Sunday, January 1, 2017

በጥልቀት መታደስ !



በጥልቀት መታደስ….!
አዲሱን ዓመት ምክንያት በማድረግ ራሳችንን በጥልቀት ፈትሸን እንታደስ ዘንድ በማሰብ ይህ ጽሑፍ ለመላው አብያተክርስቲያናት አገልጋዮችና ምዕመናን ተዘጋጅቷል፡፡
ይሁዳ 11
“ ..ወዮላቸው በቃየል መንገድ ሄደዋልና፣ ስለ ደመወዝም  ለበለዓም ስሕተት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጥተዋል፣ በቆሬም መቃወም ጠፍተዋል፡፡ 
ይሁዳ በመልዕክቱ ውስጥ የጠቀሳቸው እነዚህ ሦስቱ ሰዎች/ቃየል፣ በለዓምና ቆሬ/ በብሉይ ኪዳን በተለያየ ዘመን የኖሩ ሲሆኑ ፡ጸሐፊው በዘመኑ ወደ ቤተክርስቲያን ሾልኮ ስለገባው የስህተት ትምህርትና አስተማሪዎቹ/ሐሳውያን/ ባህሪና ምግባር በስፋት ያነሳው ቤተክርስቲያንን ከጥፋት ለመታደግ እንደሆነ ከመልዕክቱ እንረዳለን፡፡ ይሁንና  የዛሬይቱም ቤተክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ትልቅ ትምህርት የሚወስዱበት ሁኔታ አለና ከቀጣዩ መልዕክት እያንዳንዱ ለህይወቱ የሚጠቅመውን ቁም ነገር እንዲያስቀር ይሁን ፡፡
ፀሐፊው ከጠቀሳቸው፡- 1.የቃየል መንገድ
                                 2.የበለዓም ስሕተት
                                 3.የቆሬ መቃወም  ምን ማለት ነው? መቼ ነው የሆነው? እንዴት ነው የሆነው? የሚለውን ቀጥለን እንመልከት
ቃየል፡-የፍጥረት የመጀመሪያው  ሰው አዳም ልጅና የአቤል ወንድም ነበረ፡፡ የዘፍጥረት 4፡3 ማብራሪያ እንደሚነግረን  በቅንዐትና በጥላቻ ተነሳስቶ ወንድሙን አቤልን የገደለ ነፍሰ ገዳይም ነው፡፡ ወደ ግድያ ያደረሰው ጉዳይ ጥላቻ ፤ስግብግብነት፣ ምቀኝነት እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡/NIV/  የእናት አባቱ ልጅ አቤል አብሮት እየኖረ እንዴት በእግዚአብሔር ፊት ለራሱና ለመስዋዕቱ ሞገስና ተቀባይነትን እንዳገኘ ትምህርት ከመውሰድ ይልቅ ጥላቻ አደረበት፤ የቃየል ስሕተት ይህ ብቻ አልነበረም፡ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ እያዘገመ እንደሆነና ከክፉ መንገዱም እንዲመለስ እግዚአብሔር ቢያስጠነቅቀውም እንኳ መመለስ አልቻለም፡፡ ስለዚህ የቃየን መንገድ ማለት አጠገቡ ካለው ወንድሙ ትምህርት ከመውሰድ ይልቅ በተሳካላቸው ሰዎች መቅናት፣ እንዴት እንደሚወድቁ ሴራ ማሴር ፣ በሌላ በኩል ሐጢያት እንዳይነግስበት ሊጠቁመው የመጣውን ድምጽ / ምክር/ መናቅ ፤ ችላ ማለት! የሚሉት መገለጫዎቹ ናቸው፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? ወገኖች ወንድምን  መግደል የመጨረሻው የክፋት ደረጃ ቢሆንም፤ ትንንሽ ወንድሞችና መገለጫዎችም አሉት፡፡ አሁን አሁን በስፋት እየተለመዱ ያሉ ነገሮች አሉ! ለምሳሌ አንዳንድ  መጋቢዎችና ሽማግሌዎች ትውልድ እንዳይተካ  በር በመዝጋት፣ ትንሽ የጸጋ ስጦታ የሚታይበትን ሰው ድራሹን በማጥፋት፣ እንዲማረር በማድረግ ፤ አሰሪዎች ከሆኑ ከሥራቸው ያሉ ቅጥረኞችን ሁልጊዜ የበታችነት እየተሰማቸው ከስራቸው ብቻ እንዲሆኑ፣ በተለያየ ዘርፍ ሰዎች ከስር ተነስተው ልቀው እንዳይወጡ የሚደረግበት ሥጋዊ አሰራር ሁሉ የቃየል መንገድ መገለጫ ነው፡፡  በሌላ መልክ ሲነገራቸው የማይሰሙ፣ መንፈሳቸውን የማያደምጡ፣ ምክርና ተግሳጽን የሚንቁ፣ ነጋቸው/ዘላለማቸው/ የማይታያቸው ሁሉ በዚህ መንገድ ላይ ያሉ ናቸው፡፡ መጨረሻቸውም አሳዛኝ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ስለ አቤል ደም እግዚአብሔር ዝም አላለምና! ልክ እንደ ደሙም በር የተዘጋባቸው ፣ ያለ አግባብ መብታቸውን የተቀሙ፣ እንዳያድጉ የሚኮረኮሙ፣ ያለ በቂ ምክንያት ዕድገት/ሹመት/ የተነፈጉ፣ ዘራቸው ፣ቋንቋቸው ተፈትሾ የማለፊያ መንገድ የተከለከሉ፣ አድሎ የተፈጸመባቸው፣ግፍ የተሰራባቸው የበርካቶች ወንድሞችና እህቶቻችን እንባና ጩኽት እየተሰማ ነው፡፡
  በለዓም ፡-ምንም እንኳ በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተለያየ ሥፍራ ላይ የተጠቀሰ ቢሆን / ራዕይ 2፡14፣ 2ጴጥ.2፡15..ወ.ዘ.ተ./  በዋናነት ግን ታሪኩን በዘኁ.ም.22-25 ድረስ እናገኛለን፡፡ በተለይ በራዕይ መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው በአንድ ወቅት ለእስራኤላውያን እልቂት ምክንያት  የሆነውን የጥፋት ድግስ ያስደገሰ ዋነኛ ጠላት እርሱ ነበር፡፡ የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል  ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበለዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ፡፡››ይላል፡፡ በለዓም ባላቅን  ያስተማረው ምንድን ነው? መቼስ  ነው ያስተማረው? ብለን መጠየቃችን አይቀርም፡፡ በቅድሚያ ስለ ግንኙነታቸው እናንሳ፡፡ ባላቅ በአንድ ወቅት የሞዐብ ንጉስ የነበረ ሲሆን፤ በለዓም ግን ከሞዐብ ትንሽ  ራቅ ያለ ሥፍራ ላይ ተቀምጦ በረጋሚነት የሚተዳደር ሰው ነበር፡፡ እስራኤላውያን ከግብጽ ወጥተው ወደ ከነአን ጉዞ መጀመራቸውን ተከትሎ  በምድሩ እንዳያልፉ፡ በተለይም ከሰማው ዝናቸው አንጻር ሰግቶ በለዓምን አስመጥቶ በሙዋርት ሊያስረግማቸውና መንገድ ሊያስቀራቸው ሽቶ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ነው እንግዲህ በለዓምን የሚያግባቡ ተለቅ ተለቅ ያሉ ሰዎች ተልከው ከቀናት በኋላ ተክተልትለው አብረው የደረሱት፡፡ ቢሆንም እቅዳቸው ሳይሰምር ቀረ፡፡ ለሦስት እና ለአራት ጊዜ ፈጽሞ መባረክ ብቻ እንጂ መርገም ከቶ አልተቻለም ነበረና፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በስውር ለሕዝቡ እየተሟገተ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በዘኁልቁ መጽሐፍ ላይ ሁለቱ ሰዎች በዚህ መልክ እንደተለያዩ ቢገልጽም፤አዲስ ኪዳንን ጨምሮ በሌሎች ስፍራዎች ላይ በለዓም የሰራው ተንኮል ቁልጭ ብሎ ወጥቷል፡፡
 በለዓም ሁለት መልክ ያለው፣ ሁለት ምላስ ያለው፣ከባድ ሰው ነበር፡፡ ፊት ለፊት እስራኤልን ይመርቃል፣ ያደንቃል ፣እግዚአብሔር በመካከላቸው ያለ ታላቅ ሕዝብ መሆኑን ይናገራል፣ከአንበሳ ደቦል ጋር ያመሳስላቸዋል፣ ሞታቸውን እንኳ እኔ ልሙት ብሎ እስኪመኝ ደርሶ ይታያል/ዘኁ.23፡10……../፤ ዞር ብሎ ደግሞ የሚጠፉበትን፣ተሰነካክለው የሚወድቁበትን ጉድጓዳቸውን ይቆፍራል፡፡ ያወቀውን ድካማቸውን አጋልጦ ሰጠ! ድካማቸውን ፈጽመው እንዲወድቁበት ተጠቀመበት፤ ከፊት ጥሩ ስለሚናገር ማንም እርሱን ጠላት ነው ብሎ ሊፈርጀው አይደፍርም ከጀርባ ግን ሐሜት አለ! እየሳቀ የሚገድል ቀን ጠብቆ አሳልፎ የሚሠጥ ከባድ ሰው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት መተት ያላጠፋው ሕዝብ፣ ሙዋርት ያልገደለው ሕዝብ፣ ከቶ እርግማን ሊሰራበት ያልቻለ፣ ሊረገምም ያለተቻለ የእግዚአብሔር ሕዝብ በድካሙ ምክንያት መንገድ ቀረ‹! በአንድ ቀን ብቻ ሃያ አራት ሺህ ሰዎች ሞቱ! ይለናል / ዘኁ.25ቁ.9/፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን?  እየሳቁ የሚገድሉ፣ ፊት ለፊት ጥሩ ነገር ያወሩና ከጀርባ ጉድጓድ የሚቆፍሩ …በተለይ እግዚአብሔር ቤት ውስጥ በርካቶች እንዳሉ ሲሰማ አያምም ወይ? ዞረው የሚያሙ፣ ድካሙን እንዲያስተካክል ለወንድማቸው ከመናገር ይልቅ ለሌላው /ለገዳይ/ አሳልፈው የሚሰጡ፣ በለዓም ለደሞዝ ተታሎ ይህን እንዳደረገ ተጠቅሷል፡፡ እንዲህ ባለ ምድራዊ ጥቅማ ጥቅም የሚታለሉ፣ እውነትን የሚሸቃቅጡ፣ ለሆዳቸው ያደሩ፣ እውነትን መጋፈጥ አንድ ቀን እንኳ የተሳናቸው፣ ዘላለማዊውን ነገር የረሱትን ይመስላል፡፡ የበለዓም ስህተት በሐዋርያት ዘመንም ነበረ፣ ዘንድሮም በየ አጥቢያው አይጠፋም …ይህን መንገድ እየተከተላችሁ ያላችሁ ወንድሞች፣ ቄሶች፣መጋቢዎች፣ዲያቆናት፣ሽማግሌዎች፣ልዩ ልዩ ባለስልጣናት…ራሳችሁን ከዚህ ክፉ መንገድ አውጥታችሁ በመጪው አዲስ ዓመት ሰው መንገዱ የሚቀናለትን ሁኔታ በበጎ ሕሊና እንድታስቡ፣ በተግባር ሰው መንገዱ እንዲቀናለት አድርጋችሁ እንድታመቻቹ ትለመናላችሁ! ዞሮ ጉድጓድ መቆፈር  ይብቃ! ሌላው መንገድ ላይ የሚቀርበትን ሸር መስራት ይብቃ! ……
ቆሬ፡- ይህ ደግሞ  ታሪኩ በዘኁ.16  ላይ ተጠቅሶ እንደሚገኘው  የትዕቢትና የንቀት ምሳሌ ነው፡፡ በተለይ ሁሉን ማድረግ እኛም እንችላለን! እነሱ ማናቸውና! እያሉ እውነተኛ  አገልጋዮች ላይ በድፍረት የሚናገሩ፣ በንቀት ለተሞሉ፣ ሳይችሉ እችላለሁ! ለሚሉ፣ ድምጽ-ተሰጦ ሳይኖራቸው በእልኸኝነት መዘምራን መካከል ገብተው ለሚረብሹ፣ አንዳችም ነገር ሳይሰማቸው የሰውን ስነ ልቦና እያነበቡ ከልባቸው እያወጡ ለሚተነብዩ፣ ሳይሾሙ ራሳቸውን ለሾሙ፣መሪነት ሳይሰጣቸው መምራት እችላለሁ! ለሚሉ ደፋሮች፣ ቀን ተቀን ለእግዚአብሔር ቤት የማነቆ ገመድ ለሆኑ እልኸኞች፣ የቆሬ ሰዎች ሕይወት ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጥቂት ነበሩ፤ ነገር ግን አድማ ሰርተው አለቆችን አሳምነው እኛም እንደነርሱ ካህናት መሆን እንችላለን! ማጠን እንችላለን! በማለት በሙሴና በአሮን ላይ ተሰበሰቡ /ቁ.6-10/፡፡ አሳዛኙ ነገር እንዲህ በትዕቢት ተወጥረው ማድረግ የሌለባቸውን እናደርጋለን ብለው የተነሱቱ ወገኖች መጨረሻቸው አለማማሩ ነው/ቁ.31-33/፡፡
እኛስ ከዚህ ምን እንማራለን? ካህን ተደርገው ሳይመረጡ የራሳቸውን ጥና የያዙ፣ ጥሪ ሳይፈተሸ/ሳይረጋገጥ/ ቤተክርስቲያን እንመራለን ብለው ግርግር የሚፈጥሩ፣ በተቀቡ ሰዎች ላይ አድማ የሚያሳድሙ፣ ለመልካም ሳይሆን-ለክፉ፣ ለማቅናት ሳይሆን-ለማፍረስ፣ የሚሰበሰቡ፣ የማይመለከታቸውን ጉዳይ እየፈተፈቱ ቤታቸው ቁጭ ብለው ቤተክርስቲያን የሚያፈርሱ፣ ካልቻሉ አሳባቸውን በሰው ምላስ ላይ እያኖሩ ሰላም እንዳይገኝ ምክንያት የሚሆኑ ሁሉ ቆሬና ሰዎቹ ሞቱ እንጂ መንፈሱ አልሞተምና በተለያየ ተዋረድ በእጅ አዙር እየተጠቀመባቸው እንዳይሆን መፍራት ጥሩ ይመስለኛል፡፡ ሁሉን አውቃለሁ የሚልን ሰው መምከር ከባድ ቢሆንም የእግዚአብሔርን ጥልቅ አሰራር መርምሮ ሊደርስበት የሚችል የለምና እስኪ በትጋትና በደስታ ራዕያቸውን ይፈጽሙ ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው አገልጋዮቹ ላይ ዞር ትሉ ዘንድ በአዲሱ ዓመት ጌታ እንዲረዳችሁ ጸልዩ! ደግሞ በተቃራኒው ሥራውን መደገፍ ፣መጸለይ፣ የፈረሰ ጎን አይቶ መቆም….ምንም ነገር ከተቃውሞ ሳይሆን ከፍቅር እንዲመነጭ ማድረግ ብስለት ነው፡፡
 እንዲያው ባጠቃላይ ቅንነትን ተላብሰን የቀረችን ጊዜ ምን ያህል እንደሆነች አትታወቅምና እግዚአብሔር በረዳን መጠን ጥሩና ደግ ሰዎች፣ የሰላም ሰዎች፣ ራሳቸውን የካዱ ለሌላው የሚኖሩ ሰዎች ፣ ለትውልድ መንገድ ከፋቾች ፣ የማደጊያ አቅጣጫ ጠቋሚዎች ያድርገን ! በክርስቶስ ኢየሱስ ስም! አሜን!
                                                                             ብንያም በፍቃዱ /መጋቢ/
                                                                               benjabef@gmail.com