሌ ትራንስፖርት ችግር የሌለበት ቦታ ለመጓጓዝ ያን የሚያክል ጊዜ ላይፈጅ ይችላል፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ቴሌቪዥን የሚባል ነገር ጨርሶውኑ ላይኖር የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ይችላል፡፡ ከሞላ ጎደል ግን በአብዛኛዎቻችን ህይወት ውስጥ ትክክል ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

           የወንጌል አርበኞች
‹‹ እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፡፡ ጨው አልጫ ቢሆን ግን በምን ይጣፍጣል? ወደ ውጪ ተጥሎ በሰው ከመረገጥ በቀር ወደ ፊት ለምንም አይጠቅምም፡፡ እናንተ የዓለም ብርሐን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም፡፡ መብራትም አብርተው ከ ዕንቅብ በታች አይደለም እንጂ በመቅረዙ ላይ ያኖሩታል፤ በቤት ላሉትም ሁሉ ያበራል፡፡ ›› ማቴ. 5፡13-14
ከላይ የተመለከትነው ጥቅስ ክርስቲያኖች ሆይ እናንተ ጨው ይዛችኋል ፣ ብርሐን ይዛችኋል አይደለም የሞለው፡፡ የምድር ጨው ናችሁ፡፡ የኣለም ብርሐን ናችሁ፡፡ እንጂ፡፡ ዐውና ብርሐን የተደረገ ህይወት፡፡ ናችሁ፡፡በመሆኑም ዓለምን ማጣፈጥ እንድንችልና ለጨለመበት ዓለም ብርሐን እንድናበራ ጨውን ከአልጫ ፣ ብርሐንን ከጨለማ ውጪ ብናደርጋቸው ወይም ጨውን ከጨው ጋር ደራርበን ለዓመታት ብናስቀምጣቸው ፣ብርሐንንም በአንድ ላይ ጨለማ በሌለበት ቦታ ብናከማቸው የተፈጠሩበትን ሚና መጫወት ሳይችሉ ይቀራሉ፡፡ጨውም በወጥ ውስጥ እንዲያጣፍጥ፣ብርሐንም በጨለማ ውስጥ እንዲያበራ ይህ ማንነቱ ነው፡፡
በእግዚአብሔር እርዳታ በዘመናቸው በትውልዳቸው መካከል የብርሐንና የጨው ሚናቸውን በትክክል ተወጥተው ያለፉ ጥቂት የማባሉ አባቶች በታሪክ ይታወቃሉ፡፡ በአውሮፓውያን ምድር በወንጌል እሳት እየነደዱ ትልልቅ መንፈሳዊ ታሪክን ካለፉት መካከል ጥቂቶቹን ቀጥለን እናነሳለን፡-
    በ16ኛው ክፍለ ዘመን ገደማ በእንግሊዝ አገር ታላቁን የወንጌል ሪቫይቫል ሲመራ የነበረው የእግዚአብሔር ሰው ጆን ዊስሊ/ John Wisely / ይባላል፡፡ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ በመጣው መንፈሳዊ መነቃቃት ወደ ዓለም ላይ በሙሉ ሊዳረስ ችሏል፡፡ በዚህም ቢያንስ 60 ሚሊዮን ገደማ የሚሆነው ህዝብ የዚህ መንፈሳዊ መነቃቃት ውጤት ነበር፡፡ ጆን ዊስሊን ለትልቅ የእግዚአብሔር ስራ ያዘጋጀውና በወንጌል ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲል ይደመጥ የነበረው መፈክር ‹‹ የሁላችን ዓላማ አንድ ይሁን ፤ሁላችንም ለዚህ ዓላማ እንኑር ፤የራሳችንን ነፍስ ለማዳን ደግሞ እኛን የሚሰሙንን ነፍስ ለማዳን የሚል ነበር፡፡
  ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ ማለትም በ17ኛው ክ/ዘመን በዚየው በእንግሊዝ አገር ተነስቶ የነበረው እውቁ ወንጌላዊ ጆርጅ ዋይትፊልድ ይባላል፡፡ ታሪኩ እንደሚያስረዳው ብርቱ የጸሎት ሰው ነበር፡፡ ፊቱም እንደሙሴ ያንጸባርቅ ሁሉ እንደነበር ይነገራል፡፡ ጀርጅ ዋይትፊልድ እንዲህ ብሎ ይጸልይ ነበረ ‹ ጌታ ሆይ ነፍሳትን ስጠኝ ወይም ነፍሴን ውሰድ /give me souls or take my soul   /፡፡ ጌታ ረድቶት ለዚያ ዘመን ትውልድ ብርሐኑ በርቶ አንቀላፍቷል፡፡
     ሌላውና በስኮትላንድ ለተነሳው ሪቫይቫል ዋነኛ ተጠቃሽ የሆነው  ሰው ጆን ኖክስ / John Knox / ይባላል፡፡ ሌሊቱን ሙሉ በጩኽትና በሲቃ ድምጽ ስለነፍሳት በመቃተት የሚጸልይ ሰው ነበር፡፡ የገዛ ባለቤቱ ትንሽ አረፍ እንዲል በተደጋጋሚ ብትለምነውም የእርሱ መልስ ግን ‹ የአገሬ ህዝብ ሳይድን እንዴት መተኛት ይቻለኛል /    / ፡፡ሲጸልይም ‹ ስኮትላንድን ስጠኝ ወይም ግደለኝ › የሚል ነበር፡፡

   የሳልቬሽን አርሚ መስራች የነበረውና ለወንጌል ትልቅ ቅንዓት የነበረው ዊልያም ቡዝ በአንድ ወቅት የእንግሊዝ ንጉስ አንድ ጥያቄ ጠይቀውት ነበር ይባላል፡፡‹‹ ቡዝ በህይወትህ ትልቁ ትግልና ጥማትህ ምንድን ነው ሲሉ ፡፡፡ እርሱም ሲመልስ “ sir some men’s passion is for gold, other men’s passion is for fame, but my passion is for souls”/አንዳንድ ሰዎች ትልቁ ፍላጎታቸው ወርቅ ማግኘት ይሆናል ፣ ሌሎቹም ዝነኛ ለመሆን ሊመኙ ይችላሉ የእኔ የህይወቴ ጥማት ግን ነፍሳት እንዲድኑ ነው፡፡/ ብሏል፡፡
ማጠቃለያ፡-…..

          ክፍል ሁለት

     በዚህኛው ክፍል ላይ በስፋት የምናተኩረው የወንጌል ምስክርነትን ከየትና ከምን እንደምንጀምር ማወቅ ላይ ነው፡፡በክፍል አንድ ላይ እነደተገለጸው ስለ ወንጌል መቅናትን ሰዎችን የማዳን ሸክም ውስጣችን ከተቀመጠ በኋላ ቅርባችን ካሉ ፣ለምናውቃቸው ሰዎች መጸለይና መመስከር መጀመር አለብን፡፡በተለይ ወደ ፊት እመሰክርላቸዋለሁ ብለን ለምናስባቸው ህብረተሰብ ክፍሎች ቅድሚያ ለምን መጸለይ እንደሚገባን ማወቅ አለብን ፡፡ ከዚህ ንዑስ ርዕስ በፊት ግን ምስክርነታችንን ስለምንጀምርበት ትክክለኛ ቦታ ከቃሉ ላይ እንማር፡፡ታላቁ ትዕዛዝ በተሰጠበት የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 28 ፡18-20 እንዲህ ይላል፡- ‹‹ …እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና ፣በመንፈስ ቅዱስ ስም እያተመቃችኋቸው ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡››
  በዚህ ቃል ውስጥ አህዛብ ተብሎ የተጠቀሰው ቀጥታ ህዝብን ለማመልከት ነው እንጂ በአባባል ብዙ ጊዜ እንደተለመደው ከእስራኤል ውጪ ያሉ አረማውያንን የሚወክል ብቻ አይደለም፡፡ምክንያቱም ይህ ቃል ራሳቸውን እስራኤላውያንን ጭምር የሚመለከት ነውና፡፡ ትዕዛዙ ጥቅል ትዕዛዝ ይመስላል፡፡በጠቅላለው ወደ ዓለም ህዝቦች ሁሉ መሄድ፣ ማስተማር ፣ማጥመቅና ደቀ መዝሙር ማድረግን ያጠቃልላል፡፤ሰውን በመጨረሻ ልናደርገው የምንችለው ደቀ መዝሙር ነው ፡፡ በቃ ከዛ ማለፍ ነው ወደ ሌላ ጣጣ እያስገባ ያለው፤፤ ሌላ ደግሞ ወንጌል የተወሰኑ ግሩፖችን፣ ግለሰቦችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን ለአህዛብ ሁሉ እንድንሰብክ እንደታዘዘ እናያለን፡፤ጾታን፣ ዕድሜን፣ የትምህርት ደረጃን፣ ዘርን፣ ቋንቋን ፣ ሳይለይ የዓለም ህዝብ ሁሉ ወንጌል ሊሰበክልት ይገባል፤፤
አስቀድመን እንዳልን የማቴዎስ ወንጌል ጥዕዛዝ ጥቅል ቢሆንም ሐዋርያት ስራ 1፡8 ግን ከየት መጀመር እንዳለባቸው በግልጽ ተቀምጧል ‹‹…ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ሀይልን ትቀበላላችሁ፡፡ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆነላችሁ አለ፡፡››
  የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጸሐፊ ሉቃስ  ሐዋርያት የወንጌል ምስክርነታቸውን ከየት እንደሚጀምሩ ጌታ የሰጠውን ሌላ ትዕዛዝ ነው ያተተው፡፡ስትጀምሩ ከኢየሩሳሌም ነው ከዚያ ወደ ዓለም ዳር ድረስ ሂዱ ነው፡፡ ምስክርነትን ከኢየሩሳሌም መጀመር አግባብም ነው፡፡ ኢየሩሳሌም ለበጉ ሐዋርያት በጣም በቅርበት የሚያውቋትና የኖሩባት ከተማ ነች፡፡ ባህሉ፣ ህዝቡ፣ ቋንቋውን ፣መልክዐ ምድራዊ አቀማመጡን በደንብ ያውቁታል፡፡ ምናልባት የመንደሮቹ መውጫና መግቢያ በእነርሱ ዘንድ የታወቀ ነው፡፡ ከሚያውቁት ቦታ ና ህዝብ ምስክርነታችሁን ጀምሩ የሚል ነው ትዕዛዙ፡፡ከዚያም በቅርበት ወዳለ ሌላ ከተማ ወደ ይሁዳ ፣ ከዚያም ሲያልፍ ወደ ሰማርያ ከዚያም እያሉ እስከ ምድር ዳር ድራ መሄድ ነው፡፡
የእኛ ኢየሩሳሌም፣ ይሁዳና፣ ሰማርያ ማን ናቸው?

    ኢየሩሳሌምን፣ ይሁዳንና፣ሰማርያን በሐሳባችን ይዘን ለእኛ እነዚህ ምን ማለት ናቸው ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ምናልባት የእኛ ኢየሩሳሌማችን ቤተሰባችን ቢሆን፣ ጓደኞቻችን፣ አካባቢያችን፣ ያለንበት ከተማና ህብረተሰባ፣ሊወክል ይችላል፡፡ከዚያም ትንሽ ቀረብ ብሎ ያለው ይሁዳችን ይሆናል እየቆየ የሚገለጥልን በቅርብ ርቀት ላይ ያለው ደግሞ ሰማርያችን ይሆናል፡፡ ነገር ግን በማንኛውም ሁኔታና መስፈርት ቢሆን በቅድሚያ ሸክም ሊሰማን የሚገባው በቅርባችን ላለ ለምናውቀውና ላደግንበት ህብረተሰብ እንደሆነ እሙን ነው፡፡እኛው ራሳችን የዚያ ህብረተሰብ አካል ነንና፡፤ እንዲህ እያልን ወደ ሌሎች ህዝቦችና አህጉራት ምስክርነታችንን እያሰፋን እንሔዳለን፡፡
    እንግዲ ኢየሩሳሌምላይ የተጀመረው የወንጌል ስብከት ዛሬ በዓለም ላይ በርካታ ቦታዎችን በማዳረስ ቢሊዮኖችን በእግዚእብሔር መንግስት ውስጥ እንዲጨመሩ አስችሏል፡ የተቀረውና በወንጌል ያልተደረሰው ህዝብ ብዙ ቢሆንም ቅሉ ፡፡ በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው  በምንኖርባት ፕላኔት ላይ  ከሚገኙ 11,640 ብሔር ብሐረሰብ መካከል 6,734 ገደማ የሚሆነው ወንጌል ያልደረሰው እንደሆነ ታውቋል፡፤ ይህ ማለት መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ ሌሎች መንፈሳዊ ጽሑፎች በቋንቋቸው ያልተተረጎመላቸው፤በቋንቋቸው የሚመሰክርላቸው አገልጋይ የሌላቸው ናቸው፡፡ይህ ባለሆነበት ሁኔታ ደግሞ የሚካፈሉበት ቤተክርስቲያን አላቸው ብለን አንጠብቅም፡፤ እንደዚህ ያለውን ዜና ስንሰማ ልባችን ይነካል፡፤
በሌላ ሙያዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች አንድ የሚፈልጉትን ነገር ለማግኘት፣ ወይም ምድራዊውን ሐብት ለማካበት ፣የተወሰነ ዕውቀት ለመቅሰም..ሲሉ የሌላውን ህዝብ ባህልና ቋንቋ በደንብ አጥንተው ፣ጊዜ ወስደው አስበው ሙዋለ ነዋያቸውን አፍሰው የሚፈልጉትን በሚያደርጉበት በዚህ ጊዜ በተመሳሳይ መልኩ ወገኖቻችንን ከዘላለም ሲኦል ለመታደግ የእነዚያን ህብረተሰብ ባህል፣ ቋንቋ .እምነትና ስርዓታቸውን በወጉ አጥንቶ ከሞት ሊታደጋቸው የሚችል የወንጌል አርበኛ ብርቅ ሊሆንብን ባልተገባ ነበር፡፡
   በእርግጥ ጥቂቶች በመካከላችን ስላሉ ነው የተወሰነ ስራም እንኳ የተሰራው፡፡ ከሞቀ ከደመቀ ስራቸውና ኑረሯቸው እየወጡ ለሌላ አህጉር ህዝብ ራዕይን እየተቀበሉ ድንበር አቋርጠው የሚሰብኩ ጀግኖች አሉ፡፡ካልዳነው በወንጌላ ካልተደረሰው ሰፊ ህብረተሰብ አንጻር ግን ገና ሰፊ ስራ እንደሚጠብቀን ያሳያል፡፡ ጌታ ኢየሱስ እንደ ተናገረው መከሩ ብዙ ነው ሰራተኞች ግን ቂቶች ናቸው ፤የመከሩ ባለቤት ሰራተኞችን እንዲልክ ጸልዩ ብሏል፡፡ ዮሐ.4፡፡
  በምድራችን በኢትዮጵያ ላይ በተመለከተ እግዚአብሔር የረዳቸውና  የተለያየ የወንጌል እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ባለ ራዕዮች አልጠፉም፡፡አንዳንዶቹ በዩንቨርስቲ እና በኮሌጅ ለሚማሩ ሰተማሪዎች የወንጌል ሸክም ያነገቡ ሲሆን፣ ሌሎች ገና በማደግ ላይ ላሉ ህጻናት ከስር ኮትኩተው ለማሳደግ ሸክም የተሰጣቸው፣ ሌሎች በአባት ጠረተኞች፣ የጎዳና ላይ ተደዳሪዎች፣ አሁን አሁን ገዳማት ላየ፣ ሴቶች ላይ፣ ባለስላጣናት ላይ፣ እስር ቤት ላይ፣ ነጋዴዎች ላይ፣ እርቲስቶችና ሙዚቀኞች ላይ፣ እስፖርተኞች ላይ በተለየ ሸክም የሚሰሩ ተነስተዋል፡፤ በቅርቡ እንደሰማሁትም ለሱማሌያውያን ሸክም ተሰምቷቸው ቋንቋቸውን እያጠኑ ያሉ ወንድሞች እንዳሉ ነው፡፡
    በአንድ ወቅት በግሬት ኮሚሽን ኢትዮጵያ በተደረገው ጥናት መምሪያ ላይ እንደነበብኩት ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ከ83 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል 33 ያህሉ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ወንጌል ያልደረሳቸውና አንድም አጥቢያ ቤተክርስቲያን ያልተተከለባቸው ቦታዎች እንደሆኑ ነው፡፡ቢያንስ መጽሐፍ ቅዱስ እንኩዋ ገብቶ ለማደል እንዳይቻል በቋንቋቸው የተተረጎመ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር አማካኝነት ወደ ተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች አዲስ ኪዳንንና ሙሉውን የያዘ ለመተርጎም ተሞክሯል፡፡ እስካሁንም ጥረቱ ቀጥሏል ቢሆንም ገና ከ ሃምሳ በላይ ብሔር ብሔረሰቦች በቋንቋቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲተረጎምላቸው ይጠብቃሉ፡፡ እግዚአብሔር ገንዘብ የሰጣቸው ግለሰቦችና አብያተክርስቲያናት ይህ ሰፊ ስራ እንዲታያቸው ጸሎቴ ነው፡፡በእርግጥ ብዙ ነገሮችን ስላለመደረጋቸው ጉዳይ ሲነሳ የሰው እጥረት፣ የገንዘብ እጥረት መኖሩ ቢሰማም በእኔ እምነት ግን ክፍተቶችን የሚያይ መጥፋቱ እንጂ የሐብት ጉድለት ያለ አይመስለኝም፡፡ ምክንያቱም ጥቂት የማይባሉ ገንዘቦች እምብዛም አንገብጋቢ በበቂ ሁኔታ እግዚአብሔር አንዳንድ ቅዱሳንን እንደባረካቸው ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን ስንቱ ነው ጌታ ለዚህ ጊዜ አስቦ እንደሆነ የባረካቸው የገባቸው? ወንጌል ያልደረሰበት ቦታ ላይ በእነርሱ አስተዋጽኦ ሊያደርሱ፣ የጎደለውን ሊሞሉ ንደሆነ አውቀው የሚንቀሳቀሱ፤ ምናልባት ለአስቴር የተባለውን የመርዶክዮስን ቃል ማስታወስ ተገቢ ይሆን? እንዲህ ነበር ያላት ‘’ በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል : …ደግሞስ ወደ መንግስት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደሆነ ማን ያውቃል?’’ አስቴር 4፡13-14

         የጳውሎስ ጥሪ ወዳልተገረዙት

   በወንጌል ስለምንደርሰው ህዝብ አይነት ለማወቅ እና የመንፈስ ቅዱስን ትክክለኛ የተልዕኮ አቅጣጫ ለመለየት በእግዚአብሔር ፊት መቆየቱ አስፈላጊ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ በተለየ መለኮታዊ አሰራር አብረን እንድንኖርና እነድንላመድ ለተደረግንበት ህዝብ / ህብረተሰባ / ሸክም ሊሰጠን ይችላል፡፡ በስራ ጉዳይ እን በለተለያዩ ጥናቶች ትምህርቶች ወደ ተለየ ህብረተሰብ ክልል ሄደው እዚያው የቀሩ ራዕዕይና ሸክማቸው ከዚያ ህዝብ ጋር ተቆራኝቶ እስከ ህይወታቸው ህልፈት ድረስ ለተሰጣቸው አደራ ሲተጉ የነበሩ አሁን፣ም እየተጉ ያሉ በርካታ ናቸው፡፡አልፎ አልፎ ደግሞ ምንም ወደማናውቀው እና ወዳልተለማመድነው ህብረተሰብ ርቀን እንድንሔድ ልንላክ እንችላለን፡፡ለምሳሌ በቀደምት ሐዋርያት መካከል ከነበረው ታሪክ የሐዋርያው ጴጥሮስንና ጳውሎስን ታሪክ ለአብነት ብናነሳ‹‹ ..ጴጥሮስ ለተገረዙት ወንጌልን እንዲሰብክ አደራ እንደተሰጠው እኔም ላልተገረዙት ወንጌልን እንድሰብክ አደራ እንደተሰጠንኝ ተገነዘቡ፡፡ ጴጥሮስ ለአይሁድ ሐዋርያ እንዲሆነ የሰራ እግዚአብሔር በእኔ የአህዛብ ሐዋርያዊ አገልግሎትም ሰርቷል;›› ገላ.2፡7-8 እንደሚል ሁለቱንም ሐዋርያት ሰው በሚገምተው መልኩ አልነበረም የተላኩት ፡፡በተለይ ጳውሎስን ስናስብ ብዙ ጉዳዩ ከተሳሰረው ህዝብ መሀል አልነበረም ያገለገለው፤ ይልቁን ወዳልተገረዙት እንዲሔድ ታዘዘ፡፡ ትምህርቱና ባህሉ ግን ከተገረዙት ጋር እንውል የሚያስደርግ ነበር፡፡
 የሐዋርያውበ ጳውሎስ የአገልግሎት ሸክም የሚከተለውን ይመስላል፡-
 በቅድሚያ የጳውሎስ ትውልድ ስፍራው ተርሴስ ይባላል፡፡በሮማውያን የቅኝ አገዛዝ ዘመን ቤተሰቦቹ በተርሴስ ከተማ የሚኖሩ ይመስላል፡፡ በአባቱ በኩል አጥባቂ ፈሪሳዊ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ስለዚህም እንደማንናውም የፈሪሳውያን ልጆች ሐይማነኖተኛ በቀነ ሶስት ጊዜ የሚጸልይ ነበር፣ በሌላ መልክ የዓለማዊ ትምህርቶችን ከግሪክ ፍልስፍናና ከሮማውያን ስልጣኔ ጋር አዋህዶ  የሚያውቅ፤በአንዳንድ ጽሑፎቹ ውስጥ ይህንን ዕውቀቱን ሲያንጸባርቅ ይታያል፡፤ለምሳሌ ያህል ስለሮማውያን ወታደራዊ ትጥቅ /ኤፌ.6/፣ ስለ ግሪክ ስፖርታዊ ጨዋታ /ኦሎምፒክ/…./ / በተለያየ ስፍራዎች ላይ ማንሳቱን መጥቀስ ይቻላል፡፡
በመንፈሳዊው ዓለም በጊዜው ከነበረው ዕውቁ የአይሁድ መምህር ገማልያል ስር እንደተማረ ና ሂላልና ሻማይ በሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ ሰፊ ዕውቀት እንደገበየ ይነገራል፡፡ ስለዚህም ነው በበርካታ ጽሑፎቹ ውስጥ ብሉይ ኪዳንን ከአዲስ ኪዳን ጋር በማመሳከር የታወቀው፡፡
  ከዕለታት አንድ ቀን ግን ህይወቱን 360 ዲግሪ የቀየረ ክስተት ሆነ ፡፡ ቦታው የሶሪያ ዋና ከተማ ደማስቆ ላይ ሲሆን ደብዳቤ ከቤተ ክህነት አጽፎ የጌታን ደቀ መዛሙርት ክፉኛ ሲቃወምና ሲያሳድድ ብሎም እየደበደበ ሊያሳስራቸው ሲሄድ በመንገድ እንዳለ ብርሐን ከሰማይ አንጸባርቆ ‹‹ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ  የሚል ድምጽ ሰማ›› ሥራ.9 1-6፡፡ ከዚያም መሬት ላይ ተደፍቶ አንድ ጥያቄ ጠየቀ ፣ ‹ የማሳድድህ አንተ ማን ነህ ? › ጌታም አንተ የምታሳድደኝ ኢየሱስ ነኝ ፡ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሀል አለው፡፡ ከዚያም በተነገረው መሰረት ከሐናንያ ጋር ተገናኘኝቶ እርሱም ጸልዮለት፣ ከአይኑም ቅርፊት ወድቆ : በመንፈስ ቅዱስም ተሞልቶ ተመለሰ፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮም የሚቃወመውን ወንጌል እርሱ ደግሞ ይሰብካል ተብሎ  ስደት እስኪ ደርስበት ድረስ መከራ ተቀብሎአል፡፡
  የሐዋርያውን ህይወት እንደዚህ የተረዳ ሰው ህግን በዚህ መልክ ጠንቅቆ የሚያውቅ፣ እንደዚህ ያለ አክራሪ ሐይማኖተኛ በውል ከሚያውቀው ህብረተሰብ ውጪ ራዕይና ሸክም ይሰጠዋል ብሎ መገመት በጣም ከባድ ይሆናል፡፤ነገር ግን የሆነው እንደዚህ ነው በሐዋርያት ስራ 13 ላይ ነብያት ከደቀ መዛሙርት ጋር በሚጸልዩበት ጉባኤ መካከል መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስንና በርናባስን ለጠራኋቸው ዓላማ ለዩልኝ በማለት በማረጋገጫ ወደ አህዛብ አገር በመሔድ ወንጌል ሰብኳል፡፡ ከተለያዩ አገልጋዮች ጋር በመሆን በስፍራዎች ሁሉ በመዘዋወር አገልግሏል፡፤ ለምሳሌ ከዴማስ፣ ከበርናባስ፣ ከቲቶ፣ ከጢሞቴዎስ ና ከሲላስ…ጋር በመሆን በርካታዎችን ለክርስቶስ ማርኳል፤ አብያተ ክርስቲያናትን ተክሏል፡፡ጥቂቶቹ በጉዞ አብረውት ካገለገሉት መካከል በእርሱ እጅ መንፈሳዊን ነገር እየተካፈሉ ያደጉ ናቸው፡፡

       የጴጥሮስ የአገልግሎት ጥሪ

የሐዋርያው ጴጥሮስ ታሪክ የሚጀምረው አሳ ዐትማጅና ያልተማረ የገሊላ ሰው እንደነበረ ነው፡፡ ወደ ጌታ የመጣው በወንድሙ በእንድርያስ አማካኝነት ሲሆን ፤እንድርያስ በጊዜው የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረ ነው፡፤ ‹ያልተማሩ› ተብሎ በተደጋጋሚ ስለ ደቀ መዛሙርት የተጻፈበት ቦታ የሚያመለክተው የሙሴን ህግ ማለትም የሕግ መጻሕፍትንና የነብያትን መጻሕፍት አልተማሩም የሚል ነው፡፡በዚያን ጊዜ ብዙ የሐይማኖት ቡድኖች በጎራ ሆነው እንደየመረዳታቸው መጠን ለእንደሚቀኑት ዓይነት ሰዎች አለመሆናቸውን ለመግለጽኘው፡፡
በአብዛኛው ኑሮአቸውን ለማሸነፍ  ልፋት የተቀላቀለበትን ስራ ከመስራት ውጪ አማራጭ የሌላቸውና ከ የሐይማኖት ጉዳይ ብዙም ሳያውቁ ደግሞ ሳይቀኑ ዝም ብለው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ታዲያ በዘመኑ ህጉን አብጠርጥረን እናውቃለን ፣ ከኛ ወዲያ ላሳር ! ለሚሉት አይሁዶች ሐዋርያ መደረጉ ምን ያህል የእግዚአብሔር ጥሪ አስደናቂ እንደሆነ እንመለከታለን ፡፡ ያልተማሩትን ተማርን ፣አወቅን ወደ ሚሉት ህብረተሰብ ሊልክ ይችላል፡፡ የተማሩትን ደግሞ አንዳች እውቀት ወደ ሌላቸው ህብረተሰብ ክፍል ሊልካቸው ይችላል፡፡ ለዚህም ነው ስለ ጥሪ በስጋ ዕውቀት ትንታኔ መስጠት ብዙ አስቸጋሪ የሚሆነው፡፡
በኛም ዘመን እግዚአብሔር አንዳንዶቻችንን ቋንቋቸውን ወደማናውቀው ህዝብ ዘንድ ሊልከን ይችላል፡፡ወገናችን ባለሆነ እንግዳ ህዝበ መሀል ለአገልግሎት ብንሾም በዚህ አግባብ መሰረት ሊደንቀን አይገባም፡፡ ትልቁ ጉዳይ በትክክል ለማን  እና ወዴት እንደተጠራን ለይቶ ማወቁ ላይ ነው፡፡
    እንዳንድ የምዕራባውን አገሮች ስሜታችንን በስጋ ሊያዘነብሉት ያቃጣቸዋል ፡፡ እናም ብዙ ሰው በጥረ ሰበብ ኪሳራ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህ ማለት የምንጠራበት ቦታ ሁሉ ተመችቶን እንኖራለን ማለት አይደለም፡፡ ይህንን የምንለይበት ነገር ውስጣዊ ሰለምና እረፍት ስለሚሰማን እንጂ ውጫዊ በሆኑ መለኪያዎች ልንመዝን አንችልም፡፡ በጥሪው ያረፈ ሰው ነፍሱ ታውቀዋለች ፡፡ በዚህ ላይ ፍሬውን ማየት ይቻላል፡፡
ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ ያለ ስፍራ በመሆን ማለትም የተጠሩበትን ሸክም ችላ ማለት ወይም መተው አልያም ነነዌ እየተጠበቁ ተርሴስ ለመኖር መኮብለል የሚያመጣው ምስቅልቅል ብዙ ነው፡፡ ብዙዎች ደስታን አጥተው ሰላም አጥተው ከነሱ አልፎ በዙሪያቸው ላሉ ሁሉ የነውጥ ምክንየትሆነው የሚኖር አይጠፉም፡፡ቶሎ ገብቷቸው ጌታ ወደሚፈልጋቸው ህዝብና ቦታ ቢሄዱ ምንኛ እረፍታቸውበበዛ// እርሱ ያለው ላይቀር ትርፉ መላላጥ ነው፡፡ደግሞስ የተፈጠርንበትን ዓላማ ኖሮ ከማለፍ የበለጠ አስደሳች ነገር ምን አለና?!
       የወንጌል ምስክርነት ዘዴዎች

  ወንጌል ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ የእግዚአብሔር ሰዎች ሲሰበክ ቆይቶ እዚህ ደርሷል፡፡ ከአንድ ህዝብ ወደ ሌላ ህዝብ ፣ ከአንድ አገር ወደሌላ አገር ፣ወደ ተለያዩ ቋንቋዎች እየተተረጎመ በሀይል እየሮጠ ነው፡፡ ቴክኖሎጂውም ብዙ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ወንጌልን የሚሰብኩ ሰዎች ዕድሜና ሁኔታዎች ገድበዋቸው የሚቆሙ ና ብሎም የሚያልፉ ቢሆንም ፤ወንጌል ራሱ ግን አይታሰርም ! አይቆምም፡፡ ሁልጊዜ እያዳነ፣ እየለወጠ ይሄዳል፡፡ መቼም ቢሆን ወንጌል መልዕክቱ ሊቀየር አይችልም ፡፡ ወንጌል የምናሰራጭበት መንገዱ ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ወንጌልን ለዓለም እንዲሰበክ አበክሮ ይገልጻል እንጂ የማሰራጨት መንገድና  ዘዴው በየዘመናቱ ስለሚለያይ ገደብ አልተሰጠውም፡፡ ስለዚህ ወንጌልን ይዘቱንና ፣ማንነቱን ሳንሸራርፍ ልንሰብክ እንችላለን ማለት ነው፡፡
  ከዘመኑ የህብረተሰቡ ዕድገትና ፍጥነት አንጻር ስንቃኘውም ወንጌል የማሰራጫው መንገድና ዘዴ ለዚህ ትውልድ በሚመጥን መልክ መዘጋጀት እንዳለበት አምናለሁ፡፡ ለምሳሌ በድሮ ዘመን ወንጌልን በራዲዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በተለያዩ ድህረ ገጾች፣ ላይ ማስተላለፍ አይቻልም ነበር፡፤ ዛሬ ላይ ግን ምናልባት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የዚህ ነገር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡፡ እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ተጉዞ ተጉዞ በእግዚአብሔር ፍቃድ እጃችን ላይ ደርሷል፡፡
 ስለዚህ አሁን እኛ ልንጠይቅ የሚገባን እጃችን ላይ በዕድል የደረሰውን ወንጌል ለዚህ ትውልድ በምን መንገድ እናድርስ ? የሚል ነው: ትውልዱ ምን ውስጥ ነው ያለው? ምን ብናደርግ ጆሮ ሊሰጠን ይችላል?
  ቀደምት የወንጌል ሚሽነነሪዎች ለስብከት ወደ አፍሪካ በመጡበት ወቅት በርካታ ዘዴዎችን ይጠቀሙ እንደነበረ ታሪክ ይዘግባል ፡፡ በዚያን ጊዜ የሰሯቸው ሆስፒታሎች: የትምህርት ተቋማት ቋሚ ምስክር ናቸው፡፡ንጹህ ውሐ መጠጥ ባልተዳረሰበት አንዳንድ የገጠር አካባቢዎች ላይ ጉድጓድን በመቆፈር ውሐን በማቅረብ፣  ህጻናትን ከስር ኮትኩቶ ለማሳደግ እንዲመች ማሳደጊያ፣ ማቆያ፣ መማሪያ ትምህርት ቤቶችን በመገንባት አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ የተለያዩ የሙያ ማሰልጠኛ ተቋማትንም በመክፈት ለብዙ ወታቶች ሙያዊ ትምህርት እንዲቀስሙ አድርገው ራሳቸውን አስችለዋል፡፡ በዚህ ሁሉ ድርጊታቸው ዋነኛ አጀንዳቸው የሆነውን ወንጌል ለበርካቶች እንዲናገሩ ዕድል ከፍቶላቸዋል፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማደል፣ መንፈሳዊ ጽሑፎችን በማሰራጨት፣ ከዚም አብያተክርስቲናት እንዲተከሉ ምክንት ሆነዋል፡፡በእርግጥ ዛሬ ላይም ቢሆን ይህ መንገድ አዋጪ የሚሆንበት ሁኔታ በስፋት አለ፡፡ በቅርብ ጊዚት የደቡብ ኮሪያ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ውስጥ አንድ ትልቅ ዘመናዊ ሆስፒታል ከፍተው አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ አስገራሚው ነገር ዘመነኛ የህክምና መሳሪያዎች የተገየጠመበት መሆኑ ሳይሆን በሽተኞችን ከማከም ጎን ለጎን እየተሰራ ያለው የወንጌል ስራ ነው የሚያኮራው ፡፡ለምሳሌ ትራክቶች ገና መመዝገቢያው ቦታ ላ በነጻ ይታደላሉ፣ መንፈሳዊ የመዝሙር  ቪዲዮ /ቪሲዲዎች/ በቴሌቪዥን መስኮት በአደባባ ላይ ይለቀቃሉ፣ ጸሎትን ምክር ለሚያስፈልገው ለብቻው ክፍል ተዘጋጅቶለታል፤ አገልጋም መድበዋል፡፡ ይህ እንግዲህ ምን ያህል ስራ እየተሰራበት እንዳለ ሁሉም መገንዘብ ይችላል፡፡
የዘመኗ ቤተክርስቲያን የአሁኑን ትውልድ ስታስብ ልታደርግ የምትችለውን ነገሮች ጠንቅቃ ማወቅ ይኖርባታል፡፡ ለምሳሌ የወንጌልን መልዕክት ያዘሉ በራሪ ጽሑፎችን በሚስብ መልክ ማዘጋጀት፣ፊት ለፊት ካለው ርዕሳቸው ጭምር በደንብ ታስቦበት ቢዘጋጅ፤ ሌላው ደግሞ እያንዳንዱ አጥቢያ ቤተክርስቲያን አካባቢው ላ ለውን ችግሮች በደንብ አጥንቶ ችግሮችን በምን መልክ መቅረፍ እንደሚቻል መመካከር ፤ በተጨማሪ አካባቢው ላ ባለ ፍላጎት ላ ተመስርቶ ለወታቶች ፣በዕድሜ ለገፉ፣ ለህጻናት ነ ለእናቶች ..ወዘተ ብሎ በመከፋፈል በእነዚህ ላይ ራዕይ ይዞ መንቀሳቀስ ጥሩ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ባለሙያዎችን በማሰባሰብ ከሌላም ቦታ በጎ ፍቃደኞችን በማቀናጀት ነጻ የህክምና ምርመራን ለህብረተሰቡ መስጠት፣ስለ ጤና አጠባበቅ ትምህርት መስጠት፣ወጣቶች የሙያ ሰልጠና እንዲያገኙ በተለያየ መልኩ ማገዝ፣ አካባቢውን በተወሰነ ጊዜ የወንጌል ካኔቴራዎችን በመልበስ ጽዳት ማካሔድ፣ህብረተሰቡን እያሳተፉ ጉዞዎችን ማድረግ፣ አንዳንድ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ማካሔድ፣ የተማሪዎች የክረምት ስልጠና፣ ለማትሪክ ለሚዘጋጁ ተማሪዎች የትምህርትና የሞራል ድጋፍ በማድረግ ወንጌልን መስበክ ይቻላል፡፡
ብዙ ምስክርነቶች የሚካሄዱት አንድ ለአንድ የወንጌል ስርጭት ወይም ክሩሴድ፣ ፌስቲቫል በማድረግ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ለአንዱም ሆነ የጅምላው ውጤት የሚኖረው በጽኑ የነፍሳት ፍቅር ና ርህራሄ ተሞልተን እስካደረግነው ድረስ ብቻ ነው፡፡ ጀማምረን የማንተወውም ይህ ሲገባን ይመስለኛል፡፡

     የ አንድ ለአንድ ምስክርነት ዘዴ

የአንድ ለአንድ የወንጌል ስርጭት ዘዴ በጣም ውጤታማ የሚባል ሲሆን ብዙ አማኞች ለጓደኞቻቸው ወይም ለቤተሰቦቻቸው በቀላል ሁኔታ ሊመሰክሩበት የሚችሉበት ዘዴ ነው፡፡ ከማናቸውም አይነት ሰው ጋር ጨዋታ ለመጀመር ርዕስ ልንመርጥ እንችላለን ርዕሱ ማንናውም እርስ በርስ ለመግባበት የሚረዳ እሰከሆነ ድረስ ችግር የለውም፡፡ ኢኮነሚው ቢሆን፣ ሰፖርት ቢሆን፣ …ወዘተ ችግሩ በዚያው ዘልቀን መመለሻው ከጠፋን ነው፡፡ ለምሳሌ በስፖረቱ ዓለም ጀምረን ተጫዋቾችን አንድ ባንድ እያነሳን እነ ካካን ሜሲን አንስተን ኢየሱስን ካላነሳን ችግሩ ያኔ ነው፡፡ ‹‹ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን  እንሰብካለን፡፡›› 1ቆሮ.1፡23

         የወንጌል ክሩሴድ ወይም ፌስቲቫል

አሁን አሁን ክሩሴድ የሚለው ቃል ከፖለቲካዊ ነገሮች ጋር በግድ እየተገናኘ ጠማማ ሰዎች እንቅፋት እየፈጠሩበት በመሆኑ ፌስቲቫል በሚል እየተተካ ትልልቅ ፕሮግራሞች እየተካሔዱበት እንዳለ አንድ ወዳጄ አጫውቶኛል፡፡ ዞሮ ዞሮ አላማው አንድ እስከሆነ ድረስ ቃሉን በቀጥታ መጠቀምም ሆነ በተዘዋዋሪ መጠቀም ያን ያህል ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡፡ ዋናው ነገር ፌስቲቫሉ ወደ ሌላ ፌስቲቫልነት መንገዱን ስቶ እንዳይሔድ፤ ሞቅታው በጨመረ ቁጥር መቆጣጠር ሊያስፈልገው ይችላል፡፡ የፕሮግራሙ እንቅስቃሴዎች በተቻለ መጠን ከክርስቶስ የማዳን ስራ ጋር የተገናኘ እንዲሆን አበክሮ መስራት ይጠይቃል፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚሰማውና እንደሚታየው ግን ክርስቶስን ማዕከል ባላደረጉ ርእሶችና ንግግሮች ላይ ጊዜ ስለሚፈጅ የታለመለትን ግብ በትክክል ላይመታ ይችላል፡፡ የቅዱሳን ፣ የሰማዕታት፣ የመላዕክትና የመሳሰሉት ጉዳዮች ያለቦታው ማንሳት ማለት በክሩሴዱ ላይ በስንት ልፋት የሰበሰብናቸው ነፍሳት ዋናውን የወንጌል ዜና እንዳይሰሙ ጆሯቸውን መድፈን ማለት ነው፡፡ አስታውሳለሁ በአንድ ስብሰባ ላይ በርካታ አዳዲስ ሰዎች በተጋበዙበት፡ ሰባኪው ‹ኢየሱስን የማይወድ የተረገመ ነው › የሚል ጥቅስ  ከቃሉ ጠቅሶ ሰዎችን ማስከፋት ብቻ አይደለም ያስቆጣበት ክስተት፡፡ ቃሉ እውነት ቢሆንም የዚያን ቀን ግን ባይደረግ! ደግሞ ትንሽ ስሜታዊነት የሚያጠቃቸው ቅዱሳን ነገሩን በጣም እያጋጋሉ ከጎን ያለው ሰው የተረገመ እንደሆነ ይነግሩት ስለ ነበር፡ በወቅቱ በጣም ነው ያዘንኩት፡፡ ምናለበት እንደዚህ ያሉትን ጊዜያት የሰዎችን አይን ሊከፍት የሚችል በትህትና የሆነ በርህራሄ የሆነ የፍቅር ወንጌልን ብንሰብካቸው? መላዕክት፣ ቅዱሳን ሌላ የማይመለከተንን ጉዳዮች የማንቀላቅልበት ቢሆን? በእርግጥ መንፈስ ቅዱስን አድምጠን ከሆነ ሰዎችን ያበሳጫቸዋል ያልነው ነገር ይልቁንም ፈውሷቸው ይሄዳሉ፣ከስጋችን ተነሳስተን ሰዎች ለጊዜውም ቢሆን በልባቸው ውስጥ ትልቅ ስፍራ ከሰጧቸው ነገሮች ጋራ አታካራ መፍጠር ግን ብዙ አዋጭ አይደለም፡፡ ውሻ እየጋጠ ያለውን አጥንት በሀይል ለመቀማት የሚሞክር ባለቤት እንኩዋ ቢሆን መነከሱ አይቀርም፡፡ በዘዴና በጥበብ ግን ከእርሱ ማሸሽ ይቻላል፡፡ እየጋጠ ያለውን አጥንት መታገል ለጊዜው ትቶ ሌላ ሊበላ የሚፈለገውን ምግብ አጓጊ በሆነ መልክ አቅርቦ መጋበዝ ከዚያ ውሻው ተስቦ ወደ አዲሱ ምግብ ሲመጣ ቀስ ብሎ ያልተፈለገውን ምግብ ከስፍራው ላይ ማንሳት፡፡ ለሰውም እንደዚሁ ነው፡፡ አንዳንድ ክርክር የሚያስነሱ ነጥቦችን ለጊዜው አለማንሳት ና በጋራ ክርስቶስን ማዕከል ባደረጉ ጉዳዮች ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መነጋገር፡፡ በእርግጠኝነት ከጥቂት ጊዜያት በኋላ ሰዎች ቃሉ ላይ የሌለ ነገር ማመንም ፣ መጥቀስም ይተዋሉ፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዳንድ ከበድ ያሉ ሐይማኖታዊ ጥያቄዎችን ይዞ ለክርክር ወደ እኔ  የመጣ አንድ የኦርቶዶክስ ዲያቆን አስታውሳለሁ ፡ ያደረኩት ነገር ቢኖር ያነሳቸውን ጥያቄዎች በቆይታ ልንመጣባቸው እንደምንችል ነግሬው አሁን ግን ለጊዜው ቅድሚያ ሰጥተን ልንነጋገርበት የሚገባው ስለ ክርስቶስ ነው በሚል ተስማምተን ተከታታይ ትምህርት መማማር ጀመርን ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላ ህይወቱ ተለውጦ ወደነዚያ ጥያቄዎች ውስጥ እንኳ መግባት አልቻልንም፡፡ በክርስቶስ ፍቅር በጣም ተነክቶ ስለነበረ ብዙ ውሳኔዎችን ወዲያው ነበር የወሰነው፤ ይኸው በርካታ አመታት አልፈውም አስካሁን በቤቱ አለ ብዙዎችንም ወደ ክርስቶስ የሳበ ወንድም ሆኗል፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ሰዎች በእርሱ ምክንያት አግኝቻለሁ፡፡በተለያዩ አማልክት ልቡ የተሞላ ሰው እነዚያን የሚያምንባቸውን ሁሉ አውጥቶ ጨርሶ ባዶ አድርጎ ኢየሱስን ብቻ በልቡ ማንገስ የላቀ ምኞት ነው፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ይህ አይሆንም ፡፡ምክንያቱም ሰዎች ለዘመናት የኖሩበትንና የሚያምኑበትን በደቂቃዎች ውስጥ ገደል ሊጨምሩት አይወዱም፡፡ውሎ አድሮ ነገሩን እንደገና መላልሰው ማየት ይፈልጋሉ፡፡ ዙሪያቸውን ከቦ የሚያጠራጥራቸውም ፈተና ቀላል አይደለም፡፡ አንዳንዱ ማስካጃ በጥቅስ ጭምር የተደገደገፈ በመሆኑ ከበድ ይላል፡፡ አንድ አገልጋይ ስለ ዳጎን ጉዳይ አንስቶ እንደተናገረው ማለትም የእግዚአብሔር ታቦት ዳጎን ወደተቀመጠበት መቅደስ ውስጥ ገባ ፤ ደግም ዳጎንን ከላይ ታቦቱን ከስር አድርገው አስቀምጠው ሄዱ በበነጋው ሲመለሱ ግን የእግዚአብሔር ታቦት ከላይ ሆኖ አገኙት መልሰው አስተካክለው ዳጎንን ከላይ አድርገው ሄዱ ለሁለተኛም ጊዜ መጥተው ሲመለከቱ ዳጎን ተሰባብሮ ወድቆ ነበር ፡፡ በወቅቱ ለእግዚአብሔር ተሟጋች ካህን አልነበረም እግዚአብሐር አንድ ጊዜ ይግባ እንጂ ጣኦት የሞላበትም ቤት ቢሆን እንኳ ምን እንደሚያደርግ  ያውቃል፡፡
  ብዙ ነገሮች ወደ ነገሱበት ልብ ውስጥ ሰዎች ክርስቶስን እንዲጋብዙት ማድረግ ሊከብደን ቢችልም መለኮታዊውን አጀንዳ ከተረዳን ደግሞ ብዙ ሊከብደን አይገባም፡፡ ምክንያቱም ውሎ ሲያድር  ህይወታቸውን ያለ አቻ የሚገዛ እርሱ ብቻ ይሆናል፡፡ ሁሉም ነገር በአንድ ቀን እንዲሆን የሚፈልግ ግን የተለየ ተዐምራት ያስፈልገዋል እንጂ፡ ለውጦች በዝግመት የመጡ ናቸው፡፡ ለዚያም ይሆናል አልፎ አልፎ ሁሉን ነገር በአንድ ጊዜ ተናግረን ለመጨረስ ስንታገል የምንታየው፡፡ ሰዎች ልባቸው የሚነካው ምናልባት በአንዲት ጥቅስ ሊሆን ይችላል ፡፡ አብዝተን ስለተናገርንም አይድኑም አሳንሰን ስለተናገርንም አይቀሩም ፡፡ በመንፈስ የምንናገራት አንዲት ቃል ግን ስራ ትሰራለች፡፡ ልክ እንደማንኛውም ተክል የየዕለቱን ውሐ ጥቂት ጥቂት ማጠጣት እንጂ ፡፡ በነጋታው የሆነ ቦታ እንዲደርስለት አታክልቱን በውሐ የሚያጥለቀልቅ አትክልተኛ ካለ ከሰረ፡፡
   ኮንፈራንሱ ካለቀ በኋላ ነፍሳትን በትጋት መከታተል ሌላውና ወሳኙ ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ዳኑ የተባሉት ነፍሳት ቁጥሮች በነጋታው አይታዩም፡፡ የሚከታተላቸው ሰው የለም፣ በሚያጋጥማቸው ችግሮች አማካሪ ያሻቸዋል፡፡ ፍርሀት ጥርጣሬ ስላለ እየደወለ የሚያደፋፍር ሰው ይፈልጋሉ፡፡ ተምረው ፣ጠንክረው ሲወጡ ግን ተግዳሮቶችን በራሳቸው ሊቋቋሙት ይችላሉ፡፡ ለጊዜው ግን  አሁን እንደተወለዱ ህጻናት ተቆጥረው የወለዷቸው ሰዎች ባይለዩዋቸው ጥሩ ነው ፤ ደግሞ በአግባቡ ወተት ከመጋት ጀምረው በሂደት አጥንት መቆርጠም እሰኪችሉ ድረስ ተከታታይነት ያለው ትምህርት መስጠት ፍሬውን ብዙ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

     የወንጌል ተቃዋሚዎች

    ወንጌል ከጅማሬው ጀምሮ በተቃዋሚዎችና በተቺዎች ታጅቦ ነው ዛሬ ላይ የደረሰው፡፡ በሁሉ አቅጣጫ ተመቻችቶና ተስተካክሎ ያለ አንዳች ተቃውሞ የተሰበከበት ዘመንና ቦታ መጥቀስ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ኢየሱስ ወንጌልን ሲሰብክ ፈሪሳውያንና ሰዱቃውያን ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ተቃውመውታል፡፡ በሓዋርያት ዘመንም ቢሆን መንግስትና ሐይማኖት እየተፈራረቁ ከፍተኛ ስደት ጭምር በማስነሳት ሲቃወሟቸው ነበር፡፡ እንደነ ጳውሎስ ያሉትም ከፍተኛ ግርፋትና ድብደባ እየተካሄደባቸው በብዙ ፍርሀትና መከራ ውስጥ ነው ወንጌልን ከስፍራ ስፍራ የሰበኩት፡፡
 ምንም እንኳ በበርካታ ቦታዎች ላይ ሰዎች ራሳቸው ወንጌልን እንደተቃወሙ ቢገለጽም ከጀርባ ሆኖ ሞተሩን የሚያንቀሳቅሰው ቀንደና የወንጌል ተቃዋሚና ጠላት ዲያቢሎስ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ይህም የሆነው ለዘላለም ጥፋቱ ወደሚቃጠልበት ሲኦል ውስጥ ብቻውን ላለመግባት ሲል የሚያካሂደው የሞት ሽረት ስረ ነው፡፡ የማያምኑትን ልብ በመድፈን፣ በግጽ የተጻፈላቸውን የወንጌል ቃል ወደ ጎን አድርገው ሌላ ሌላ ትውፊቶችን እንዲያምኑና እንዲቀበሉ በማድረግ ተቃዋሚዎችን በተለያየ ጎራ አሰልፏል፡፡ /2ቆሮ.4፡4/
  የጨለማው ስልጣን የሚጠቀምባቸው ቡድኖች፣ መንግስታት ም ሆኑ ግለሰቦች በርካታ ሲሆኑ ገሚሶቹ ሀይማኖተኞች ብር በጅተው ና ጊዜ ሰጥተው ሰው ነጻ የሚወጣበት ቅዱስ ቃሉን የያዘውን መጽሐፍ ቅዱስ ገዝተው ያቃጥላሉ፤ ገደል ውስጥ ይጨምራሉ፡፡ ይህ አይነት ስራ ምን ያህል የከፋ እንደሆነ ማስተዋል አያዳግትም፡፡ ገሚሶቹ አብያተክርስቲያናትን እየዞሩ የሚፈርሱ፣ የሚያቃጥሉ ፣ ወንጌል በመስበክ የሚታወቁትን በማሳደድ ፣ በገዛ አገራቸው መብትና ጥቅሞቻቸውን እንዳያገኙ በማድረግ ከፍተኛ ተጽዕኖ እየፈጠሩ ናቸው፡፡ እንደውም አንዳንድ ሀገራት ክርስትናን በህገ መንግስታቸው ውስጥ የማይቀበሉ፣ ሲሰብክ ሲያስተምር የተገኘ ቢኖር በአሰቃቂ ግድያ የሚገድሉ ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡
ዲሞክራሲን አጎልብተዋል በሚባሉ ያደጉ አገሮችም ላይ ቢሆን ያን ያህል ወንጌል በተደላደለ ሁኔታ ላይ አይደለም ያለው፡፡ ዘመናዊነት ከመብዛቱ የተነሳ ክርስትና እንደ ኋላ ቀር አስተሳሰብ ይቆጠራል፡፡ በርካታ የክህደት መጽሐፎች፣ መጽሔቶች ይታተማሉ፤ ክፋት የተሞሉ የክህደት ፊልሞች ይዘጋጃሉ፡፡ ድህረ ገጾቻቸው በአብዛኛው ክርስትናን ና ስርዓቱን የሚያጣጥል ነገር የሚዘጋጅበት ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ወንጌል ይሰበካል፡፡ የወንጌሉ ባለቤት በተለያየ ዘመን ታማኝ ምስክሮቹን ያስነሳል፡፡ እንደ አንቲጳስ ያሉ የሰይጣን ዙፋን ባለበት ስለ ጌታ ስም ጸንቶ ያልደከመ ታማኝ ምስክር /ራዕይ 2፡13/፤ እንደ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ በኃይማኖተኛ ነኝ ባይ ወጋሪዎች ፊት ቆሞ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል እርግጡን የተናገረ ፣ ስለ እምነቱ ተወግሮ የሞተ /ሥራ.7፡59/፡፡ በእናም ዘመን በመከራ ውስጥ እለፉ ወንጌልን በተለያየ አህጉራት የሚሰብኩ አሉ፡፡ በቻይና ፣በህንድ፣ በፓኪስታን፣ በኢራቅ ፣ በአፍጋኒስታን ፣ በሳውዲ አረቢያ ፣ እና በመሳሰሉት ተቃውሞ የሚበዛባቸው ቦታዎች እየኖሩ ለክርስቶስ ታማኝ ምስክር የሆኑ አሉ፡፡ በአገራችንም በኢትዮጵያ ቢሆን ለከተማው ፣ለገጠሩ፣ ለሴቶች ፣ ለነጋዴዎች ፣ ለተማሪዎች ፣ እያሉ ህብረት በመፍጠር ለወንጌል የሚተጉ በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካቸው፡፡
  ልብን የሚሳዝነው ግን እንቅፋት ከቤተክርስቲያን ውስት የተነሳ እንደሆነ ነው፡፡ እዚህ ግቡ ለማይባሉ በርካታ ጉዳዮች ገንዘብ እየወጣ ለወንጌል በጀት የለም የተባለ እንደሆነ፣ ስንት ተያያዥነት የሌላቸው ቁሳቁሶችን ለመግዛት ሳያመን ወንጌልን ለሚያገለግሉ ሰዎች መክፈል ሲያዳግተን ሲታይ የቆረጥነው የምር ምን ላይ እንደሆነ በግልጽ እያሳበቀብን ነው፡፡ ቤተክርስቲያን የዓመት እና የአምስት ዓመት ዕቅዷ ውስጥ ወንጌልን ያማከለ ነገር ከሌላት ኪሳራ ውስት ነች ያለቸው ፡፡ ሌሎች በሰልን ፣ አደግን የሚሉ ወንድሞች ደግሞ ይችው የምንሰብካትን ወንጌል አኮስሰው በመናገር ‹ዋናው ህይወት ነው› ፣ ‹ ቃልህ ሳሆን ተግባርህ ይግለጥ› በሚሉና በመሳሰሉ መንፈሳዊ በሚመስሉ ቃላት ተጀቡነው በሚያቀርቧቸው መፈክሮች በየስብሰባው ቦታ ና በመድረክ ጭምር የሰዎችን ሞራልና ተነሳሽነት እየገደሉ ናቸው፡፡ ወይም የሆነ ተዐምር ፣አዲስ ነገር ተከስቶ ካልሆነ በቀር ዛሬ የምናደርገውን እደረግን የትም አንደርስም የሚሉ ወገኖችም አይጠፉም፡፡ ለእርሱም ቢሆን የምናደርገው የተገለጠልንን ያቺኑ ዘዴ ተጠቅመን እየመሰከርን ተዐምሩን መጠባበቅ እንጂ እጅን አጣጥፎ ሰውን እንዲቀመጡ በማድረግ መሆን የለበትም፡፡ እነዚህ መወገድ ያለባቸው የውስት የቤታን እንቅፋቶች ናው፡፡

   መጽሐፍ ቅዱስ  ወንጌልን ስለመናገር   ምን ይላል?

ወንጌልን ላልዳኑ ሰዎች ለማድረስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትዛዝ አለ፡፡ የተወሰኑትን ቀጥለን እንመለከታለን፡-
  • ‹‹ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ለፍጥረትም ወንጌልን ስበኩ፡፡›› ማር.16፡15
  • ‹‹ እንግዲህ ሂዱና አህዛብን በአብ፣ በወልድ፣ና፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው  ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፡፡ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡›› ማቴ.28፡18-20
  • ‹‹ ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌምም፣ በይሁዳም ሁሉ ፣ በሰማርያም  እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ፡፡›› ሥራ.1፡8
  • ‹‹ ከዚህም በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፡፡ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡ ድምጼን ይሰማሉ አንድም መንጋ ይሆናሉ፡፡ እረናውም አንድ፡፡›› ዮሐ.10፡16
  • ‹‹ ከእንግዲህ ወዲህ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ፡፡››  ሉቃ .5፡10
  • ‹‹ ቃሉን ስበክ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና›› 2ጢሞ.4፡2
  • ‹‹ ለአህዛብ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግስት ወንጌል  በዓለም ሁሉ ይሰበካል፡፡ በዚያን ጊዜ መጨረሻው ይመጣል፡፡›› ማቴ.24፡14
  • ‹‹ በወንጌል አላፍርም›› ሮሜ.1፡16
  • ‹‹ ወንጌልን ባልሰብክ ወዮልኝ››
  • ‹‹ የጌታ የእግአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው ፡ለድሆች የምስራቹን እሰብክ ዘንድ እግዚአብሔር ቀብቶኛል፡፡›› ኢሳ.61፡1
  • ‹‹…ከክፉ መንገዱ ይመለስ ዘንድ ለኃጢያተኛው አስጠንቅቀህ ባትነግረው ያ ኃጢያተኛ በኃጢያቱ ይሞታል፡፡ ደሙን ግን ከእጅህ እፈልጋለሁ፡፡›› ሕዝ.3፡18

     ምስጢረ ድነት

/በምስክርነት ጊዜ የምንጠቀምባቸው የድነት ጥቅሶች/
''ወይቤ፡ መጽሐፍ፡ ኩሉ፡ ዘየአምን፡ ቦቱ፡ የሐዩ  ሮሜ.1011
       በክርስትና ውስጥ ሊታወቁ የሚገባቸው ትክክለኛ የደህንነት /ድነት/ መሰረቶች እና ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
 በቅድሚያ ድነት የምንለው የነፍስ ድነትን ነው፡፡ ይኸውም ሰው በሐጢያተኝነቱ ሊቀበለው ካለ ፍርድና ኩነኔ አምልጦ በክርስቶስ የዘላለም ህይወትን ስለ ሚወርስበት ጉዳይ ነው፡፡
1- ሁሉም ሰው ሐጢያትን ሰርቶአል?
" ልዩነት የለምና ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤በኢየሱስ  ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡በግዕዙ እንዲህ ይላል / ወኢፈለጣ፡ ወኢሌ ለየ፡፡እስመ፡ ኩሉሙ፡ አበሱ፡ወጌጋዩ፡ ወኀደጉ፡ ስብሐተ :እግዚአብሔር /   ሮሜ 323       
 " ልዩነት የለም" የሚለው ቃል የሰውን ስጋ ለብሶ ከመጣው ከጌታችን በስተቀር ስጋን የለበሰን ሁሉ ሰው ማለት ነው፡፡ የሐጢያት መንስኤውም አንድም የአዳም አለመታዘዝ ሲሆን / ሮሜ .519/ :ቀጥሎም ሰው ሁሉ በነፍስ ወከፍ ያደረገው ሐጢያት ነው፡፡
2- የሐጢያት ደሞዝ  ሞት ነው?
" የኀጢያት ደሞዝ ሞት ነውና ::የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ህይወት ነው፡፡" ሮሜ.620 : ጢይት ልክ  እንደማንኛውም ስራ የራሱ ደሞዝ አለው፡፡ ክፍያው ከበድ ያለ ስለሆነም ነው ንስሀ መግባት አስፈላጊ የሆነው፡፡ የኃጢያት ደሞዝ የዘላለም ሞት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የዘላለም ሞት ሊታደገን  ፡እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለእኛ ሰጠን /ዮሐ.316/፡፡
3- ከሞት ፍርድ እንዴት ማምለጥ ይቻላል?
የዮሐንስ ወንጌል .3 16-18 ሲናገር " በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ  ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ፤ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አላከውምና፡ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ  በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡ " ከላይ እንደተጠቀሰው  ከዘላለም ፍርድ ከዘላለም ሞት ለመዳን መንገዱ በክርስቶስ ማመን ነው፡፡ 
4- መዳን ወይም መጽደቅ  በእምነት ነው፡፡
 የእግዚአብሔር ቃል በሮሜ 10 .9 ሲናገር / እምከመ፡ ተአምን፡ በአፉከ፡ከመ፡ክርስቶስ፡ውእቱ፡እግዚእ፡ወተአምን፡ በልብከ፡ከመ፡አንሥኦ፡ እግዚአብሄር እምውታን፡ተሐዩ፡፡ወልብን፡ ዘየአምን፡ቦቱ፡ይጸድቅ፡ወአፍኒ፡ዘየአምን፡ቦቱ፡የሐዩ፡፡ " ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና፡፡ መጽሐፍ በእርሱ የሚያምን አያፍርም ይላልና፤" ሮሜ.109-11፡፡ በቃሉ እንደተጠቀሰው የክርስቶስን ጌትነት በአፍ መመስከርና፣ ተሰቅሎ ለኃጢያት ስረየት የሚሆነውን ደሙን አፍስሶ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ማመን ደግሞ ሁለተኛው ዋና ነገር ነው፡፡
5- ንስሐ መግባት!
 ኢየሱስም ራሱ " ተነስሑ እስመ ቀርበት መንግስተ ሰማያት"- /መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ፡፡/ ወንጌል ዘማቴዎስ 417፡፡ በሌላም በኩል ማመንና ንስሐ መግባት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ ሌላ አነጋገር ንስሐ መግባትና ማመን የማይነጣጠሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ንስሐ ስንገባ ኃጢያታችን ይቅር እንደሚባል ተስፋ ተሰጥቶናል፡፡ " በኃጢያታችን ብንናዘዝ  ኃጢያታችንን ይቅር ሊለን ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡ኃጢያትን አላደረግንም ብንል ሀሰተኛ እናደርገዋለን፡፡ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም፡፡ " / 1ዮሐ.19-10/፡፡ መናዘዝ ማለት በስውርና በግልጽ፤ በስህተትና በድፍረት የሰሩትን ሐጢያት ለእግዚአብሔር ዘርዝሮ መናገር ማለት ነው፡፡
6- ጌታን መቀበል ምንድን ነው?
 ጌታን መቀበል የሚለው ቃል የመጣው ከዮሐንስ  ወንጌል .1 .11-13 ባለው  መሰረት ነው፡ " ወለእለስ፡ ተወክፍዎ፡ወሀቦሙ፡ሥልጣን፡ውሉደ፡ እግዚአብሔር፡ ይኩኑ ለእለ፡አምኑ፡በስሙ፡፡ " /የእርሱ ወደ ሆነው መጣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም ፡፡ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው፡/ ይላል፡፡ ጌታችን  መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምንቀበለው  /የምናስተናግደውየልባችንን በር በመክፈት ሲሆን በህይወታችን ላይ እርሱን እንደ ሊቀ ካህን፣ እንደ ነቢይ  የዘላለም ጌታና  ንጉስ አድርጎ መሾም ነው፡፡ራዕይ 320
7- ዳግም መወለድ ማለት ምንድን ነው?
   ከላይ የዘረዘርናቸውን መንፈሳዊ እውነቶች በህይወቱ  በመታዘዝ ያደረገ ሁሉ ዳግመኛ ተወለደ ማለት ይቻላል፡፡ በዮሐንስ  ወንጌል .3 .3 እንደሚናገረው  " ኢየሱስ ወይቤሉ፡አማን፡አማን፡እብለከ፡ዘኢተወልደ፡ዳገመ፡አይክል፡ርዕዮታ ለመንግሥተ፡ እግዚአብሔር፡፡" /...እውነት እውነት እልሀለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም ! ማለት ነው ትርጉሙ::
ለምሳሌ በዚህ ታሪክ ላይ የምናገኘው ኒቆዲሞስ  ሽማግሌ ነበር፣ የአይሁድ አስተማሪ ነበር፣ ይህ ብቻ አይደለም አጥባቂ ፈሪሳዊ  ነበር፣ ደግሞ የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡ ረጅም ዘመን ብሉይ ኪዳንን ያስተማረ እንኩዋ ቢሆን፣ ወይም አለቃና በእድሜው የበሰለ የሚባል ሰው ቢሆን?  ዳግመኛ  ካልተወለድክ፤ የእግዚአብሔርን መንግስት አታይም ነው የተባለው፡፡ ስለዚህ ዳግም ሳንወለድ የምናደርጋቸው የትኞቹም ኀይማኖታዊ  እንቅስቃሴዎች  ለመዳናችን  ፋይዳ  የላቸውም፡፡
7- ንስሐ  ለገቡ / ዳግመኛ ለተወለዱ / የሚሰጡ  በረከቶች:-
  •  የዘላለም ህይወት ያገኛሉ፡፡ ዮሐ.318 1ዮሐ.113
  •  ስማቸው   በህይወት  መዝገብ  ላይ ይጻፋል፡፡ ሉቃ.1020 ራዕይ 2015
  •   ከድቅድቅ  ጨለማ ወደሚደነቅ  ብርሀን  ይወጣሉ፡፡1ጴጥ.29
  •  
  •   የክርስቶስ  ክብር  ተካፋይ  ይሆናሉ፡፡2ተሰ.21
  • አዲስ   ፍጥረት ይሆናሉ፡፡ 2ቆሮ.517
  •   ይጸድቃሉ፤  ይድናሉ ፡፡ ሮሜ.10 9 ዮሐ.316-18
  •   የእግዚአብሄርም ቤተሰብ ይሆናሉ፡፡ ኤፌ.219 1ዮሐ.51
    በምስክርነት ጊዜ የገጥሙን  ነገሮች
ወንጌልን ለመመስከር ስንወጣ ሊገጥሙን የሚችሉ ነገሮች ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ ምናልባት የሚሳደቡ፣ የሰጠናቸውን በራሪ ጽሑፍ የሚቀዳድዱ፣ በተደፈርኩኝ ኤነት ስሜት ለድብድብ የሚዘጋጁ ፣ሌሎች ደግሞ ሽንጣቸውን ገትረው የሚከራከሩ፣ የማይሆን አምባጓሮ የሚያስነሱና ሰው በከንቱ የሚሰበስቡ ፣ ሲያልፍም ለእንግልትና ለእስር የሚዳርጉ ናቸው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ስላለ ሁሉንም እንደየ አመጣጡ የምንመልስበትን ጸጋ ይሰጠናል ፤ በግድ ለክብሩ ማለፍ  ያለብን ሁኔታም ካለ እንድናልፈው ያግዘናል፡፡በአንዳንድ ምስክርነት ወቅት ሊጠቅመን እንዲችል የምንመሰክርላቸው ሰዎች በተደጋጋሚ የሚያስቡትንና የሚሟገቱባቸውን የተወሰኑ ምክንያቶቻቸውን ቀጥለን እንዳስሳለን፡፡

  1ኛ-ኃይማኖተኛ የሆኑ ሰዎች

   ኃይማኞተኛ ሰዎች በአብዛኛው ከሚያነሱት ሀሳብ አንዱ ‹ የእኔ ሐይማኖት ምንም አይወጣለትም! ወይም ትክክለኛ እና ብቸኛ አምላክ የፈጠረው ሐይማኖት ውስጥ ነው ያለሁት! ስለዚህ በእምነቴ እኮራለሁ፤ የያዝኩት ይበቃኛል፡፡› ይላሉ ፡፡ በሁሉም ዘንድ ሊታወቅ የሚገባው አንድ ነገር የትኛውም ሀይማኖት በእግዚአብሔር ያልተፈጠረ መሆኑ ነው፡፡ ሰዎችን ሐይማኖት ሊያድናቸው አይችልም፡፡ ማለትም የዚህኛው ቡድን ደጋፊ ፣አልያም የዚያኛው ቡድን ደጋፊ በመሆን ሳይሆን በክርስቶስ በማመን ነው ልንጸድቅ የምንችለው፡፡ እግዚአብሄር አንድያ ልጁን ሰጠን እንጂ ሐይማኖት አልሰጠንም፡፡ ወንጌል ሊሰብኩ፣ እግዚአብሔርን በእውነት ሊያከብሩ በክርስቶስ ስም ከሚሰበሰቡ ጋር ህብረት እያደረግን ራሳችንን እናንጻለን፡፡

       2ኛ-በልዩ ልዩ ሱሶች ተጠቂ የሆኑ

  የተወሰኑ ሰዎች እግዚአብሔርን በመፍራት ይሆናል ወይም በሌላ ምክንያት ሱስ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያስቸግረኝ ስለሆነ ንጹህ ስሆንና መተው ስችል እመጣለሁ ይላሉ፡፡ ልብ ሊሉ የሚገባው ነገር ግን እግዚአብሔር በድካም ለሚመላለሱ ሰዎች ምን እንደተናገረ ነው ፤ በማቴዎስ ወንጌል ም.11 ቁ.28 እንደተጻፈው ‹‹ እናንተ ደካሞች ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ! እኔም አሳርፋችኋለሁ፡፡›› ነው፡፡ ሰዎች ከነ አቃታቸው ነገር ቢመጡ፡ ማለትም ካስቸገራቸውና ከከበዳቸው ነገር ጋር መጥተው እንዲያርፉ ነው የተፈለገው፡፡ የእግዚአብሔር ቤት ነጻ የምንወጣበት፣ ቀንበራችን የሚሰበርበት ፣ ሸክማችን የሚቃለልበት ፣ ቤት ነው እንጂ፡ የመላዕክት ህይወት የሚኖሩ ሰዎች መሰብሰቢያ አይደለም፡፡ የነጹትም ጻድቃን ቢሆን መጀመሪያ ሲመጡ ከናቃታቸው ነገር ጋር ነው፡፡ በተቃራኒው ዝም ብሎ ሰው የድካሙ መደበቂያ ሊያደርገውም ደግሞ አይገባም፤ ጸጋን እየተቀበሉ መለወጥም እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

    3ኛ-ቀድሞውኑም አልተመረጥኩም የሚሉ

  ዝም ብለው ራሳቸውን በመኮነን የሚታወቁ ሰዎች አሉ፡፡ ዕድሌ ነው በማለት ዕድላቸውን ይረግማሉ፤ አሁን ያሉበት ሁኔታ በመለኮት የተፈረደባቸው አይነት አድርገው ይቆጥራሉ፡፡ መድኃኒዓለም የሆነው ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ ኃጢያት ተሰቀለ፣ ሞተ፣ተቀበረ፣ በሦስተኛው ቀንም ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፡፡ አንድም አድሎ አልተፈጸመም፤ ሞቱ ለሁሉም ስርየት ነበር፡፡ አምኖ የተቀበለው ሁሉ ይድናል፡፡ ከኃጢያተኛ ዋና የነበሩ በርካቶችም ክርስቶስን በማመን ህይወታቸው እስከ ወዲያኛው ተለውጧል፡፡ ዛሬም የማይጠቅምን ወስዶ የሚጠቅም አድርጎ ወደሚቀይር ፡በነጻ ወደተሰጠ ጸጋው በእምነት እንቅረብ፡ እንጂ እንዳይጠቅም ሆኖ የተፈረደበት አንድም ሰው የለም፡፡

     4ኛ -በእግዚአብሔር ህልውና የሚጠራጠሩ

   እግዚአብሔር የለም፡፡ ክርስትናም ሞኝነት ነው፡፡ የሚሉ ምን ያህል ያልታደሉ ሰዎች ናቸው? እነዚህንም ቢሆን ልንበሳጭባቸው ሳይሆን ታግሰን ልናድናቸው ይገባል፡፡ በመሰረቱ የእግዚአብሔርን መኖር ልናረጋግጥ የምንችልበት መንገዱ ራሱ እምነት ነው እንጂ እንደ ቁስ ነገር እዚህ ጋር አምጥተህ ወይም አስመጥተህ አሳየኝ የምንለው አይደለም፡፡ ቃሉ ሲናገር ‹‹ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ ይሰጥ ዘንድ እንዲያምን ያስፈልገዋል ይላል›› ዕብ .11፡3-6፡፡ የእግዚአብሔርን መኖር ፍጥረታቱ ሁሉ ይናገራሉ; ጸሐይ ፣ ጨረቃ፣ ሌሊቱና ቀኑ፣ ህጽዋቱ፣ እንስሳቱ፣ ራሱ የሰው አፈጣጠር ፣ውስጣዊና ውጫዊ ስሪቱ ከኋላ የመለኮት ጣት እንዳለበት ያሳያል፡፡ እንዲያማ ካልሆነ ይህን ሁሉ ውብ ነገር ማን ሰራው ሊባል ነው?  ማነው ተቆጣጣሪው?  ፍርድ ሰጪው// ማንስ ነው ሁሉን ወደ መኖር ያመጣው? በእርግጥ ጠቢባን ነን ለሚሉ ፣ለዚህ ዓለም አዋቂዎች እውነቱ ተሰወረባቸው /1ቖሮ.3፡18-23/፡፡ እግዚአብሔር ለሚፈልጉት ቅርብ ነው፡፡ /ኤር.29፡13/ በእምነት ሆነው የእውነት ለሚፈልጉት ሁሉ ራሱን ይገልጣል፡፡

     5ኛ.ሰውን በመፍራት የሚቀሩ

 ጥቂት የማይባሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ለወንጌል መልዕክትም ሆነ ለወንጌላውያን በጣም መጥፎ አመለካከት አላቸው፡፡ በኛ ክልል ወንጌል እንዲሰበክ አንፈቅድም የሚሉ፣በድፍረትም ባህላችን ወጋችን ይህንን አይፈቅድም ብለው የሚሞግቱ ናቸው፡፡ በክርስቶስ ያመነ ደቀመዝሙርም ካገኙ ከቤተሰብ ፣ከጓደኛ ፣ ወይም በስራ ቦታ ፣በትምህርት ቤት ጀምረው እነዲገለል ያደርጋሉ፡፡ ከመተሳሰቢያ ዕድር ያስወጣሉ፡፡ ስለሆነም ብዙዎች ይህንን እንግልት በመፍራት ቤተሰቤን እንዳላጣ፣ መቀበሪያ እንዳላጣ ..ወዘተ በማለት በወንጌል እውነት እንኳ ውስጣቸው ቢነካም እጅ ሳይሰጡ ዘውትር በመፍራት ይኖራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሰላም ሳይኖራቸው ነው የሚኖሩት፡፡ በህይወታቸው ያለውን ጨለማ ሊያበራ የሚችለውን እውነተኛ ብርሀን እስካልተቀበሉ ድረስ በምን መንገድ ደስታና ሰላም ሊገኝ ይችላል?
የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ ከእኔ ይልቅ አባቱን ወይም እናቱን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡ ከእኔ ይልቅም ወንድ ልጁን ወይም ሴት ልጁን የሚወድ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡ መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም፡፡ ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል ፤ነፍሱን ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል፡፡›› /ማቴ.10፡37-39 / እንደሚል ሰዎች በማናቸውም ጉዳይ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰዎችን በመፍራት እንዳይኖሩ ልንጸልይላቸውና ልናሳስባቸው ይገባል ፡፡ በማናችንም ህይወት ሰዎች ተጠያቂ አይሆኑልንም ፤ ስለ ራሳችን ህይወት ጉዳይ መልስ የምንሰጠው ራሳችን ነንና፡፡

    6ኛ-ሁሉም ሀይማኖት ወደ እግዚአብሔር ያደርሳል ብለው የሚያምኑ
   ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቀስ በቀስ ትውልዱን እየወረሰ ያለ አመለካከት አለ፡፡ ይኸውም ሁሉም ለራሱ ትክክል ነው፤ የሐይማኖት መንገዶች በሙሉ ወደ እግዚአብሔር ሊያደርሱ ይችላሉ፡፡ ብለው የሚያምኑ ናቸው፡፡ እንቅስቃሴው የ ኒው ኤጅ ሙቭመንት በመባል ይታወቃል፤ ከዘመናዊነትና ከድህረ ዘመናዊነት አስተሳሰብ ጋር ተዳብሎ ትውልድ እየጨረሰ ያለ ጽንፍ ነው፡፡ ነገር ግን ሁሉም መንገዶች ወደ እግዚአብሔር ሊያደርሱን አይችሉም ! ጌታ ኢየሱስ ራሱ ‹‹ እኔ መንገድና ህይወት፣ እውነትም ነኝ ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡›› /ዮሐ.14፡6 /ብሎ ስለተናገረ ወደ እግዚአብሔር መቅረቢያ በሆነው በመድሀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ሰዎች ሁሉ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲታረቁ  ልንነግራቸው ይገባል፡፡

    የእግዚአብሔር ዋነኛ አጀንዳ በሆነው የወንጌል አገልግሎት ውስጥ ድርሻ ያላቸውና አብረው ተሳትፎ የሚያደርጉት ማን ማን ናቸው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ፡፡ ቀጥለን ይህንን አሳብ ሰፋ አድርገን እንመለከታለን፡፡

       በወንጌል አገልግሎት ውስጥ የአብ ድርሻ

ከጅማሬው የሰው ልጆችን የድነት ዕቅድ ያወጣውና ጊዜው ሲደርስም አንድያ ልጁን ወደዚህ ዓለም የላከልን እግዚአብሔር አብ ነው፡፡ በስላሴ ህብረት ውስጥ የስራ ድርሻክፍፍል እንጂ የዕቅድ፣ የአቋም፣ የሥልጣን ና የአገዛዝ ልዩነት በፍጹም የለም፡፡ የአብ ዕቅድ የሆነው ሁሉ የተቀሩት የሁለቱ የስላሴ አካላት የወልድ እና የመንፈስ ቅዱስም ዕቅድ ነው፡፡
  ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው የመጀመሪያ መልዕክቱ ላይ እንደጠቀሰው ፡ እግዚአብሔር በወንጌል ስራ ውስጥ ዋናውን ድርሻ የሚወስድ ነው፡፡ ‹‹…እኔ ተከልሁ አጵሎስም አጠጣ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ያሳድግ ነበር፡፡›› /ም.3 ቁ.6/ ብሏል፡፡ እንደተሰጠን ጸጋ ስራዎችን ተከፋፍለን በመስራት ምንም እንኳ ብንደክም ነገር ሁሉ የሆነው በእርሱ ነው፡፡ ከእርሱና ለእርሱ ነው፡፡በቁጥረ 9 ላይ እንደተገለጠው በህነጻ እና በእርሻ የተመሰለው መንፈሳዊ ስራ ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው፡፡ አምላካችን እኛ ብቻችንን ለፍተን ያመጣነውን ውጤት ጠባቂ ሳይሆን የምንሰራውን ሁሉ የምንሰራው ከእርሱ ጋር ነው፡፡ ‹ ከእርሱም ጋር አብረን የምንሰራ ነንና፡፡›

          የወልድ ድርሻ

  ወንጌል ዜናው ራሱ የሚጀምረው ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመናገር ነው፡፡ የምስራቹም ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ማዕከላዊነቱ ክርስቶስ ባለሆነበት በየትኛውም አገልግሎት ግን አላማውን ይስታል፡፡
ክርስቶስ የምስራቹን ወንጌል ሰብኮ ፣ አስተምሮ፣ ጊዜው ደርሶ ወደ አባቱ ሲሄድም አደራውን ለደቀ መዛሙርቱ ሰጥቷል፡፡ ይሁንና ደግሞ አሁንም ሁልጊዝ ከአማኞች ጋር በአገልግሎት ውስጥ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ታላቁን ተልዕኮ በሰጠበት የማቴዎስ 28 ቁ.18-20 ቃል ላይ ‹‹…እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ እኔ ከእናንተ ጋር አሉ፡፡›› በማለት አስታውቋል፡፡ ይህንንም ያሳየበት አንዳንድ ክፍሎችን ማየት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ እስጢፋኖስ ስለ ወንጌል እየተናገረ አይሁድ በጭካኔ በድንጋይ ሲደበድቡት በዙፋኑ በአብ ቀኝ ሆኖ ታይቶታል /ሥራ.7፡56/ ይህንን መገለጥ አንዳንድ ስኮላርስ እስጢፋኖስን በወንጌል ስብከቱ ወቅት አብሮት እንዳለ እንዲያውቅ ሊያበረታታው ነው ብለው ይናገራሉ፡፡ በሌሎች ብዙዎች ህይወት ጣልቃ ገብቷል፣ ታድጓል ፣ ስለወንጌል የተለያየ ፈተና ከደረሰባቸው ጋር አብሮ ሆኗል፡፡ እንደ አስጢፋኖስ ያሉት ስለወንጌል ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ በሐዋርይት ሥራ 9 ላይ እንደምናገኘው አይነት ደግሞ ተቃዋሚዎችን አስጠንቅቆ ወደ እውነት መልሷቸዋል፡፡ ‹‹ ሳኦል ሳኦል ስለምን ታሳድደኛለህ// ሳኦልም አንተ የማሳድድህ ማን ነህ? አንተ የምታሳድደኝ እኔ ክርስቶስ ነኝ፤ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሐል፡፡›› ሥራ.9፡4 በጣም ድንቅ ነገር ነው፡፡ የወንጌል ሰራተኞች ሲሰደዱ አብሮ የሚሆን፡፡

          የመንፈስ ቅዱስ ሚና

  ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር የመጣበትን የድነት ሥራ ፈጽሞ ወደ ላይ ሲያርግ ፡ ለደቀ መዛሙረቱ በሰጠው ተስፋ መሰረት ከአስር ቀናት በኋላ በተሰበሰቡ አማኞች ላይ የመንፈስ ቅዱስ ሀይል ወረደባቸው፡፡ መንፈስ ቅዱስ በተለይ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የተመዘገቡትን አስደናቂ የወንጌል ሥራዎች በአማኞች ውስጥ በመሆን ሰርቷል፡፡ የመመስከር አቅምና ሐይል የሚገኘው በእርሱ ነው፣ የማያምኑ ሰዎች በሚመሰከርላቸው የወንጌል መልዕክት ልባቸው እንዲነካና ቶሎ እንዲወስኑ የሚረዳቸው ይኽው የአግዚአብሔር መንፈስ ነው፡፡ የሚሰራውን ሥራዎች ከወንጌል አንጻር ለሁለት ከፍለን እንመልከት፡-
1-መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ውስጥ
አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ /ኢዩ.2፡8 ና 1ቆሮ.  2፡11 / ፣ የክርስቶስ መንፈስ /1ጴጥ.1፡11/ ፣ የጌታ መንፈስ /2ቆሮ.3፡17/ ተብሎ የተጠራው መንፈስ ቅዱስ አማኞችን በማበረታታት ፣ መልዕክት በመስጠት ፣በማደፋፈር ፣ በመምራትና አቅጣጫን በመጠቆም ..ወዘተ ከፍተኛ የወንጌልን ሥራ ይሰራል፡፡ /ሥራ.8፡28 ፤ 16፡7/
    2-መንፈስ ቅዱስ ባልዳኑ ሰዎች ሕይወት

መንፈስ ቅዱስ ወደ ዓለም የመጣበት ሌላው ዋነኛ ጉዳይ ዓለምን ስለ ሐጢያት ፣ ስለ ጽድቅና ስለ ፍርድ ለመውቀስ ነው፡፡ /ዮሐ.16፡8/፡፡ ይህም የወንጌል ሰዎች ስለ ወንጌል የቱንም ያህል ቢናገሩ እርሱ የሰዎችን ልብ ስለ ሐጢያታቸው ወቅሶ ካልነካቸው በቀር በቀላሉ ንስሐ ገብተው ውሳኔ ሊወስኑ አይችሉም፡፡ በፍጹም ሊነኩና ሊለወጡ አይችሉም! ብለን ድምዳሜ የሰጠናቸውን ስንት አመጸኞችን በወንጌል ፍቅር ልባቸውን አቅልጦ ለጌታ እንዲንበረከኩ ያደረገ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ ዛሬም በስራ ላይ ነው፡፡
 በአጠቃላይ  እግዚአብሔር አብሮን የማይሆን ቢሆን ኖሮ ቤተክርስቲያንም ሆነ አገልጋዮች ፍሬ ቢሶች በሆንን ነበር፡፡ የወንጌል ሥራውም ከባድና ውስብስብ በሆነ ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህ ዓለም በሰይጣን ቁጥጥር ስር ነው ያለው፡፡ ትግሉ ከስጋና ደም ጋር ብቻ እንደሚደረግ ዓይነት አይደለም፡፡

    የመላዕክት ድርሻ በወንጌል ሥራ ውስጥ

ቅዱሳ መላዕክት በወንጌል ስራ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርጉ ባንመለከትም፡፡ የተለያዩ ድርሻዎች እንደነበራቸው ግን ማስተዋል ይቻላል፡፡ለምሳሌ በሐዋርያት ሥራ 8፡26 ላይ ወንጌላዊው ፊሊጶስ ለኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ወንጌል እንዲሰብክለት ‹‹ ተነስተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደ ሚወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ›› ብሎ የተናገረው የጌታ መልዐክ እንደሆነ ተጽፏል፡፡በቀጥታ ወንጌል ባይሰብክለትም ወንጌል የሚሰብክለትን አገልጋይ ግን መርቷል ፣ እረድቷል፡፡ በሌላም ስፍራ ላይ ቆርነሌዎስ የተባለውን ባለስልጣን ጴጥሮስ የተባለውን ስምኦንን ካረፈበት  ቤት አስመጥቶ ወንጌልን ከእርሱ አፍ እንዲሰማ ጠቁሞታል፡፡ /ሥራ 10፡26/፡፡ በአጠቃላይ የዕብራውያን ጸሐፊ እንደገለጠው መላዕክት መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ መናፍስት ናቸው፡፡
         
             በተደጋጋሚ የሚነሱ ጥያቄዎች

በመቀጠል ደግሞ የተለያዩ ሰዎች ብዙ ጊዜ በተደጋጋሚ የሚያነሷቸውን አንኳር ጥያቄዎችን ተራ በተራ እንዳስሳለን፡፡ በእርግጥ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ሁሉንም አንስቶ በዚች አነስተኛ መጽሐፍ ውስጥ ለመጻፍ አይቻልም፡፡ ቢሆንም የተወሰኑትን መጥቀስና ማብራራት ግን ወሳኝ ሚና አለው፡፡
ሰው ሁሉ የሚድነው ጥያቄው ሁሉ ተራ በተራ ተመልሶለት ሲያበቃ በፍጹም አይደለም፡፡ አኔን ጨምሮ ከናልተመለሰ ብዙ ጥቄዎቻችን ጋር ነው የዳንነው፡፡ ምናልባትም ከረጅም ቆይታም በኋላ ቢሆን እስካሁን ያልተመለሱ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ ይሁንና ዋናው የመዳን ዕውቀት ብርሐን ግን ስለበራልን ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን፡፡ አርሱ ከስላሴ ጋር የታረቅንበት ፣ ከዘላለም ሞት የተረፍንበት ዕውቀት አልተመለሱም ከምንላቸው ጥያቄዎች ጋር በምን መልክ ይወዳደራሉ?
  • የክርስቶስን ወንጌል የምንመሰክርላቸውም አዳዲስ ሰዎችም በርከት ያሉ ጥያቄዎች እንደሚኖራቸው ምንም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህ ቢሆንም ዋናው የመዳን ጉዳይን እንዲያምኑና እንዲቀበሉ ማድረግ እንችላለን፡፡ ቀስ በቀስ ደግሞ ውስጣቸው ያለ ጥያቄ እየተመለሰ ይመጣል፡፡ በአንድ ቀን ቅጽበት ጥያቄዎችን ሁሉ ከሰዎች ህይወት አጥፍቶ ማደር አይቻለንም፡፡ አንዳንዱ ነገር ጊዜን ይፈልጋል፡፡ የእግዚአብሄርን ሐይል እያወቁ ቃሉን እየተረዱ ሲመጡ በራሱ ጊዜ ከውስጣቸው የሚጠፋ ጥያቄም ይኖራል፡፡ አሁን ዋና የሆነው ርብርቦሽ ሰዎችን ከዘላለም ሞትና፣ ከሲኦል ማትረፉ ነው፡፡ ዘመኑ አልቋል፣ ጊዜ የለም፡፡ ክፉው ባለው በሌለው ሐይሉ እየሰራ ይገኛል፡፡ እኛም በመንፈስ ቅዱስ ሐይል እየታገዝን በብዙ ምጥ ወገኖቻችንን ከዘላለም ሞት ልናተርፋቸው ይገባል፡፡ አንዳንዱ ጥያቄዎች ቀጥለው ቀርበዋል እነሆ፡-
  • ትክክለኛው ሐይማኖት የቱ ነው?
በመሰረቱ ክርስቶስ ሐይማኖትን መስርቶ አልሔደም፡፡ ሐይማኖቶች በተለያየ አቋምና ስም ሊለያዩ የበቁት በሚከተሏቸው አስተምህሮዎች እና ዶክትሪናቸው አንጻር  ነው፡፡ በጥንት ጌዜ ቤተክርስቲያን በተተከለችበት ቦታ ስም ጋር የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ተብላ ትታወቃለች፡፡ ለምሳሌ ‹በቆሮንቶስ ያለች የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን› 1ቆሮ.1፡2 እንደሚለው ማለት ነው፡፡ አማኞች ብዙ ጊዜ ይሰበሰቡ የነበሩትም የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ነበር፡፡ ቤተክርስቲያን ሁለትና ከሁለት በላይ የሆኑ የአማኞች ስብስብ ነው እንጂ ስፍራ አይደለም፡፡ ቤተክርስቲያን የሚባል የመሰባሰቢያ ለይቶ እንዲታነጽ ማድረጉ ግን ንም ወንጀልነት የለውም፡፡
አማኞች ክርስቲያን የሚለውን ስም የተጎናጸፉት አንጾኪያ በምትባለው ከተማ ሲሆን ይህም ደቀ መዛሙርቱ ግብራቸው፣ አካሄዳቸው እንደ ኢየሱስ ሆኖ ስላገኙት እንደነበረ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡/ሥራ.11፡26/
    በዓለም ላይ ከ4,200 በላይ ሐይማኖቶች እንዳሉ Wikipedia, the free encyclopedia ዘግቧል፡፡ በዓለም ላይ በቁጥር አንድ ላይ የተቀመጠው ሐይማኖት ክርስትና ሲሆን ከዓለም ህዝብ 35% /ፐርሰንት/ ያህሉን ማለትም 2.3 ቢሊዮን ገደማውን የያዘ ሲሆን በሁለተኝነት የሚከተለው እስልምና 1.6 ቢሊዮን ህዝብ ማለትም 23  %/ ፐርሰንቱን/ የያዘ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ክርስትና ስንል በዓለም ላይ ያሉትን ምናልባትም ከ33 ሺህ በላይ ተከፋፍለው ያሉትን ዲኖሚኔሽኖችን ማለት ነው፡፡ እንደሚታቀወቀውም በክርስትና ስም የታወቁት ሐይማኖቶች እንደ ግሪክ ኦርቶዶክስ፣ የግብጹ ኮፕቲክ ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ፣ የካቶሊክ እና በርካታ የወንጌላውያን /ፕሮቴስታንት/ አብያተክርስቲያናት በተወሰነ መልክ በሚቀበሏቸውና በማይቀበሏቸው አንዳንድ ዶክትሪኖች ምክንያት የተለያዩ ናቸው፡፡ በተለይ ሌሎችን ለመርዳት ጭምር ሲባል በክርስትና ውስጥ የሚታወቁ እምነቶች በውስጣቸው ያለውን አንዳንድ ሁኔታና አቋም መረዳት በጣም ጠቃሚ ነው የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ስለ ስላሴ አንድነትና ሶስትነት  ያላቸው እምነት ፣ ስለ አዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣  የእምነታችን መመሪያ ስለሆነው መጽሐፍ ቅዱስ፣ ስለ ፍርድ ፣ የዘላለም ህይወት ፣ የዘላለም ሞት ፣ስለ ሐጢት ስርየት ፣ ዳግም ምጽዐት ፣ የመሳሰሉት መሰረታዊ እውነቶች ላይ ያላቸውን ልዩነትና አንድነት ጠንቅቆ ማወቅ ጥሩ ነው፡፡
አንዳንድ የእምነት ድርጅቶች ዶክትሪናቸው በግልጽ ባለመቀመጡ ብዙዎች ወገኖቻችን የሆኑ ወንድሞች  ከእነርሱ ጋር ማምለክ ምንም እንዳይመስላቸው አድርጓቸዋል፡፡ ጥልቅ የሆነ ስህተታቸው እንኳ እንዳይነቃበት ረድቷቸዋል፡፡ይሁንና በክርስቶስ ኢየሱስ የመስቀሉ የማዳን ስራ ላይ ፣ ሞትና ትንሳኤው ፣ ወደ ፊት መምጣቱ ላይ፣ ስለ ስላሴ ማንነት ተዛብቶ የተቀመጠበት የትኛውም እምነት በስህተት ውስጥ ያለ መሆኑን አማኞች ጠንቅቀው ሊረዱ ይገባል፡፡ቃሉ እንደሚናገረው ‹ የእግዚአብሔር ልጅ እንደመጣ እውነተኛም የሆነውን እናውቅ ዘንድ ልቦናን እንደሰጠን እናውቃለን፡፡ እውነተኛም በሆነው በእርሱ አለን፡፡ እርሱም ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ እርሱ እውነተኛ አምላክና የዘላለም ህይወት ነው፡፡› 1ዮሐ 5፡20
ደግሞ በሌላ ስፍራ ላይ ‹ ወዳጆች ሆይ መንፈስን ሁሉ አትመኑ፡፡ ነገር ግን መናፍስት ከእግዚአብሔር ሆነው እንደሆነ መርምሩ፡፡ ብዙዎች ሐሰተኞች ነብያት ወደ ዓለም ወጥተዋልና ፡፡ የእግዚአብሔርን መንፈስ በዚህ ታውቃላችሁ፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ እንደመጣ የሚታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ በስጋ እንደመጣ የማይታመን መንፈስ ሁሉ ከእግዚአብሄር አይደለም፡፡ ይህም የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው፡፡ ይህ እንደመጣ ሰምታችኋል፡፡ አሁንም እንኳ በዓለም አለ፡፡›› 1ዮሐ.4፡1-3
ስለዚህ በእግዚአብሔር ቃልና ጸጋ ራሳችንን ከረቀቀ ስህተት እየጠበቅን ከክርስትና ጋር ተመሳስለው ካሉ የስህተት አስተምህሮዎች ለመለየት ፣ደግሞ በዚያ ስህተት ውስጥ ሲያውቁም ሆነ ሳያውቁ የገቡትን ወገኖች ለመታደግ በጸሎት በመትጋት ጭምር  መፍጠን  አለብን፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናም ዛሬም እስከ ዘላለሙም ድረስ ያው ነው አሜን፡፡
አስኪ ከዚህ ቀጥለን በቅርብ የምናውቃቸው ሐይማኖቶች አንዳንድ መረዳታቸው ምን እንደሚመስል  እንመልከት፡

አስቀድመን በ2004 ከቀረበው ከ1 እስከ 10 ድረስ ደረጃውን የያዙትን የዓለም ሐይማኖቶች ሰንጠረዥ ቀጥሎ ይቀርባል፡-
1-
2-
3
4
5
6
7
8
9
10
Source: Encycloprdia Britannica ; Adherents.com

በመቀጠል የተወሰኑ እምነቶች ስለ ስላሴ ፣ ስለ መዳን፣ ስለ ሙታን ትንሳኤ፣ …ወዘተ ምን ብለው እንደሚያምኑ  እንመልከት፡-
ኦርቶዶክስ
ካቶሊክ
ፕሮተስታንት
አይሁድ
አድቬንቲስት
ሞርሞን
---------------------------------//

    ከነዚህ ውጪ ሞርሞኖች 12 ሚሊዮን ገደማ አባላት ሲኖራቸው፤ የጆሆቫ ዊትነስስ / መጠበቂያ ግንብ/ ተከታዮች ወደ 6.6 ሚሊዮን ገደማ ሀዝብ እንዳላቸው ይገመታል፡፤ በአጠቃላይ ሐይማኖቶች እንደዚህ የተለያዩ ገጽታዎች ያሏቸው ቢሆኑም ሰዎችን ለማዳን የሚፈይዱት ነገር እምብዛም ነው፤ በሰማይ በክርስቶስ መሆንና አለመሆን እንጂ የየትኛውም ሐይማኖት አባል መሆንና አለመሆን እንደ መስፈርት አይታይም፡፡በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቁጥር 16 ላይ እንደተገለጸው በእግዚአብሔር ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምንና ንስሐ የሚገባ  ሁሉ ይድናል ፡፡ የእግዚአብሔርን ልጅ የማይቀበልና የማያምን ማንኛውም /የምንም ሀይማኖት ተከታይ ቢሆን /የዘላለም ፍርድ ይሆንበታል ማለት ነው፡፡

            አማላጅነት
                ክርስቶስ ፈራጅ ነው /አማላጅ  ?
             የጻድቃን አማላጀነት ያስፈልጋል ወይ ?
     የመላዕክት ድርሻስ ምንድን ነው ? የሚሉትን ነገሮች      በስፋት እንዳስሳለን፡፡
በቅድሚያ ጻድቅ የሚባለው ማን ነውምን ያደረገ ነውየሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ተመስርተን እንመልስ፡ ጻድቅ ማለት በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነ ፣ተቀባይነትን ያገኘ ማለት ሲሆን፡፡ ህግጋትን በመፈጸምና አንድም ሀጢያት ባለመፈጸም የታወቀው ብቸኛ ሰው የሆነው ደግሞ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ሁሉ በደልን እንደሰሩ ቃሉ እንዲህ ይላል፡ ‹‹ልዩነት የለምና ሰዎች ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል በክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ  ››  ሮሜ.320-23 ይላል፡፡ 'ልዩነት የለምየሚለው ቃል ጻድቅ  እንደሌለ እና በራሱ ተቀባይነትን በእግዚአብሔር ፊት ያገኘ አንድም እንደሌለ ነው የሚያሳየው፡፡ ስለሆነም በክርስቶስ በኩል በእምነት የሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ወደ ሰዎች መጣ  /ሮሜ.51/፡፡
       ‹‹እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ
        
ሰው ሁሉ እንደ መጣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ ምክንያት ስጦታው ህይወትን ለማጽደቅ  ወደ ሰው ሁሉ መጣ፡፡በአንዱ ሰው አለመታዘዝ  ብዙዎች ኀጢያተኞች እንደሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ፡፡›› ሮሜ.518 19
እግዚአብሔር ያዘጋጀው ጽድቅ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው፡፡ እንጂ ህግን በመፈጸም በጎ ተግባራትን በመከወን  አይደለም /ሮሜ.328/፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ጻድቅ ማለት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ  አምኖ የዳነ፣ በደሙም ኀጢያቱን የታጠበ እና በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በጽድቅ እየኖረ ያለ ሰው ነው፡፡
ክርስቶስ ለተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል አይደለም የሞተው ::ለዓለም ሁሉ እንጂ፡፡ስለዚህም ነው መድኀኒዓለም ብለን የምንጠራው፡፡የእርሱ ስቅለትና ሞቱ እኛን ለማዳን በቂ ነው፡፡ለኀጢያታችን የከፈለው ዋጋ፣የፈሰሰው ደም፣የተሰቃየው ስቃይ የሁላችንን እርግማን ለመሻር ዕዳችንን ለመክፈል በቂ፣ ከበቂም በላይ ነው፡፡አባቱ በቂ አይደለም! ብሎት በነበረ ኖሮ ሌሎች ተጨማሪ የመዳን ስራዎችን በሰራን ነበር፡፡ነገር ግን እኛን ለማዳን ያነሰ የቀረ ነገር አልነበረም የመስቀሉ ስራ አብን አርክቶታል፡፡ ተፈጸመ ብሎኣል፡፡ ስለዚህ ጽድቅ  የማግኛው መንገድ ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ ምዕራፍ 14 ቁጥርእንዲ ይላል፡-" እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፡፡በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡"  'በእኔ በቀርየሚለው ከጌታችን ኢየሱስ  በስተቀር ማንም ማዳን እንደማይችል ያሳያል፡፡
አማላጅነት የሚለው ቃልና ሀሳብ ብዙ የተሳሳቱ ትርጉም ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡ማማለድ ማለት ማስታረቅ፣ማስማማት ማለት ነው:: ይህን ነገር በሁለት ሊስማሙ በሚገባቸው መሀል ገብቶ የሚፈጽመው ሰው አማላጅ /አስታራቂ / ይባላል፡፡ለምሳሌ በዚህ ዘመን እንደሚታወቀው አንድ አገር ከሌላ አገር ጋር ሲጣሉ ሊሸመግሉ የሚገቡት ከተጣሉት አገራት በብዙ ነገራቸው የሚበልጡና ከፍ ያሉ አገራት ናቸው፡፡ለምሳሌ ሁለቱ ሱዳን አገራትን እያስማሙ ያሉት አገራት ፕሬዝዳቶችን ብናይ በፍጹም ከተጣሉት ያነሱ አይደሉም እንደውም ብዙ ጊዜ ከበድ ያለ ሰው ሲመጣ ሽምግልናው ይሳካል፡፡በቤተሰብ ደረጃም ብንሔድ ልጅ ከአባቱ ወይም ከእናቱ ጋር ቢጣላ ወደ ወላጆቹ ለዕረቅ የሚላከው ሰው እናትና አባት ሊሰሙትና ሊያከብሩት የሚችሉት ሰው መሆን አለበት፡፡ይህን ሁሉ የምንለው ማማለድ ማለት የማነስ ምልክት አይደለም ለማለት ነው፡፡
ታዲያ ሰውና እግዚአብሄርንም ለማስታረቅ ከሰውም ሰው የሆነ: ከእግዚአብሔር ጋርም እኩያ የሆነ አስፈላጊ ነበር፡፡ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆነ አምላክ በመሆኑ የማማለድን ስራ ሰራ፡፡ እርቁ ግን ከአብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱም ጋር ነበር፡፡
ይማልዳል / ያስታርቃል/ ሲባል ተንበርክኮ ይለምናል ፣ዝቅ ብሎ ይለማመጣል ማለት አይደለም፡፡እንኩዋን እርሱ ከላይ የጠቀስናቸው የአገራት ሽማግሌዎች  ተደፍተው አይለምኑም፡፡ነገር ግን ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ የሆነበት ደሙ በአብ ፊት ዘውትር ይታያል ማለት እንጂ፤ ስለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ ሲጠቅስ ''እርሱ ግን ስለ ኀጢያት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ  ተቀመጠ፡'' የሚለን፡፡ ዕብ. 1012  በተጨማሪ  928 ያንብቡ፡፡
አሁን በሰማይ እገሌንም ይቅር በለው እገሊትንም ይቅር በላት እያለ የሚለመንበት ዓይነት የምልጃ ስርዐት  ይኖራል ብለን አንጠብቅም፡፡ በክርስቶስ በኩል የቀረቡትን ሁሉ  ከሐጢያትና ከበደል ነጻ የሚያደርግ ቅዱስ  ደም ግን አለ፡፡ ደሙ ስለ ሁላችን ሐጢያት ማስተሰርያ እንዲሆን የፈሰሰ ነው፡፡
ክርስቶስ ስለ እኛ ይማልዳል! የሚለውም ቃል /ሮሜ 834/ ከላይ በተገለጠው አግባብ ካልተፈታ በቀር ሌላ ነገር እንድንረዳ ሊያደርገን ይችላል፡፡አምላክ ሆኖ እንዴት ዝቅ ይላል እንዴት ይማልዳል ? ክርስቶስ ፈራጅ ነው አማላጅየሚሉ ጥያቄዎች/ አሳቦች/ በስፋት  ይነሳሉ ፡፡ለነገሩ አምላክ ሆኖ እንዴት ያማልዳል? ከሚለው ነገር ይልቅ አምላክ ሆኖ እንዴት ይሞታል? የሚለው ነው ከባድ መሆን የነበረበት፡፡ነገር ግን አምላክ የሆነው ኢየሱስ  መከራን ተቀብሎአል፣ ተገርፎአል፣ ተሰቅሎአል፣ ሞቶኣል፡፡የማዳን ስራውም ተፈጽሞአል፡፡ ወደ እርሱ የሚቀርቡ ማናቸውም ሰዎች በደሙ ነጽተው ይጸድቃሉ፡፡እርሱ በስጋው ወራት የከፈለው የሀጢያት ክፍያና ከብርቱ ጩኸት ጋር ያቀረበው ምልጃ፣ አጠቃላይ የመስቀል ስራው ህያው ሆኖ ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ ይታይላቸዋል፡፡ክፍያው ስለ ሰው ልጅ ሁሉ  ነውና፡፡
የጻድቃን ምልጃ
ጻድቃን በምድር ላይ  ሳሉ በምድር ላይ ገና በህይወት ላሉት ሰዎች ሊጸልዩ ሊያማልዱ ይችላሉ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያምም አማልዳለች፡፡የሰዎችን ጉዳይ ለልጁዋ ነግራለች ከዚህም በላይ ከበጉ ሐዋርያት ጋር አብራ ጸልያለች፡፡ምናልባት ወንጌል ገና ስላልደረሰበት የአለም ክፍሎች አሳስበው ይሆንሌላም ብዙ የሰዎችን የተወሳሰበ ጉዳይ ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ቀርበው ይሆናል፡፡ምን እንደ ጸለዩ ነው እንጂ የማናውቀው መጸለያቸውን እናውቃለን፡፡ሐዋ. ስራ 114፡፡
አለምን ሁሉ ከአብ ጋር የማስታረቅና የማዳን ስራ ግን የተሰራው በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራ በመሆኑ፤ ጻድቃንም ሆኑ ሰማዕታት ሰዎችን የማዳንም ሆነ መንግስተ ሰማይ የማስገባት ስልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ የዘላለም ህይወት ጉዳይ እንዲህ ቀላል ነገር ቢሆንማ ኖሮ  ክርስቶስ መጥቶ ባልተሰቀለ፤ያን ሁሉ ዋጋ ባልከፈለ ነበር፡፡ እርሱ በስጋ ሳይወለድ እኮ ነብያት፣ አባቶች፣ ነበሩ፡፡ግን መዳን በእነርሱ በኩል ሊፈጸም የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ ነው የጌታችን መምጣት የግድ የሆነው፡፡
ከመዳን ጉዳይ ባሻገር ለተለያዩ ጉዳዮችም ቢሆን የሞቱ ቅዱሳን በህይወት ስላሉት ሊለምኑና የሰዎችን ጸሎት ሁሉ ሊሰሙ  እንዴት ይችላሉ? በመጀመሪያ ከፈጣሪ በስተቀር ሁሉ ፍጡራን  ናቸው፡፡ምድራዊ እናትና አባት ኖሮአቸው የተወለዱ በጊዜና በስፍራ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው መሞታቸው፡፡ ከላይ ሆነው ሁሉን ማየት እንደ እግዚአብሔር ከቻሉ እኮ: መለኮት ሆነዋል ማለት ነው ፤ግን እንደዛ አይደለም፡፡
              መላዕክት
በዚሀም ላይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ እልፍ አዕላፋት የሆኑት፤ አንድ መልዐክ ሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘት ስለማይችልና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መስማት ስለማይችል ነው፡፡ለምሳሌ አብሳሪውን የጌታ ታማኝ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤልን እንውሰድ ዕለተ ቀኑ በሚባለው 19 ምናልባት ታህሳስ 19  ንግስ ተብሎ በሚነገረው ቀን ፤ካሉት በርካታ በስሙ የተሰየሙ አብያተክርስቲያናት መካከል መርጦ የሚገኘው የትኛው ክልል ነው? የትኛውስ ቤተክርስቲያን ነው? ምክንያቱም አንድ ነው ብለናል፡፡ ሁሉን መቻል / Omnipotent / ሁሉን ማወቅ / Omniscience  / በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት / Omnipresent    / የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ባህሪ ነው፡፡ሁሉም ጻድቃን፤ መላዕክት ሁሉን ማወቅ፤በሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘትና የሁሉን ሰው ጸሎት ማድመጥ የሚችሉ ከሆነ እግዚአብሔር የሚባለው አምላክ ምን ልዩነት አለው ታዲያነገር ግን እውነቱ እነዚህ ባህርያት ማንንም ያላጋራበት የስላሴ ብቻ የሆነ ነው፡፡ ስላሴን የተለየ የሚያደርጋቸውም ይህ ባህሪ ነው፡፡
ለምሳሌ ቅዱስ ገብርኤል የኢየሱስን እናት ማርያምን ሊያበስራት የመጣ ጊዜ እርሱን ሌላ ቦታ ማግኘት አይቻልም፡፡ ምናልባት በዚያ ጊዜ አጣዳፊ ጉዳይ ካለ እንኩዋ ሌላ መልአክ ነው የሚላከው:: ምክንያቱም አንድ መልዐክ መገኘት የሚችለው በአንድ ቦታ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ወደ ዳንኤል መልስ ይዞ  እየበረረ ይመጣ የነበረውን መልዐክ  /አንዳንድ ሰዎች ገብርኤል  እንደሆነ ይላሉየፋርስ አለቃ  (የፋርስ መንግስት አገር  ላይ በአየሩ ላይ አለቃ የነበረ አጋንንት) እንዳያልፍ ከልክሎት እንደነበር፤ 21 ቀናትም ተቸግሮ እንደነበር ማወቁ ጥሩ ነው፡፡በሁዋላም ወደ ዳንኤል መምጣት የቻለው የመላዕከት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው ስለመጣ ነበር /ዳን.1013-20/፡፡ መላዕክት ሲላኩ በቦታ በስፍራ የሚወሰኑ መሆናቸውን ተመለከታችሁ? እንዳይመጣ ተከልክሎስ እንደ ነበረ አያችሁ?
መላዕክቶችም ሆኑ ቅዱሳን ወደ ጠሩአቸው ሁሉ የመሄድ፣ እንደወደዱ የማድረግ ማንነት አይደለም ያላቸው፡፡ መላዕክትነታቸው ለእግዚአብሔር ነውና እርሱ ወደ ላካቸው ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ እርሱ ያዘዛቸውንም ይፈጽማሉ፡፡ ይህን እውነት ማወቅና መናገር እነርሱን ማዋረድ ማለት አይደለም፡፡ በፍጹም እነርሱን ዝቅ ማድረግም አይደለም፡፡ እውነት አርነት ያወጣል፡፡አብርሐም ቤት የመጡት መላዕክት አብርሀም ቤት ጉዳያቸውን ሲፈጽሙ ነው  ሎጥ ዘንድ ሰዶም የሄዱት፡፡
ከመጀመሪያው ግን ከዘላለም  ሞት እንዲያድኑንና እንዲያስታርቁን ተሹመው በነበረ ፡አለመታዘዛችን ነበር ሀጢያት የሚሆን፡፡እነርሱም ብዙ በታዘቡን ነበር፡፡ አሁን ግን ከገረማቸው እንኩዋ  ሊገርማቸው  የሚችለው እነርሱ  ለእረኞች ያበሰሩትን ጉዳይ ያለመታዘዛችንን ሲያዩ ነው  /ሉቃ.29-14/፡፡ የፃድቃንም አግራሞት ለእነርሱም መደሀኒት ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ አለማተኮራችን ነው፡፡ ቅድስት  ማርያምም ከገረማት እንኩዋ የሚገርማትአርሱን ሰሙት›  ያለችውን፣ መድሀኒቴ አምላኬ ባለችው ልጁዋ አለማመናችን ነው፡፡ስለ ሁሉም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በመስቀል ላይ ስለ ከፈልክልኝ ዋጋ አመሰግንሀለሁ፡፡በቀራንዮ መስቀል በፈሰሰው ደምህ ሀጢያቴን እጠብልኝ ከበደሌም አንጻኝ፤ወደ ልቤም ገብተህ አብረኸኝ ኑር በማለት ከልባችን  ንስሀ  እየገባን በመጸለይ   ራሳችንን ለመንግስተ ሰማይ እናዘጋጅ፡፡የጌታችን ዳግም ምፅዐት ቀን ተቃርቡዋል፡፡ ከእግዚአብሔር በኩል ያለው ነገር ሁሉ ተሰርቶ አልቁዋል፤ ከእኛ በኩል የቀረውን እናድርግ!! ሰምተን እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡
በዚህ በክፍል ሁለት ትምህርት ውስጥ ካለፈው የቀጠለውንና ከዚህ ሐሳብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች እናነሳለን፡፡
  • ሐጢያትን  ለካህን  መናዘዝ  ተገቢ  ነውን ?
  • የአዲስ ኪዳን  ዘመን  ካህናት  እና ሊቀ  ካህን  ማን ነው?
  •  በጻድቃን  ስም  ቀዝቃዛ  ውሀ  ማጠጣት  ያጸድቃል?
  •  ዝክር  መዘከርና  ምጽዋት  ማድረግ  ለጽድቅ  ይጠቅማል?
  • የሙታን  ተስካር  ወይም  /ፑርጋቶሪ/ ምንድን  ነው?
                  የአዲስ ኪዳን  ካህናት እነማን ናቸው?
        ስለ ካህናት ስናነሳ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ፡ ካህናት በብሉይ ኪዳን የነበራቸው ሚና እና የአዲስ ኪዳን ክህነት ምን እንደሆነ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህናት የሚመረጡት ከሌዊ ነገድ ሲሆን ምግባራቸውም የቤተ መቅደሱን መንፈሳዊ ስርዐት መምራት ነው፡፡ በተለይም ለኀጢያት ስርየት የሚቀርቡ መባ መስዋዕቶችን ህዝቡን ወክለው በእግዚአብሄር ፊት የሚያቀርቡት እነርሱ ነበሩ፡፡ የብሉይ ኪዳን ህዝብ ሐጢያቱን የሚናዘዘው የሚሰዋው በግ ወይም ጠቦት ላይ ሲሆን ሊቀ ካህኑም ደሙን ይዞ በአመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፡፡/ ዕብ.96-7 /
  በአዲስ ኪዳን ዘመን ለሐጢያት ተብሎ የሚቀርብ መስዋዕት ወይም ደም የለም፡፡ሊቀ ካህናችን የሆነው ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ ደሙን ይዞ ወደ እውነተኛው የሰማይ መቅደስ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡/ዕብ.1011-18/ በአሁኑ ሰዐት እስራኤላውያን፣ ካህናቱ ሌዋውያንን ጨምሮ በተወሰነ መንገድ ስርዐቱን የሚከተሉ ቢሆንም የእውነተኛውን አዳኝ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ጌትነት ግን አልተቀበሉም፡፡
           የማሰርና የመፍታት ስልጣን...!
        የማሰርና የመፍታት ስልጣን የተሰጣቸው ካህናት እነማን ናቸው? በማቴዎስ ወንጌል .18 .18 ላይ እንደተጠቀሰው "...እውነት እላችሁዋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡":: በሌላም ስፍራ  ጌታ ለጴጥሮስ እንደተናገረው " የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሀለሁ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ማቴ.1618 አንባቢ  እንደሚረዳው እነዚህ ቃላት የተነገሩት የመጀመሪያው ጥቅስ የጌታችን ደቀመዛሙርት ለነበሩት ለመጀመሪያዎቹ የበጉ ሐዋርያት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለሊቀ ሐዋርያው ለጴጥሮስ የተነገረ ነው፡፡መሰረታዊውን ታሪክ ለማስታወስ ብዬ ነው እንጂ፤ በሌላ ዘመን ለሌሎች ክርስቲያኖች ቃሉ አይሰራም ለማለት አይደለም፡፡ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ሰዎች ናቸው፤ በክርሰቶስ በመሲሁ አዳኝነት ያመኑ እስራኤላውያን ናቸው፤ ደግሞ የክርስቶስ ሞቱና ትንሳኤው ምስክር ለመሆን የተመረጡ ወንጌል ሰባኪዎች  ናቸው፡፡ ለእነርሱ ግን የተለየ ልብስ እና የተለየ ጥምጥም አልነበራቸውም፡፡
     ሁለቱም ሐሳብ የብሉይ ኪዳንን ስርዐት ስለሚከተሉ ካህናት አይናገርም፡፡ ለእነርሱ እንዲህ ያለ ስልጣን የላቸውም፡፡ እንደዚህ ለመሆን አስቀድሞ በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነበረባቸው፡፡
     ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ያንን ለምጻም ከፈወሰ በሁዋላ " ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ !" ሉቃ.514 ያለውስ ጉዳይ ? ብለን ብናነሳ፡ በቅድሚያ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣበት ጊዜ በምድር ላይ የነበረው ስርዐት የአይሁድ ስርዐት እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ስራውን ፈጽሞ አዲስ ኪዳንን እስኪተካ ድረስ የሙሴን  ህግ በመታዘዝ ነው ይህንን ያደረገው፡፡ አንደኛ ህግን ልሽር ሳይሆን ልፈጽም ነው የመጣሁት ስላለ ማቴ. 517፡፡ ሁለተኛው በዘመኑ የነበሩ ፈሪሳውያን ሙሴን ህግ ይሽራል የሚል ተደጋጋሚ ክስ ቢያነሱም፡ እርሱ ግን ያንን አለማድረጉን ካሳየበት አንዱ ማሳያ ይህ ታሪክ ነው፡፡በሙሴ ህግ እንደተቀመጠው ሰው በለምጹ ከሰፈር ከተወገደ በሁዋላ ሌላ ጊዜ በሆነው መንገድ ቢፈወስ ወደ ህብረተሰቡ ከመቀላቀሉ በፊት ራሱን ለዘመኑ ካህናት ማሳየት ነበረበት፡፡ካህኑም መንጻቱን አረጋግጦ ወደ ሰፈር ይቀላቅለው ነበር፡ ዘሌዋውያን 142-32፡፡ ስለዚህም ጌታ የፈወሰውን ያንን ለምጻም በህጉ መሰረት በካህናቱ እንዲታይ ነው የሰደደው፡፡ ያንንም ያደረገው በትህትናና በታዛዥነቱ ነው፡፡ በዚህም ላይ የነጻን ለምጽ ሄዶ ለካህናት ማስፈተሸ ሐጢያትን ለእነርሱ ከመናዘዝ ጋር ምን ግንኙነት አለው? በዘመኑ የብሉይ ኪዳን ካህናት ከለምጹ የነጻን ሰው የሚፈትሹት እነርሱ ነበሩና ያንን አደረገ፡፡ከህጉ በላይ የሚቀኑለትን ወግና ስርዐታቸውን ግን አጥብቆ ይኮነንን ነበር፡ /ማር.714-21/
     የአዲስ ኪዳን ዘመን ህዝብ ሐጢያቱን መናዘዝ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኩል  በቀጥታ ለእግዚአብሔር ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህንና መካከለኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ዕብ.915፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ደግሞ ካህናት ተብለው ተጠርተዋል፡፡!1ጴጥ.29 ፡፡በዚህ መሰረት አንዱ ስለ አንዱ እርስ በእርስ ሊጸልይ ይችላል እንጂ፤ ለብቻው የተለየ ልብስ የለበሰ እና ለእርሱ ብቻ የሚገባ የጸሎት መጽሐፍ እያነበበ ንስሐ የሚያድል እና የህዝብን ሐጢያት የሚያስተሰርይ ሰዋዊ የክህነት ስርዐት የለም፡፡እግዚአብሔር  ሁሉንም ሰው በአንድ ጊዜ መስማት ስለሚችል፤ በፊቱ ንስሀ የሚገቡትን ሁሉ በክርስቶስ ይቅር ይላቸዋል፡፡ 1ዮሐ.14-9፣ሥራ.1048፡፡ከዚህ ውጪ የቤተክርስቲያን መሪዎችና መጋቢዎች የከፋ ሐጢያት በሚፈጸምበት ጊዜ ወይም በሚስጥር ተይዞ ሊጸለይ የሚገባ ነገር ይዘው ለሰዎች ሊማልዱላቸው ይችላሉ፡፡
             በጻድቅ ስም  ውሀ  የሚያጠጣ ይጸድቃልን ?
" እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይወስዳል፡፡ማንም  ከእነዚህ  ከታናናሾቹ ለአንዱ  ቀዝቃዛ  ጽዋ ውሀ  ብቻ  በደቀ መዝሙሩ ስም የሚያጠጣ አውነት እላችሁአለሁ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ " ማቴ.1040-42፡፡
 በጥሞና አንድ ጥያቄ እናንሳ የነቢያትና የጻድቃን ዋጋቸው ምንድን ነው ነቢይ እግዚአብሄርን ሰምቶ ላመጣው መልዕክት፡ ዋጋው ሰው ሲመለስ ፣ንስሀ ሲገባ ማየት ፣ከመቅሰፍት ከዕልቂት አምልጦ በፈንታው ለእግዚአብሔር እየተገዛ ሲኖር ማየት ነው፡፡ ጻድቅም አመጻን ጠልቶ  በጽድቅ ለኖረበት ኑሮ ጌታ የሚከፍለው መንፈሳዊና ስጋዊ በረከት ነው፡፡ ስለ መንግስተ ሰማይ ስለ መግባት ጉዳይማ ቢሆን ማንም ቢሆን በህግ እና በስራ አይድንም /ኤፌ.28-9/፡፡ ከዚህ ጋር ሌላው ዋና ነገር  " እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል " የሚለው ቃል ነው፡፡ ጻድቃንን ስንቀበል የምንቀበለው እነርሱ የሚሰብኩትን መድሐኒታችንን ኢየሱስን ነው፡፡ እርሱ እነርሱን ያዳነና ያጸደቀ በመሆኑ ልክ እነርሱን ተቀብለን ስናስተናግድ፣ ስንሰማቸው ፡ስበኩ ብሎ የላካቸውን ጌታ እንቀበላለን፡፡ ጻድቃንን የተቀበላችሁ ወገኖቼ  መስክሩ ብሎ የላካቸውን ኢየሱስንስ ተቀብላችሁዋል?? እርሱ እናንተን  የሚቀበል እኔን ይቀበላል ብሎአልና፡፡  በደቀ መዝሙሩ ስም ቀዝቃዛ ውሀ  የሚያጠጡ ሰዎችም ዋጋቸው አይጠፋም! ነው  እንጂ  የሚለው  አጸድቃቸዋለሁ አይደለም፡፡ ዋጋው /ክፍያው/ ብዙ ዓይነት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ለዘላለም ህይወት መንገዱ ግን አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ሰው በሆነው በክርስቶስ አምኖ ንስሐ መግባት ነው፡፡/ዮሐ.146/፡፡
  አያይዘን ዝክርን፣ ምጽዋትን፣ ሌሎች ለጽድቅ ተብለው የሚደረጉትን ነገሮች ሁሉ ብንመለከት እንዴት መንግስተ ሰማይ ለመግባት ሊጠቅሙን ይችላሉበእንደዚህ ሁኔታ መዳን ቢቻል ኖሮ ለምን መድኀኒዓለም መጥቶ ዋጋ  ከፈለልን ? ለምን ተገረፈ ? ተሰቀለ ? ሞተ ? ተቀበረ ? ለምን ?? ቃሉ የሚለን  " ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን አንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ስራ እንዳይሆን ስጋን የለበሰ ሁሉ በህግ ስራ ስለ ማይጸድቅ እኛ ራሳችን...እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፡፡ ገላ.216፡፡ በሐዋርያት ሥራ 4 .12 ላይ እንደተገለጠውም ወአልቦ፡ ካልእ፡ ሕይወት፡ ወአልቦ፡ ካልእ፡ ስም፡ በታሕተ፡ ሰማይ፡ ዘይትወሀብ፡ ለእጉዋለ፡ እመሕያው፡ በዘ፡ የሐዩ፡፡ /መዳን በሌላ በማንም የለም፡እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ  ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፡፡"
   ቆርነሌዎስ የሚባለው ሰው / በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 101-48 ላይ የምናገኘው/ ለጽድቅ ብሎ ብዙ ነገሮችን ይፈጽም ነበር፤ ለምሳሌ ይጾም ነበር፣ ከቤተሰዎቹ ጋር እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመልክ ነበር፣ ለድሆች እጅግ ምጽዋት ያደርግ  ነበር፡፡ ምንም እንኩዋ ድርጊቱ ደስ የሚያሰኝና እግዚአብሔር ዘንድ የደረሰም ቢሆን ለመጽደቅ ግን ዋነኞች ጉዳይ ስላልነበሩ፡ መልዐክ  ወደ እርሱ ዘንድ ተልኮ ስለ ክርስቶስ ወንጌል የሚነግረው፣ እንዲያምን የሚረዳውና የሚያስተምረው ደቀመዝሙር ጠቁሞት ልኮ አስመጥቶታል፡፡ ያደረገው ነገር ሁሉ ለመዳኑ በቂ  ከነበረ  ጴጥሮስ ለምን ወንጌል እንዲነግረው ታዘዘ ?  መልካም ስራዎች ሁሉ በጌታ ያመኑና የጸደቁ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመልካም ስራቸው ጌታቸውን ማስመሰገንና መግለጥ ስላለባቸው፡፡ በጎ ስራ መስራት ዝክር፣ ጾምና ጸሎት፣ ምጽዋት ማድረግ ግን ብቻውን አያጸድቅም፡፡
              የሙታን ተስካር
  ለሞቱ ሰዎች መጸለይ ይገባል! የሚሉ ሰዎች መነሻ ጥቅሳቸው 2 መቃቢያን 1241-46 / 66 መጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ባለ አዋልድ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ/ ሲሆን፤ በእርገግጥ በጥንት ጊዜ ጀምሮ በቻይናውያን እምነትም ዘንድ እንደ ቡዲዝም ባሉት እምነቶች ሙታንን ወክለው መስዋዕት ማቅረብ የተለመደ ነገር ነው፡፡
 ለሙታን መጸለይ /ፑርጋቶሪ/ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ ሲኦል ትገባለች፤ ነገር ግን ቤተሰቦቹና ዘመድ አዝማድ ከሞተበት ዕለት ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በየተወሰነው ጊዜ በስሙ ዝክር ቢያወጡለት ቀስ በቀስ ከሲኦል እየወጣ ይመጣና በሂደት ገነት ይገባል የሚል የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት የምናነሳቸው የገድላት መጽሐፍት ለዚህ ትምህርት አስተዋጽኦ አድርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡
  1.   ነገር ግን ሉቃስ 16 .19-31 ከቀረበውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው ምሳሌ እውነቱን  መማር እንችላለን፡ አንድ ሰው የሆነውን ሆኖ ከሞተ ወዲያ ሰማይ ላይ ሔዶ የሚያስቀይረው ሐሳብ የለም፡፡ በጻድቃን ሰማዕታት ምልጃና ልመናም መዳን አይችልም፡ ክፍሉ ላይ እንደተመለከተው ሐብታሙ ሰው ከሲኦል ሆኖ ምንም አብርሐምን በእሳት እየተንገበገበ ቢለምንም '' በዚህ ያሉ ማለትም በአብርሐም እቅፍ ውስጥ በእረፍት ያሉ ወደ ስቃዩ ስፍራ መሄድና ማዳን እንዳይችሉ በመካከል ታላቅ ገደብ ተደርጎአል:: '' ነው ያለው፡፡ / በገነት ያሉ ወደ ሲኦል ፤በሲኦል ያሉ ወደ ገነት መምጣት አይችሉም ! / ፡፡ ከዚያ በኋላ በምድር ላይ አባቱ ቤት ስላሉ 5 ወንድሞቹ  ነው መጨነቅ የጀመረውው፡፡ ወደዚህ ስቃይ ስፍራ እንዳይመጡ አንድ ሰው ከሞት ተነስቶ ይመስክርላቸው ብሎ ተማጸነ፡፡ ምናልባት እንደርሱ ሰማይ ስንሔድ ጻድቃን ሰማዕታት አሉልን! ብለው ተዘናግተው ከሆነ እንኩዋ፤እውነቱ እንዳልሆነ ስለተረዳ ይሆንለማንኛውም ለዚህም ጥያቄ ቢሆን እዛው ምድር ላይ ያሉትን መስካሪዎች /ሙሴና ኤልያስ አሉላቸው / እነርሱን  ይስሙ ነው የተባለው፡፡ ተመለከታችሁ በሰማይ ምንም አይነት ቀልድ እንደሌለ? ሐጢያተኛ ሰው ከሞተ ወዲያ፡ ፍርድ ብቻ ነው የሚጠብቀው፤ አንድ  ጊዜ  በፍርድ  ሲኦል  የገባን   ነፍስ  ተከራክሮ ውሳኔ  አስቀይሮ  ወደ ገነት ሊያመጣ  የሚችል  አንድም  መልዐክ  ወይም  ጻድቅ  የለም!!!   ወገኖቼ አንሞኝ ዛሬውኑ ፡ቀን ሳለልን ፣ትንፋሻችን ሳይቆም በክርስቶስ አምነን እንዳን ! አውነተኛ ንስሐም እንግባ፡፡ ጌታ ሆይ ሐጢያቴን ይቅር በለኝ ልጅህን ኢየሱስን የህይወቴ አዳኝ አድርጌ እቀበላለሁ እንበል፡፡ አሁኑኑ ባሉበት ቦታ ሆነው ንስሐ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

ሌላው ጥያቄ ሰንት ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ አለ ?
በርካታ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጉዳይ ፡ 81 አሀዱ ነው ትክክል ?  ወይስ 66ቱ ? ወይስ 72ቱ የካቶሊኮች መጽሐፍ ? ለመሆኑ የእነዚህ ቁጥሮች መለያየት እና መስፈርቱ ምንድን ነው ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በዚህም መነሻነት ይህንን ርዕስ ትንሽ ሰፋ አድርጎ መመልከቱ ሳይበጅ አይቀርም፡፡
መፅሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚቀርቡ ብዙ የሰዎች አስተያየቶች በመኖራቸው ይህንን ትምህርት ሰፋ አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ በዚህ ክፍለ ትምህርት ውስጥ በተለይ ጎላ ብለው የሚታዩትን ልዩነቶች እንጂ ተያይዘው የሚነሱትን ሐሳቦችና ጥያቄዎች ሁሉ አንስቶ መፃፍ እንደማይቻል አንባቢ ሊረዳው ይችላል ፡፡ ምክንያቱም እጅግ ሰፊ በመሆኑ ነው፡፡
ከምናነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ  ቁጥር  ስንት  ነው ? የሚለውን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በኦርቶዶክስ 84 ወይም በተለምዶ 81 ካቶሊክ 72 መፅሐፍትን ስትቀበል ፕሮቴስታንት /ወንጌላውያን አማኞች/ ደግሞ 66 ቁጥር  ያለው መፅሐፍን ይቀበላሉ፡፡ ማናቸው ናቸው ትክክል? ወይም እውነቱን እንዴት ልናገኝ እንችላለን? ብለን መጠየቃችን አይቀርምና፡፡

መፅሐፍ  ቅዱስ የእግዚአብሔር  ቃል ነው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው በሰዎች ቁዋንቁዋ ባህል የተጻፈ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ /2ጢሞ. 315 1ጴጥ.21/
መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ትልልቅ ኪዳኖች ያሉት ሲሆን በብሉይ ኪዳን  /አሮጌው/ እና አዲስ ኪዳን በመባል ይታወቃሉ፡፡ ብሉዩ በዕብራይስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈ ሲሆን ፤አዲስ ኪዳን ግን በዘመኑ  ታዋቂ በነበረው የግሪክ ቋንቋ ነበር የተፃፈው፡፡ ከዚያ በኋላ  በብዙ መቶ ቋንቋዎ በዓለም ዙሪያ ተተርጉሞአል ፡፡ በዓለም ላይ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ መጽሐፍ ነው፡፡
ከላይ ያነሳነውን  ጥያቄ ለመመለስ የግድ የመጀመሪያዎቹን ትርጉሞችና ቅጂዎች ማንሳት ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው በአብዛኛው በዕብራውያን /እስራኤላውያን ህዝብ /መካከል ነው ፡፡ የታሪኮቹ ባለቤቶችና ጸሐፊዎች እዚያ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡በነገራችን ላይ ቢያንስ አርባ የሚሆኑ ሰዎች እንደጻፉት ይታመናል፡፡ ባለታሪኮቹ እነርሱ ከሆኑ ደግሞ በአሁን ጊዜ ጭምር እጃቸው ላይ ያለና የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ምን እንደሚመስል ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ይህም በተለይ ብሉይ ኪዳንን በተመለከተ እንጂ አዲስ ኪዳንን ጉዳይ ላይ አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም እስራኤል ስለ ሐጢያታችን በምድራቸው ላይ ሞቶ የተነሳውን መሲሁ ክርስቶስን እስካሁን ድረስ ስላልተቀበሉትና ሌላ መሲህ እየጠበቁ ከመሆናቸው አንጻር ነው፡፡/ሮሜ.9/
የዕብራይስጡ መፅሐፍ ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፡-
          /የመጽሐፉ ይዘት 24 ነው፡፡/

1-የሕግ መፃሕፍት /5/
   /አሪት ዘፍጥረት፣ ዘጸዐት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም/
2-የነብያት መጻሕፍት-/8/
  -ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ 1-2 ሳሙኤል፣ 1-2 ነገስት፣
  -ኢሳያስ፣ ኤርሜያስ፣ ሕዝቅኤል፣ 12 የነብያት     መጻሕፍት
3-የጥበብና ምሳሌ መጻሕፍት./ 11/
   -የጥበብ  መዝሙር ፣ምሳሌ፣ ኢዮብ
   -5 ጥቅል መጻሕፍት . መኃልየ ፣ሩት፣ ሰቆቃው ኤርሜያስ፣ መክብብ፣ አስቴር፡፡
   -3 መጻህፍት. ዳንኤል፣ ዕዝራ-ነህምያ፣ ዜና መዋዕል

የፕሮቴስታንት ቀኖና እንደሚከተለው ነው፡፡
      / የመጽሐፉ ይዘት 39 ነው፡፡

1- የሕግ መጻሕፍት./5/
  / ዘፍጥረት፣ ዘጸዐት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም/
2-ታሪካዊ መጻሕፍት./11/
 / ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ 1ሳሙኤል፣ 2 ሳሙኤል፣ 1ነገስት፣ 2 ነገስት፣ 1ዜና መዋዕል፣ 2ዜና መዋዕል፣ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ አስቴር፡፡
3-የጥበብ መጻሕፍት./5/
  /ኢዮብ፣ መዝሙር፣ ምሳሌ፣ መክብብ፣ መኀልዬ ዘሰሎሞን/
4- ትልልቅ /አበይት/ ነብያት./5/
  / ኢሳያስ፣ ኤርሜያስ፣ ሰቆቃው ኤርሜያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል/
5- ትናንሽ ነብያት. /12/
  / ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብዲዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ሚልክያስ/
     ከላይ እንደተመለከተው መጻሕፍቱ በአከፋፈል ረገድ ካልሆነ በቀር በዕብራይስጡ እና በፕሮቴስታንቱ ቀኖና መካከል የይዘት ልዩነት የለውም፡፡/ በኦርቶዶክስና በካቶሊካውያን መካከል እነዚህን መጽሐፍት በተመለከተ ምንም ጥያቄ የሌለ እና ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት በመሆናቸው ልዩነቶቹ ላይ ማለትም የተጨመሩ አዋልድ መጻሕፍቱ ላይ ማተኮሩን መርጫለሁ፡፡
 አስቀድመን ከላይ እንዳነሳነው ካቶሊክ የባሮክ፣ ጦቢት፣ ዮዲት፣ ሲራክ፣ 1-2 መቃብያን  ከሚባሉ ጋር 72 መጻሕፍትን፡፡ ኦርቶዶክስ  ደግሞ  ተረፈ ዳንኤል፣ መቃብያን ቀዳማዊ፣ መቃብያን ካልዕ፣ 3 መቃቢያን፣ ሲራክ፣ ጸሎተ ምናሴ፣ ተረፈ ኤርምያስ ሶስና፣ ባሮክ፣ መጽሐፈ ጥበብ፣ በዕዝራ ሱትኤል፣ ዕዝራ ካልዕ፣ ጦቢት፣ ዮዲት፣ አስቴር፣መዝሙረ ሰልስቱ  ደቂቅ፣ ተረፈ ዳንኤል፣ ኩፋሌ፣ ሄኖክ  የሚባሉ  84 ይዘት ያላቸው መጻህፍት አሉዋቸው፡፡ይህ ማለት ዕብራይስጡ 24 ወይም ፕሮቴስታንቱ 39 የሚባሉ የብሉይ ኪዳን ቀኖና መጻሕፍትን ጨምሮ ነው፡፡
አንባቢ እንደሚያስተውለው ዋናዎቹ  የመጻሕፍቱና የታሪክ ባለቤቶች ዕብራውያን እነዚህን አዋልድ ያካተተ መጻሕፍት የላቸውም፡፡ ይህ ማለት የታሪክ ባለቤቶቹ ያልተቀበሉዋቸው መጻህፍት እንደሆነ ልብ ይሉዋል፡፡
ከዚህ በመቀጠል የምንመለከተው የጥንት አባቶቻችን በምን መስፈርት ቀኖናውን /የመጻሕፍቶቹን ይዘትና ዝርዝር / እንደወሰኑ ነው፡፡
     ቀኖና የተወሰነበት  አራት ዋና ዋና መመዘኛዎች -
1- በዋናው የዕብራይስጡ ዝርዝር ላይ የተካተተ መሆኑን፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ዕብራይስጡ የራሳቸው የባለታሪኮቹ መጻሕፍ በመሆኑ ከምንም ነገር ይልቅ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡የዕብራይስጡ መጽሐፍ 24 መጻሕፍትን የያዘ ነው፡፡
2- በአዲስ ኪዳን ዘመን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ዘመኑ ዕውቅና ሰጥቶ የጠቀሰው መሆኑ፡፡ ይህም ጌታችን በስጋው ወራት ባስተማረበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍት፣ ከነብያትና ከመዝሙራት የተነገሩትን ቃላት ይጠቅስ ነበር፡፡በአንድ በኩል መጽሐፍቱ ልብ ወለድ ታሪኮች ሳይሆኑ የእግዚአብሔር ቃል እንደነበሩ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፤

3- በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ስልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በመጥቀሳቸው ነው፡፡ ይህም ከጌታ በመቀጠል እርሱ ያስተማራቸውና የመረጣቸው አገልጋዮቹ ለብሉይ ኪዳን መፃህፍት ይሰጡ የነበረውን ክብርና ጥንቃቄ፤ ብሎም ጥላውን እያሳዩ ፍጻሜው እንዴት እንደሆነ በመንፈስ እየመረመሩ ይገልጡ እና ይተነትኑ ስለነበረ ሌላው ማረጋገጫ ነበር፡፤
4- የጥንቱዋ ቤተክርስቲያን /ቅዱሳን/ ይህነንን መጽሐፍ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይጠቀሙበት እንደነበረ ከታወቀ ቀኖና /canon / ይጸድቅ ነበር፡
ከላይ የተመለከቱትንና ሌሎች እውነታዎችን በማገናዘብ የጥንት አባቶቻችን ቀኖናውን ወስነውልናል፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት ውጪ ያሉት አዋልድ መጻሕፍት የጨለማ ዘመን ተብሎ በሚታወቀው 430 የዝምታ ዓመታት ውስጥ አብዛኛዎቹ እንደተጻፉ በስፋት ይታመናል፡፡ ይህም ደግሞ የብሉይ ኪዳን ቀኖና ተወስኖ ከተዘጋ በሁዋላ  የተጨመሩ እንደሆነ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ከተወሰኑ አብያተክርስቲያናት ውጪ መላው ዓለም የሚጠቀምበትን የታወቀውን መጽሐፍ በማንበብ እንድንጠቀም እመክራለሁ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል መጨመርም ሆነ መቀነስ መርገምን ያስከትላል፡/ራዕይ 22// ‹ ስለ ራዕዩ መጽሐፍ ሲናገር የጨመረ መቅሰፍት ይጨመርበታል ፤ሲል የቀነሰ ደግሞ ዕድሉን ያጎድልበታል፡፡ይላል፡፡ስለዚህ  መንፈስ ቅዱስ የቤተክርስቲያን አበውን ተጠቅሞ የወሰነልን ፣ለዚህ ህይወታችን ተመጥኖ የተሰጠን ቃል በቂ ነው፡፡እርሱን በቅጡ ለማወቅ ቅን ልቦናችን ቢነሳሳ፣ለማንበብ፣ ለማጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ ቢኖረን ህይወት ለዋጭ ቃል ነው፡፤ተግሳጽንም ታላቅ ምክርን ከጽድቅ ጋር የምንቀስምበት ጭምር፡፡ከዚህ በተጉዋዳኝ ግን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ እንደሚታመነው ተጨማሪ መጻህፍትን ለተጨማሪ እውቀቶች ብናነብ ምንም አይጎዳም! ስለሚሉ፤እንደ ፕሪስቢቴሪያንና አንግሊካል የመሳሰሉ አብያተክርስቲያናት ለዚህ ነገር ዋና ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለዕውቀትም ቢሆን ልንጠቀምበት የምንችለው፡ እውነትን እስካላፋለሰ እና ትክክለኛውን መለኮታዊ የድነትና የህይወት መርህ እስካልበረዘ ድረስ ብቻ ነው ፡፡

             አዋልዱ በቀኖናው ላይ ለምን አልተካተቱም ?
1-   በዕብራይስጡ ዝርዝር ላይ የሌሉና ቀኖናው ከተዘጋ በሁዋላ የተጨመሩ በመሆናቸው ነው፤
2-   በአዲስ ኪዳን ዘመን ያልተጠቀሱ ሲሆኑ፤ አሉ የሚባሉም ካሉ እንደ አባባል የተጠቀሱ እንጂ እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚወሰዱ አይደሉም፡፡
3-   የአይሁዳውያን ታሪክ አጥኚ ጆሴፈስ ፈጽሞ አላካተታቸውም፡፡ ይህ ማለት ታሪክ አያውቃቸውም እንደማለት ነው፡፡
4-   አዋልድ  መለኮታዊ ቃል እንደሆነ የሚገልጽ አንድም ማስረጃ የለም፤
5-   የታሪክ፣ መልክዐ-ምድር አቀማመጥ፣ ወይም ጊዜንና ክስተቶችን አዛብቶ የማቅረብ የጎላ ችግር ይታይበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ ወደ መጨረሻ ላይ ከአዋልዱ ላይ አንዳንድ ጥቀቅሶችን ስንመለከት የበለጠ ይገባናል፡፡
6-   የእግዚአብሔርን ቃል የሚጻረር ትምህርት /ዶክትሪን/ ያስተላልፋሉ፤ ለምሳሌ፡-ውሸትን ይፈቅዳል፤ ሰይጣንን ያሞጋግሳል....ወዘተ፡
 7-   በስነ ጽሁፋዊ ይዘቱ በታሪክና ምሳሌ ወይም ተረት ውስጥ የሚመደብ ነው፤
8-   መንፈሳዊና ሞራላዊ ይዘቱ / አቁዋሙ/ ከብሉይ ኪዳን አጠቃላይ ታሪክ አንጻር በጣም የራቀ ወይም የወረደ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
     አዋልድ መጻሕፍት  አዛብተው ከሚናገሩት ነገር በጥቂቱ-
  • ኩፋሌ 1624 ያዕቆብ  ከአብርሐም ጋር ተኛ  ይላል፡፡ ነገር ግን ዘፍ.257 ላይ እንደዚያ አይገልጽም፡
  •  መቃብያን ሳልስ 27 ላይ የሰይጣንን ፉከራ  ይገልጻል፡፡ እንደውም ቃሉ ከቁራን ላይ ቀጥታ የተወሰደ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በተጨማሪ 3 መቃብያን 16-24 .21-2 ከቁራን ላይ ከአል አእራፍ ቁጥር 11-27 7ኛው ሱራ ላይ እንደተወሰደ ማመሳከር ይቻላል፡፡
  • መጽሐፈ ጥበብ  66 ላይ ደግሞ በቀጥታ የመዳንን እውነት የሚያፋልስ ሆኖ ቀርቦአል፡
  • ሲራክ 2525 እግዚአብሔር በመሰረተው የተቀደሰ ጋብቻ መካከል ሊኖር የማይገባውን ነገር ይናገራል፡፡
  •  ሲራክ 2410-11 በተለይም .8 ላይ ስለ ማርያም፣ ሐዋርያት ወንጌል ጉዳይ በግልጽ ያወራል ፡፡ መጽሐፉ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተጻፈ አይመስልም፡
  •  እዝራ ሱትኤል 529 ላይ እንዲሁ ስለ መንግስተ ሰማይ ስለ ክርስቶስ ይናገራል፡፡ መንግስተ ሰማይ በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጽ ይታወቃልን ?
  •  ሄኖክ 3724 ሐጢያተኞች እንድናለን ብለው ተስፋ እንዳያደርጉ ተስፋ ያስቆርጣቸዋል፡፡
  •  ሔኖክ 191 ላይ ቅዱስ ሚካኤል የመንፈስ ቅዱስ እውቀቱ ያበሳጨኛል ብሎ እንደተነናገረ ተገልጹዋል፡፡ በውኑ ቅዱስ ሚካኤል በመንፈስ ቅዱስ እውቀት ይበሳጨጫልን? ሌላም ሌላም በርካታ የተፋለሱ ነገሮችን የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ አንባቢያን ተጨማሪ ጥቅሶችን ሲፈልጉ በአድራሻችን ሊጽፉልንና ተጨማሪ እውነቶችን ሊረዱ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግን የተጠቀሱት ነገሮች ለማመሳከሪያነት በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
 ማስታወሻ፡- ከላይ ያሉ መግለጫዎች  ከተለያየ መንፈሳዊ መጻሕፍት እና የተዘጋጁ የስልጠና ትምህርቶች  ላይ ተገናዝቦ የቀረቡ ናቸው፡፡

  ያላመኑ ሰዎች በምን በምን ተመስለዋል?

ወደ ክርስቶስ መንግስት ገና ያልተጨመሩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ  በተለያየ ነገሮች ተሰይመዋል ፡፡ ለምሳሌ በመከር፣ በዓሳ ፣ በጠፉ በጎች..ወዘተ፡፡
   ሀ. በመከር -ዮሐ.4
መከር የሚባለው ነገር በተለይ በግብርናው ዘርፍ አካባቢ በጣም የታወቀ ቃል ሲሆን ትርጉሙ ሊታጨድ የደረሰ ሰብልን ለማመልከት ነው፡፡ ወደ መታጨድ ከመድረሱ በፊት የመዝራት ወይም የመትከል ወራት ነበረ፡፡ እየታረመ እና እየተኮተኮተ አድጎ ነው ለአጨዳ ጊዜ የሚደርሰው፡፡ ለሰብሉ ዕድገት የሚጠቅሙ እንደ ውሐ ምናልባት ዝናብ፣ የተለያዩ ዓይነት  ማዳበሪያዎች እና ሌሎችም እንክብካቤዎች ይደረግለታል፡፡  
         በአዳዲስ ሰዎችም ጉዳይ እነደዚሁ ነው ፤ ብዙ ነፍሳት ረጅም ልፋት የተደረገባቸው የብዙ ታጋሽ ሰዎች ውጤቶች ናቸው፡፡ ገና ከጅማሬው የወንጌል ቃሉን ልባቸው ውስጥ ከመዝራት ጀምረው ቀስ በቀስ እየኮተኮቱ አብስለው ነው ሰዎችን ለውሳኔ ያበቋቸው፡፡ ምክንቱም ሰውን የሚያክል ነገር ስለወንጌል አስረድቶ እና አሳምኖ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ለማምጣት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ የአንዳንዶቻችን ህይወት ራሱ በቂ ምስክር ነው፡፡ ምናልባትም የሚታገሱ ሰዎች ልኮልን ባልነበረ እስካሁንም የምንድን አይመሰለኝም፡፡ በዚህ ዘመን ክሽን ያለ የወንጌል መልዕክት በማቅረብ የሚታወቅ አንድ አገልጋይ ሰዎችን ወንጌል ላስተምራችሁ ብሎ የሚለምንበትንና የሚታገስበትን ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ነበር ያለው ‹‹ ለማያምኑ ሰዎች ወንጌል ለመስበክ ወይም ለማስተማር የመጀመሪያዎቹ ጊዜ አካባቢ ላይ እኛ ለምነን ልናደርገው ሁሉ ይገባል ምክንያቱም የወንጌል ጥቅሙ የገባን እኛ ስለሆንን፤ በኋላ ላይ ግን እነርሱ ራሳቸው ይለምኑናል፡፡›› ይህ ነገር እውነት ነው፡፡ ሌላው ከዚህ ጋር ተያይዞ በወንጌል ጉዳይ ፍሬያማ ከሚያደርገን ነገር አንዱ የቃሉን ዘር በሰዎች ልብ ከዘራን በኋላ መከታተል አለብን፡፡ እንዴት? ከተባለ አትክልትን ውሐ እንደሚያጠጣ ጥቂት  በጥቂት ቃልን መናገር ፣ ስለ እነርሱ አበክሮ መጸለይ፣ ከውስጣቸው አረምን በሂደት ማጥፋት /ስንዴውም አብሮ እንዳይነቀል በመጠንቀቅ/ ፣ከዚያም ዕድገቱን በየጊዜው መከታተል ነው፡፡
       ለ. ዓሳ
ለሰዎች መመስከር ከዓሳ ባህላዊ አጠማመድ ዘዴ ጋር በማያያዝ ብዙ ትምህርት ልናገኝበት እንችላለን፡፡ለነገሩ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የበጉ ሐዋርያት በዚያን ዘመን ዓሳ በማጥመድ ይተዳደሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከዚህም በኋላ ሰዎችን አጥማጆች አደርጋችኋለሁ በሚለው ቃሉ መሰረት እየሳበ ነው የወንጌሉ ሰራተኞች ያደረጋቸው ፡፡ እነርሱም ዓሳዎችን የሚያጠምዱበትን መረብ ትተው ሰዎችን የሚያጠምዱበትን የወንጌል መረብ ጨብጠዋል፡፡ አንድ ባህላዊ ዓሳ አጥማጅ ወደ ጥልቁ ባህር በመምጣት ዓሳን አንድ በአንድ የሚያጠምድበትን መንገድ /ዘዴ/ ልብ ብለን እንደሆነ በቅድሚያ ዓሳው ሊበላው የሚችለውን የምግብ ዓይነት ለይቶ በማጥመጃ መንጠቆው ጫፍ ላይ ያደርግና በረጅም ገመድ አንጠልጥሎ ከላይ ወደ ታች ይለቀዋል ፡፡ ከደቂቃዎች በኋላ የወረወረውን ቀጭን ስቦ ከውሐው ሲያወጣው ሊገጥመው የሚችሉ ሶስቱ ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፡፡ አንደኛ ምግቡም ሳይበላ አንድም ዓሳ ሳይያዝ እንዲሁ የተወረወረው መንጠቆ ይወጣል፡፡ ሁለተኛ ምግቡ ተበልቶ ዓሳው ግን ለጥቂት በመንጠቆው ሳይያዝ ይወጣል፡፡ ሶስተኛው በመንጠቆው ላይ የቀረበለትን ምግብ እየበላ እያለ ድንገት የተያዘ ዓሳ እየተጎማለለ በወጥመዱ ተይዞ ይወጣል፡፡ ልክ እንደዚሁ በወንጌል ምስክርነት በምንወጣበት  ወቅት ፡-
1-የሚነገራቸውን የወንጌል ቃል የማይቀበሉ፣ የሰጠናቸውን መንፈሳዊ በራሪ ወረቀት በንዴት የሚቀዳድዱ፣ እምቢተኞች ይገጥሙናል፡፡
2-የቀረበላቸውን የወንጌል መልዕክት በጥሞናና በትዕግስት ካደመጡ በኋላ የመጨረሻዋ ውሳኔ ላይ ሲደርሱ ወደ ኋላቸው የሚያፈገፍጉ ና የማይቀበሉ ሰዎች ይገጥሙናል፡፡ አንዳንዶቹ የውሸት ቀጠሮ ሊሰጡ ይችላሉ፤ ምናልባትም ወዲያውኑ መወሰን የሚቸገሩ፣ ነገሩን ውሎ አድሮ ማሰብ የሚፈልጉ ከእነደዚህ ዓይነት ጎራ ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
3-ሶስተኛው እውነት ቀደም ብለን እንዳየነው ደስ የሚያሰኝ ሲሆን ይህም የቀረበላቸውን የወንጌል መልዕክት ሲሰሙ ልባቸው ተነክቶ እሺ አሁን እኔ ምን ላድርግ? የሚሉ ናቸው፡፡ ልክ በወትመድ ተይዞ ከውሀው እንደወታው ዓሳ ዚያኑ ዕለት ከዓለም ጋር የሚያቆራርጣቸውን ብርቱ ውሳኔ የሚወስኑ ዕድለኞች ናቸው፡፡
ልብ ልንል የሚገባው ወደ ሶስተኛው ደረጃ ለመድረስ ትዕግስት እንደሚያስፈልገን ነው፡፡ ዓሳዎች ቶሎ ባይያዙም ተግተን ሳንታክት ካጠመድን የተወሰኑ ዓሳዎች ይዘን ወደቤታችን መሔዳችን አይቀርም ፡፡ ወጥተን ምንም ሳንይዝ የገባንባቸውም ቀኖች ተስፋ ሊያስቆርጡን አይገባም፡፡ እነ ጴጥሮስ እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰ ቢያንስ ሁለት ጊዜ ያህል ዓሳ ያላጠመዱባቸው ቀናት ነበሩ በሉቃስ 5 ላ ይ እና በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 21 ላ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ያልተመዘገበ በርቃታ ጊዜያት እንደነበሩ መገመት አያስቸግርም፡፡ ነገር ግን አይታክቱም ፣ ነገ ተመልሰው ትንንት ወዳላተመዱበት ጥብርያዶስ ባህር በተስፋ ይሄዳሉ፡፡ ምስክርነት እንደዚህ ነው፡፡ ደጋግሞ ወደ ዓለም መሄድ ፣ አንዳንድ ጊዜ ምንም የሚሰማን እንኳ ላይኖር ይችላል፤ ያን ጊዜ ቸኩለን በቃ እኔ ለወንጌል አልተጠራሁም ማለት ነው ብለን ሁሉን እርግፍ አድርገን መተውና ቅናታችንን መጣል የለብንም፡፡ መታገስና በተደጋጋሚ መውጣት በእርግጠኝነት ዓሳው ይያዛል፡፡
ካልሆነ እንኳ ራሳችንን ዝ እንደሚዘር እንደዘሪ መቁጠር እንችላለን /ዮሐ.4፡36/ የሚያጭዱና የሚሰበስቡ ምናልባት ሌሎች ሊላኩ ይችላሉ፡፡ ደስ የሚለው ነገር የሚዘራም የሚያችድና የሚሰበስብም ዋጋው አንድ ነው፡፡
     ሐ. በጎች
በጎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተለየ እንድምታ አላቸው፡፡ ከብሉይ ኪዳን ዘመን  ጀምሮ አቤል ፣ አብርሐም ያቀረቧቸው መስዋእቶች ጋር ፣ እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡበት ምሽት የታረደው የፋሲካ በግ ….ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በአዲስ ኪዳንም በርከት ያሉ ቦታዎች ላይ እናገኛለን ፤ ለምሳሌ ጌታ ራሱ የበጎች በር ፣ እረኛ እንደሆነ ተናግሯል /ዮሐ.10፡7 ና 14 /፣ ክርስቲያኖችም በበጎች ተመስለዋል / ማቴ 25፡33 /፡፡ በዚህ ርዕስ ስራ የምናነሳው ግን ከዚህ በረት ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ እነርሱን ደግሞ ላመጣ ይገባኛል፡፡› ዮሐ.10፡16 እንደተባለ ፤ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ስላልመጡ በጎች/ ሰዎች/ ይሆናል፡፡
‹‹ ከእናንተ መቶ በጎች ያለው ከእነርሱም አንዱ ቢጠፋ ሊፈልገው የማይሔድ ፡ ባገኘውም ጊዜ በጫንቃው ላይ ተሸክሞ ወደ ቤቱ ይመጣል፤ ጎረቤቶቹንም ከእኔ ጋር ደስ ይበላችሁ ፡ የጠፋውን በጌን አግኝቼዋለሁ ይላቸዋል፡፡›› ሉቃስ 15፡1-7፡፡ በግ የዋህ እንሰሳ ነው ከአራጁ ጋር እንኳ ሲሄድ ክፉ ሊያደርግብኝ ነው ብሎ የማይጠረጥር ቢጤ ነው፡፡ በቀላሉ ይታለላል፣  እረኛም የሚያስፈልገው ለዚያ ነው፡፡ የጠፋ ጊዜ ደግሞ አጥብቆ ፈላጊ ያሻዋል፡፡ አለዚያ መመለሻም የለውም እንዲሁ ምድረ በዳ ላይ ሲቅበዘበዝ በተኩላዎች ተበልቶ ፍጻሜው ይሆናል፡፡ ሁሉ ለመብላት የሚፈልገው ስለሆነ በእረኛ ነው የሚጠበቀው፡፡
በዓለም ያሉ ሰዎችን እንደ ዓሳ አጥምደን እንጂ እንደ በግ ነድተን እንድናመጣቸው ማሰብ የለብንም፡፡ ምናልባት ጥቂቶች ላይ እንደዚያ ሆኖ ሊሆን ይችላል፡፡ አስቀድመን በሉቃስ 5 ላይ እንዳነበብነውም በብዙ ዘዴ ና ትዕግስት ሰዎችን አጥምደን ወደ መንግስቱ እንድናመጣ ያበረታታናል፡፡ ይህም በጉን ወደ በረቱ ለማምጣት ሌላ ብዙ ዘዴ እንደሚያስፈልገን ያሳያል፡፡ ዘዴዎቻችን ደግሞ እንደየ አካባቢው የበጎች ጸባይ አይነት ተመጥነው ሊዘጋጁ ይገባል፡፡ ለምሳሌ ለዘመነኛው ስልጡን በጎች ምን ማድረግ አለብን ብሎ ማሰብ፡፤ ምን ምን ለማያውቀው በገጠር አካባቢ ላለ ሰውስ ወንጌል እንዴት ይቅረብ ብሎ ማቀድ፡፡ ስለ ምናዘጋጃቸው የወንጌል ምስክርነቶች ፣ ጉባኤዎች፣ ኮንፈራንሶች፣ ክሩሴዶች …ወዘተ ውጤታማነታቸው ላይ የበለጠ ቢሰራ ጥሩ ነው፡፡

         ጥንቃቄዎች
ቀጥለን የምናነሳው መስካሪዎች ለምስክርነት በሚወጡበት ጊዜ ሊያደርጓቸው የሚገቡ መንፈሳዊና አካላዊ ዝግጅቶች /ጥንቃቄዎች/  ምን መምሰል እንዳለበት ነው፡፡ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ወደ ምድር ከመጣበት ጊዜ አንስቶ የእርሱን ሞትና ትንሳኤ ለመናገር ወደ ተለያየ ስፍራ መጓጓዝ የተለመደ ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ ራሱ ‹‹ ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግስተ ቀርበለች  ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ ››/ ማርቆስ 1፡15 / እያለ ይሰብክ ነበር ፡፡ ደቀ መዛሙርቱ የሆኑ ሐዋርያትም በእርሱ ተልከው ወደ ዓለም ሁሉ በመሔድ የምስራቹን ዜና ለሰው ሁሉ ይናገሩ ነበር፡፡ከዚያም በኋላ ዓለም በብዙ መንገድ እየሰፋች ፣ህብረተሰቡ  እየበዛ ከመምጣቱ አንጻር የወንጌል ማሰራጨቱም መንገድ የተለየ ዘዴና ስልት መከተል አስፈልጎታል፡፡ ዘመኑ ያመጣቸውን ቴክኖሎጂዎች መጠቀምም የግድ ነበር፡፡ ለምሳሌ በድሮ ጊዜ ከአገር አገር መዞሪያው በእግር ወይም በእንሰሳ ሲሆን አሁን አሁን የመኪና ትራንስፖርት፣ የባቡር ትራንስፖርት…. አውሮፕላንም አለ፡፡በሌላ ረገድ ለወንጌል ስርጭት የሚጠቅሙ የሬዲዮ ና የቴሌቪዥን አገልግሎቶችም ከዚሁ ጋር የሚዛመዱ ናቸው፡፡
 በተለይ አንድ ለአንድ ምስክርነት ተወጥቶ በሚደረግበት ጊዜ አስቀድሞ ጥንቃቄዎች ሊደረግባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ የተወሰኑትን  ቀጥለን እናነሳለን፡-
1-ርህራሔ፡- በክርስቶስ የማያምኑ ሰዎች የመጨረሻ ዕጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል የተረዳ ሰው ፡ ሲመሰክር በምን ያህል ርህራሔ ተሞልቶ መሆን እንዳለበት ነጋሪም አያሻውም፡፡ ከዚህ ሌላ ቀድሞ እኛን ታግሰው መስክረው ያዳኑትን ሰዎች ሁኔታም መመልከት ለግንዛቤ ይረዳል፡፡ የኛን ኮስታራ ፊት ፣ ዛቻና ስድብ ሳይበግራቸው የመሰከሩልን የወንጌል ሰዎች!
  አንዳንድ ሰዎች በሚመሰክሩበት ወቅት ርህራሄ የጎደለው የሚመስል ነገር ይናገራሉ፡፡ ለምሳሌ ‹‹ ወንጌልን በግድ የማትቀበሉ ከሆነ በእገሊትና በእገሌ ማመኔን እቀጥላለሁ የምትሉ ከሆነ በገሐነመ እሳት ትቃጠሏታላችሁ!!!›› የሚል ማስፈራሪያ ይጠቀማሉ፡፡ በመሰረቱ ክርስቶስ የሌለው ሁሉ ፍርድ እንደሚጠብቀው የታወቀ ቢሆንም ወንጌልን በፍቅር መናገር ፣ እሳቱ ውስጥ እንዳይገቡ በሚቀና የርህራሄ ልብ ተሞልተን ብንነግራቸው ደግሞ የተሻለ ነው፡፡
2-የጋለ ስሜት ፡- በአንድ ወቅት የእንግሊዝ የጦር አለቃ ቀርቦ ስለ ክርስቶስ መስክሮለት ለነበረ ለዘብተኛ ክርስቲያን ጓደኛው እንደዚህ ብሎ ተናግሯል ይባላል፡ ‹ እኔ እንዳንተ አንድ ሰው ወንጌልን ባለመቀበል ብቻ ለዘላለም ትሉ በማያንቀላፋ ፣እሳቱ በማይጠፋ የዘላለም ስቃይ ውስጥ እንደሚገባ ባምን ኖሮ የእንግሊዝ ምድር ሁሉ በጦር ብትሰካካ ም እንኳ ባዶ እግሬን እየሮጥኩ የአገሬን ህዝብ ከጥፋት አስመልጥ ነበረ፡፡›› ይህን ማለቱ ክርስቲያኑ በምን ያህል የቀዘቀዘ ስሜት መስክሮለት እንደነበረ መገመት አያዳግትም፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገረ ስራችንን ስቃኘው በትክክል ሲኦል እንዳለ የምናምንም እንኳ አይመስልም፡፡ ሰውየው ለማለት እንደሞከረው ተረባርበን ፣የምንችለውን ሁሉ ተጠቅመን ሰዎችን ስናተርፋቸው አንታይማ ፤ ስብከታችን ና ምስክርነታችን ሪቻርድ ባክስተር እንደተናገረው በቀዘቀዘ ስሜት የሚነገር ነዋ፡፡ ምናልባትም ከኛ ሁኔታ የተነሳ ለብዙዎች ሲኦል የሚባለው ነገር አልታይ ብሏቸው እንዳይሆን! እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
በአንድ ወቅት አንድ አዛውንት ለረጅም ጊዜ ለተጎራበቱዋቸው የማያምኑ ወዳጃቸው በሌሊት እንደ መርዶ አርጂ ደጃቸውን ቆርቁረው ከእንቅልፍ ቀስቅሰው ስላደረጉት ነገር ከመጽሐፍ ላይ አንብቤ ነበር፡፡ እናም ሰውየውን ቀስቅሰው ካዘጋጁአቸው በኋላ እግራቸው ላይ በመውደቅ ስለ መድኃኒዓለም ይዤሀለሁ ክርስቶስን አዳኝ አድርገህ እመን ብለዋቸዋል አሉ፡፡ ሰውየውም ክርስቲያን ሆነዋል፡፡ እንዲህ አይነቱ የልብ መቃጠል ከመንፈስ ቅዱስ የሚገኝ ነውና በምዕራፍ አንድ ላይ እንዳነሳነው ቅናቱን ፣ ጥማቱን ፣ ተነሳሽነቱንና ግለቱን እንዲሰጠን እንጸልይ!

3-በክርስቶስ የድነት ስራ ላይ ያተኮረ ይሁን
  ‹‹…………›› 1ቆሮ.1፡23
ለምስክርነት ስንወጣ ጊዜያችንን የምንፈጀው ክርስቶስን ባላማከለ ጉዳይ ከሆነ ፡ በተለይም ክርክርና ጠብ በሚያስነሱ የ’’ቅዱሳንና’’ ‘’ ሰማዕታት   ‘’ ጉዳይ ላይ ከሆነ ብዙ ኪሳራ ይሆናል፡፡ ስለ ነዚህ ጉዳዮች የምናነሳበት ሁኔታ ሊፈጠር ቢችልም ቶሎ ብለን ግን በወንጌል ዙሪያ ውይይታችንን ለማድረግ መገፋፋት አለብን፡፡ ዳጎንን በሰው ልብ እያየን ታቦቱን ጨምሮ መክተት ደስ ላይል ይችላል ፡ ግን አስቀድመን እንዳልን ሌሊቱን አሸንፎት ያድራል ብለን ደግሞ ማመን አለብን፡፡ በእገሌስ አትምጡብኝ ያልነውን ስንቶቻችንን ዛሬ ስለ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አውርተን እንዳንጠግብ አልተደረግንምን? ዛሬስ በሌሎች ህይወት የማይደገምበት ምን ምክንያት አለ?
ያልዳኑ ሰዎች አስር ጊዜ ከመስመር እየወጡ በርካታ ጥያቄዎችን ሊያዥጎደጉዱ ይችላሉ ግን በዚያ መደናገጥ የለብንም ፤ ደግሞ ሁሉን ነገር ለመመለስ የግድ መታገልም ላይኖርብን ይችላል፡፡

4- ብዙውን ነገር ለመንፈስ ቅዱስ መተው

እንዲህ አይነቱ ልምምድ ከድሮ ጀምሮ ኖሮን በነበር ስንት ጊዜዎቻችን በከንቱ ባልተቃጠሉብን ነበር፡፡ ሰምተን መውጣት ፣ ምን እንደምንናገር ና ምን ላይ እንደምናተኩር መጠየቅ ፣ ከዚያም መልዕክታችንን ከጨረስን በኋላ ደግሞ ለመንፈስ ቅዱስ አሳልፎ መስጠት፡፡ ሰውን ወቅሶ ውደ ንስሐ የሚያደርሰው መንፈስ ቅዱስ ነው ፤ የመሰከርነውን ቃል ቀን ከሌሊት በሰዎች ልብ ውስጥ መላልሶ የሚያስታውሳቸውም ጌታ መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ አሜን፡፡
   እንዲህ ሲሆን ስራው ይቀለናል፡፡ ሁሉ ነገር በኛ ጫንቃ ላይ ብቻ የወደቀ ያህል እየተሰማን ነፍሳትን በአንድ ጀንበር አሳምነን ፣ መልዐክ ሆነው እንዲያድሩ የምንጥረው ከዚያ የተነሳ ነው፡፡ ስናምነው ፣ ደግሞ ስንሰጠው እናርፋለን ደግሞ እርሱ ፈጣሪ፣ ሁሉን ቻይ መሆኑን ደግሞ መዘንጋት የለብንም፡፡

5- የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በአግባቡ ማጥናት

  በምስክርነት ጊዜ ሊረዱን የሚችሉ ዋና ዋና የሆኑ የድነት ገላጭ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅሶችን በቃል ማጥናት ሊጠበቅብን ይችላል፡፡ በተደጋጋሚ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሙሉ ለሙሉ የሌሉ ፣ወይም በከፊል ብቻ ያሉትን ጥቅሶች መጠቀም ትዝብት ውስጥ ይጥላል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ፣ልናድናቸው የሄድነውን ህዝብ እነዳናሳስትም ነው፡፡ ስለዚህ መጠንቀቁ ጥሩ ነው፡፡ ይህን ማድረግ በተለያየ ምክንያቶች የማንችል ቢሆን ከምስክርነት መቅረት አይደለም ያለብን፡፡ የተዘጋጁ በራሪ ወረቀቶችን፣ ብሮሸሮችን በመጠቀም ፣አልፎ አልፎም ወረቀቱን በማንበብ ወጥ የሆነ መልዕክት ለማስተላለፍ መሞከር ነው፡፡ የምስክርነታችን ምንጭ የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስንም ከቻልን ይዞ መውጣት ጥሩ ነው፡፡
እስኪ ቀጥለን ወንጌልን ስንመሰክር በቃል ልንይዛቸው የሚገቡ ጥቂት ጥቅሶችን እንመልከት፡፡ አንባቢ ይህችን መጽሐፍ ሲያነብ ጥቅሶቹን አብሮ በማጥናት በቃል ለመያዝ ቢሞክር የተሻለ ነው፡፡
  .ሮሜ.3፡23 ‹‹ ልዩነት የለምና ሁሉ ሐጢያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል››
 .ሮሜ.6፡23 ‹‹ የሐጢያት ደሞዝ ሞት ነውና የእገዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ህይወት ነው፡፡››
 .ዮሐ.3፡16 ‹‹ …ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ አላከውምና ፤ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡››
 .ራዕይ 3፡20 ‹‹ እነሆ በደጅህ ቆሜ አንኳኳለሁ ማንም ድምጼን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ አብሬውም እራት እበላለሁ፡፡››
በተጨማሪ፡-
. ስለ ንስሐ እና ሐጢያት መንጻት 1ዮሐ.1፡4-9
.እግዚአብሔር ስለ ልጁ የመሰከረው ምስክርነት 1ዮሐ.5
.የጽድቅና የድነት ምንጭ ሮሜ 10፡9 …የመሳሰሉት ናቸው፡፡

6-የሰዎችን ቋንቋ፣ ባህልና ወግ አስቀድሞ መረዳት

   በተለየ ሁኔታ ወንጌል እንድንመሰክርላቸው በልባችን ከብዶ ለሚሰማን ህብረተሰብ /ህዝብ/ ወደእነርሱ ከመሄዳችን በፊት ወጋቸውን፣ ባህላቸውን፣ ቋንቋቸውን አስቀድሞ ማጥናት በቀላሉ ከእነርሱ ጋር እንድንግባባ ይረዳናል፡፡ ጥቂቶች ይህንን ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ የእነርሱ ያልሆነውን ቋንቋ ሲያጠኑ ፣ የተለየ ምግብ ለመብላት ሲለማመዱ ፣ ሌላም ብዙ ጥቅማቸውን የሚያስተው ነገር ስለወንጌል ሰውተው ሲያደርጉ ተስተውሏል፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
  በእንዲህ አይነቱ የሚሲዮናዊነት አገልግሎት ውስጥ የግል ጥቅም አይታሰብም፡፡ እንዲያውም ያለንን ሐብት/  /፣ ዕውቀት/   /፣ ልምድ ለህብረተሰቡ የምናካፍልበት ምቹ ሁኔታ ነው ሊታየን የሚገባው፡፡ በእነዚህ ነገሮች ተንደርድሮ ዋነናኛ ግባችን ወደ ሆነው የወንጌል ምስክርነት ውስጥ መግባት ነው፡፡
7-የጠላትን ስራ አስቀድሞ ማፍረስ /ሀይለኛውን ማሰር/
የእግዚአብሔር ቃል እንደሚናገረው የሐይለኛውን ቤት ለመበዝበዝ አስቀድሞ ሐይለኛውን ማሰር ይገባል፡፡ እንኳን ጠላት ሰይጣን ተጨምሮበት የህብረተሰቡ ባህልና ወግ በራሱ የሰውን ልብ ለወንጌል ክፍት እንዳይሆን አድርጎታል፡፡ ስለዚህ እንዲ ያለውን ነገር በጸሎት ነው ማሸነፍ የምንችለው፡፡ ክፉውን እየተቃወምንና እያሰርን ለምስክርነት መውጣት፤ እግዚአብሔርም ተናጥቆ ብዙ ነፍሳትን ይሰጠናል፡፡

8-ተገቢውን አለባበስ መልበስ
 ወንጌል ከአለባበሳችን አንጻር እንቅፋት እንዳይገጥመው መጠንቀቁ ጥሩ ነው፡፡ በተለይ ሐይማኖተኛ ሰዎች ቶሎ ብለው እንከንና ሰበብ ስለሚፈልጉ ለምስክርነት ሲወጣ አግባብ ያለው ጨዋነትን የሚገልጽ አለባብ መልበስ አለብን፡፡ ለምሳሌ እህቶች ከሆኑ ዕርቃንን የሚያሳይ ልብስ ባይለብሱ ፣ ጸጉራቸው ብዙም ሳቢ ባልሆነ ሁኔታ ቢሸረቡ ከራሳቸው ይልቅ ክርስቶስን ለማሳየት ቅድሚያ እንደሰጡ ሁኔታቸው ሊገልጥ ይችላል፡፡ ደግሞ ሐዋርይው ጳውሎስ እንደተናገረው ስለወንጌል፣ ሌሎችን ለማዳን ‹‹ ከሁሉ ጋር ሁሉን ሆንኩ››/ 1ቆሮ. / እንዳለ ብዙ መብታችንና ነጻነታችንን እንኳ ስለ ሌሎች መዳን ስንል ልንተው ይገባል፡፡

9-ተገቢ ንግግር መናገር

አልፎ አልፎ ወንጌል ሲነገራቸው ቶሎ ግንፍል ብሎ ንዴታቸው የሚመጣባቸው ሰዎች አይጠፉም፡፡ ይህ ቢሆንም ባይሆንም ሁልጊዜ ጥበብ የጎደላቸው ንግግሮችን ፣ ተራ የሆኑ የዓለም ቋንቋዎችን ፣ ተረት ተረትና ቀልዶችን መጠቀም የለብንም፡፡ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚለው ‹‹ ንግግራችሁ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን፡፡›› /   / ቁጣና ፍርድ ያልተቀላቀለበት የፍቅር ንግግር ይሁን! በተለይ ሁለት ሁለት ሆኖ መውጣት ብንለምድ መልካም ነው ፡፡ በማናቸውም ሁኔታ አንዱ አንዱን ያግዛልና፡፡ ምናልባት ከዚህ አልፎ ነገሮች ወደ ጥልና ክርክር ካመዘኑ ሰዎቹን ባርኮ በፍቅር መለያየትን መምረጥ ያስፈልጋል፡፡ /ሥራ.18፡5/

10-ደስ የተሰኘ ገጽታ

    የምስራች የያዘ ሰው ገና በፊቱ ያስታውቃል፡፡ ፈገግታ አይጠፋውም፤ የሆነ አንዳች ሊያካፍለው የሚጓጓለት ነገር እንዳለው አስኪያስታውቅበት ድረስ ፤ በተቃራኒው ሐዘንተኛ ፣የተጎዳ ፣ግራ የተጋባ ሰው መስለን በምስክርነት ጊዜ ለሰዎች መታየት የሚያንጸባርቀው ነገር ጥሩ አይደለም፡፡ ዓለማዊው ሰው ገና ስንቀርበው ምን ስጠኝ ፣ምን እርዳን ሊለኝ ነው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ ራሳችን ከፍቶን ሰው እንዴት የኛን ዓይነት ኑሮ ሊመኝ ይችላል? ይህ ማለት መቼም ሊከፋን አይገባም ወይም የሚጎድለንና የምናዝንበት ቀን በፍጹም ሊኖር አይችልም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን ኑሮ እንኳቢጎድል በጌታ ግን ደስ ይለናል፡፡ በክርስቶስ የማዳን ስራ ከሲኦል አምልጠን ዘላለም እረፍት ያለበት መንግስቱ ውስጥ መግባታችን ደስ ይለናል፡፡ አሜን፡፡

     ማጠቃለያ

የፀሐፊው ልመናና ጸሎት

በክርስትና ውስጥ ጌታ እረድቶኝ በኖርኩባቸው በእነዚህ ሁለት አስር ዓመታት ውስጥ ትነስም ትብዛም በወንጌል ምስክርነት ውስጥ ተሳትፎ አድርጌያለሁ፡፡ እንደውም በሳምንት ውስጥ የተወሰነ ቀናት በመለየት ለምስክርነትና ለጸሎት እጠቀም ነበር፡፡ በእውነት ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ከአገር ቤት ከወጣው በኋላ በምዕራባውያን ምድር ላይ ይህንን አገልግሎት በምን መልክ ማስቀጠል እንደሚቻል ጊዜ ወስጄ አስብና እጸልይ ነበር ፡፡ ከዚያም አልፎ የተገለጠልኝን ጥቂት ነገሮች ለማድረግ ሞክሬአለሁ፡፡ እንደውም ብዙውን አገራት ላይ የተሰደዱት ህዝቦችን በወንጌል መልዕክት ለማግኘት አጋጣሚው ሰፊ ነበር፡፡ በምዕራቡ ዓለም ፣ በአንዳንድ የአፍሪካና አረብ አገራት ውስጥ ያሉ ህዝባችን  በአብዛኛው የቴክኖሎጂ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው የወንጌልን መልዕክት በስልክ ላይ ቴክስት በማድረግ፣ በቫይበር-ግሩፕ ፣ በፌስቡክ ላይ የተለያዩ ድህረ ገጾችን በመክፈት ፣ በጉግል ፕላስ ፣በኢ-ሜይል እና በብሎግ ጽሁፍ  ብዙዎችን ለመድረስ ተችሏል፡፡ ከዚህም በኋላ ይህችን አነስተኛ መጽሐፍ እንደ ወንጌል መቀስቀሻነት በመጠቀም በወንጌል ስራ ውስጥ ጥቂቶችን ብቻ ሳይሆን ሁሉን ክርስቲያን ተሳታፊ የሚያደርግ አዲስ ስልት ነድፎ መስራት እንደሚቻል ያለፈው ትንሽ ጥረት ያመላክታል፡፡
   ቤተክርስቲያን በየጊዜው ከጠላት እየተቀነባበረ የሚሰጣትን የቤት ስራዎች ከመስራት ወጥታ የታዘዘችውን የታላቁ ተልዕኮ አጀንዳ እነድትፈጽም፤ በሁላችንም የወንጌል መሳካሪነት  ክርስቶስን ያላወቀ የተቀረው የዓለም ክፍል የወንጌል ብርሀን በርቶለት እግዚአብሔርን ሲያከብር ማየት የጸሐፊው ትልቅ መሻት፣ልመናና ጸሎት ነው፡፡