Tuesday, November 27, 2018

ታላቁ ተልዕኮ በኢትዮጵያ


የወንጌል ሪፖርት

እግዚአብሔር ይመስገን! ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት ገደማ ስጥቶ የሄደውን አደራ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ በህብረትም ሆነ በግል እየተሰራ ግስጋሴውን ቀጥሏል።  በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጌልን ላልሰሙ ሁሉ በማድረስ ረገድ ከፍተኛ ሥራ አየሰሩ ካሉት ተቋማት መካከል ታላቁ ተልዕኮ አገልግሎት ዋነኛው ነው። ወንድም ግርማ አልታዬ በአሁኑ ሰዓት የተቋሙ (አገልግሎቱ) ዋና ዳይሬክተር በመሆን ያስተባብራል፤ ከዚህ በፊት ጋሽ አሸናፊ ፣ ጋሽ ማስረሻ፣ ወንድም ዳምጠው ክፈለው እና ዶ'ር በቀለ ሻንቆ በተለያየ ጊዜ ይህንን ተቋም መርተዋል፤ ጌታ እንደሰጣቸው ጸጋ የተለያዩ ንድፎችን በመንደፍ ወንጌልን በኢትዮጵያ ውስጥ አሠራጭተዋል። በአሁን ሰዓት <ታላቁ ተልዕኮ በኢትዮጵያ >አዳዲስ ዕቅዶችን ይዞ በመላው ኢትዮጵያ ወንጌልን እያዳረሱ ና አዳዲስ ሕብረቶችን እያቋቋሙ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የቀረበው ያለፈው ዓመት ሪፖርት የሚከተለውን ይመስላል፡-
    2,588,572 ወንጌል የተመሰከረላቸው።
    62,954 ሰዎች ክርስቶስን ለመከተል የወሰኑ፤
    15,901 በክትትልና በደቀመዝሙር ት/ት የተያዙ ሰዎች
     60,401 ሰዎች የረዥም ጊዜና የአጭር ጊዜ ስልጠናዎችን ወስደዋል፤
     5,636 አዳዲስ ህብረቶች ተተክለዋል። (መረጃው ከወ/ም ሀብታሙ ኪታብ ዘገባ)  

" እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ፣በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። "ማቴ.28:19-20

ክብር ሁሉ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁን! ደስ ሲል!

<<  LET US BE WITNESSES FOR CHRIST! >>

ትልቅ ክፍተት ይሰማኛል....!

ዕለቱ ማክሰኞ በቨርጂንያ ሳምንታዊ ጸሎት የሚደረግበት ዕለት ነው ይህ የኦክቶበር 2018 ማስታወሻ ነው። ቀን ቀደም ብለን ሻይ ስንጠጣ S.Backs ላገኘነው ከኢትዮጵያ ከመጣ ሳምንት ላልሞላው ወንድም መሰከርንለት ዘላለም በግል ስራ የሚተዳደር ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው ነው የተነጋገርነውን ነገር ሳንቋጭ የአክስቱ ልጅ መጥታ ወሰደችው ደግነቱ አድራሻ ተቀያይረናል። ልቡ ተከፍቶ ስለ ወንጌል እውነት የሰማ ሰው ነው። ጸሎት ቤት እንደገባን አንድ ስልክ ተደወለልኝና ወጣ ብዬ አናገርኩ አንድ እህታችን አዲስ ሰው ወደ እኔ ልትልክ ፈልጋ ስለነበር ይህንኑ ለማስታወቅ ነው። በሰጠሁት ቁጥር መሠረት በነጋታው ተደወለልኝ። ሄሎ! ሐናን እባላለሁ አለች አንድ ሴት ..ተቀጣጠርንና ስልኩን ዘጋሁ። የቀጠሮአችን ቀን ዛሬ ሐሙስ ይህንን በምጽፍበት ቀን ላይ ነበር። ሐናን ቤተክርስቲያን ድረስ መጣች የዛሬ ሰባት ወር ገደማ ከሆነው ታሪክ ጀመረችልኝ። አንድም ክርስቲያን ከሌለበት ቤተስብ ነው የተወለደችው ኦርቶዶክስ እምነት የሚከተል ሰው ጋር ተጋብታ ልጆች ወልደው በአሜሪካን አገር መኖር ከጀመሩ ጥቂት ዓመታት አልፈዋል። አንድ ቀን በህልሟ ያየችውን አጫወተችኝ የመጨረሻ ሰዓት ይመስለኛል ጠቅላላ ጀለቢያ የለበሱ እና የጠመጠሙ ሰዎች በቅጽበት መሬት በትልቁ ተከፍቶ ሲገቡ አየኋቸው እኔ ምንም የለበስኩት ነገር አልነበረም፤ የቆምኩባት ቦታ ትንሽዬ አራት መዐዘን ቀርታለች። አትፈርስም፤ አትደረመስም ከሰማይ ልናገር የማልችለው አንድ ጣት ወደ እኔ እየጠቆመች ወፈር ያለ ግርማ ሞገስ ባለው ድምጽ አንድ የማላየው ሰው ለእኔ ተናገረ፤ አንቺን ግን ምሬሻለሁ! አለኝ አለች። ባነንኩ ህልም ነው ብዬ ራሴን ለማሳመንና ነገሩን እምብዛም ክብደት ላለመስጠት በጣሙን ጣርኩ። ይሁንና እየባሰ መጣ እንጂ እንዳሰብኩት ቀለል ማድረግ አልቻልኩም። ሁለት ሦስት ህልም ከዚያ በኋላ አየሁ...ለባሌ ሳማክረው በቤተሰቤ ካገኘሁት እምነት ወጥቼ ወደ እርሱ እንድጠቀለል መከረኝ። ለተግባራዊነቱም ተንቀሳቀስኩ፤ ተምሬ ስጨርስ ልቤ አልሞላ አለኝ! አንድ ትልቅ ክፍተት ይሰማኛል አለች። በህልም ማየት የጀመርኩትም ጉዳይ ቀጥሏል። መዝሙር ለመስማት እሞክራለሁ እጅግ አያለቀስኩ ራሴን አገኛለሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ የሚል ጽሁፍ ከመኪና ላይ ተለጥፎ እንኳ አይቼ አለቅሳለሁ። በቃ አብጄ ነው..ያገሩ እብደት ሲጀምር እንዲህ ነው ብዬ ከአንዴም ሁለቴ ደመደምኩ ግን ነገሩ እንደዚያ አይደለም። ያጣሁትና የጎደለኝ አንድ ነገር አለ! እምላክ እያሳየኝ ያለ አንድ የእውነት መንገድ አለ...አንድ እዚህ ምድር የማውቃት ወጣት ጋር ደውዬ እርሷ የምትሄድበት ቤ/ክ እንድትወስደኝ ለመንኳት አለች፤ እርሷም ወደ አንተ መራችኝ፤ እነሆ ዛሬ መጣሁ አለች። ጌታ እራሱ እየመሰከረላት እየሰማሁ የንስሃ ጸሎትን እንኳ ቆሜ መምራት ስላቃተኝ ተንበርክኬ ፡እኔ ከምልሽ ቀጥለሽ በማለት ክርስቶስን የህይወትሽ አዳኝ ና ጌታ አድርገሽ ትቀበያለሽ? አልኳት በደስታ  ተቀበለች። ጸሎት ጨርሰን እንኳን ደስ አለሽ ብዬ ፊቷን ስመለከት ፊቷ በማያቋርጥ እንባ ታጥቧል። ጌታ ራሱ የነካት ሴት! ከእርሷ ከተለየሁ በኋላ ለምን ወደ እኛ እንደመጣች ሳጤን ያገኘሁት  የሐሥ 12 ጴጥሮስ ሊገደልበት ከነበረው እስር ቤት መልዐክ ተልኮለት በተዓምር ከወጣ በኌላ ወዲያው የሄደው ሰዎች ተከማችተው ይጸልዩበት ወደ ነበሩበት ቤት ነው። እነርሱ ሰለጴጥሮ መፈታት እየጸለዩ ነበርና ጌታ ጴጥሮስን ወደዚያ ጸሎት ቤት አመጣው። ሰሞኑን ለብዙዎች መፈታት ምክንያት የሆነ ሪቫይቫል እንዲመጣ እየጸለይን ነውና ይህ መሆኑ እምብዛም አያስገርምም። ሌላ ምስክርነት ይቀጥላል.....
የጌታ ጸጋ ይብዛ

< Let us be witnesses for Christ! >

ቤተሰቦቻችን በሪቫይቫሉ ውስጥ..!

ቤተሰቦቻችን በሪቫይቫሉ ውስጥ..!

በ ኦገስት 30/2018 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝ ስለተቀበሉ አባቷ አንዲት በመካከላችን ያለች እህታችን እንዲህ ስትል መስክራለች። አባቴ በጣም አክራሪ ኦርቶዶክስ ተከታይ ነው። ብሎም በአንድ ደብር ውስጥ የሰንበቴ ጸሃፊ ሆኖ ያገለግላል። ላልዳኑ ቤተሰቦቼ ሸክም ስላለኝ ብጸልይም በቀላሉ ልባቸው የማይረታ በመሆናቸው ግን ተስፋ ያስቆርጠኛል። ይሁንና አንድ ቀን በአዲስ ልደት ቤ/ክ የሐሙስ የጾም ጸሎት ፕሮግራም ላይ እንደ ልማዴ ልጸልይ ከቤቴ ገስግሼ መጣሁ። በዚያን ቀን በልቤ ያለው ትልቅ ሸክም አባቴ ከ4ት ቀናት በኋላ በ08/27/2018 ሆስፒታል የኦፕራሲዮን ቀጠሮ ስለያዘ፤ የሚፈጠረው አይታወቅምና ጌታን እንዲያገኝ አጥብቄ ልጸልይ ወስኛለሁ። ገና ጉባኤው ውስጥ ስገባ በመንፈስ የተጋጋለ ጸሎት ተቀበለኝ። ...ጆሮዬ ውስጥ ስላልዳኑ ቤተሰቦቻችን እንጸልይ፣ እንናጠቃቸው! እያሉ ጉባኤው  ምልጃም... የተቃውሞም ጸሎትም እያደረገ ነበር።  በመንፈስ ቅዱስ አሠራር ተገርሜ እኔም ቤተስቤን በኃይል እየተናጠቅኩ መጸለዬን ቀጠልኩ። በተለይም ስለ አባቴ ! የዛሬ አንገብጋቢው ርዕሴ ነውና። ጸሎቱ አልቆ ከሰዓት በኋላ  ወደ ጉዳዬ ሄድኩ። ከሶስት ቀናት በኋላ አባቴ ሰርጀሪ ሊያደርግ ሆስፒታል ገባ! ዶክተሩ ክርስቲያን ነበርና ሰርጀሪውን ከመጀመሩ በፊት ተንበርክኮ ጸለየ አለች።  እግዚአብሔር ይመስገን ከሰዓታት በኋላ.. በሰላም ተጠናቆ ወደ ማገገሚያ ክፍሉ ገባ ። ክርስቲያን የሆኑ ነርሶች በየ ክፍሉ እየዞሩ ለበሽተኛ የመጸለይ፣ የተጎዳን የማጽናናት ልማድ አላቸው። ከሰርጀሪው በፊት  አባቴ የተኛበት ክፍል ገብተው "አባባ እንጸልይልዎት? ብለዋቸው  አባቷ " እኔ ኦርቶዶክስ ስለሆንኩ አልፈልግም! " ብለው ነበር። ከ3ት ቀናት በኋላ ግን በ08/30/2018 አባቷ በክርስቲያን ዶክተሩና በነርሶቹ በተደረገላቸው እንክብካቤ ልባቸው ተንክቶ ኖሯልና ነርሶች ድጋሜ ሊጠይቁ ወደ ክፍላቸው ሲገቡ የጠበቃቸው ፊትና ምላሽ እንደፊተኛው አልነበረም። አባባ የእግዚአብሔርን ቃል እናካፍልዎ? እንጸልይልዎ?  አዎ አሉ አባባ! በዚያች ዕለት በደስታ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ የህይወቴ አዳኝ ነው ብለው መሠከሩ! በሰማይም ታላቅ ደስታ ሆነ! ለአባቷ ጾም ጸሎት ይዛ በ08/23/2018 የጸለየችውም እህት ደስታ አሠከራት! በሐሙስ ጉባኤ ፊት በደስታ ሲቃ ቆማ የጌታን ስራ መሰከረች። ክብር ለእግዚአብሔር ይሁን!  ሃሌ ሉያ!!! ወገኖች ለቤተሰቦቻችን መጸለይና መመስከርን አንርሳ! ይቀጥላል....

<< Let us be witnesses for Christ!>>

በመገኘቱ ውስጥ..!

በመገኘቱ ውስጥ..!

ዕለቱ ዓርብ ምሽት በቤ/ክያናችን የአዳር ጸሎት እየተካሄደ ነበር መንፈስ ቅዱስ በለሆሳስ ሽው! ሽው እንደሚል ነፋስ በጉባኤው ላይ ሲነፍስ ይሰማል። እዚህም እዚያም ጩኽት አለ ግንባራቸውን መሬት አስነክተው ድፍት ብለው የሚጸልዩ፣ ደግሞ ወዲህና ወዲያ ጎርደድ ጎርደድ እያሉ የሚጸልዩ ወጣት ጎልማሶች ፣ ሹል ክ ብለው መጥተው በትግርኛ ጮክ ብለው የሚጸልዩ ጥቂት ኤርትራውያንም በመካከላችን አሉ፤(ትውልድ የሚወለድበት ቤትም አይደል! Delivery room ውስጥ ጩኽት አመሉ ነው ይላሉ፤ ጩኽት ካልፈለክ semitary ሂድ ብሏል አሉ አንድ የእግዚአብሔር ሰው፤( መቃብር ቦታ ማለቱ ነው።)  ሙሉ ቤተሰቡን ይዘው ጥግትግት ብለው የሚጸልዩም አሉ ትናንሽ ልጆቻቸውም ሳይቀሩ ማለቴ ነው። መቼም እነዚህ ወላጆች  ልጆቻቸው ላይ እያደረጉት ያሉት አስተዋጽኦ ኣሌ የማይባል ነው። "ልጅን በሚሄድበት መንገድ ምራው በሸመገለ ጊዜ ከእርሱም ፈቀቅ አይልም" ይል የለ መጽሐፍ! በእነዚሁ የምሽት ጸሎቶች ላይ በመሃል መስመር 2ኛ መደዳ ላይ በጉልበቷ ተንበርክካ፡ አልያም በሆዷ ተኝታ የመጸለይ ልማድ ያላት ከሁለት ትንንሽ ልጆቿ ጋር መጥታ የምትጸልይ እህት አለች።ልጇ ህመም የጀመራት ገና የ3 ወር ህጻን ሳለች ነበር እስከ 4 ዓመቷ ድረስም በመታመሟ በርካታ ዶላሮችን ለመድኃኒት፣ለህክምና ጨርሳለች ። በጣም ውድ የሚባሉ መድኅኒቶችን በየጊዜው ትወስዳለች።  የህመሙ ዓይነት ኤር ዌይ ዲዝዝስ (air way diseases) ይባላል። አተነፋፈስ ላይ ያለ ከፍተኛ ችግር ነው ፤ ህመሙ ሽቶ፣ የቡና፣የምግብ..ወዘተ ሽታዎችን የማይወድ በመሆኑ ቤት ውስጥ እነዚህ ነገሮች መጠቀም ለረጅም ጊዜ አዳግቷል። ሰው ቤት  ወይም ቤ/ክ መሄድ ከዚህ ጋር ተያይዞ ባለ ችግር ምክንያት ነጻነታቸው ተነፍጎ የኖሩ ቤተሰቦች ናቸው። እስከመቼ? የሚልጥያቄ አላት።.. ጸሎትን የሚሰማ አምላክ አንድ ምሽት ልመናዋን ሰምቶ ፈረደላት፤ መንፈስ ቅዱስ ልጇን በፈውስ ሲጎበኝ በቅርብ ሆኜ አይቻለሁ ። በዚያን ምሽት ቮሚት  አደረገች ለዓመታት ያስቃያት ህመም ንቅል ብሎ ጠፋ! ይህ ከሆነ ይኽው ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት ሞላው። ሽቶ፣ የምግብ፣ የቡና ሽታ የሚባል ችግር ታሪክ ሆኗል። ...ጌታ ስለሰራላት ነገር በጉባኤ ፊት ቀርባ ስትመሰክር እንዲህ አለች፡ "መንፈስ ቅዱስ በመካከላችሁ በኅይል እየሰራ ነው፤ እናንተ ግን  አልተዘጋጃችሁም!"  ይህን ያለችው ፈውስ ይኖራል ብለን ... አንዳንድ ዕቃዎችን ገዝተን ባለማስቀመጣችን ነበር። ..  አዎ! በየሐሙሱና ዓርብ የሚፈወሰው ሰው ቁጥር እየጨመረ ነው፤  ጌታ በመካከላችን እየሰራ ነው። የሚበልጠውም ነገር ገና ከፊት አለ! በዚህች እህት ቤት ሌላም የሆነ ተዐምር አለ፤ ነገሩ እንዲህ ነው፡ ከዕለታት አንድ ቀን ባለቤቷ የአባቱን ሞት መርዶ ሰምቶ እቤት ተቀምጧል!ተብለን የቤ/ክ አገልጋዮች ተጠራርተን ቤቷ ሄድን፤ በእርግጥ በሰዐቱ ባለቤቷ ቤት ውስጥ አልነበረም፤  ነገር ግን ለቅሶ ሊደርሱ የመጡ ሌሎች ሰዎች ስለነበሩ ከእነርሱ ጋር  ተዋወቅን፤በተለይ አንደኛዋ ክርር ያለ ሙስሊም ባግራውንድ የነበራት ሴት ነች። ሳዑዲ ድረስ በመሄድ እስልምናን የሚያጸኑ አንዳንድ ስርዓቶችን የፈጸመች....ይሁንና ስለክርስቶስ ተመሰከረላት ልቧ ተነካ፤ በስጋ ያላት ሃብቷ ወይም የቤተሰብጉዳይ አልያዟትም፤ብዙ ነገሮችን  ቤቷ ጠርታ አስረከበችን። ህይወቷ ተለወጠ! በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም ጌታ ያዘዘውን ጥምቀት ተጠምቀች፤.. አሁንማ ሌሎች ወደ ጌታ እንዲመጡ ተግታ እየሰራች ነው...ስለ ጌታ ፍቅር ስትናገር "ብዙ ነገሬ የተቀረፈበትን የቤ/ክ ን የጾም ጸሎት ቀን መቅረት እንዴት ይሆንልኛል? ትላለች። ሁላችን የእግዚአብሔርን ፊት ሁልጊዜ ብንሻ አንድ ቀን ከመልሳችን ጋር ወደ ቤታችን እንመለሳለን። ዳዊት " ቆይቼ እግዚአብሔርን ደጅ ጠናሁት እርሱም ዘምበል አለልኝ፡፡" እንዳለ እኛም ፊቱን በመፈለግ እንትጋ!  በመካከላችን በኃይል እየሰራች ያለችውን የእግዚአብሔርን ጣት እንናፍቅ!  እንምጣና በመገኘቱ ውስጥ እንሁን!! ሪቫይቫል ይቀጥላል....

<<Let us be witnesses for Christ!>>
     

ደብተራን የሚያድን ጌታ!

ደብተራን የሚያድን ጌታ!

በቅርቡ ነው ዩትዩብ ከፍቼ አንድ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ማይክራፎን በእጁ ይዞ። ያለ ምስል ከፊት ለፊት ገጽ ላይ  አየሁ ፤ ሁለት ጊዜ ገጹን ስጫን ከፈተልኝ ፤ አጠር ካለ ማስታወቂያ በኋላ አንድ ከጥቂት ዓመታት በፊት የማውቀው ሰው ለጉባኤ ምስክርነቱን እየሰጠ ይታያል። ምስክርነቱ እንደዚህ ነው ተቀጥሮ በሚሰራበት NGO ድርጅት ለስራ ወደ አንድ ራቅ ያለ ቦታ ሲጓዙ...  በጣም ረጅም ከሆነ ገደል ውስጥ እርሱንም ይሁን ይዟቸው ይጓዝ የነበሩ የውስጥና የውጭ አገር ሰዎችን ጌታ በተዓምር እንዴት እንዳተረፋቸው ተናግሮ ጌታን ከጉባኤው ግልር እያመሰገነ ነበር። ከዚህ ሰው ጋር ከ10 ዓመት በፊት አዲስ አበባ ውስጥ ከሳሪስ ወደ ስታዲየም የሚሄድ ታክሲ ውስጥ በጋቢናው በኩል ተሳፍሬ ስጓዝ ነበር የተዋወቅነው፤ በወቅቱ ሲጃራ ያጨስ ነበር፣ የሲዲ ማጫወቻው ደግሞ መዝሙር ይዘምራል ፤ በእኔና በሹፌሩ በኩል የነበረ ተሳፋሪ በመሃል እንደወረደ እኔ ወደ ሹፌሩ በኩል ወደቀረበው ጠበብ ያለች የመሃል ወንበር ፎቀቅ አልኩ...እናም "ወንድም! መዝሙሩና ሲጃራው እኮ አይሄድም! ከሚል አስተያየት ንግግሬን ጀመርኩ ...እንድ ሁለት እየተባባልን፣ እያወጋን ተጉዘን የምወርድበት ቦታ ከመድረሱ በፊት አድራሻ- ማለቴ ስልክ ተቀያየርን ፤ ስማችንን እርስ በርስ ተዋወቅን..ሄኖክ እባላለሁ አለኝ ..። ሁለት ወር ያህል አልተገናኘንም ምክንያቱ ደግሞ የእርሱ ስልክ አይሰራም ነበር፤ አንድ ቀን ግን ነግሬው በነበረ አድራሻ ፈልጎ በር አንኳኳ ..ተገናኘን.. ጸሎት ቤት አስገብቼ ጥቂት የሆድ የሆዳችንን አወጋን...በአጭሩ ከአጋንንት ጋር ተባብሮ የሚሰራ፣ብዙዎችን በጥንቆላ ያሳተ፤ በድግምት ለሃብታሞች የሚመትት፤ እንደነገረኝ መተት ሰርቶላቸው ውጭ አገር የሄዱ፣ ንግድ የሰመረላቸው፣ የሚዘፍኑ፣ የሚሮጡ..ምን ልበላችሁ ሁሉ ነገር ከተማ ውስጥ ንጹህ አይመስልም! ተነካክቷል። አንዳንዶቹ ከውጭ አገር በሚልኩት ገንዘብ ሁለት ሚኒባስ ገዝቷል። አንዱ እኔ ባለፈው ዕለት የተሳፈርኩበት መሆኑ ነው...የጥንቆላው መንፈስ የተወራረሰው ...ገዳም ውስጥ ነው። አባቱም ድግምት የሚሰሩ ደብተራ እንደሆኑ ነግሮኛል። ሁለት ልጆችና ...ሌላ አንድ ልጅ አለው፤ ለሁሉም ኃላፊነት አለበት። ማለቴ ወጪዎች አሉበት።...ብዙ ከሰማሁት በኋላ ቃል ክርስቶስ ኢየሱስ ከዚህ ሁሉ ነጻ ሊያወጣህ ይችላል! ዛሬ ራስህን ወደህ ትሰጠዋለህ ወይ? አልኩት። እፈራለሁ!  ኪዳን ከአጋንንት ጋር ስለገባሁ ይገድለኛል አለኝ፤ ጌታ ኢየሱስ ነው የሚበልጠው አይገድልህም! አልኩት...እሺ ብሎ ጌታን እንደ ግል አዳኙ አድርጎ ተቀበለ..ንስሐ ገባ። ክፉ መንፈስም ጮሆ ወዲያው ከእርሱ ወጣ ፤የቀረም ነበር ለካ ..ሌላ ጊዜ በህብረት ጸሎት መካከል ራሱን ገልጦ ከእርሱ ጮሆ ወጣ። ብዙ ትግሎች አሳልፎ፣ ደህንነት ትምህርት ጨርሶ፣ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም የውሐ ጥምቀትን ወሰደ። ይኽው ስንት ዓመት ጌታ ተሸክሞት...እኔ ከአገር ብወጣም ጌታ ከእርሱ ጋር ሆኖ ከክፉ ሁሉ እያዳነው መሆኑን ዩትዩብ ያለሁበት ድረስ ምስክረነትን ይዞልኝ መጣ። ለሰዎች ከመሰከርን በኋላ ለመንፈስ ቅዱስ አሳልፎ መስጠት ያለውን የላቀ ትርፍ አይቻለሁ። ሰዎች ምንም ያህል እስራት ውስጥ ቢሆኑ ጌታ ነጻ ሊያወጣቸው ይችላል። ለማንኛውም ሰው  ከመሰከራችሁ በኋላ ማድረግ የሚገባችሁን ብቻ እያደረጋችሁ ቀሪውን ለመንፈስ ቅዱስ ተውለት። ውጤቱን ታያላችሁ!  ጌታ ይባርካችሁ ይቀጥላል…
   <<Let us be witnesses for Christ!>>
          benjabef@gmail.com

በቤሩት-ሊባኖን የተፈጸመ!

በቤሩት-ሊባኖን የተፈጸመ!
    ******************
  የእግዚአብሔር ቃል "ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤" ማር.16፡15 እንደሚል፤  የዳነችበትንና የገባትን ወንጌል በዓረብ አገር ላገኘቻቸው አንድ ቤተሰብ ስትመሰክር ስለገጠማት አስደናቂ ነገር እህታችን ነጻነት ተከታዩን ታሪክ አጫውታኛለች:-

እ.ኤ.አ. 1997  በኤጀንሲዎች በኩል ተቀጥሬ ለሥር ወደ አረብ አገር ለመሄድ ተነሳሁ። ለመብረር ሁለት ቀን ሲቀረኝ ...አንድ አገልጋይ አገኝኝና ሲጸልይልኝ  እንዲህ የሚል መልዕክት ተናገረኝ " እህቴ ሆይ የምትሄጅው ለወንጌል አገልግሎት ነው! በዚያ ለስሜ ትመሰክሪያለሽ! ይልሻል፤" የሚል ነበር፤ አገሩ ቤሩት -ሊባኖን ይባላል፤ የተቀጠርኩበት ቤተሰብ በቁጥር 7ት ያህል ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 4ቱ ልጆች ፣ እናትና አባትን ጨምሮ አያታቸው (የሰውየው እናትም) አንድ ላይ ነበሩ። ከ4ቱ ልጆች 3ቱ ዩንቨርስቲ የተመረቁ ሲሆኑ አንድ ልጅ ብቻ ገና በትምህርት ላይ ነበረ።

ቤተሰቡ የካቶሊክ አማኝ ቢሆኑም ያን የሚያህል አጥባቂ አይደሉም፤ እንደውም በቤታቸው ፊት ለፊት አንድ ወፍራም ዛፍ አለ፤ አጠገቡም  በመስታወት የተከበበ ሻርቤል ተብሎ የሚጠራ ጣኦት ፤ በየጊዜውም ልዩ ልዩ ስጦታዎች የሚቀርቡለት  ነበር። ....እንደሄድኩ ሰሞን በር እየቆለፉብኝ ተቸግሬ ነበር፤ ስለዚህም በጥንቃቄ ነበር የምኖረው፤ እኔ እንደገባኝ ስጋታቸው  ጠፍታ ሌላ ቦታ ትሄድብናለች ! የሚል ጥርጣሬ ነው፤ ወደ ዓረብ አገር እንደዚህ  ተቀጥረው የሚሄዱ ሰራተኞች ባልተመቻቸው በማንኛውም ሰዓት ጠፍተው ይወጡና  በሌላ ደላላ ሌሎች ቦታዎች ላይ የመቀጠር ልማድ አለ። እኔ ትንሽ ተስፋ ልሰጣቸው ሞከርኩ! ...አይዞአችሁ እኔ ክርስቲያን ነኝ! የትም  ሄጄ አልጠፋባችሁም፤ ብዬ ላረጋጋቸው ሞከርኩ፤ ማዳም አለፍ አለፍ ብላ ጥያቄ ትጠይቀኝ ነበር ...ስለላ ቢጤ  መሰለኝ! ስለ እኔ ማንነት የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለች፤ ይሁንና በደፈናው ክርስቲያን ነኝ! ከማለት ውጪ ስለ አማኝነቴ በዚህ ፍጥነት ለማስታወቅ አልፈለኩም ነበር። ስራዬን በትክክል እሰራለሁ፣ ጌታን በሕይወቴ ለማሳየት እጥራለሁ፤ በቃ ከዚያ ጌታ የፈቀደው ይሆናል፤...  አየሩንም ሆነ የቤተሰቡን ሁኔታ በተወሰነ መልክ እየተላመድኩ መጣሁ፤ ... እስትንፋሴ እስካለች ድረስ መቼም ቢሆን የትም፣ ከምንም ነገር በላይ ማስረዳትና  መናገር የምፈልገው አንድ ብርቱ ዜና አለ! ይኽውም የዳንኩበት የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል ጉዳይ ነው። እናም እግዚአብሔር ዕድሉን ሰጠኝና ወንጌልን በዓረብ አገር ሁሉ ተዘዋውሬ ባልሰብክ እንኳ፤ ቢያንስ ባለሁበት ቤት ውስጥ ግን ምስክርነቴን መጀመር እንዳለብኝ ገብቶኝ የአቅሜን አድርጌያለሁ።

የዳንክበትን ወንጌል የትስ ቢሆን እንዴት ልትደብቅ ትችላለህ?... አንድ ቀን ቤቱን እያስተካከልኩ ሳለ የአረብኛ መጽሐፍ ቅዱስ አየሁ፤ እርሱን መነሻ አድርጌ ውስጤ የታፈነውን ምስክርነት የምጀምርበት  ሆነኝ! ልጆቹን ይሄ ምንድን ነው? አልኳቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ነው! ብለው መለሱልኝ፤ ታዲያ ለምንድን ነው? ስታነብቡት የማላያችሁ? ብታንነቡት እኮ መልካም ነው! ማንም አንዳች አልመለሱልኝም። ጥቂት ግፊት ማድረግ ጀመርኩና ማታ ማታ አብረን ማንበብ ጀመርን፤ እነርሱ አረብኛውን ማንበብ ይችላሉ፤ እኔ ደግሞ አማርኛውንና እንግሊዘኛውን ቨርዥን እያፈራረቅኩ አነባለሁ፤ በንባባችን እየገፋንበት መጣን፤ በተለይም አንደኛዋ ልጅ በደንብ እየወደደችው መጣች። የልጅቷ ስም ሞንያ ነው።

  ሁለተኛ ጊዜ ለቤተሰቡ ስለ ወንጌል የምናገርበት  ሌላ ዕድል ተፈጠረ፤ ነገሩ እንደዚህ ነው፤ ማዳም አንድ ቀን ጠዋት የጣኦት ቤቱን ሄጄ አዋራውን እንዳጸዳ ትዕዛዝ ሰጠችኝ፤ እኔም ውስጤ በኃይል ተቆጥቶ አላደርገውም! አልኳት፤ ማዳምም ለምንድን ነው? የምልሽን የማትታዘዢኝ? አለችኝ። በዚያ ጊዜ ልትመታኝ ትችል ነበር፤ እኔም በወቅቱ ይህን ግምት ውስጥ አላስገባሁም ነበር።  እናም መለስኩላት  መጽሐፍ ቅዱስ አምጥቼ ዘዳግም 5 ላይ ያለውን ቃል አነበብኩላት ፤ እርሷ የተማረች ነርስ ናት፤ ቢሆንም የመንፈሳዊ እውቀት ግን አልነበራትም።  ቃሉን አምጥቼ አነበብኩላት እንዲህ ይላል "በላይ በሰማይ ካለው በታችም በምድር ካለው ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ ፤...አትስገድላቸው! አታምልካቸውም።" ዘዳ.5:8-10። ስለዚህ  እግዚአብሔር ጣኦትን ይጠላል! አልኳት። ለጊዜው መልስ አልሰጠችኝም። ሞንያ ግን ይህ ያነበብሽው እኮ የድሮ /የብሉይ ኪዳን/ ህግ ነው! አሁን ሊሰራ አይችልም! አለችኝ። እኔም" ዓይን ስለ ዓይን ፣ ጥርስም ስለ ጥርስ " (ምናልባት ጥርስህን ለሚያወልቅህ ጥርሱን አውልቀው! እንደማለት ነው) የሚለው ነው ተሽሮ አንድ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን አዙርለት፣...አንድ ምዕራፍ ለሚጠይቅህ ሁለት ምዕራፍ አድርግለት፣..(ማቴ.5፡38-42) ፤ ...እንዲህም ስለሚመስል ነገር እንጂ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ፤ ወይም አትስረቅ፣ አታመንዝር! የሚሉት ትዕዛዛት  ለዘላለም የማይሻሩ ናቸው! ብዬ አስረዳኋት። አሃ..! አለችና ጭንቅላቷን ነቅንቃ ጥቂት ዝም አለች ፤ ሲመስለኝ ቃሉን እየተረዳች ነው፤ እግዚአብሔርም በልጅቷ ህይወት ውስጥ አንድ የሆነ ዓላማ ያለውም ይመስለኛል ። ብዙ ጊዜ ስራዬን በጊዜ ጨራርሼ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብ የበለጠ ፍላጎት ስላሳየችኝ ይህንን ለማድረግ ተጋሁ። ...በተለይ ወንጌልን በደንብ አድርጋ ነው የተማረችው፤ ጥቅስ አወጥተን እናነባለን ፤...እያንዳንዱ ታሪክ ይመስጣል፣ ህይወት ሰጪው ቃል በየማታው በውስጧ ይንቆረቆራል።

  ነገሩ በእንደዚህ ሁኔታ እየቀጠለ ሳለ አንድ ቀን ቤተሰቧ ከካናዳ የመጣ ባል አዘጋጅተውላት ነበረና ከመቅጽበት እቤት ውስጥ ወሬው ሁሉ እርሱ ሆነ፤ እኔ በጣም ተጨነቅኩ! ጠላት ይህን ሰበብ ፈጥሮ ከኔ ሊለያት ነው አልኩ፤ እስካሁን የለፋሁበትም ገደል ሊገባ ነው ? ብዬ መጸለይ ጀመርኩ፤ ሰውየው ሃብታም ቢጤ ነው ሲባል ስምቻለሁ፤ ያው ደግሞ ዘመዳቸው ነው፤ በባህላቸው መሠረት ሊባኖናውያን ከአክስትና ከአጎት ልጅ ጭምር ጋር እርስ በርስ ጋብቻሞች መሆን ይችላሉ መሰለኝ። ሰውየው አንድ ምሽት ላይ ጠቅላላ ቤተሰቡን እራት ሊጋብዝ ነው ተብሎ ተለቅ ወዳለ ስመጥር ሆቴል ለመሄድ ሲዘጋጁ ሳለ እኔም   እንድዘጋጅና አብሬያቸው እንድሄድ ተነገረኝ። እኔ ግን እራሴን አሞኛል! በሚል ሰበብ እንደማልሄድ ገለጥኩላቸው። ለነገሩስ የሞንያ ነገር ስላሳዘነኝ ጌታ ጣልቃ እንዲገባ ለመጸለይ አስቤ እንጂ አሞኝ አልነበረም የቀረሁት። ሞንያ ወደ እራት ስፍራ ከመሄዷ በፊት ወደ እኔ መጥታ <..ግን ምን ይመስልሻል?> አለችኝ። ውሳኔው የራስሽ ቢሆንም በፍጹም የማያምን ሰው ጋር  መጋባት ግን አለብሽ ብዬ አላምንም! አንቺ ማግባት ያለብሽ እንዳንቺ ክርስቶስን የሚያምን ክርስቲያንን ነው...።  ሁሉም ተከታትለው ሲሄዱ እኔ ተንበርክኬ መጸለይ ጀመርኩ፤ ከሰዓታት በኋላ ሞንያ ብቻዋን በመኪናዋ ወደ ቤቷ መጣች፤ ..ብዙ ነገር አላስደሰታትም መሠለኝ! እራት ብቻ በልታ፥ ጭፈራ ስትጋበዝ አምልጣ ነው የመጣችው፤ ቤተሰቡ ገና አልመጣም። ሰውየው ተናዷል አሉ! ቤተሰቦቿም በልጃቸው ድርጊት ተበሳጭተው ፊታቸው ፍም መስሎ ነው የተመለሱት። በቃ እልወደደችውም! ጌታ ጣልቃ የገባ ነው የሚመስለኝ! ትላለች ነጻነት።

እነ ሞንያ ቤት ከገባሁበት ጊዜ አንስቶ የሚረብሸኝ ሌላው ነገር ቅጥ የሌለው የዘፈን ድምጽ ነው፤ ሞንያ በጣም ነበር ዘፈን የምትወደው፤ ስትዘፍን፣ ስትደንስ" ነፍሷንም አታውቅ" ነበር። ዛሬ አልጨፍርም! ብላ ንቃ መጣች! እቤት ውስጥም ቢሆን ጸጥታ ሰፍኗል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ቤተሰቡን አሳስቦታል። ይህች ልጅ ምን ሆና ነው የተቀየረችው? ይባባላሉ፤ በማናቸውም ሰዓት ያን ለብዙ ጊዜ ዝም ብሎ የተቀመጠ መጽሐፍ ስታንብ ነው የምትታየው። <ከነጻነትና ከዚህ መጽሐፍ ራስ ላይ አንወርድም!> የተባባሉ ይመስላል። ምክንያቱም እኔ ላይ ፊታቸውም ሆነ ቃላታቸው ተለውጧል። ትንሽ መፍራት ጀመርኩ!  ከአገራቸው  እንኳ ሊያስባርሩኝ ይችላሉ ብዬ ሰጋሁ። በተለይ በተለይ ግን በዚህ ሁኔታ ከሞንያ ጋር እንዳያለያዩን ነው ዋናው ስጋቴ። ሁሉም ሰው ልጅቷን ያበላሸችው ነጻነት ነች! ሲባል እየሰማሁ ነበር። ወይ ዓለም! ዘፈን፣ ጭፈራ፣ ስካር፣ ዝሙት ..መተውን <መበላሸት!> ብለው ነው የሚገልጹት፤ የሚጠቀሙበት ዲክሽነሪ ምን ዓይነት ነበር..?! ይገርማል!

የሆነ ቀን ቤተሰቡ አንድ ከባድ ውሳኔ ወሰነ፤ ውሳኔው ሞንያና እኔ በምንም መንገድ  አብረን እንዳንገናኝ ነበር ። አንዳንድ ጊዜ <ኪችን> ስንገናኝ ከቤተሰቡ መካከል አንዳቸው ይመጣሉ፤ በመሃላችን ይገቡና ይለያዩናል፤ እርሷም ወደ ሌላ ክፍል ትሄዳለች። ስለዚህ ሞኒያ ዘዴ ዘየደች። ዘዴውም እንዲህ ነው፤ ሁሉም ከተኙ በኋላ በሌሊት ከክፍሏ ወጥታ ወደ እኔ ትንሽ ክፍል ትመጣለች፤ የተወሰነ ሰዓት የእኔን ጋቢ ትለብስና ታጣፊ አልጋዬ ጥግ ትንበረከክና አብረን እንጸልያለን። ጥቂት ጊዜ በዚህ ሁኔታ እያሳለፍን....፤ አንድ ቀን ልዩ ነገር ሆነ፤ ሞንያ በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች! በልሳን መናገር ጀመረች! እኔ ደስታዬ ወደር አልነበረውም፤ እርሷ ግን ምን ሆኜ ነው? ብላ ስትደነግጥ፤ ስለ መንፈስ ቅዱስ አሰራር ከቃሉ ላይ አስረዳኋትና ተደነቀች። ከዚያ በኋላ ባሰባት! በተገናኘን ቁጥር እንጸልይ ብቻ ነው የምትለው።

በ15 ቀን አንድ ጊዜ እረፍቴ በመሆኑ ከቤት ውጥቼ አንዳንድ ቦታ እሄድ ነበር። በእርግጥ ብዙ ጊዜ የምሄደውና የማልቀርበት ቦታ ቤተክርስቲያን ነው። የምታደርሰኝ ደግሞ ሞንያ ነች። ብዙ ጊዜ እኔን ቸርች አድርሳኝ እርሷ ትመለስ ነበር። አሁን ደግሞ ያ ቀርቶ፥ አብራኝ ገብታ በአበሾች መካከል ፥ ቋንቋው ባይገባትም በእማርኛ ዘምራ ፣ አምልካ መውጣት ጀመረች። ሌላ ጊዜ ደግሞ እየሆነ ያለውን ታሪክ ያጫወትኳት አንዲት አበሻ እህት ጥቂት የዳኑ አረቦች ተሰባስበው የሚጸልዩበትን ቦታ ጠቆመችንና ወደዚያ ሄድን። ...ይህማ ቋንቋዋ ነው፤ በአረብኛ ቃል ሰማች፤ ጌታን አመለከች....ደስ አላት፤ የአገሯን ሰዎች አገኘች። ከዚያ ስትመለስ እቤት ውስጥ በግልጽ መመስከር ጀመረች! ፍርሃት ቀረ!

የዚህ ሁሉ ምክንያት ነጻነት ነች! ተብዬ ቤተሰቡ የበለጠ ስለጠመደኝ፥ አትገናኙ የሚለው ህጋቸው እስካሁን አለ። ይሁንና ለቃል ረሃብተኛዋ ልጅ በኪሴ ጥቅስ እይዝና ወደ ማዕድ ቤት/Kitchen / እሄዳለሁ ፤ ቀስ ብላ ትመጣና ጥቅሱን እንቀባበላለን ፤ በዚህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበች ትውላለች፣ ታመሻለች። ከጊዜ በኋላ -ነገሩ በጣም እየከረረ ሲሄድ ከቤታቸው እንድወጣ ተፈረደብኝ። አንድ ቀን ቸርች ደርሼ ስመጣ ግቢው ውስጥ ጠቅላላው ቤተሰብና ጎረቤት ተሰባስበዋል፤ እንደገባሁ በይ! "ልብስሽን ያዢና ውልቅ በይ!" ተባልኩ። ያን ጊዜ የት እንደምሄድም አላውቅም፤ በመካከላቸው ሞንያን አላያትም፤ የት ሄዳ ይሆን? አልኩ በልቤ፤ በኋላ ስሰማ ክፍሏ ውስጥ ነበረች። እንዴት ወደ ውጭ  እንደወጣች አላውቅም፤ ከደቂቃዎች በኋላ ወደ ስብስቡ ቀረበች!...አለቀሰች! እኔ ሻንጣዬን ይዤ-- ፣ ታናሽ እህቴም አጠገቤ ነበርች፥ ልንወጣ ነው፤... <እኔን ለማን ትተሽ ነው የምትሄጂው? አለችኝ።> አንጀቴ ተላወሰ! ቢሆንም ቆፍጠን ብዬ አይዞሽ! ይህ ቤተሰብ ሁሉ ቆይተው ወደ ጌታ ይመጣሉ። ቃሉ" አንተ እመን ቤተሰብህም ይድናል!" ይላል አልኳት / በጊዜው የመጣልኝ ቃል ነው/፤ አንቺ ቤተሰብሽ ጋር አብረሽ ሁኚ! አልኴት። ...በነገሩ ብግን ብላ ነው መሰል፥ አክስቷ ተንደርድራ መጥታ አንድ ጊዜ አቀመሰችኝ! ንዴቷ ከፊቷ ላይ ይነበባል! ኽረ...በደንብ አድርጋ ነው ያቀመሰችኝ! የልቧ የደረስላት እንኳ አይመስለኝም፤ እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ጸጋውን አብዝቶልኝ የለ!? <ማዳም ሆይ እወድሻለሁ! /I love you!> አልኳት፤ <መበዴ!> አለች፤ በአረብኛ <አልፈልግም!> ማለቷ ነበር። ሞንያ ክፍሏ ገብታ ተንሰቅስቃ አለቀሰች፤ ወደ እናቷም መጣችና፥ ማማ ዛሬ የዚህን ቤት መብራት እንዳጠፋሽ እወቂው ? ብላት ገባች።...

ቤታቸው በኖርኩበት ጊዜ ያልመሰከርኩለት አባታቸውን ብቻ ነው፤ ስለ ሌሎቹ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። ከወጣሁ በኋላ እዛው አገር ሌላ ቦታ ስራ ጀመርኩ። ይሁንና የሞንያ ቤተሰቦች ሞንያን ወደ ጋና እንደላኳት ቆይቼ ሰማሁ። አባቷ ለስራ ጉዳይ ወደዚያ አገር ይሄድ ነበርና፤..ዶክመንቷን፣ ፓስፖርቷን ቀምተው ሰው አገር ወስደዋታል/አፍሪካ/። ትንሽ አዘንኩ! ግን ጌታ አዋቂ ነው።

እ.ኤ.አ.2000 ላይ ከሞንያ ጋር በደንብ ተለያየን። ጋና ምን ገጥሟት ይሆን? ህይወቷ እንዴት ሆኖ ይሆን? ...በልዑል እግዚአብሔር ፊት ከመጸለይ በቀር ምን ማድረግ እችላለሁ? እኔም ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ አሜሪካን አገር ገባሁ፤ እርሱም የራሱ ታሪክ አለው፤ እህቴ ቀደም ብላ ወደ አሜሪካ መጥታ ነበር።

ከሞንያ ጋር ከተለያየን ድፍን 18 ዓመት ሞላን። አንድ ቀን ስልክ ተደወለ! ቁጥሩ የዱባይ ነው። ሠላም ለእናንተ ይሁን! ማን ልበል? የወንድ ድምጽ ይመስላል! መጋቢ በርናባስ እባላለሁ አለ! ...እሺ ምን ልታዘዝ? አኧይ.. አንድ ጓደኛሽ ነች ስልክሽን የሰጠችኝ! ለአገልግሎት ሊባኖን ሄጄ ሞንያ ከምትባል  ሴት ጋር በድንገት ተገናኘን፤ ..እንዴት ጌታን እንዳገኘች፤ የህይወት ምስክርነቷን ስታጫውተኝ ቆየን...በአንዲት አበሻ ሴት አማካኝነት ብላ በዋናነት ስለ አንቺ አነሳች፤... ወደ ጋና ሄዳ ስትመለስ አንቺን ማግኘት አልቻለችም ፤ አፈላልጋ፣ አፈላልጋ ደክሟት ሳለ፤ ከእኔ ጋር ሰሞኑን  ተገናኘን...አንቺን የሚያውቅሽ ሰው ሳጠያይቅ ነበር፤ በእግዚአብሔር ቸርነት የምታውቅሽን አንድ  እህት ዱባይ አገኘሁ እናም... ደወልኩልሽ። ቃላት ጠፋኝ....ዝቅ ብዬ መሬቱን ሳምኩት! ወደ ስልኩ ተመለስኩና...እባክህ ሞንያን አሁን እንዴት ማግኘት እችላልለሁ? ስል ጠይኩት፤ ይኽው ቁጥሯን ልሰጥሽ  አለኝ! ተቀበልኩት !

የሞንያ ቁጥር ላይ ደወልኩ፤ ስልኩ ተነሳ፥ በጌታ ልጄ፣ እህቴ ሞንያ... <ሄሎ!> አለች። ክብር ለጌታ ይሁን!!! ይህ የሚገርም አምላክ...አሁን ጉጉቴ 18 ዓመት ሙሉ እንዴት እንዳሳለፈች መስማት፤ ደግሞ አሁን  በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ  ማወቅ! በቃ ሌላ ጥማት የለኝም። ሞንያ የሆነባትንና የደረሰውን ሁሉ አንድ በአንድ ዘረዘረችልኝ፤ የዛሬሽ 18 ዓመት ወደ ጋና ከሄደች በኌላ....ሰዎችን አጠያይቃ ከተለያየ አገራት የመጡ ክርስቲያኖች በሳምንት አንዴ እየተሰባሰቡ የሚያመልኩበት ቦታ ጠቁመዋት ከእነርሱ ጋር ተገናኝች፤ አብራቸው የጌታን ጸጋ እየተካፈለች ከቆየች በኋላ ፤ እዚያው ቸርች በኳየር አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ ጀመረች፤ ለሚስዮናዊ አገልግሎትም ወደ አውሮፓና ወደ ተለያዩ ቦታዎች ከሌሎች ጋር እየሄደች ታገለግል ነበር። በኋላም ሙሉ ለሙሉ ወደ ቤሩት ተመልሳ ከአበሻው ቸርች በመቀጠል ለመጀመሪያ ጊዜ በአረብኛ ጌታን ያመለከችበት ቤተክርስቲያን ውስጥ መጋቢ ሆና እንድታገለግል ተሹማ አገልግሎቷን ቀጥላለች!

መጋቢ ሞንያ በተወለደችበት ምድር ላይ ለብዙዎች አርዓያ በመሆን፣ ወንጌልን በድፍረት በመናገር አያሌዎችን ከሲኦል እያስመለጠች ሲሆን፤ ቤተሰቧ ሙሉ ለሙሉ ማለት እስኪቻል ድረስ ንስሐ ገብተው የክርስቶስ ተከታይ ሆነዋል። ነጻነትን በጥብቅ የምትጠላት  የሞንያ እህትማ በመንፈስ የተቃጠለች የወንጌል አማኝ ሆናለች፤ አባትና እናቷ አገልግሎቷን በአሁን ሰዓት በገንዘብ እየደግፉ ሲሆን፤ እህቶቿና የእህቶቿ ልጆች የቤተክርስቲያና አሸሮች፣ ሌሎቹም የህጻናት አስተማሪዎች ሆነዋል። በርካታዎች በየሳምንቱ ጌታን የሚቀበሉበት ቤ/ክ እንደሆነ መሰከረችላት፤ ከዚህ በተጨማሪ  በአሜሪካን ፣ በእንግሊዝ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ላይ ተደጋጋሚ ጊዜ በመሄድ ወንጌልን ታገለግላለች። እህታችን ነጺ አብራን የጌታን ስራ የምትስራ የጌታ ሰው ናት። በቅርብ ጊዜ ወደ ቤሩት ሄዳ ጌታ እየሰራ ያለውን ነገር ለማየት ዕቅድ ስላላት ጸልዩላት። ክብር ሁሉ ለጌታ ይሁን!

አንዳንዶቻችን በጣም ትልልቅ የወንጌል ገድል ላንፈጽም እንችላለን፤ በርካታ የወንጌል ገድል የሚፈጽሙ እንደ ጳውሎስ፣ ፣ እንደ ቢሊግርሃም...ደግሞ እንደ ሞንያ ያሉትን የወንጌል ጀግኖች ግን ወደ ጌታ ልናመጣ እንችላለን!! ስለዚህ የምትመሰክሩለት ሰው ነገ ምን ሆኖ እንደሚገለጥ አታውቁምና ሳትታክቱ መስክሩ!** ከመሰከራችሁ በኋላ ጸልዩላቸው፣ ለመንፈስ ቅዱስም አሳልፋችሁ ስጧቸው። ሌላ ታሪክ ይቀጥላል....

<< LET US BE WITNESSES FOR CHRIST! >>

ኢጆሌ! ..ኢጆሌ..ነምኒ ኢንጅሩ?

ኢጆሌ! ..ኢጆሌ..ነምኒ ኢንጅሩ?
/ልጆች!..ልጆች!..ማንም የለም?/
      ♠♠♠♠♠♠
ሰሞኑን ከምስራቅ ወለጋ አካባቢ ሚድያዎችን ጭምር እያነጋገረ ስላለ ጉዳይ ሰምተዋል?አቶ ሂርጳ ነገሮ ይባላሉ ፤ አባወራ ናቸው ፤ከታመሙ ዓመታት ሞላቸው። አንዴ በንቀምት ከፍ ሲልም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጭምር ለመታከም ሞክረዋል። እምብርታቸው አካባቢ ነው የሚያማቸው፤ ምናልባት የጉበት በሽታ ይሆናል ብለው ይጠራጠራሉ። እንደውም የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ  ...ቀዶ ህክምና አድርገውም ነበር። መፍትሄ ግን አልመጣም። እናም ህመሙ ጸንቶባቸው ባለፈው ማክሰኞን ዕለትን  መሻገር ሳይችሉ ቀርተው ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ነፍሳቸው ከስጋቸው ተለያየች። ገናዣቸው አቶ ኢታና ይህንን እውነታ አረጋግጠው ሬሳውን ገንዘው፣ ራሳቸው ባመጡት ሳጥን ውስጥ ከተቷቸው፤ ሳጥኑ ታሸገ! ከዚያም ቀድሞ በአካባቢው እንዳለው ልምድ ጥሩንባ ተለፈፈ፣ ግቢ ውስጥ ድንኳን ተጣለ ፤ ብዙ ጊዜ ወንዶች ይህን ሲያደርጉ ፣ ሴቶች ደግሞ በፊናቸው ለንፍሮ የሚሆን ስንዴና ሽንብራ ያዘጋጃሉ፤ ምስር ይለቅማሉ..ሌላም ሌላም...፤

የሰማ ሰው ሁሉ እየመጣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ያለቅሳል...ከሞቱ 4 ሰዐታት ቆይታ በኋላ ከሳጥን ውስጥ ኢጆሌ! ኢጆሌ...የሚል ድምጽ ይሰማል! በቅርበት የነበሩ የሟች እናትና ባለቤታቸው ፈርጥጠው ወደ ውጭ  ወጡ! ...ገሚሱም በድንጋጤ አካባቢውን ጥለው ፈረጠጡ፤ ከገናዡ ከአቶ ኢታንል በቀር መጠጋት የቻለ አልነበረም። << ኢጆሌ! ኢጆሌ! ነምኒ እንጅሩ!>> ደጋግመው ይናገራሉ፤ በኋላም ሳጥኑን ፈንቅለው ወጡ! ሁሉን ግርምት ሞላ! ..አመሻሽ ላይ ሚሪንዳ ቀማመሱና አቅማቸው ተመለሰ...የተሰበሰበ ብዙ ህዝብ ነበረና..ግማሹ እልልታ ያሰማል! ገሚሱ ያለቅሳል! አቶ ሂርጳ ጆሯቸው መስማት ጀመረ! ምንድን ነው? ብለው ጠየቁ፤ ተነገራቸው! ...ከሰዓትልት በፊት ሞተው ነበር እኮ አሏቸው፤..ለዚህም ነው ድንኳኑ፣ ለቅሶው...

የአማርኛ ጣቢያ ቢቢሲ ሞተው የተነሱትን አቶ ሂርጳንና አረጋግጠውና አስተክልክለው ገንዘው ሳጥን ውስጥ የከተቷቸውን አቶ ኢታናን ቃለ መጠይቅ አርጒልልቸዋል። በዚህ ክፍል ውስጥ ለአቶ ሂርጳ የቀረበው ጥያቄና መልሳቸው ተካቷል።  

፨ ቢቢሲ፡- አቶ ሂርጳ ከሞቱ በኃላ ምን ተመለከቱ? አቶ ሂርጳ ሲመልሱ:- ብዙ ነገር እንዲህ ነው ብዬ መግለጥ አልችልም። አንዳንዱ ተዘንግቶኛል...አሁን የማየው ያህል የሚታየኝ ግን ብዙ ነገር አለ!  ለምሳሌ አንድ በብረት ሰንሰለት የታጠረ የሚመስል፤ በርካታ ሰዎች የተሰበሰቡበት ግቢ አይቻለሁ..በሩ የሳንቃ ይሁን የብረት ትዝ አይላቸውም፤ እዚያ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ ሶስቱን ብቻ ነው የማውቃቸው፤  አንደኛው የራሴ ወላጅ አባት ሲሆኑ፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነው የሞቱት፤ ሁለተኛው ሰው አማቻቸው፤ ሦስተኛውም ሰው አጎታቸው ናቸው፤ እነዚህ ደግሞ ከሞቱ በርከት ያሉ ዓመታት አልፈዋቸዋል። ...ሰዎቹ ተከተለን ብለዋቸው ነበርና ሲከተሉ ሊደርሱባቸው እንዳልቻሉ ይናገራሉ እንደ ህልም ጉዞ አይነት ሆነ። ከዚህ ውጭ ግን እርስ በርስ ምን እንዳወጉ ትዝ አይላቸውም።

፨ ሌላው የማይረሱት ነገር ነጭ ልብስ የለበሰውን መልዐክ ነው..ኢየሱስን ይመስላል ይላሉ። ቢቢሲ አስረግጦ ለማወቅ ያዩት መልዐክ ጥቁር ነው? ቀይ? አላቸው፤ አቶ ሂርጳ ሲመልሱ  ቀይ መልዐክ ነው ፤ ነጭ ልብስ ግን ለብሶ ነበር አሉ።

፨ ቢቢሲ፡- ፊቱስ ምን ይመስል ነበር? የሰው ወይስ የመልዐክ? አላቸው።
አቶ ሂርጳ:-በእርግጥ ፊቱን በደንብ አላየሁትም። እኔ ውጭ ነበርኩ፤ እርሱ ደግሞ በውስጥ በኩል ቆሞ ነበር...ሰዎችንም ወደ ውስጥ አስገባና ይዟቸው ሄደ!

፨ ቢቢሲ ቀጠለና ሌላ መልዐክ አጠገቡ አልነበረም? አቶ ሂርጳ መለሱ አላየሁም! እርሱን ብቻ ነው ያየሁት።
ምን አለዎት?
አቶ ሂርጳ "አንተ የት ትሃልዳለህ? ተመለስ አለኝ።
በምን ቋንቋ አናገረዎት? በኦሮምኛ ነዋ!
አልፈሩም? በፍጹም! ክልከላውን/ኬላውን አልፌ መሄድ አምሮኝ ነበር ..ነገር ግን ውስጥ አልፎ ለመግባት አቅም አልነበረኝም!

፨ ቢቢሲ ወደ ምድር በመመለስዎ ቆጨዎት እንዴ?
አቶ ሂርጳ:- እዚያው ብሆን ደስ ይለኝ ነበር። አሁንም ግን ከቤተሰቤ ጋር ተመልሼ ስለተቀላቀልኩ ቅር አላለኝም።

፨ ቢቢሲ:- ከዚህ በኋላ በቀሪው ዘመንዎ ምን ማድረግ ያስባሉ?
አቶ ሂርጳ:- ከዚህ በኋላ የኃይማኖት ትምህርት በመስጠትና ሰዎችን በማስታረቅ ጉዳይ ላይ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
(ምንጭ:- BBC Amharic  Nov.23 2018)

♥ ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ እሙን ነው። ሰዎች ወይ የዘላለምን ህይወት፤ አልያም የዘላለምን ሞት ሊወርሱ የሚችሉበት ሁለት ዕድሎች አሏቸው፤ ሲኦልም ሆነ መንግስተ ሰማይ ዘላለማዊ ቦታዎች ናቸው። አማኞች (ሁላችንም) የክርስቶስን ወንጌል ለሰዎች ሁሉ በመመስከር፡ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ንስሐ እንዲገቡና ከወዲሁ ምርጫቸውን እንዲያስተካክሉ እንድንተጋ አደራ እላለሁ። አቶ ሂርጳ ብቻ ሳይሆኑ እኛ ሁላችንም ወንጌልን እናስተምር! የተጣሉትን እናስታርቅ!!
------------
" እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።
እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።"
                           2ኛ ቆሮ.5 ቁ 19ና 20

                 ♠♠♠♠♠♠♠
<< LET US BE WITNESSES FOR CHRIST! >>