Wednesday, August 8, 2018

እኛ ግን የተሰቀለውን...!

እኛ ግን የተሰቀለውን.....

በሆነ አንድ ወቅት በአንድ ቤተክርስቲያን የማምለኪያ አዳራሽ ፊት ተሰቅሎ የነበረ አንድ የጨርቅ ባነር ነበር በአቡጀዴው ጨርቅ ላይ ተጽፎ የነበረው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ "እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን!" የሚል ነበር። ነገር ግን ከጊዜ ወደ ጊዜ ከጨርቁ ላይ ፊደሎች  መጥፋት ጀምረው ነበር። በመጀመሪያ < እኛ ግን> የሚለው ቃል ቀለም በመጥፋቱ ምክንያት አረፍተ ነገሩ<<.. የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን" የሚል ጽሁፍ ሆነና ስብከቱን በውል ማን እንደሚሰብክ የማይታወቅ ሆነ። ቀጥሎም <የተሰቀለውን> የሚለው ስለለቀቀ <..ክርስቶስን እንሰብካለን> የሚለው ቀረ። ይህም የበለጠ የተለያየ ትርጉም ወደሚሰጠው ደረጃ ደረሰ። ምክንያቱም ብዙ ክርስቶስ ስላለ የትኛውን ክርስቶስ? የሚል ጥያቄ ያመጣልና። ክርስቶስ ራሱ በስሜ ብዙዎች ይመጣሉና ...ማቴ.24 &25 
በመጨረሻም <ክርስቶስን'> የሚለው ጠፍቶ .."..እንሰብካለን!" የሚለው ብቻ ቀረ።
ዋናው መስበካችን ሳይሆን ምን እንደምንሰብክ ፣ ማንን እንደምንስብክም ሌላው ዋና ነገር ነው። የስብከታችንና የአገልግሎታችን ማዕከላዊ አሳብ የተሰቀለው ክርስቶስ መሆን አለበት። ወንጌል ሙሉ የሚሆነው ክርስቶስ በስጋ መምጣቱ (መወለዱ)፣ መሰቀሉ ፣ መሞቱና መነሳቱ ነው። ቤተክርስቲያን በምድር ላይ የቆየችበት ምክንያት ይህንን እውነት እንድትመሰክር ነው። ወንጌል ሙሉ ነው ይዘቱም ይኽው ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት ስለሚሰብከው ነገር ለዋኖች ለማስታወቅና ለማስመርመር በመንፈስ መገለጥ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ነበር። ገላ.2፡ 1-10...እነርሱም የሚሰብከው ምን እንደሆነ ከመረመሩ በኋላ ለእርሱና ለበርናባስ ቀኝ እጃቸውን ሰጥተዋቸዋል። ሃሌ ሉያ! ከተሰቀለው ክርስቶስ ውጪ ለመስበክ ብቻ ሳይሆን ሌላ ነገር ላለማወቅም ቆርጦ እንደነበር ተናግሯል።.....
ዝም ብሎ እንሰብካለን ብለን እንደቤተክርስቲያን መናገር አንችልም። የክርስቶስ አብያተክርስቲያናት መስበክና ማወጅ ያለባቸው የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው። ዋናው መልዕክት እርሱ ነውና።
 የምትወዱንና የምትጸልዩልን ወዳጆቻችን ሁሉ ይህንን የወንጌል መልዕክት ለሌሎች ሁሉ ለማድረስ አብራችሁን እንድትሆኑ በፍቅር እንጋብዛችኋለን። መልዕክታችን ሁለት ነገር ነው ጠቅለል አርጎ ለማስቀመጥ:-
1ኛ እኛ ነን መስበክ ያለብን!
ይህ ቃል ሌሎች እንዲሰብኩ፣ ሌሎች ወንጌል እንዲንገሩ የሚጠቁም ሳይሆን  እኛ ራሳችን  ሃላፊነቱን ወስደን ወንጌል እንድንሰብክ የሚያሳስብ ቃል ነው።

2ኛ. የተሰቀለውን ክርስቶስን ነው መስበክ ያለብን!
ያልተሰቀለልን፣ ያልሞተልን ሌላ ክርስቶስ ስላለ ነው። ዘንድሮ ብዙ የሚሰብኩ /preachers and teachers/ ቢኖሩም መልዕክታቸው ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን ማሳየቱን፣ማላቁን ልብ ብለን ማየት አለብን። ክርስቶስ እስኪመጣ የቤ/ክ ስብከት ገንዘብ መሆን የለበትም፣ ስለ ሰው መሆን የለበትም፣ ሌላ ወንጌል መሆን የለበትም(ገላ 1 :6-9)   ስብከታችን የተሰቀለው ክርስቶስ ብቻ ነው!!!