Friday, May 29, 2015

ፎርሙን ሞልተው ይላኩልን !!!

  ‹ ወንጌልን  በደብዳቤ ፣ በኢ-ሜይል፣ በፌስቡክ ፣  በሞባይል እና በቫይበር  ማድረስ ! ›  
              
                '' ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡ "
 /ወይቤሎሙ፡ ሑሩ፡ ውስተኩሉ፡ ዓለም፡ ወሰብኩ፡ ወንጌል፡ ለኩሉ፡ ፍጥረት፡፡ / ማርቆስ 16፤15፡፡
  • በየትኛውም ዓለም ለሚገኙ ወዳጅ፣ ዘመድ ፣ ጉዋደኛዎ ወንጌልን በስልክ ላይ ቴክስት በማድረግ ፣ በቫይበር ፣ በኢ-ሜይል፣ በፖስታ መልዕክት በመጠቀም ይመስክሩ፡፡
  • ቀጥሎ በቀረበው ፎርም መሰረት ሊመሰክሩላቸው ልብዎ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር እና አድራሻ ቢልኩልን በቀጥታ መልዕክቱን እንልክላቸዋለን፡፡ አለዚያም የእርስዎን አድራሻ ይስጡንና ፤ እርሶ ካሉበት ቦታ ሆነው ሊልኩላቸው ይችላሉ፡፡
  •  መልዕክቶቹ በተለይ ለኦርቶዶክስ ህዝባችንና፤  በክርስቶስ አምነው ላልዳኑ ሌሎች ሰዎች በተለያየ ርዕስ የተዘጋጀ ነው፡፡ ለምሳሌ ያህል፡-  
  •  
     
  1.  የድነት መልዕክቶች ፡-‹ እንደ ሚስጥረ ድነት › ፣ ‹ አስቸኩዋይ መልዕክት › ፤ በክርስቲያን በዐላት ላይ ተመርኩዞ የተጻፈ ‹ ፋሲካ ›፣ ‹ የክርስቶስ ልደት -ገና ›፣‹ ሕማማት ›..የመሳሰሉ፡፡
  2.   መንፈሳዊ ነክ ጥያቄዎችን የሚዳስስ ‹ ስለ አማላጅነት ›፣ ‹ ስንት ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስ አለ? ›፣ ‹ ሐጢያትን ለካሕን መናዘዝ ይገባልን ? ›፣ ‹ ስለ ሙታን ተስካር ›፣ ‹ ሚስጥረ ቁርባን ›..የመሳሰሉ፡


 የእርስዎ አድራሻ እና  ስም .--------------------------ሞባይል ቁ.----------------ፖ.ሳ.ቁ.-----------------------ኢ-ሜይል-----------------------------
      
                                        የሚመሰከርላቸው

  ሥም ዝርዝር፡- 1. ስም --------------------------------ሞባይል ቁ.--------------------------ኢ-ሜይል---------------------------ፖ.ሳ.ቁ.------------------------------------

                                             2. ስም.-------------------------------ሞባይል ቁ.---------------------ኢ-ሜይል-------------------------ፖ.ሳ.ቁ.------------------------------------

                                             3. ስም.----------------------------ሞባይል ቁ.------------------------ኢ-ሜይል-----------------------------ፖ.ሳ.ቁ.-----------------------------

                                            4. ስም.--------------------------------ሞባይል ቁ.----------------------ኢ-ሜይል-----------------ፖ.ሳ.ቁ----------------------------

                                            5. ስም.-------------------------ሞባይል ቁ.------------------------ኢ-ሜይል--------------------ፖ.ሳ.ቁ.--------------------------------


   ስለ ቁጥሩ ብዛት አይጨነቁ! የሰዎቹን ስም ዝርዝር እና የእርስዎን አድራሻ በሚከተሉት አድራሻዎች በኩል ይላኩልን፡፡ 240-481-5970ላይ ቴክስት ያድርጉ ፤ ወይም‹ benjabef@gmail.com /info.lemekeru@gmail.com ላይ  email ይላኩ፡፡

     < PREACH THE GOSPEL !  BY EMAIL , LETTER , FACE BOOK , TEXT on MOBILE and  VIBER >        

Wednesday, May 27, 2015

የሐሳብ መበላሸት!

      የሐሳብ መበላሸት

   ለሰው ልጆች ሁሉ ውድቀት ሰበብ  የሆነው  የህይዋን  ስህተት የመጣው ሰይጣን ሐሳቡዋን አበላሽቶት ነው፡፡ 2ቆሮ.11፤3 ፡፡ ሐሳቡ የተበላሸበት ሰው ወደ ድርጊቱ ለመግባት ቀላል ይሆንለታል፤ ልክ እንደ ቃየን ሁሉ የዳዊት ልጅ አቤሴሎምም ወንድሙን አምኖንን ከመግደሉ በፊት ረጅምና የቆየ የግድያ ሐሳብ አርግዞ ነበር፡፡ ጊዜውና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ደግሞ አስገደለው፡፡ 2ሳሙ.13፤2፡፡

   አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሐሳብ ያድርና ድርጊቱ ሊቆይ ይችላል፤ ይህን ጊዜ መንቃት ነው፡፡ ምንም እስካላደረኩ ድረስ ንጹህ ነኝ  ማለት አይቻልም፡፡ ቀን የሚጠብቅ ክፉ ምኞት ላይ መንገስ ያስፈልጋል፡፤ እግዚአብሔር ቃኤልን ቀድሞ ያስጠነቀቀው ለዚያ ነው፡፡ ደጅህ ላይ ሐጢያት እያደባች ነው ንገስባት አለው፡፡ አለዚያ እርሱዋ  ትነግስብሃለች፡፡ ያን ጊዜ ፍቃዱዋን ታደርጋለች፡፡እግዚአብሄር ወደ ቃየን መጥቶ ከነገረው ነገር የምንማረው ኀጢያት ላይ እኛ መንገስ ካልቻልን ኀጢያት በእኛ ላይ መንገስ ይጀምራል፡/ ዘፍ.4፤7/የሚለውን ነው፡፡

   ያዕቆብ 1፤15 ላይ ሲናገር '' ምኞት  ጸንሳ  ሐጢያትን  ትወልዳለች ፡ሐጢያትም  ጸንሳ  ሞትን ትወልዳለች፡፡ " ሞት የሚባለው /ውድቀት ሊሆን ይችላል/፤ ከመከሰቱ በፊት ውስጥን ይዞ  የሚከርመው ሐሳብ  /ምኞት/ ነው፡፡ ምኞት ዝም ከተባለ ቆይቶ ቆይቶ  ሀጢያትን ይወልዳል፡፤ ከዚያም ወደ ሞት ያመጣል፤ ሁሉም ሂደት ነው ማለት ነው፡፡ ሐጢያትን፣ሞትንና ውድቀትን በህይወቱ ማየት የማይፈልግ ሰው ራሱን ማንጻት ያለበት ከውስጥ ነው፡፡ ምን አርግዣለሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ እንዲሰጥ በቅድሚያ ሐሳብ ነው የመጣበት፡፡ '' ዲያቢሎስም ሐሳብ ካስገባ በሁአላ ''ይላል፡ ምናልባት ዲያቢሎስ ወደ አዕምሮው የላከበትን ሐሳብ መቃወም ይችል ነበር ፡፡ ምናልባትም ወደ ሌሎች ደቀመዛሙርትም ሐሳብ ቀርቦም ይሆናል፡፡ ምናልባትም እነርሱ ተቃውመውት ይሆናል፡፡ ይሁዳ ግን ሐሳቡን አስተናገደ፤ ወደ ቀጣዩ ና ከባዱ ነገርም አለፈ፡፡ ሮሜ 6፤12 ''...ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ስጋችሁ ሐጢያት አይንገስ '' ስጋችን ላይ ሐጢያት ሲነግስ  እንደ ስጋ ፈቃድ ለመኖር የስጋን ነገር አዘውትረን እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ /ሮሜ.8፤5/

   ውስጡ የተሸነፈን ሰው ወደተገዛለት ነገር በቀላሉ መጎተት ይቻላል፡፡ ብዙ የሚያቅተው ከነገሮች ውስጥ መውጣት ሳይሆን ነገሮችን ከውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስራኤላውያን በእግራቸው ከግብጽ ውስጥ ወጥተው ነበር፡ ነገር ግን በቆይታ እንደታየው ግብጽ ውስጣቸው ነበረ፡፡ ስለዚህም በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ ይለናል፡፡/ሥራ.7፤39/፡፡ ከዓለም ወጥተን ግን ዓለም ውስጣችን ካለች  እየዘመርን ፣ እየጸለይን ፣ ቤተክርስቲያን እየሄድን የሐጢያት ተጠቂዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ከሁሉ ነገር ተገልለው አንድፊቱኑ ገዳም ለገቡ መነኮሳት እንኩዋ ትልቁ  ትግል የውሰጥ ነው፡፡ ከግብጽ ወጥተህ ግብጽ ግን ከልብህ ካልወጣ ችግር ነው፡፡የሎጥ ሚስት  ከሶዶም በእግሩዋ ወጥታለች ነገር ግን ሶዶም ከውስጥዋ አልወጣም ነበርና እንቅፋት ሆነባት፡፡ መቀየር ፣መለወጥ  ከውስጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በአዕምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ......" የሚለን፡፡ ከየ ዕለቱ ኑሮአችን እንኩዋ ብንመለከት አንድ ሰው ወተት ወይም ጎመን የሚጠላ ቢሆን፡ ከፈለገ  ቦታ ቢመጣም ወይም ነጻም ቢሆን አይነካውም፡፡ ሐጢያትን ከውስጥ ስንጠላ አዩኝ አላዩኝ ከሚል መሳቀቅ እንወጣለን፡፡ በዚህም ላይ ውስጣችንን ቦርቡሮ በጊዜ ሒደት ከሚጥለን ነገር እንገላገላለን፡፡ ልክ እንደ ጎመኑ ና ወተቱ  የትም ብንሆን ፣መቼም ቢሆን አንነካውም፡፡

     አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር ውስጡ ችግር ያለበት  ሰው ያማረ  ህንጻ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ውስጥ ቢገባ  ችግሩ አያቆምም ብሎአል፡፡ የገባበት ቦታ ነገሩን ሊለውጥ ስለማይችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት አንድ በጣም ወፍራምና ዕድሜ ጠገብ ዋርካ አውቃለሁ፡፡ነገር ግን በሆነ ወቅት እምብዛም ነፋስ ባልነበረበት ጊዜ ነው ሌሊት ላይ ወድቆ የተገኘው ፤በጊዜው ሁኔታው ሲጠና ዛፉ በከፍተኛ ሁኔታ ውስጡ በብል ተቦርቡሮ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ቅርፊት ተሸፍኖ ያለ እየመሰለ ኖረ፤ነገር ግን ባልታሰበ ቀን ወድቆ ተገኘ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደዚያ ይመስሉኛል ተሸፍነን ጠንካራ ሰዎች እንመስላለን፣ አስተማማኝ እና የመላዕክት ህይወት ያላቸው እንመስላለን፤ ምናልባት ውስጣችን ግን በብዙ እየተገዘገዘ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን በየ አደባባዩ ላይ የሚሰሙት ውድቀቶቻችንም የዚህ ውጤት ይሆናል፡፡እስቲ  ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ ና ነጻ እንውጣ ፡፡ ውድቀትን ብዙ ሰው ሊያየው ፣ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ያለን የውስጥ መቦርቦርና ትናንሽ ልምምዶች ግን እምብዛም አይታይም፡፡እኛው ከጌታ ጋር እንፍታው፡፡ልምምዱ ከፍ ያለ ደረጃ እንኩዋ የደረሰ ቢሆን በጾም ጸሎት በፊቱ ብንሆን የማይለወጥ ነገር ምንም የለም፡፡ ጌታ ሁሉን ይችላልና፡፡
  • የዚህን ሙሉ ትምህርት ‹ ንገስባት › ከሚለው ሊንክ ርዕስ ስር ማየት ይችላሉ፡፡

ማስታወሻ:- ይህን ትምህርት ቅዱሳን እንዲጠቀሙበት ያድርጉ፡፡

                                                                        benjabef@gmail.com

Monday, May 18, 2015

ራዕይ እንዴት ይጀመራል...?

እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ?

" ኢየሱስም ዓይኖቹን አንስቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊሊጶስን ፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? አለው፡፡ ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ፡ ሊፈትነው ይህንን ተናገረ፡፡ '' ዮሐ.6፤5ና 6፡፡

 በዚህ ትምህርት ብዙዎቻችሁ  የተቀበላችሁትን ራዕይ  ከየት እና እንዴት እንደምትጀምሩ መርህን የምትማሩበት ፡፡ ወይም ደግሞ በህይወቴ አንድ ነገር ሰርቼ ማለፍ እፈልጋለሁ ፤ግን ከየት እና ከምን እንደምጀምር አላውቅም ለምትሉ መንገድ መንገዱን ጠቁዋሚ ትምህርት ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡

   ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ጥያቄ ሲጠይቃቸው እንመለከታለን፡፡ ‹ህዝቡን ለማብላት እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?› በመሰረቱ እየመጣ የነበረው ህዝብ፡ ወንዶች ብቻ ተቆጥረው 5ሺህ ህዝብ ነበሩ፡፡ ሴቶችና ህጻናት ሲቆጠሩ 13 ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገሩን እነዚህን ሁሉ የመመገብ የራዕይ ጅማሬ ብለን ልናስበው እንችላለን፡፡ ረዕዩ ሲታይ በጣም ሰፊ እና ገና በሐሳብ ደረጃ ያለ ነገር ነው፡፡እነርሱም ማሰብ ጀመሩ ፤ ከየት ነው የሚጀመረው? ሰዎች አንድን ራዕይ ለመጀመር ከሐሳብ ቀጥሎ የሚያነሱት ጥያቄ አላቸው፡፡እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሙዋሉ ድረስ ምንም ነገር መጀመር ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ የሚጠይቁዋቸው ወሳኝ የሆኑ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ፊሊጶስና እንድርያስ ጠይቀውልናል፤ ወይም በራዕይ ጅማሬ ላይ ሊነሱ የሚገባቸውን ቁልፍ ሁለት ሐሳቦችን አንስተውልናል ፡፡ ቀጥለን  እንዳስሳቸዋለን፡፡

                ሀ. ለራዕዩ የሚያስፈልግ ነገር ሲሙዋላ መጀመር...?
ፊሊጶስ፡- '' ፊሊጶስም እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኩዋ እንዲቀበሉ የ 200 ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት፡፡ ቁ.7፡፡ በዚያን ጊዜ ከጌታ የተሰጣቸውን አንድ ፕሮጀክት ወይም ራዕይ ለመጀመር የሚያስፈልገውን መነሻ ካፒታል ነው አስልቶ የተናገረው፡፡ 200 ዲናር በጊዜው በጣም ብዙ ብር ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ለመረዳት ያህል፡ ጌታ ኢየሱስን አሳልፎ ለጠላቶቹ ለመስጠት ይሁዳ ከካህናት አለቆች ጋር የተደራደረበት ብር 30 ብር ነው፡፡ በዚህ ብር በዚያን ጊዜ እንጀራ ቀርቶ መሬት እንኩዋ የሚገዛበት ብር እንደነበረ  ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ጌታውን የሸጠበትን ገንዘብ በቤተ መቅደስ ሄዶ በተነ፤ ነገር ግን መሬት ገዙበት፤ ቦታውም አኬልዳማ ተባለ ፤የተባለው ነገር ነው፡፡ እንግዲህ 30 ብር በጊዜው እንዲህ ትልቅ ከነበረ፡ 200 ብር ምን ያህል ይሆናል? የፊሊጶስ ሒሳብ ለሰው አዕምሮ ትክክል ይመስላል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለመመገብ ይህን የሚያክል በጀት አስፈላጊ ነው ማለቱ፡፡
                      ለ. ራዕዩን በእጅ ላይ በተገኘው ነገር መጀመር......?
እንድርያስ፡-''..አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሳ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል፡፡ '' ቁ.9 ፡፡ ይህ  ሁለተኛው የአማራጭ ሐሳብ ነው፡፡ ፈንድ ተፈላልጎ፡  አልያም በሆነ መንገድ ከሚገኝ ካፒታል መጀመር የማይቻል ከሆነ፡ ምናልባት እጃችን ካለው ጥቂት ነገር መጀመር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም ካልሆነስ ነው ጥያቄው? ፐሮጀክቱ ያቀፈው ህዝብ በሺህ የሚቆጠር ፡ በእጃቸው ያለው መነሻ ካፒታል ደግሞ ለአንድ ለሁለት ሰው ብቻ የሚበቃ፡፡ 'ይህ ምን ይሆናል ? ' አለ እንድርያስ !

   በነገራችን ላይ በርካታ ራዕዮችና ውጥኖች ሳይሰራባቸው ተቀምጠው ያሉት፡ በነዚሁ ሁለት ግዙፍ ጥያቄዎች  ውስጥ ወድቀው ነው፡፡ መነሻ ካፒታል ሲታሰብ ፣ ለመነሻ የሚሆን ብር ሲጠበቅ አይሞላም፡፡ ስለዚህም ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡ ቤሳ ቤስቲ የሌላቸው ሰዎች ከመሬት ተነስቶ 200 ዲናር ከየት ያመጣሉ? ሌላው ደግሞ እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም የማይበቃ መሆኑ ነው ፡፡ በተለይም ከታሰበው ራዕይ ጋር ሲነጻጸር ማለቴ ነው፡፡ ጀምሩት ቢባል እየቆረሱ ድንገት ቢያልቅስ ? ፣ ጀምሮ መዋረድ አይሆንም ? አዕምሮ ያለው ሰው ይህንን ሊያደርግ ይችላልን ?  ስለዚህም ነው በሁለቱም ጎራ የተነሱት ሐሳቦች ብዙዎቻችንን ይወክላሉ ብዬ የማምነው፡፡ ሁለቱም ነገሮች ከባባዶች ናቸው፡፡ ሙሉ የፐሮጀክቱን መነሻ ካፒታል ማግኘትም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ካላችሁ ነገር ጀምሩ ማለትም በሁዋላ ላይ የሚመጣውን መዘዝ በማሰብ የሚያንቀሳቅስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ የጌታ ሐሳብ ለመሆኑ ምንድን ነው?

     የጌታ ሐሳብ ‹ ከየትን እንጂ በምንን አታስብ ! ›
 ታስታውሱ እንደሆነ  ሲጀመርም የጌታ ጥያቄ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? ነው እንጂ በምን እንገዛለን? የሚል አልነበረም፡፡ ለጌታ በምን? የሚለው አያስጨንቀውም፡፡ ስለዚህም ነው በምን? ን ትቶ ከየት? የሚለውን የጠየቀው፡፡ ሰው ደግሞ በምን? የሚለው ሳይመለስለት ከየት? ወደሚለው ቀጣይ ነገር ውስጥ መግባት አይፈልግም፡፡ ስለ ዚህም ነው ሳይጠየቁ ሒሳብ መስራት የጀመሩት ፡፡ ለተሰጠ ራዕይ ሁሉ የሰው አስተሳሰብ ይኸው ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲመለስለት የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ካልተመለሰለት በቀር መጀመር ይፈራል፡፡ ጌታ ደግሞ እርሱን ለእኔ ተወውና ከየት እንደሚገዛ ንገረኝ ይላል፡፡ በተለይ '' እራሱ ሊያደርገው ያለውን ነገር አውቆ ይህን አለ፡፡'' የሚለው ቃል አስደናቂ ነው፡፡ ምንም ወደ ሌላቸው ሰዎች ትልልቅ ራዕይ ሲያመጣ እርሱ አዋቂ ነው፡፡ እርሱ ሊያደርግ ያለውን ነገር ስለሚያውቅ ነው ፡፡ በቅድሚያ በጀቱን ሰጥቶ ሂዱና ህዝቡን  አብሉ!፤ ይህንና ይህን ስሩ! ቢለን መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደዚያ አይሆንም፡፡

  ለመሆኑ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገሮች ፡ማለትም ፊሊጶስ ካቀረበውና፡ እንድርያስ ካቀረበው ሐሳብ፡ ጌታ የትኛውን መረጠ ? ወይም ምን አደረገ ? የሚለውን ነገር ከቃሉ ላይ አብረን እንመልከት፡፡ '' ኢየሱስም ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ አለ፤በዚያም ስፍራ ብዙ ሳር ነበረበት፡፡ወንዶችም ተቀመጡ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር፡፡ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ ፡አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፤ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡዋቸው፡፡ ''ቁ.11-12
  እንዳነበብነው እጃቸው ላይ ያለውን ያውም የራሳቸው ያልሆነ ግን በመካከላቸው የተገኘ የአንድ ብላቴና እራትን ተጠቀመበት፡፡ አመስግኖ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፡፡ በአዕምሮአችን ውስጥ መሀል ላይ ቢያልቅስ? ፣ ባይዳረስስ? ....ወዘተ የሚሉ አሳቦች ይኖራሉ ፡፡ ነገር ግን እነርሱን  እንተዋቸው፡፡ ዝም ብለን ባለን ነገር እንጀምር፡፡ አርሱ አያሳፍረንም፡፡ በጣም መጠንቀቅ ያለብን ፡ መነሻ ላይ ማነው የተናገረኝ? የሚለው ላይ ብቻ ነው፡፡ራዕዩ የትኛውንም ያህል ትልቅ ይሁን  እግዚአብሔር ተናግሮን ከሆነ መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለህዝቡ ቆርሰው ማደል ጀመሩ ፤ አይናቸው እያየ ሁሉ እንደሚፈልገው መጠን ወስዶ ፣ጠግቦ ፣ የተረፈውን ቁርስራሽ 12 መሶብ ሞሉ፡፡ የኛ ጌታ እንደዚህ ነው ፡፡ የመጨረሻውን ውጤት ከመነሻህ ጋር ማመሳከር እስኪያዳግት ድረስ የሚባርክ አምላክ ነው፡፡

  በጣም ትልልቅ ነገር የሰራባቸውን ሰዎች ምስክርነት መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ዎርልድ ቪዥን ዛሬ ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ከመድረሱ በፊት፡ መነሻ ካፒታሉ ቦብ ፒየርስ የሚባል የድርጅቱ መስራች  በወንጌል ምክንያት የተሰደደችን አንዲት ብላቴና በጊዜው ከረዳበት አምስት /5/ የአሜሪካን ዶላር እንደተጀመረ ጋሽ በቀለ ስለ ዎርልድ ቪዥን በጻፈው መጽሐፉ ላይ ታሪኩን አስፍሩዋል፡፡
 ከብዙዎች ንግግር እንደተረዳሁት ሁሉም ክርስቲያኖች ማለት ይቻላል፡ በተለይ ከሆነ ጊዜ በሁዋላ በህይወታቸው አንዳች ነገር ሰርቶ የማለፍ ጥማት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ግን ከየት? እና እንዴት? እንደሚጀምሩት አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ብዙ ህጻናትን የማሳደግ እና አዛውንቶችን የመንከባከብ አልያም ሌሎች በጎ የልማት ስራዎችን ስለ መስራት አስበው ከሆነ ፡ ቢያንስ ከአንድ ህጻን ወይም አንድ አዛውንትን ከመርዳት መጀመር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ከቆይታ በሁዋላ ስራው /ራዕዩ/ እየሰፋ ይሄድና ለብዙዎች ጥላ ለመሆን ይበቃል፡፡ ራዕዩ ከጌታ ይሰጠን እንጂ፡ ያለንን ጥቂት ነገር  ባርኮ መጀመር ብቻ ነው ፡፡

  ጥርት ያለ ራዕይ ተቀብለው : ለመጀመር  ሚሊዮን ብሮችን ሲጠብቁ ሲጠብቁ ፡ ራዕያቸው አጀንዳቸው ላይ ብቻ የቀረባቸው አያሌዎች ናቸው፡፡የምንፈልጋቸው ውጤቶች ስንጠብቃቸው ሳይሆን እየሰራን እያለ የሚመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ከመጠበቅ መንፈስ ወጥተን ፡ባለን ነገር እንቅስቃሴ ውስጥ እንግባ፡፡ ነገሮች እንደ መብረቅ ድንገት ላይከሰቱ ይችላሉ፡፡ ትልልቅ ነገሮችን እጃችን ባለው ትንሽ  ነገር እንጀምራቸው ፡፡ ነገ ትልቅ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ አንዳንዶቻችን ይህ እውቀት ጎድሎን ነው ነገራችንን ያዘገየነው፤ አንዳንዴም  ያበላሸነው፡፡ እስኪ ዛሬ እንደገና ለመነሳት እንሞክር ፤ ዓላማችንን አንስተን በእምነት እንጀምር፡  መክሊታችንን ሳንነግድበት ጌታ ድንገት እንዳይመጣብን  እፈራለሁ፡፡ ነገ ዛሬ ሳንል ስንፍና መጥቶ እንደ ወንበዴ ሳይከበን፣ ምክንያቶቻችንን ሁሉ ጥለን፡ ራዕያችንን ለመፈጸም  እንነሳ፡፡ ቢያንስ እኮ አንድ  ለወንጌል ልቡ የሚቃጠልበትን የገጠር ወንጌላዊ መርዳት፣ አንድ ወይም ሁለት ልጆችን አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት መነሳት፣ ወይም በተለያየ ጊዜ ከቡና ቤት በወንጌል አምነው የወጡትን ሌላ  ስራ እስኪይዙ ድረስ  ኑሮአቸውን ማገዝ፣ ወይም አንድን ድሀ ቤተሰብ ፈልጎ መርዳት፣ ወይም ትራክቶችን ማሳተም....ወዘተ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ  በጣም ብዙ ብዙ በጎ ራዕዮች አሉ፡፡ እባካችሁ እንፍጠን!!!

ማስታወሻ፡- አስተያየት ካላችሁ በአድራሻው /ከታች ባለው ኢሜይል/ ሐሳባችሁን መጻፍ ትችላላችሁ፡፡ ሳንሰበሰብ በፊት ራዕያችንን እንድንፈጽመው ጌታ በቀሪ ዘመናችን በነገር ሁሉ ይርዳን፡፡ አሜን!

                                                                                                       benjabef@gmail.com

Sunday, May 17, 2015

ስለ ታቦት ሚስጥር...

        በስመ አብ ፡ ወወልድ፡ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ አሜን፡፡
      በዛሬው ርዕስ ውስጥ ቀጥሎ የምትመለከቱትን ቪዲዮ ሰሞኑን ከዩቱዩብ ላይ አግኝቼ ልቤ በጣም ስለተነካ ፡ትምህርቱን ሁሉም ሰው ቢሰማው ይጠቀማል ብዬ አሰብኩ፡፡ እንደነዚህ የሆኑ የክርስቶስን ክቡር ወንጌል ለህዝቡ የሚናገሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ካህናትና አባቶች  ስላሉ እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ የቤተክርስቲያን ራስ እና ጌታ የሆነው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለህዝቡ ና ለቤተክርስቲያኑዋ አሁንም በጎ ሐሳብ እንዳለው ያሳያል፡፡ አባታችን ያስተማሩትን ይህንን ትምህርት ሰምተን መለወጥ ይሁንልን፡፡ እግዚአብሔር ለሁላችን ልቦናን ይስጠን፡፡ አሜን!

አስተያየት፡- ስለ ታቦት በተሰጠ ሶስተኛው ትርጉም ወይም ትንታኔ ላይ ብዙዎች የተለየ ሐሳብ አላቸው፡፡ ይኸውም በኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ታቦታት ሁሉ በአብዛኛው ስያሜያቸው በጌታችን በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ባለመሆኑና  በምትኩ  በሌሎች ሰማዕታትና መላዕክት ስም የተሰየመ በመሆኑ ‹ጉልበት ሁሉ ለስሙ /ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ / ይንበረከካል› ፊሊ.2 ቁ.10 ከሚለው አውነተኛ ቃል ጋር የሚጋጭ ነው፡፡በመሆኑም በአዲስ ኪዳን ዘመን ለምሳሌነት የተቀመጠ እና በሰው እጅ ለተቀረጸ  ነገር መገድ ተገቢ  አይደለም ይላሉ፡፡

ማስታወሻ ፡- ለወገኖቻችን፣ ለወዳጅ -ዘመዶቻችን ሁሉ ሼር በማድረግ  የወንጌልን እውነት አብረን እንድናሰማ  እጠይቃለሁ!!

                                                                                                                    benjabef@gmail.com


Friday, May 8, 2015

Urgent message
Dear family, friends and brothers and sisters : May the peace of the Lord be with you.
I am writing to you that the end days are very near and we need to aware our destination before the days are ended. As you may already hard, Jesus Christ is the key for our salvation. Anyone who believes in Jesus Christ will get eternal life. If you don’t, there will be a punishment of Hell as a consequence. I believe this is very important to you to understand and respond accordingly before the end of your days.
Jesus Christ was buried, and that He was raised on the third day. He appeared to hundreds of the brothers and sisters for forty days. He was lifted up into heaven and sat down at the right hand of God.  This Jesus, who has been taken up, will come soon in just the same way as he ascend into heaven, and this will be the end of the world. Anyone who believes in this truth will escape God’s judgment and receive eternal life. The Bible says  If we confess our sins, he is faithful and just and will forgive us our sins and purify us from all unrighteousness.
   Jesus said: "I am the way, the truth, and the life: no one comes unto the Father but by me." (John 14:6). This clearly shows the only way to heaven is through Jesus. Similarly, John 3:16-18 said: “For God so loved the world that he gave his one and only Son, that whoever believes in him shall not perish but have eternal life. For God did not send his Son into the world to condemn the world, but to save the world through him. Whoever believes in him is not condemned, but whoever does not believe stands condemned already because they have not believed in the name of God’s one and only Son.”
We have limited time on this world and death was completely unexpected. How will you use the precious time you have will determine where you spend eternal life. If you accept Jesus Christ as your personal savior and confess your sins, he is faithful and just to forgive you and to cleanse you from all unrighteousness and write your name on the Book of life. Unless you recognize Jesus as your savior and your Lord, you have NO right to approach God's throne of grace. "For by grace are ye saved through faith; and that not of yourselves: it is the gift of God: Not of works, lest any man should boast." (Ephesians 2:8-9). If anyone's name was not found written in the book of life, he was thrown into the lake of fire (Revelation 20:15). You must first come by way of the cross of Jesus Christ, for there is only one way to God the Father, and that is through God the Son. "For there is one God, and one mediator between God and men, the man Christ Jesus" (1st Timothy 2:5). 
The major points from the verses are:
  1. God gave his begotten Son for the world
  2.  Jesus come to this world to save all human kind
  3.  Anyone who believe in Jesus will be saved
  4. Anyone who ignores this salivation will condemn. 
Trust Jesus Christ today! Here's what you must do: 
  1. Admit you are a sinner.
"For all have sinned, and come short of the glory of God;" (Romans 3:23)
Therefore, just as sin entered the world through one man, and death through sin, and in this way death came to all people, because all sinned (Romans 5:12)
"If we say that we have not sinned, we make him a liar, and his word is not in us." (1 John 1:10)
  1. Be willing to turn from sin (repent).
Jesus said: "I tell you, no! But unless you repent, you too will all perish.” (Luke 13:5)
  1. Believe that Jesus Christ died for you, was buried, and rose from the dead.
"For God so loved the world, that he gave his only begotten Son, that whosoever believeth in him should not perish, but have everlasting life." (John 3:16)
"But God commendeth his love toward us, in that, while we were yet sinners. Christ died for us." (Romans 5:8)
If you declare with your mouth, “Jesus is Lord,” and believe in your heart that God raised him from the dead, you will be saved" (Romans 10:9)
  1. Through prayer, invite Jesus into your life to become your personal Savior.
"For with the heart man believeth unto righteousness; and with the mouth confession is made unto salvation." (Romans 10:10)

Dear God, I am a sinner and need forgiveness. I believe that Jesus Christ shed His precious blood and died for my sin. I am willing to turn from sin. I now invite Christ to come into my heart and life as my personal Savior. In Jesus name I pray, Amen.
Once you pray this, believe Jesus cleans your sin. Read your Bible daily. Pray continuously.
Note: Please share this good news for 10 people and show how you care for them.

                                                                              for any suggestion : benjabef@gmail.com

Monday, May 4, 2015

ስንት አይነት መፅሐፍ ቅዱስ አለ?

         ክፍል አንድ

መፅሐፍ ቅዱስን በተመለከተ የሚቀርቡ ብዙ የሰዎች አስተያየቶች በመኖራቸው ይህንን ትምህርት ሰፋ አድርጎ ማቅረቡ ተገቢ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡ በዚህ ክፍለ ትምህርት ውስጥ በተለይ ጎላ ብለው የሚታዩትን ልዩነቶች እንጂ ተያይዘው የሚነሱትን ሐሳቦችና ጥያቄዎች ሁሉ አንስቶ መፃፍ እንደማይቻል አንባቢ ሊረዳው ይችላል ፡፡ ምክንያቱም እጅግ ሰፊ በመሆኑ ነው፡፡

ከምናነሳቸው ጥያቄዎች ውስጥ ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ  ቁጥር  ስንት  ነው ? የሚለውን ይሆናል፡፡ ምክንያቱም በኦርቶዶክስ 84 ወይም በተለምዶ 81 ፣ ካቶሊክ 72 መፅሐፍትን ስትቀበል ፕሮቴስታንት /ወንጌላውያን አማኞች/ ደግሞ 66 ቁጥር  ያለው መፅሐፍን ይቀበላሉ፡፡ ማናቸው ናቸው ትክክል? ወይም እውነቱን እንዴት ልናገኝ እንችላለን? ብለን መጠየቃችን አይቀርምና፡፡

መፅሐፍ  ቅዱስ የእግዚአብሔር  ቃል ነው፡፡ ይህ ማለት ሰዎች በእግዚአብሔር መንፈስ ተነድተው ፣ በሰዎች ቁዋንቁዋ ና ባህል የተጻፈ እስትንፋሰ እግዚአብሔር ያለበት መጽሐፍ ነው፡፡ /2ጢሞ. 3፡15 ና 1ጴጥ.2፡1/

መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ትልልቅ ኪዳኖች ያሉት ሲሆን በብሉይ ኪዳን  /አሮጌው/ እና አዲስ ኪዳን በመባል ይታወቃሉ፡፡ ብሉዩ በዕብራይስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የተጻፈ ሲሆን ፤አዲስ ኪዳን ግን በዘመኑ  ታዋቂ በነበረው የግሪክ ቁዋንቁዋ ነበር የተፃፈው፡፡ ከዚያ በሁዋላ  በብዙ መቶ ቁዋንቁዋዎች በዓለም ዙሪያ ተተርጉሞአል ፡፡ በዓለም ላይ አንደኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ መጽሐፍ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነውን  ጥያቄ ለመመለስ የግድ የመጀመሪያዎቹን ትርጉሞችና ቅጂዎች ማንሳት ተገቢ ስለሆነ ነው፡፡ እንደሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የተፈጸመው በአብዛኛው በዕብራውያን /እስራኤላውያን ህዝብ /መካከል ነው ፡፡ የታሪኮቹ ባለቤቶችና ጸሐፊዎች እዚያ የነበሩ ሰዎች ናቸው፡፡በነገራችን ላይ ቢያንስ አርባ የሚሆኑ ሰዎች እንደጻፉት ይታመናል፡፡ ባለታሪኮቹ እነርሱ ከሆኑ ደግሞ በአሁን ጊዜ ጭምር እጃቸው ላይ ያለና የሚጠቀሙበት መጽሐፍ ምን እንደሚመስል ማወቁ ተገቢ ነው፡፡ ይህም በተለይ ብሉይ ኪዳንን በተመለከተ እንጂ አዲስ ኪዳንን ጉዳይ ላይ አይሆንም ፡፡ ምክንያቱም እስራኤል ስለ ሐጢያታችን በምድራቸው ላይ ሞቶ የተነሳውን መሲሁ ክርስቶስን እስካሁን ድረስ ስላልተቀበሉትና ሌላ መሲህ እየጠበቁ ከመሆናቸው አንጻር ነው፡፡/ሮሜ.9/

የዕብራይስጡ መፅሐፍ ዝርዝር እንደሚከተለው ነው፡-
          /የመጽሐፉ ይዘት 24 ነው፡፡/

1-የሕግ መፃሕፍት /5/
   /አሪት ዘፍጥረት፣ ዘጸዐት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም/

2-የነብያት መጻሕፍት-/8/
  ሀ-ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ 1-2 ሳሙኤል፣ 1-2 ነገስት፣
  ለ-ኢሳያስ፣ ኤርሜያስ፣ ሕዝቅኤል፣ 12ቱ የነብያት     መጻሕፍት

3-የጥበብና ምሳሌ መጻሕፍት./ 11/
   ሀ-የጥበብ  መዝሙር ፣ምሳሌ፣ ኢዮብ
   ለ-5ቱ ጥቅል መጻሕፍት . መኃልየ ፣ሩት፣ ሰቆቃው ኤርሜያስ፣ መክብብ፣ አስቴር፡፡
   ሐ-3ቱ መጻህፍት. ዳንኤል፣ ዕዝራ-ነህምያ፣ ዜና መዋዕል

የፕሮቴስታንት ቀኖና እንደሚከተለው ነው፡፡
      / የመጽሐፉ ይዘት 39 ነው፡፡/ 

1- የሕግ መጻሕፍት ./5/
  / ዘፍጥረት፣ ዘጸዐት፣ ዘሌዋውያን፣ ዘኁልቁ፣ ዘዳግም/
2-ታሪካዊ መጻሕፍት./12/
 / ኢያሱ፣ መሳፍንት፣ ሩት፣ 1ሳሙኤል፣ 2 ሳሙኤል፣ 1ነገስት፣ 2 ነገስት፣ 1ዜና መዋዕል፣ 2ዜና መዋዕል፣ ዕዝራ፣ ነህምያ፣ አስቴር፡፡
3-የጥበብ መጻሕፍት./5/
  /ኢዮብ፣ መዝሙር፣ ምሳሌ፣ መክብብ፣ መኀልዬ ዘሰሎሞን/
4- ትልልቅ /አበይት/ ነብያት./5/
  / ኢሳያስ፣ ኤርሜያስ፣ ሰቆቃው ኤርሜያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤል/
5- ትናንሽ ነብያት. /12/
  / ሆሴዕ፣ ኢዩኤል፣ አሞጽ፣ አብዲዩ፣ ዮናስ፣ ሚክያስ፣ ናሆም፣ ዕንባቆም፣ ሶፎንያስ፣ ሐጌ፣ ዘካርያስ፣ ሚልክያስ/

     ከላይ እንደተመለከተው መጻሕፍቱ በአከፋፈል ረገድ ካልሆነ በቀር በዕብራይስጡ እና በፕሮቴስታንቱ ቀኖና መካከል የይዘት ልዩነት የለውም፡፡/ በኦርቶዶክስና በካቶሊካውያን መካከል እነዚህን መጽሐፍት በተመለከተ ምንም ጥያቄ የሌለ እና ሙሉ ለሙሉ ተቀባይነት ያገኙ መጻሕፍት በመሆናቸው ልዩነቶቹ ላይ ማለትም የተጨመሩ አዋልድ መጻሕፍቱ ላይ ማተኮሩን መርጫለሁ፡፡
 አስቀድመን ከላይ እንዳነሳነው ካቶሊክ የባሮክ፣ ጦቢት፣ ዮዲት፣ ሲራክ፣ 1-2 መቃብያን  ከሚባሉ ጋር 72 መጻሕፍትን፡፡ ኦርቶዶክስ  ደግሞ  ተረፈ ዳንኤል፣ መቃብያን ቀዳማዊ፣ መቃብያን ካልዕ፣ 3ኛ መቃቢያን፣ ሲራክ፣ ጸሎተ ምናሴ፣ ተረፈ ኤርምያስ ፣ ሶስና፣ ባሮክ፣ መጽሐፈ ጥበብ፣ በዕዝራ ሱትኤል፣ ዕዝራ ካልዕ፣ ጦቢት፣ ዮዲት፣ አስቴር፣መዝሙረ ሰልስቱ  ደቂቅ፣ ተረፈ ዳንኤል፣ ኩፋሌ፣ ሄኖክ  የሚባሉ  84 ይዘት ያላቸው መጻህፍት አሉዋቸው፡፡ይህ ማለት ዕብራይስጡ 24 ወይም የ ፕሮቴስታንቱ 39 የሚባሉ የብሉይ ኪዳን ቀኖና መጻሕፍትን ጨምሮ ነው፡፡

አንባቢ እንደሚያስተውለው ዋናዎቹ  የመጻሕፍቱና የታሪክ ባለቤቶች ዕብራውያን እነዚህን አዋልድ ያካተተ መጻሕፍት የላቸውም፡፡ ይህ ማለት የታሪክ ባለቤቶቹ ያልተቀበሉዋቸው መጻህፍት እንደሆነ ልብ ይሉዋል፡፡

ከዚህ በመቀጠል የምንመለከተው የጥንት አባቶቻችን በምን መስፈርት ቀኖናውን /የመጻሕፍቶቹን ይዘትና ዝርዝር / እንደወሰኑ ነው፡፡

     ቀኖና የተወሰነበት  አራት ዋና ዋና መመዘኛዎች ፡-

1- በዋናው የዕብራይስጡ ዝርዝር ላይ የተካተተ መሆኑን፡፡ አስቀድመን እንደተመለከትነው ዕብራይስጡ የራሳቸው የባለታሪኮቹ መጻሕፍ በመሆኑ ከምንም ነገር ይልቅ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡የዕብራይስጡ መጽሐፍ 24 መጻሕፍትን የያዘ ነው፡፡

2- በአዲስ ኪዳን ዘመን ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ ዘመኑ ዕውቅና ሰጥቶ የጠቀሰው መሆኑ፡፡ ይህም ጌታችን በስጋው ወራት ባስተማረበት ጊዜ ከሙሴ መጽሐፍት፣ ከነብያትና ከመዝሙራት የተነገሩትን ቃላት ይጠቅስ ነበር፡፡በአንድ በኩል መጽሐፍቱ ልብ ወለድ ታሪኮች ሳይሆኑ የእግዚአብሔር ቃል እንደነበሩ ማረጋገጫ ይሰጣል፡፤

3- በሶስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የመጀመሪያዎቹ ሐዋርያት ስልጣን ያለው የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ በመጥቀሳቸው ነው፡፡ ይህም ከጌታ በመቀጠል እርሱ ያስተማራቸውና የመረጣቸው አገልጋዮቹ ለብሉይ ኪዳን መፃህፍት ይሰጡ የነበረውን ክብርና ጥንቃቄ፤ ብሎም ጥላውን እያሳዩ ፍጻሜው እንዴት እንደሆነ በመንፈስ እየመረመሩ ይገልጡ እና ይተነትኑ ስለነበረ ሌላው ማረጋገጫ ነበር፡፤

4- የጥንቱዋ ቤተክርስቲያን /ቅዱሳን/ ይህነንን መጽሐፍ እንደ እግዚአብሔር ቃል ይጠቀሙበት እንደነበረ ከታወቀ ቀኖና /canon / ይጸድቅ ነበር፡

ከላይ የተመለከቱትንና ሌሎች እውነታዎችን በማገናዘብ የጥንት አባቶቻችን ቀኖናውን ወስነውልናል፡፡ ከእነዚህ መጻሕፍት ውጪ ያሉት አዋልድ መጻሕፍት የጨለማ ዘመን ተብሎ በሚታወቀው የ 430 የዝምታ ዓመታት ውስጥ አብዛኛዎቹ እንደተጻፉ በስፋት ይታመናል፡፡ ይህም ደግሞ የብሉይ ኪዳን ቀኖና ተወስኖ ከተዘጋ በሁዋላ  የተጨመሩ እንደሆነ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ በዚህም ሆነ በዚያ ከተወሰኑ አብያተክርስቲያናት ውጪ መላው ዓለም የሚጠቀምበትን የታወቀውን መጽሐፍ በማንበብ እንድንጠቀም እመክራለሁ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቃል መጨመርም ሆነ መቀነስ መርገምን ያስከትላል፡/ራዕይ 22// ‹ ስለ ራዕዩ መጽሐፍ ሲናገር የጨመረ መቅሰፍት ይጨመርበታል ፤ሲል የቀነሰ ደግሞ ዕድሉን ያጎድልበታል፡፡› ይላል፡፡ስለዚህ  መንፈስ ቅዱስ የቤተክርስቲያን አበውን ተጠቅሞ የወሰነልን ፣ለዚህ ህይወታችን ተመጥኖ የተሰጠን ቃል በቂ ነው፡፡እርሱን በቅጡ ለማወቅ ቅን ልቦናችን ቢነሳሳ፣ለማንበብ፣ ለማጥናትና ለማሰላሰል ጊዜ ቢኖረን ህይወት ለዋጭ ቃል ነው፡፤ተግሳጽንም ፣ ታላቅ ምክርን ከጽድቅ ጋር የምንቀስምበት ጭምር፡፡ከዚህ በተጉዋዳኝ ግን በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ እንደሚታመነው ተጨማሪ መጻህፍትን ለተጨማሪ እውቀቶች ብናነብ ምንም አይጎዳም! ስለሚሉ፤እንደ ፕሪስቢቴሪያንና አንግሊካል የመሳሰሉ አብያተክርስቲያናት ለዚህ ነገር ዋና ተጠቃሾች ናቸው፡፡ ለዕውቀትም ቢሆን ልንጠቀምበት የምንችለው፡ እውነትን እስካላፋለሰ እና ትክክለኛውን መለኮታዊ የድነትና የህይወት መርህ እስካልበረዘ ድረስ ብቻ ነው ፡፡

             አዋልዱ በቀኖናው ላይ ለምን አልተካተቱም ?

1-   በዕብራይስጡ ዝርዝር ላይ የሌሉና ቀኖናው ከተዘጋ በሁዋላ የተጨመሩ በመሆናቸው ነው፤
2-   በአዲስ ኪዳን ዘመን ያልተጠቀሱ ሲሆኑ፤ አሉ የሚባሉም ካሉ እንደ አባባል የተጠቀሱ እንጂ እንደ እግዚአብሔር ቃል የሚወሰዱ አይደሉም፡፡
3-   የአይሁዳውያን ታሪክ አጥኚ ጆሴፈስ ፈጽሞ አላካተታቸውም፡፡ ይህ ማለት ታሪክ አያውቃቸውም እንደማለት ነው፡፡
4-   አዋልድ  መለኮታዊ ቃል እንደሆነ የሚገልጽ አንድም ማስረጃ የለም፤

5-   የታሪክ፣ መልክዐ-ምድር አቀማመጥ፣ ወይም ጊዜንና ክስተቶችን አዛብቶ የማቅረብ የጎላ ችግር ይታይበታል፡፡ ይህንን በተመለከተ ወደ መጨረሻ ላይ ከአዋልዱ ላይ አንዳንድ ጥቀቅሶችን ስንመለከት የበለጠ ይገባናል፡፡
6-   የእግዚአብሔርን ቃል የሚጻረር ትምህርት /ዶክትሪን/ ያስተላልፋሉ፤ ለምሳሌ፡-ውሸትን ይፈቅዳል፤ ሰይጣንን ያሞጋግሳል....ወዘተ፡
 7-   በስነ ጽሁፋዊ ይዘቱ በታሪክና ምሳሌ ወይም ተረት ውስጥ የሚመደብ ነው፤
8-   መንፈሳዊና ሞራላዊ ይዘቱ / አቁዋሙ/ ከብሉይ ኪዳን አጠቃላይ ታሪክ አንጻር በጣም የራቀ ወይም የወረደ ነው ተብሎ ይታመናል፡፡

     አዋልድ መጻሕፍት  አዛብተው ከሚናገሩት ነገር በጥቂቱ፡-
  • ኩፋሌ 16፤24 ያዕቆብ  ከአብርሐም ጋር ተኛ  ይላል፡፡ ነገር ግን ዘፍ.25፤7 ላይ እንደዚያ አይገልጽም፡
  •  መቃብያን ሳልስ 2፤7 ላይ የሰይጣንን ፉከራ  ይገልጻል፡፡ እንደውም ቃሉ ከቁራን ላይ ቀጥታ የተወሰደ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በተጨማሪ 3ኛ መቃብያን 1፡6-24 ፣ ም.2፤1-2 ከቁራን ላይ ከአል አእራፍ ቁጥር 11-27 ከ7ኛው ሱራ ላይ እንደተወሰደ ማመሳከር ይቻላል፡፡
  • መጽሐፈ ጥበብ  6፤6 ላይ ደግሞ በቀጥታ የመዳንን እውነት የሚያፋልስ ሆኖ ቀርቦአል፡
  • ሲራክ 25፤25 እግዚአብሔር በመሰረተው የተቀደሰ ጋብቻ መካከል ሊኖር የማይገባውን ነገር ይናገራል፡፡
  •  ሲራክ 24፤10-11 በተለይም ቁ.8 ላይ ስለ ማርያም፣ ሐዋርያት ና ወንጌል ጉዳይ በግልጽ ያወራል ፡፡ መጽሐፉ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተጻፈ አይመስልም፡
  •  እዝራ ሱትኤል 5፤29 ላይ እንዲሁ ስለ መንግስተ ሰማይ ና ስለ ክርስቶስ ይናገራል፡፡ መንግስተ ሰማይ በብሉይ ኪዳን ዘመን በግልጽ ይታወቃልን ?
  •  ሄኖክ 37፤24 ሐጢያተኞች እንድናለን ብለው ተስፋ እንዳያደርጉ ተስፋ ያስቆርጣቸዋል፡፡
  •  ሔኖክ 19፤1 ላይ ቅዱስ ሚካኤል የመንፈስ ቅዱስ እውቀቱ ያበሳጨኛል ብሎ እንደተነናገረ ተገልጹዋል፡፡ በውኑ ቅዱስ ሚካኤል በመንፈስ ቅዱስ እውቀት ይበሳጨጫልን? ሌላም ሌላም በርካታ የተፋለሱ ነገሮችን የያዘ መጽሐፍ እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ አንባቢያን ተጨማሪ ጥቅሶችን ሲፈልጉ በአድራሻችን ሊጽፉልንና ተጨማሪ እውነቶችን ሊረዱ ይችላሉ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ ግን የተጠቀሱት ነገሮች ለማመሳከሪያነት በቂ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

 ማስታወሻ፡- ይህ ትምህርት ከተለያየ መንፈሳዊ መጻሕፍት እና የተዘጋጁ የስልጠና ትምህርቶች  ላይ ተገናዝቦ የቀረበ ነው፡፡

        ለተጨማሪ ትምህርቶች እዚህ ይጫኑ  http://tehadesothought.blogspot.com                       

Friday, May 1, 2015

ለቤተክርስቲያን መሪዎች!

                            ክፍል ሁለት
 ወንጌልን መመስከር ከልባችን ተነክተን እንድናደርገው፡ ነፍሳትን የመታደግ ቅንዓት እንዲጨምርብን አስቀድመን ብንጸልይ መልካም ነው፡፡ ፍሬያማ ና ውጤታማ እንድንሆን ያግዛልና፡፡ ብንጸልይ ሊሰጠን እንደሚችል ከተጻፈልን ተስፋ ቃሎች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት፡-

1-  ማቴዎስ  ወንጌል 7፤7-8 '' ለምኑ ይሰጣችሁአል፤ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኩዋኩ  ይከፈትላችሁዋል፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኩዋካ ይከፈትለታል፡፡'' እንደሚል፤ ከልባችን እየፈለግን እንለምን፡፡ በሩን እስኪከፍትና እስኪሰጠን  ድረስ  ደጋግመን በሩን እንቆርቁር፡፡ በተስፋ ቃሉ መሰረት በሩን ይከፍትልናል፡፡ ሌሎችን የምናተርፍበትም የወንጌል ቅንዐት ከብዙ ጥበብ ጋር ወደ ልባችን ይገባል፡፡

2-  ሁለተኛው የያዕቆብ መልዕክት 1፤17 ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ይላል፡-'' በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው ፤መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡''  ለወንጌል  የመቅናት ስጦታ በጎም ፍጹምም ነው፡፡ ይህን በረከት ከጌታ ልንቀበል እንደምንችል ቃሉ ያሳያል፡፡

ፀሎት፡- ጌታ ሆይ  የወንጌልን ቅናት እንድትሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምንሀለሁ!! 
       
               አሁን ለኛ ቀን ነው ሌሊት?
'' ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ላደርግ  ይገባኛል፡፡ማንም ሊሰራ   የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡'' ዮሐ.9፤4፡፡
    በሰው ህይወት ውስጥ ቀንም ሌሊትም አለ፡፡ ይህ ሁሉን ሰው ሲያጋጥም የኖረ፣ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡የምንሰራበት ምቹ ጊዜና ሁኔታ ይሰጠናል ፤ደግሞ ሌላ ጊዜ መስራት ብንፈልግና ጊዜ ቢኖረን እንኩዋ የወደድነውን ማድረግ የማንችልበት ሌሊት ደግሞ ይመጣል፡፡የተመቻቸው ቀን ላይ ያልሰራ፣ያልተጋ ሰው የማይሰራበት ሌሊት ሲመጣበት ይቆጨዋል፡፡
     ከወንጌል መስበክ አኩዋያ እነዚህን ሁለት ሁነቶች በምድራችን ላይ እንኩዋ ማሰብ ይቻላል፡፡ አንዱ  ወንጌልን በነጻነት መስበክና ማስተማር የማይቻልበት  ጊዜ ነበር፡፡ ምናልባት ደግሞ አሁን በአንጻራዊ  ሁኔታ ቤተክርስቲያን በድብብቆሽ  ከምትሰበሰብበትና ከምትሰራበት ሁኔታ ወጥታ ወንጌልን በትልልቅ  አዳራሾች ና በአደባባይ መስበክ ችላለች፡፡ ይህ ሲባል ግን መቼም ዘመን ቢሆን ወንጌልን ከመስበክ ጎን ለጎን ከሚገጥሙ ትንሽም፣ ትልቅም  ተግዳሮቶች ጋር ማለት ነው፡፡
  ይሁንና ይህንን ነጻነት ተጠቅመን የማንሰብክበት፣ የማንመሰክርበት ከሆነ ነገ ደግሞ ሌሊት ሊመጣብን ይችላል፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚከሰት አይታወቅም፤ የወንጌል ተቃዋሚዎች በዓለም ላይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አይለው ተነስተዋል ጌታም ለጊዜው ስለ ፈቀደላቸው ይመስለኛል፡ አንዳንድ በጸሎት መከልከል የማንችላቸውን ድርጊቶች ሁሉ እያደረጉ ያሉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ነገ በእኛ አካባቢ ምን ሊከሰት ይችላል?  ከህግ ፣ከዲሞክራሲ አንጻር የሰው መብት አትንካ ፣የራስህን አመለካከት ሰው ላይ መጫን አትችልም፤ የስብከት ፍቃድ፣ የአገልጋይነት ፍቃድ....ወዘተ የሚሉ ነገሮች ከአሁኑ በራችንን እያነኩዋኩ ነው፡፡ ለምሳሌ  የኤርትራ ወንድሞችና በዚያም ያለች ቤተክርስቲያን ሌሊት ውስጥ ናቸው ያሉት፡፡ እንደሚሰማው መስበክ ና መናገር አይቻልም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር ምናልባት በቅርብ ጊዜ ምቹ ቀን ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ ሀዘናቸውም ይጽናናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሁንና እኛ ግን ከእንደነዚህ  አይነት ሁኔታዎች መማር አለብን እላለሁ፡፡
   
            ወንጌልን በራሳችን ዘመን ...!
" ዳዊት በራሱ  ዘመን  የእግዚአብሔርን  ሐሳብ  ካገለገለ  በሁዋላ  አንቀላፋ፡፡" ሥራ.13፤35
 ዳዊት በተሰጠው በራሱ ዘመን እንዲሰራው የተቀመጠለትን ነገር አድርጎ ማለፉን ነው ቅዱስ ሉቃስ የዘገበልን፡፡አሁን እኛ በእኛ ዘመን እንድንሰራው የሚፈለግ ታላቅ የእግዚአብሔር ዓላማ፡ በዋነኛነት ምን ሊሆን ይችላል?  ይህንን ጥያቄ  ለመመለስ  በሚደረጉ ጥረቶች ብዙ ሰዎች የተለያየ በጎም የሚመስሉ፣  በጎም ያልሆኑ አመለካከቶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፊት ለፊት የተቀመጠላቸውን የእግዚአብሔርን አጀንዳ ችላ ብለው ሲመራመሩ ፡አላስፈላጊ ወደ  ሆኑና ከእግዚአብሔር የልብ ትርታ ጋር ግንኙነት ወደሌላቸው ፣ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን፣ ከትህትና ይልቅ ትዕቢትን ፣ለሌላው ከማሰብ ይልቅ ለራስ ብቻ በሚያደላ አፍቅሮ ነዋይ እየተሳቡ ገብተው ሲለፉና ሲሰቃዩ ማየት የተለመደ ነገር  ሆኑዋል፡፡ሁሉም ድርጊቶች የሚፈጸሙት የእግዚአብሔር የዘመኑ አሳብ ፣ ራዕይ ና ጥሪ ስም ነው፡፡ በተለይም  ቤተክርስቲያን  ዋና ነገሩዋን ስትስት ከማየት በላይ የሚያም ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር ግን በዚህ ዘመን ማድረግ የፈለገውን አሳቡን በግልጽ ተናግሩዋል '' በክርስቶስ ለማድረግ እንደወደደ እንደ አሳቡ የፍቃዱን ሚስጥር አስታውቆናልና፡፡'' በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን በክርስቶስ ለመጠቀቅለል ነው''  ኤፌ.1፤10፡፡ ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንዲሆንና ለእርሱም እንዲሆን ባለ የመለኮት አጀንዳ ውስጥ ተሳታፊ መሆን  ምን ያህል ታላቅ ዕድል ነው?! ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ  የምናደርግበት መንገዱ ደግሞ ወንጌልና ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ለሰው  የሞኝነት መንገድ የሚመስል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን አስቀድሞ የታሰበ ዘዴ ፣ጥበብ ፣ ብልሀት ነው፡፡ '' ....ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ፣ ካልሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ''----የተባለበት ሚስጥር፡፡
               
             ቤተክርስቲያን ሆይ ንቂ !
  ጾምና ጸሎት ይዘን በወንጌል ሳይሆን በተለያዩ ዘመነኛ ሃጢያቶች ና ሱሶች ቀስ በቀስ እየተወረሰ  ያለውን ህብረተሰብና አካባቢ እንዲሰጠን መጸለይ ብንጀምርስ ? ክፉ በብዙ እየተጋ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያን በሰበብ አስባብ የጸሎት ቀናት ፣ሰዐታት እያስቀነሰ ፣የማለዳ  ጸሎቶች ፣ አዳር ጸሎቶችን እያስተወ፡ ያለምንም ውጊያ እየሰራ ያለ ይመስላል፡፡ መሳሪያዎቹዋን ቀስ በቀስ የተዘረፈችዋ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዐት መንቃት ይጠበቅባታል፡፡ ሙሽራው ሊመጣ በደጅ ነው !እያልን ሙሽሪት ተገቢውን ልብስ  ሳታደርግ ፣ ሳትዘጋጅ እንዴት ይሆናል?
  ቤተክርስቲያን ትውልዱን እየተናጠቀች  ካልጸለየች ሌላ የተጋ ይወስዳቸዋል፡፡ ዲያቢሎስ ለራሱ አጀንዳ እንደሚጸልይ  የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ሰይጣን እንደ  ስንዴ  ሊያበጠጥራችሁ ለመነ" ሉቃ.22፤31 ፡፡ የሰይጣን ልመና ትውልድን የማበጠር፣ የማድከምና የመበተን ሲሆን : ጌታ ግን ስለ ጴጥሮስ '' እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ '' ይላል፡፡ምንም እንኩዋ ጴጥሮስ በፈተናው ተሸንፎ ክዶ ሄዶ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ በንስሀ ተመልሱዋል፡፡ ለመመለሱ ምክንያት የነበረው ግን ጌታ ስለ እርሱ ስለ ማለደለት ነው፡፡/ቁ.32/
     ቤተክርስቲያን ዕቅድ ያላወጣችበትን ህዝብ እና ስፍራ ጠላት እያቀደበት ነው ፡፡ ሰሞኑን አይ ኤስ የተባለው እስላማዊ ድርጅት ምን እየደረገ እንደሆነ ለማንም ጆሮ ባዳ አይደለም፡፡ የደከሙ መንግስታትን እያሰሰ ይቆጣጠራል ፣ ይደራጃል፤ ለምሳሌ ጋዳፊ የወደቁበት ሊቢያ፣ ሳዳም ሁሴን የወደቁበት ኢራቅ፣ በብዙ ጦርነት የደቀቀችውን ሶሪያ....እንደ የመን ያሉ ሌሎችንም አገሮች፡፡ በትንሽ ተዋረድ ደግሞ ወንጌል ለመስበክ ያላሰብንባቸው አካባቢዎች ና ጠንካራ ጸሎት የማይደረግባቸው ልል ቦታዎች ልክ ጠንካራ መንግስት እንደሌለባቸው አገሮች ለክፉው ስራ የተጋለጡ  ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ምን ምን ያልነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች  እንደ ወረርሽኝ የጫትና የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች ማከፋፈያ እና መጠቀሚያ ሆነው ሲታዩ ፤የዝሙት ማስፋፊያ፣ የመጠጥ ንግድ ቤቶች ፣ዳንኪራ ቤቶች እንደ ሰደድ እሳት በየቦታው በፍጥነት ሲስፋፉ፡ ከሁዋላ  ደጀን የሆናቸው ና ዕቅድ አውጪው  ማን ነው?  በዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያን የት ነች? ለትውልዱ ምን እያሰበች ነው?

በዚህና  በዚያ ተወጥሮ  ያለውን  ወጣት ትውልድ  ከጠላት  መንጋጋ  ለማላቀቅ  ተግቶ  እየጸለየ ያለ ማን ነው? የትውልድ  ሸክም ያለበት የዘመኑ  የወንጌል ሰው ማን ነው? ቀድማ አይታ  የተነሳች ፣ እንደ ሰራዊት  እየጸለየች ያለች  የዘመንዋ  ቤተክርስቲያን  የቱዋ ነች?  ለሚከፈቱ  አጥቢያዎች አጀንዳ  ያላት፣ ለወንጌል በጀት ያላለቀባት፣ የጌታ  ዋነኛ  አሳብ  የገባት  አጥቢያ  የት ናት? ሲመስለኝ ሰይጣን የቤት ስራ ሰጥቶን ፡እርሱ የራሱን ስራ እየሰራ ነው፡፡ አንገብጋቢና ዋና  ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ እንድንፈጅ ፣ እርስ በርስ እንድንለያይ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲጠላ ፣ቤተክርስቲያን  ከቤተክርስቲያን ፣መሪዎች ከመሪዎች  እንዲራራቁና እንዳይግባቡ ተደርገናል፡፡ እንደ ጥንቱዋ ቤተክርስቲያን መሪዎች ስለ ተሐድሶ ወይም ስለ ሪቫይቫል ሊያስቡ በሚገባበት ጊዜ ላይ '' የማርያም አይን ጥቁር ነው ቡናማ ?''፣ '' በአንድ መርፌ ላይ ስንት መላዕክት ይቆማሉ?''፣ '' ቅዱስ ቁርባን ውስጥ ዝንብ ብትገባ ዝንቡዋ ትቀደሳለች ወይስ ቁርባኑ ይረክሳል ? '' በሚሉ ጭቅጭቆች ተወጥረው፣  በሐሳብ ተለያይተው፡ ውድ ጊዜያቸውን እንዳቃጠሉ ፤ ሰይጣንም ኑፋቄዎችን በቤተክርስቲያን አሾልኮ ለማስገባት ዕድል እንዳገኘ፡ ዘንድሮም ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ብናስተውል መልካም ነው፡፡
   ሩቅ የመሰሉን ነውሮች ቤተክርስቲያን ደጅ ላይ፣ ብቻ አይደለም ምስባኩ ላይ ከወጡ ቆዩ፤ የጺዮንን በር የተዳፈሩ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች  እየሆኑ ነው ፡፡ እኛስ እንደ ዳነ ሰው ፣ እንደ ቤተክርስቲያን  ምን እያሰብን ነው?

በመጨረሻ፡- ቢቻል የቤተክርስቲያን መሪዎች እና የሚመለከታቸው ሁሉ ተሰብስበው ዘመኑንና ትውልዱን ያማከለ አዳዲስ  የወንጌል ምስክርነት ዕቅድ ቢያወጡ ፣
                  -ጥቂት በእግዚአብሔር ፊት ጊዜ እንዲወስዱና እንዲሰሙት ቢሆን መልካም ነው፡፡
                - በማንኛውም የወንጌል ዕቅዶች ላይ ለመመካከር ከፈለጉ  በሚከተለው አድራሻ  ይጻፉ E-mail ‹ benjabef@gmail.com ›

ማሳሰቢያ ፡- ይህንን መልዕክት የቤተክርስቲያን መሪዎች ለሆኑ ሁሉ እንዲደርስ ያድርጉ!!! ሃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ!!!

                                                                                          benjabef@gmail.com                                       

ለቤተክርስቲያን መሪዎች!

                      ክፍል አንድ
ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡
 /ወይቤሎሙ፡ ሑሩ፡ ውስተኩሉ፡ ዓለም፡ ወሰብኩ፡ ወንጌል፡ ለኩሉ፡ ፍጥረት፡፡ / ማርቆስ 16፤15፡፡

ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክ ትዕዛዝ የሰጠን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወንጌል መስበክ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም፡፡ እኛ ወደ ጌታ እስከምንሔድ ወይም ጌታ በዳግም ምፅዓት እስኪመለስ ድረስ የምንከውነው ታላቅ የሆነ ሰዎችን የማዳን ተገግባር ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ይኸው ወንጌልን የማሰራጨት ተልዕኮ ለጥቂቶች ብቻ የተተወ  ይመስላል፡፡ ሌሎቹ  ምንም የማይመለከታቸው ነውን? አንዳንድ ጊዜም በዘመቻ ይጀመርና በዘመቻ ሲተውም ይታያል፡፡ በእኔ እምነት አንድ ቤተክርስቲያን ወንጌል መስበኩዋን ማቆም ያለባት በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ድነው ካበቁ እና የዓለም ፍጻሜ ደርሶ ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ወንጌልን መስበክ ማቆምና እንደፈለግን አጀንዳውን መቀያየር የምንችል አይመስለኝም ፡፡ ቤተክርስቲያንን የመሰረታት እና ራስ የሆነላት ጌታ እስኪመለስ ድረስ አድርጉ ብሎ ያዘዘውን ተልዕኮ መፈጸም ይኖርብናል፡፡ ተቁዋሙ የእርሱ ነውና፤ በቤቱ የእርሱ ትዕዛዝ ሊተገበር እንደሚገባ አስባለሁ ፡፡

 መሰረታዊው  ነገር ይህ ሆኖ ሳለ፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌልን በግድ ፣በፍርሀትና በመጨነቅ እንዳንሰብክ ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ እንዴት እንስበክ ?... ከውስጥ በሆነ ፍቅር! በጋለ ስሜት! ነፍሳት እንዲድኑ ባለ እውነተኛ ቅንዐት  / passion   /፡፡ በነገራችን ላይ ለወንጌል ብቻ ሳይሆን፡ ሰለ ሌላውም  ስለምናደርገው ነገር አስቀድሞ ፍቅርና መነሳሳት ቢኖረን ጥሩ ነው፡፡ ቶዘር የሚባል አንድ መንፈሳዊ ሰው እንደተነናገረው '' አንድን ነገር ከመስራት በፊት ለዚያ ነገር ፍቅርና መነሳሳት ያሻል፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ትልቁ ነገር፡ ከሌሎች ነገሮች ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ የውስጥ መነሳሳት፣ ለነፍሳት የሚኖረን ፍቅር ፣ ተልዕኮና አገልግሎት ሁሉ የሚገኘው ወይም የሚገነባው ለክርስቶስ ኢየሱስ ባለን ጥልቅ ፍቅር ላይ ተመስርቶ ነው '' ብሎአል፡፡

            ከውስጥ የሆነ ፍላጎት /passion/ እንዴት ይመጣል?
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለምሳሌ የነህምያን ታሪክ ብንመለከት፡ ከጦቢያና ሰንበላጥ  የመጣበትን ዛቻ ና ማስፈራሪያ ሳይበግረው ህዝቡን አስተባብሮ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በ 52 ቀናት  ሰርቶ የጨረሰ ታላቅ ባለ ራዕይ ነው፡፡ የትልቅ ነገር ባለ ራዕይና ባለ ገድል ከመሆኑ በፊት ግን፡ እስራኤላውያን፡ ተግዘው በሄዱበት በስደት ምድር - በባቢሎን ቤተመንግስት ውስጥ በጠጅ አሳላፊነት ሙያ ተቀጥሮ ኑሮውን ሲገፋ የነበረ ሰው ነው፡፡አንድ ቀን ግን አናኒ የሚባል ወንድሙ ስለ ኢየሩሳሌም ጉዳይ ወሬ ይዞ መጣ፡፡ ያንን ወሬ ሌሎችም  የእስራኤል ሰዎች ሳይሰሙ አይቀርም፡፡ ከሰማው ነገር ተነስቶ አንድ ነገር ለማድረግ የወሰነ ግን አናይም፡፡ ነህምያ ግን የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስና ፣የአባቶቹ መቃብር ያለበት ከተማ በር መቃጠሉን ሲሰማ  ልቡ ተነካ፤ አያሌ ቀን ተቀምጦ  አለቀሰ፡፡/ነህ.1፤3-4/፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡ በሰማይ አምላክ ፊት እያዘነ ይጾምና ይጸልይ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ውስጡ ሲነካ ነው ፡ወደ ቀጣዩ እንቅስቃሴ የተራመደው፡፡ ከሞቀ ስራው አስፈቅዶ ወጥቶ የሄደው፤ ሌሎችን ሁሉ አስተባብሮ ቅጥሩን ሰርቶ የጨረሰው፡፡

ልክ እንደዚህ የሆነ ነገር ስንሰማ፣ ስንሰበክ፣ ስንማር ወይም  ስናነብ፣ ቅዱስ ቅንዓት ውስጣችን ሊገባ ይችላል፡፡ የወንጌል ቅንዓትም ወይ በዚህ መልኩ አልያም በሌላ መንገድ ውስጣችን ይመጣል፡፡ ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል 15 ላይ የምናገኘውና ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት፡፡ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ነበሩት ፤ከመቶዎቹ መካከል አንደኛው በግ ወደ በረሀ ኮበለለ፡፡ ወዲያውም ሰውዬው የነበሩትን ዘጠና ዘጠኙን በመተው የጠፋውን አንዱን ሊፈልግ እንደሄደ ይገልጻል፡፡ያሉትን ዘጠና ዘጠኙን ይባርክልኝ ብሎ እንደ መቀመጥ ፡እንዴት ስለ አንድ በግ  ብሎ ፍለጋ ወጣ  ? ብንል፤ መልሱ ሊሆን የሚችለው ስለ አንድ ግድ የሚያሰኝ ጥልቅ ፍቅር ገብቶበት ነው! በጉ ጠፍቶ መተኛት አይችልም፡፡ ቀጥሎም ነገሩን ከልቡ ሆኖ እንደሚያደርገው የሚያሳየን  '' እስኪያገኘው ድረስ  አጥብቆ መፈለጉ ነው፡፡'' ቁ.4 ፡፡ ካገኘው በሁዋላ ደግሞ፡ ደስታውን የገለጠበት መንገድ በተጨማሪ ልቡንና ቅንዐቱን ያሳየናል፡፡ በጫንቃው ተሸክሞ ወደ ቤት አምጥቶ፣ ጎረቤቶቹን ጠርቶ፣ ደስታውን ገለጸ ይላል፡፡ ካደረጉስ ማድረግ እንዲህ ነው፤ እስኪያገኙ ድረስ አጥብቆ መፈለግ !

     ዛሬ በኛ ዘመን ስንት በግ ጠፍቶብን ነው የተቀመጥነው?

እ.ኤ.አ. ሚያዚያ ወር 2012  ላይ ስለ ዓለም ህዝብ ቁጥር  አንድ አለም አቀፍ ሪፖርት ወጥቶ ነበር ፡፡ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ሰዐት የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን ገደማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ ውስጥ 750 ሚሊዮን ወይም 11% የሚሆነው ህዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት  የሚያምን፣ 2.6 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ወይም  38%  ገደማ የሚሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሰማ ነገር ግን ያልተቀበለ  / ሌሎች አዳኞች አሉ ብለው የሚያምኑ/ ፣ የተቀረውና ሰፊው ህዝብ ማለትም 3.5 ቢሊዮን ወይም  50% ገደማ የሚሆነው ምንም የወንጌል መልዕክት ያልሰማና የክርስቶስን አዳኝነት ያልተቀበለ ነው፡፡
   ከነበሩት መቶ  በጎች  አንዱ ቢጠፋ አክንፎ ያስኬደው ፍቅር ተጽፎልን ፡ከሶስት  ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ጠፍቶ ምንም ሳይመስለን ተረጋግተን መቀመጣችን  ምን ያህል አዚም ቢደረግብን ነው ? ማን ነው ይህን ታላቅ ቅንዐት ከውስጣችን የዘረፈብን ? እርግጥ ነው በዚህ የተቀደሰ ተግባር ላይ የተሰለፉ ተግዳሮቶች በርካታ ናቸው፡፡ ውስብስብም ናቸው፡፡ ነገር ግን ጌታ ተልዕኮውን በሰጠበት ጊዜ " አይዞአችሁ እኔ  እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎናል '' ማቴ.28፤20፤

ነፍሳትን ከሲኦል የመታደግ አገልግሎት በእግዚአብሔር መንግስት ካሉት አገልግሎቶች ሁሉ ላቅ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ትልቅ ውጊያ ያለበት አገልግሎት ነው፡፡ በስጦታ ካልሆነ በቀር ብዙዎች በምርጫ ደረጃ ላይመርጡት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ታላቅ የነፍስ እርካታ የሚገኘውም ፡ የነፍስ ማዳን ርብርቦሽ ውስጥ እንደሆነስ  ያውቃሉ? ሰው  ከሲኦል ሲያመልጥ ያለ እርካታ!

 ወንጌልን መመስከር ከልባችን ተነክተን እንድናደርገው፡ ነፍሳትን የመታደግ ቅንዓት እንዲጨምርብን አስቀድመን ብንጸልይ መልካም ነው፡፡ ፍሬያማ ና ውጤታማ እንድንሆን ያግዛልና፡፡ ብንጸልይ ሊሰጠን እንደሚችል ከተጻፈልን ተስፋ ቃሎች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት፡-
.........................ይቀጥላል..................!