በወንጌል ስለተሰራው ስራ የቀረበ
ሪፖርት
ተሐድሶ ቶውት በሚል በተከታታይ
መንፈሳዊ ጽሁፎችን ማቅረብ የተጀመረው በ 2014 እ.አ.አ. ሲሆን በዚህ ብሎግ እስካሁን በእግዚአብሔር ፍቃድ የተሰሩትን
ክንውኖች ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ በቅድሚያ ለዚህ ነገር ያነሳሳኝንና ስለ ህዝቤ በተለይም ስለ ጥንቷ ቤተክርስቲያን ምዕመናን
ሸክምን ሰጥቶ እያተጋኝ ያለውን ልዑል እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ፡፡ በጸሎትና በተለያዩ ድጋፎች ከጎኔ የቆሙትንም እግዚአብሔር
ከጸባኦት ይባርካቸው እላለሁ፡፡
በብሎጉ ላይ የሚጻፉት ጽሁፎች
በአብዛኛው ድነት ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ አልፎ አልፎ ከዚያ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ለሌሎች ቅዱሳን ወንድሞችና እህቶች የሚጠቅሙ
ተሐድሶአዊ መልዕክቶችም ይቀርባሉ፡፡ ለምሳሌ በድነት ዙሪያ ከሚቀርቡት መካከል ሚስጥረ-ድነት ፣ አስቸኳይ መልዕክት ፣ ከሲኦል
የተላከ ደብዳቤ ፣ ንስሐ ገብተዋልን? የሚሉ ይገኙባቸዋል፡፡
በፌስ ቡክ ላይ እንዲቀርብ ታስቦ የተሰሩ በጥበባዊ መንገድ ወንጌልን የሚናገሩ ጽሁፎችም አሉበት:: ለምሳሌ ለቪዛ ፈላጊዎች ፣ ነጻ
የትምህርት ዕድል ፣ ክፍት የስራ ቦታ ፣ ዜና ማህደር ፣ የሰርግ ጥሪ… የመሳሰሉት ናቸው፡፡
ከዚሁ የድነት መልዕክት ጋር
የተያያዘ እና የክርስቲያን በዐላትን አስመልክቶ የተጻፉ መልዕከቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ ፋሲካ ፣ የገና መልዕክት ፣ ስለ ስቅለት ፣ ስለ
ሰሞነ ህማማት ሲሆኑ በቀጣዩ ታንክስ ጊቪንግ ላይ እና የአዲሱ ዓመት መልዕክቶች እየተዘጋጁ ነው፡፡ የአበሻው ህብረተሰብ በዓለም
ላይ ሁሉ የተበተነ እንደመሆኑ አንዳንድ በዐላት ሁለት ጊዜ የመከበር
እድል አላቸው፡፡ ከዚህም የተነሳ እንደየ አውዱ እና የአገራቱ በዐል መሰረት፤ በተለይም በዌስተርን አገሮችና ከራሳችን ባህል አንጻር
ተመጣጥነውና ታስቦ የቀረቡ መልዕክቶች ናቸው፡፡ ከዚሁም ጋር አንዳንዶቹ በውጪ አገር ተወልደው ያደጉ በመሆኑ፡ ከቋንቋ አንጻር እንዳይቸገሩ ዋና ዋና የድነት መልዕክቶች በእንግሊዝኛ ጭምር ተጽፏል፡፡ ለምሳሌ urgent message , Don’t Delay ,the secret of Salvation….etc ሲሆኑ፡፡ በቀጣይም በኦሮምኛ /ቁቤ/
እና በእስፓኒሽ ቋንቋ ለማስተርጎም ዝግጅቶች ተጠናቀዋል፡፡ ይህም በተለይ በሰሜን አሜሪካ ብዙ ህዝብ ከመኖሩ አንጻር ነው ፡፡ በሌሎችም
ቋንቋዎች ሁኔታው እንዳመቸ መጠን ለማድረስ ጥረት ይደረጋል፡፡
የቆዩ ክርስቲያኖችን በመንፈሳዊ ህይወታቸው ለማበረታታትና የበለጠ እንዲተጉ
ለማስቻል የተጻፉ መልዕክቶችም አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- ቀን ሳለ ፣ እግሬን አታጥብም ፣ አገልጋይና አገልግሎቱ ፣ ሰጥቶም ነስቶም ፣
ንገስባት ፣ የእግዚአብሔር አሳብ እና ስለ አራቱ ጨረቃዎች ከመጨረሻው ዘመን ጋር በማያያዝ ተጽፈው ቀርበዋል፡፡
ከዚህ ሌላ የኦርቶዶክስ ህዝባችንን ጥያቄ ከመፍታት አንጻር ሰው ሁሉ
በዚህች ቤተክርስቲያን ስላለው የኑፋቄ አስተምህሮ እውነቱን እንዲያውቅ እና ለሌሎችም በጥሞና እንዲያስረዳ በማሰብ የተወሰነ ዕውቀት
የሚያስጨብጡ ርዕሶችን በማንሳት በሰፊው ለመጻፍ ተሞክሯል፡፡ በዚህም አመርቂ ውጤት ታይቷል፡፡ ለምሳሌ ፡- ስንት አይነት መጽሐፍ
ቅዱስ አለ? የሚል ከአዋልድ መጽሐፍት ጋር ተያይዞ የቀረበ ፣ አማላጅነት የሚል ስለ ቅዱሳን ምልጃ ፣ የቅዱሳን መላዕክት ድርሻ ፣ ስለ ዝክር ፣ የሙታን ተስካር
፣ ስለ ካህናት ስልጣን ፣ ..ወዘተ የቀረበ ፤ በቀጣይ ስለ ቀኖና ና ዶግማ ፣ ሚስጥረ ቁርባን ፣ ጾም በሚል ርዕሶች በተከታታይ
የሚቀርቡ ትምህርቶች ተዘጋጅተዋል፡፡
እስካሁን የወንጌል መልዕክቶችንና ፣ ሌሎች ተያያዥ ትምህርቶችን በፌስ
ቡክ ፣ በኢ-ሜይል ፣ በጉግል ፕላስ ፣ በስልክ ቴክስቶችና በቫይበር
እየቀረቡ ያሉ ሲሆን፤ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች መልዕክቱን እያነበቡ እንደሆነ የሚቀርበው ዘገባ ያሳያል፡፡ በአንባቢያን መከታተያ
ብሎጉ ላይ እንደሚያሳየው እስካሁን በ24 የተለያዩ አገራት ላይ በዓለም ዙሪያ ጽሁፎቹ ደርሰው እየተነበቡ ነው እነዚህም በአሜሪካ
፣ ኢትዮጵያ፣ ካናዳ ፣ እንግሊዝ፣ ኩዌት ፣ ባህሬን፣ ኔዘርላንድ፣ ሱዳን፣ ፈረንሳይ፣ ፖላንድ፣ ዩክሬን ፣ ግብጽ፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ
፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኢንዶኔዢያ፣ ብሩንዲ ፣ የመን፣ ጣሊያን፣ ኤርትራ፣ ኖርዌይ፣ ሀንጋሪ፣ ኬንያ ፣ ሩማንያ እና ሳውዲ አረቢያ ናቸው፡፡
ለወገኖቻችሁ የሚደርሳችሁን መልዕክት እያነበባችሁ ወደ ተለያየ ዓለም በመላክ የተጋችሁትን ሁሉ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርካችሁ፡፡
እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት በዓለም ላይ 2.1 ቢሊዮን ሰው የኢንተርኔት ተጠቃሚ እንደሆነ በ2014 ላይ የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በኦክቶበር 3, 2013 እንደወጣው መረጃ ደግሞ ከ 500 ሚሊዮን በላይ የሆነ ህዝብ የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ነው ፡፡ ይህ ማለት ጌታችን
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማቴዎስ ወንጌል 28፡ 18-20 እና ማርቆስ 16፡15 ‹‹ ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ና ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ንገሩ ብሎ እንዳዘዘ ….›› በትዕዛዙ መሰረት
ይህን ለመተግበር ህዝቡ የት ነው ያለው ? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ይኸው ከላይ እንደተገለጠው ከ 7 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ውስጥ
ከ 2 ቢሊዮን በላይ የሚሆነውን ኢንተርኔት ላይ ነው የምናገኘው ማለት ነው ፡፡ የዳኑ ሰዎች ምን ያህሉ በዚያ ውስጥ እንዳሉ የሚታወቅ
ነገር የለም፡፡ ለማንኛውም ይህን መንገድ ተረባርበን ካልዋጀነው ሌሎች ገብተው ህዝቡን ይዘርፉብናል፡፡
በዚህ አገልግሎት እሰካሁን በፌስቡክ 12 ያህል ግሩፖች ላይ መልዕክት በየሳምንቱ የሚደርስ ሲሆን በመጀመሪያው ግሩፕ
3,792 አባል አሉት/ መዝሙሮችና የመዝሙር ግጥም ለማቅረብ የተሰበሰበ ስብስብ ነው፡፡/ 2ኛው 46 / በአሜሪካን አገር የሚገኙ
አበሻ የኮሌጅ ተማሪዎች ስብስብ ነው፡፡ /፣ 3ኛው 326 ገደማ ነው / በአንድ የአረብ አገር ላይ ያሉ ለመጸለይ እና ርዕሶችን
ለመለዋወጥ የተሰበሰቡ ናቸው፡፡ /፣ 4ኛው 2,311 ሲሆኑ / ኢትዮጵያ ላይ ቪዥን ያነገቡ ናቸው፡፡ /፣ 5ኛ 1,583 ገደማ ሲሆኑ
እነዚህ አባላት በኢትዮጵያ ስላለው የመንፈስ ቅዱስ እንቅስቃሴ ትኩረት አድርገው የሚጻፉ ናቸው፡፡ 6ኛ 20 አባላት የሚሆኑ ናቸው፤
በአብዛኛው አማኞች አይመስሉም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ላይ ዓላማ ያላቸው ይመስላል፣ 7ኛ 7,657 ያህል አባላት
ያሉበት ና ዓላማቸውም ወንጌል ነክ የሆነ ግሩፕ ነው፡፡ 8ኛ 149 ያህል ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የአንድ ቤተክርስቲያን ወጣቶች
የመሰረቱት እና እርስ በርስ የሚተናነጹበት ድረ ገጽ ነው ፣ 9ኛ በዓለም ላይ ያሉ ሴቶች ላይ መንፈሳዊ ራዕይ አንግቦ የተመሰረተ
ግሩፕ ነው፤ በአንዲት ነጭ አገልጋይ ይመራል፡፡ ከዚህ በተረፈ ያለው 3ት ያህል ገጾች እኔ የመሰረትኳቸው ናቸው ፡፡ አንደኛው ላይ
ከ475 በላይ አባላት ያሉበት ኢየሱስ ያድናል የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የሚል ከግዕዝ ጋር የተቀላቀሉ የድነት
መልዕክቶች የሚወጡባቸው ና በመጠይቅ መልክ የወንጌል መልዕክት የሚቀርብባቸው ናቸው፡፡ ሶስተኛው ትምህርታዊ ድረ ገጽ ነው ፤ ሪፎርሜሽን
ባይብል ስኩል ይባላል፡፡ ጠንከር ያሉ ህይወት ተኮር መንፈሳዊ ትምህርቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡
በተጨማሪ በጉገል ፕላስ ላይ 9,326 ተመልካቾች/ views/ ና
29 ተከታዮች /followers/ አሉ፡፡ ቢያንስ በሳምንት አንድ ጊዜ በእንግሊዝኛ እና በአማርኛ የተዘጋጀ የድነት መልዕክት ይቀርብበታል፡፡
ተሐድሶ ቶውት በሚለው ብሎግ 51 ያህል ልዩ ልዩ መልዕክቶች እሰካሁን ቀርበዋል፤ 13068 ጊዜ ተነበዋል ከላይ እንደተገለጸው በቁጥር አንድ የተነበበው
10060 ገደማ ሰሜን አሜሪካ ውስጥ ሲሆን፤ 1129 በኢትዮጵያ እና
ሌሎች አገሮች በቅደም ተከተላቸው ይከተላሉ፡፡ በብሎጉ ላይ የተወሰኑ የቪዲዮ መልዕክቶች እና ትምህርቶች በክርስቶስ አምነው በዳኑ
መርጌታዎችና መምህራን ተዘጋጅቶ ለህዝብ እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ አንዳንድ
ጽሑፎችም እንደ አስፈላጊነቱ ከሌሎች አገልጋዮች ማስታወሻ ላይ ተወስዶ
እንዲወጣ ተደርጓል፡፡ ወደ ፊትም እንደ ሁኔታው የሚቀጥል ይሆናል፡፡ አብዛኛው መልዕክቶች ለሰዎች የሚደርሱት በሞባይላቸው ላይ ቴክስት
በማድረግ ሲሆን እስካሁን ከ360 በላይ መልዕክት አድራሾች እና መልዕክት ተቀባዮች ቁጥር በእኔ ሞባይል ውስጥ አሉ፡፡ በቫይበር
የሚጠቀሙ እና መልዕክት የሚደርሳቸው 268 ግለሰቦች ሲሆኑ ከ60 በላይ የሚሆኑ ቢያንስ ከ10 እስከ 25 የሚደርሱ አባላት ያሉባቸው
ግሩፖች ውስጡ አሉ፡፡ ለእነርሱም በተመሳሳይ በየ ግሩፑ መልዕክት ይላክላቸዋል ፡፡ በታማኝነት አንብበው ለወዳጅ ቤተሰቦቻቸው መልዕክቱን
የሚያጋሩ ብዙ አሉ፡፡ ጌታ ልፋታችሁን ቆጥሮ ዘመዶቻችሁንና ጓደኞቻችሁን ያትርፍላችሁ፡፡ ከዚህ በተረፈ በርካታ የኢሜይል ላይ ደንበኞች
አሉ ፡ ብዙ ጊዜ ሞባይሌ ላይ አማርኛ አልሰራልኝም ከሚል ጋር ተያይዞ ነው ኢሜይል አድራሻቸውን የሚልኩት፡፡ ሁሉንም ቴክኖሎጂዎች
መጠቀም ለማይችል ደግሞ የደብዳቤ አገልግሎት ተዘጋጅቷል፡፡ በየትኛውም ስፍራ ላሉ ሰዎች የድነት ደብዳቤ በአድራሻቸው የመላክ አገልግሎት
ነው ፡፡ በዚህም አንዳንዶች ወደ ቤተሰቦቻቸው በመላክ ፣ለስራ አለቆቻቸው
በመስጠት ድርሻቸውን ተወጥተዋል፡፡ ሁላችሁን ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ፡፡
እግዚአብሔር እንደረዳን እስካሁን በዚህ መልክ ተንቀሳቅሰናል፡፡ ዓለም
ሁሉ ድኖ እስኪያበቃ ወይም ጌታ ተመልሶ እስኪመለስ ወንጌል መስበካችንን በአዳዲስ ሌሎች ስልቶችም እንቀጥላለን፡፡ቀደም ብለን የጀመርነውን ይህንን የስርጭት ዘዴም በስፋት እንቀጥላለን፡፡ በተለይ በቀጣይ
ሁሉም ክርስቲያን ቢያንስ ለ 10 ሰዎች ከቀረቡላቸው አማራጮች በአንዱ መንገድ ወንጌልን እንዲመሰክሩ ፤አልያም 10 ሰዎችን አድራሻ
በመስጠት እንዲጸለይላቸውና እንዲመሰከርላቸው እንዲያደርጉ በስፋት ከአብያተ ክርስቲያናት ጋር በመቀናጀት ለመስራት ዕቅድ አለ፡፡
ለነፍሳት ለመጸለይ ሸክም ለተሰጣቸው ሰዎችም ርዕሶችን በመስጠት በቤታቸው
ሆነው ለነፍሳት እንዲተጉ ይደረጋል፡፡ በዚህ መልክ ለአገልግሎት የተለዩትን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ክርስቲያኖች መስካሪ የማድረግ
ጥረት ይቀጥላል፡፡ በዚህ ሪፖርት ላይ ያልተገለጡ ሌሎች ዕቅዶችም አሉ፡፡ ጌታ በነገር ሁሉ ያግዘን ዘንድ መጸለይና በአስፈላጊው
ነገሮች ሁሉ ከጎን በመቆም የወንጌል ማህበርተኝነታችንን እናሳይ፡፡ የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል እኛም ባሪያዎቹ ተነስተን እንሰራለን፡፡
በጌታ አገልጋያችሁ ብንያም በፍቃዱ አቦዬ
ከሜሪላንድ
benjabef@gmail.com
No comments:
Post a Comment