Monday, March 30, 2015

በሰሞነ ህማማት!

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በድምቀት ከሚታሰቡና ከሚከበሩ በዐላት መካከል የሰሞነ ህማማት አንዱ ነው፡፡

   ጌታችን መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ዓለም ሁሉ ሐጢያት በመስቀል ላይ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት በቃላት ሊነገር የማይችል ስቃይና መከራ ውስጥ እንደነበረ የአይን እማኞች ጽፈዋል፤ መስክረዋልም፡፡ ያ የህማሙ ሳምንት ነው ፡ ሰሞነ ህማማት ተብሎ የተሰየመው፡፡ ጌታችን በእነዚያ ቀናት ተጨንቆ ነበር፣ የደም ላብ አልቦት ነበር፣ ስድብና ውርደትን ሁሉ ተቀብሎአል፤ ይህ ሁሉ ስለ እኛ ነበር፡፡ ነቢዩ ኢሳያስ ስለ መከራው እንዲህ ነበር የተናገረው፡-

  " ከመ ፡በግዕ፡ አሞጽእዎ፡ ይጠባሕ፡ ወከመ፡ በግዕ፡ ዘኢይነብብ፡ በቅድመ፡ ዘይቀር፡ ከማሁ፡ ኢከሰተ፡ አፋሁ፡ በሕማሙ፡፡ወተንሥአ፡ እምኩነኔ፡ ወእምነ፡ሞቅሕ፡ ወመኑ፡ ይንገር፡ ልደቶ፡እስመ፡ ትትእተት፡ እምድር፡ሕይወቱ፡፡ / ተጨነቀ ፣ ተሰቃየም አፉንም አልከፈተም፣ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቶቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም፡፡ በማስጨነቅ ና በፍርድ ተወሰደ፤ ስለ ሕዝቤ ሀጢያት ተመትቶ ከሕያዋን  ምድር እንደተወገደ ከትውልዱ ማን አስተዋለ? '' ኢሳይስ 53፡ 7 ና ሥራ. 8፤32-33

የህማሙን ሳምንት እንዴት ማሰብ ይጠበቅብናል?

  ምዕመናን ሁሉ ሐጢያታቸውን  በሚናዘዙበት ጊዜ  እውነተኛ ንስሐ  እና መድሐኒዓለም ክርስቶስ ስለ በደላችንና መተላለፋችን የከፈለውን ዋጋ በፍጹም ልብ  ማመንና መቀበል ይገባል፡፡
 ሐጢያት በመጀመሪያ እግዚአብሔር በላከው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ አለማመን ሲሆን በመቀጠል አለመታዘዝን ጨምሮ እንደ ዘፈን፣ ስካር፣ ዝሙት፣ ጣኦትን ማምለክ፣ ጥልና ክርክር የመሳሰሉት የስጋ ስራዎች እንደሆኑ በገላቲያ.5፤16-19 ላይ ተዘርዝሮአል፡፡ ሁሉንም ሐጢያታችንን ለእርሱ ዘርዝረን ስንነግረው በደላችንን  ሁሉ ይቅር ሊለን እንደሚችል በቃሉ ተናግሩዋል፡፡ /1ዮሐ.1፤9/፡፡
 ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒ ሐጢያት እንደሆኑ የሚታወቁ ስንት ጉዳዮች እያሉ ፡ ሐጢያት ተብለው በቃሉ ያልተጠቀሱትን  ለምሳሌ በህማማቱ የሰው እጅ እንደ መጨበጥና፣ ጥራጥሬዎችን መፍጨት ወይም ማስፈጨት ....ወዘተ እንደ ሐጢያት ሆኖ ቀርቦ ብዙ ሰዎች ባለማወቅ ያንን ውድ የሆነ የንስሐ ጊዜን  በትክክል ሳይጠቀሙበት  ሲቀሩ ይታያል፡፡ እርሶ ግን  ከእግዚአብሔር ጋር እውነተኛ  ህብረት ቢያደርጉ እና በግልጽ ሀጢያትዎትን ቢናዘዙ ከበደልዎ ሁሉ ይነጻሉ፡፡
  ከኑዛዜ በሁዋላ ያለው ህይወታችንም የተለወጠ እና ክርስቶስን የሚያከብር እንዲሆን ህይወታችንን ለመንፈስ ቅዱስ መስጠት ይጠበቅብናል፡፡ ዘውትርም በእግዚአብሔር ፊት መጸለይ እና ቅዱስ ቃሉን / መጽሐፍ ቅዱስን/  ማንበብ አስፈላጊ ነው፡፡

                     የሚከተለውን የንስሐ ጸሎት ከልብዎ ሆነው ይጸልዩ!

ጌታ ሆይ እኔ ኃጢያተኛ ነኝ፤ከልጅነት ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ ባለማወቅና በድፍረት የሰራሁትን 

ኃጢያት ሁሉ ይቅር  በለኝ፡፡ጌታ ኢየሱስ ሆይ ስለ እኔ ሐጢያት መከራን እንደተቀበልክ ፣ደምህን 

እንዳፈሰስክ ና እንደሞትክልኝ እምናለሁ፡፡ ስለ ሐጢያቴ በፈሰሰው ደምህ  ከበደሌ ሁሉ አንጻኝ 

፤ልጅህ አድርገኝ፡፡ ከዛሬዋ ዕለት ጀምሬ አንተን  የህይወቴ ጌታና አዳኝ አድርጌ  

እቀበልሀለሁ፡፡በልቤም ላ ይ ንገስ ! ስሜንም በህይወት መዝገብ ላይ ፃፍልኝ በኢየሱስ ክርስቶስ  ስም 

አሜን፡፡"

 ማስታወሻ፡-  ለቤተሰብዎ እና ለጉዋደኞችዎ  ይህንን እውነት ያጋሩአቸው !
                                                                                                                       
                                                                                                                   benjabef@gmail.com

Saturday, March 28, 2015

New Ethiopian Orthodox Sibket By Memehere Asegid Sahelu -Eyesus Ende Cheger

          ወይቤ መጽሐፍ ኩሉ ዘየአምን ቦቱ የሐዩ ሮሜ.10፤11
         / መጽሐፍ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላል፡፡ /

     የጌታችን  የመድሀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክቡር ወንጌል ለምዕመናኑ እያቀረቡ ላሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ልጆች ሁሉ እንጸልይላቸው፡፡ይህ የአቢይ ጾም እውነተኛ ንስሐ ገብተን ከአምላካችን ጋር የምንታረቅበት፣ የህማማቱን ሳምንት ብቻ ሳይሆን ስለ እኛ የታመመውንና የተገረፈውን ጌታ፣ የተሰቀለበትን ቀን ብቻ ሳይሆን ስለ እኛ የተሰቀለልንን ጌታ፣ የተነሳበትን የፋሲካ ቀን ብቻ ሳይሆን ስለ እኛ ሐጢያት ሞቶ የተነሳውን ጌታ፣ የምንቀበልበት ና ህይወታችን የሚለወጥበት መልካም የሆሳዕናና የፋሲካ ጊዜ ይሁንልን !አሜን፡፡

ማሰታወሻ፡- ይህንን መልዕክት ወደ ሌሎች ወገኖች ማስተላለፍዎትን አይዘንጉ፡፡

Friday, March 20, 2015

በ መሪጌታ ጽጌ ና መሪጌታ ሙሴ...






ለቤተሰብዎና ለጉዋደኞችዎ ያጋሩአቸው፤ እውነቱንም ያውቁ ዘንድ ወንጌልን ለህዝባችን ተባብረን እናገልግል፡፡ የወንጌል እውነትን ለመግለጥ ደፋ ቀና ለሚሉት ሁሉ እንጸልይ!
ይህ የተሐድሶ ዘመን ነው!!!

Saturday, March 14, 2015

ቀን ሳለ !

                                        
       . የእድሜህ  ዘመን ስንት ነው ?
     .  የሚሰራበት ቀንና ስለ ማይሰራበት ሌሊት አውቀዋልን?

                 የመግቢያ ጥቅሶች


''....ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ልፈጽም ይገባኛል፡፡ ማንም የማይሰራባት ሌሊት ትመጣለችና፡፡'' ዮሐ.9፤4

''.....አንተ እንድሰራው የሰጠኸኝን ስራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ ፡፡'' ዮሐ.17፤4

 እነዚህ ሁለት  ጥቅሶች የሚያስረዱት የመጀመሪያው የተሰጠንን ተልዕኮ እና ዓላማ በተሰጠን ቀን ቶሎ ልንፈጽመው እንደሚገባ እና በሌላ በኩል ደግሞ ቀኑ አልፎ ማንም ሊሰራባት የማይችልባት ሌሊት እንደምትመጣ ነው፡፡ ከተፈጥሮ እንደምንረዳው ቀን የሚባልና ሌሊት የሚባሉ ጊዜዎች አሉ፡፡መንፈሳዊውም ልክ እንደዚሁ ነው፤ ከተፈጠርንበት ዓላማ ጋር የምንሰራበት ጊዜም አብሮ ይሰጣል፡፡ እርሱን በዋዛ፣ በፈዛዛ ካሳለፍነው ደግሞ ቢመኙም እንኩዋ ከብዙ ነገር አንጻር ምንም ማድረግ የማይቻልበት ጊዜ ይመጣል፡፡
   ቀኖቻችን የተመቻቹ አጋጣሚዎቻችን  ናቸው፡፡ጤናችን አፍላ ጉልበታችን፣ የተትረፈረፈ ሰዓታችን ሊሆን ይችላል፡፡ብዙ ነገሮችን በቀላል መንገድ መስራት የሚያስችሉን የዘመነኛው ቴክኖሎጂዎችም በተወሰነ መልኩ መልካም አጋጣሚዎቻችን ሊሆኑልን ይችላሉ፡፡ ምናልባት አንዳንድ ህጎች፣ፖሊሲዎች...ወዘተ ቀን እንደሆነልን ሊጠቁመሙን ይችላሉ፡፡ ምናልባት ዛሬ ክፍት የሆኑ ነገሮች ነገ ላይዘጉ ፤ ዛሬ እንደልብ ልናገኛቸው የምንችላቸው ነገሮች ነገ  ላይወደዱ የሚችሉበት ምንም መተማመኛ ነገር የለም፡፡ የተትረፈረፈ  ጊዜያችን ነገ ላይ በጭንቅም ላይገኝ ይችላል፡፡መጠቀም ዛሬን ነው፡፡ የምንችለውን ሁሉ አድርጎ ማለፍ !

  ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሰጠው ጊዜ ጨርሶ በሰማይ ወደ ነበረው ክብር እንደሚመለስ ያለውን ነገር ነው የሚያስረዳው፡፡ ተልዕኮን በአንድ በተሰጠ ጊዜ ጨርሶ ፈጸምኩ ማለት እንዴት ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው ?! ጳውሎስም ይህንኑ ነው ያለው .....ሩጫውን ጨርሼአለሁ ...........!

   በሰው ህይወት ሁሉ የምንሰራበት ቀን እና የማንሰራባት ሌሊት አለች፡፡አሁን ቀን የሆነላችሁ ፡ ማለትም ከብዙ ነገር አንጻር ነገሮችን ለማድረግ ዕድሉ የተመቻቸላችሁ፣ በመንገዳችሁ ላይ የይለፍ አረንጉዋዴ መብራት የበራላችሁን......የሚወክል ሲሆን፤ለሌሎች ደግሞ ሌሊት ውስጥ ያላችሁ ትኖራላችሁ ፡፡ ማለትም ምንም ነገር ለማድረግ ነገሮች ያልተመቻቸላችሁ፣ ማድረግ ብትፈልጉም ማድረግ ያልቻላችሁ፣ የጊዜ እጥረት ያለባችሁ፣ በመንገዳችሁ ላይ ቀይ መብራት ስለበራ ማለፍ የማትችሉትን ጭምር ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ቀን ለሆነላችሁ በአግባቡ ጊዜውን እንድትጠቀሙበት ፣ ሌሊት የሆነባችሁ ደግሞ ተመልሶ  በቸርነቱ  ቀን  እስኪያመጣላችሁ በጸሎት በመትጋትና በእምነት ጠንክራችሁ እንድትጠብቁ እመክራለሁ፡፡

 ጊዜ ማለት ውድ ነገር ነው፡፡ የሚቆምበት እግር ያልተፈጠረለት ወፍ እንደማለት ነው ፡፡ ልናቆመውና እንዲጠብቀን ልናደርገው አንችልም፡፡ ለምሳሌ የትናንትናው ቀን   ተመልሶ ሊመጣ ይችላልን ? አይችልም፡፡ ልክ  ከአፋችን እንደወጣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ  /የተቃጠለ አየር/ ነው፡፡ ያስወጣነውን አየር መልሰን ልናስገባ አንችልም፡፡ ተቃጥለው ያለፉ ጊዜዎችም ልክ እንደዚህ  ናቸው ፤ በነበራቸው ጊዜ አንዳች ሳይሰሩበት ከርመው በባነኑ ሰዐት ማጣፊያው ያጠራቸውና የቆጫቸው አያሌ ናቸው፡፡ የሌሊቱ ባህሪ ብዙ ጊዜ ጸጸትንና ቁጭትን ብቻ ነው የሚፈጥረው፡፡

   በዘፍጥረት 47 ላይ ፈረኦን የያዕቆብን ዕድሜ  ጠይቆት ነበረ፡፡ ‹‹..የእድሜህ ዘመን ስንት ነው? ለሚለው ጥያቄው የመለሰው ከቁጥር ጋር ክፉም ጥቂትም የሚሉ ቃላቶች ነበሩ፡፡እነዚህ ቃላት የሚያሳዩት በተለያየ ሁኔታ ስለ ተቃጠሉት ጊዜዎቹ ቁጭቱን ሲገልጽ ነው፡፡ ቢያንስ ሁለት ሰባት ዓመታቶች ሚስትን ለማግባት የተፈጁ እና ንጹህ ስድስት ዓመታት ደግሞ  የግልን ንብረት ለማከማቸት ያለፈ ጊዜ ነው፡፡ በርከት ያሉ የመከራ ዓመታትንም ከስደት ጋር አሳልፉአል፡፡

                         እድሜህ ስንት ነው ?
'' የዘመኖቻችን ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፡፡ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና ፡እኛም እንገሰጻለንና ፡፡''መዝ.90፤10

በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በርካታ ክፍሎች ላይ ስለ እድሜያችን የተጠቀሱት ጥቅሶች የሚያስገነዝቡን ዕድሜያችን እምብዛም የሚያደላድል ና የሚያስፋፋ ነገር እንዳልሆነ ነው፡፡ በጣም ብዙ ዘመን እንደቀረው ሰው እንዳንኖር ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ነገር ግን የሆነ ዓላማ ግን ፈጽመን ልናልፍበት እንችላለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ  ውስጥ ስለ ዕድሜያችን ምን እንደተባለ ቀጥለን ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
  •  ዘመኖቻችን እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ፡፡ መዝ.90፤9
  •  በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፡፡ መዝ.39፤6
  •  ህይወታችሁ ምንድን ነው ? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ሁዋላ እንደሚጠፋ እንፉዋሎት ናችሁና፡፡ ያዕ.4፤1
  •  .....እንደ ተን.....መዝ.38....
  • እንደ ሸማኔ መጠቅለያ፡፡ ኢሳ.38፡12
  •  
    ከላይ የተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የሚያስረዱን ዘመኖቻችንን /'ዕድሜዎቻችንን'/ በቁም ነገር ላይ ካላዋልነው ና ለአንድ ለታለመ ዓላማ ካልተጠቀምንበት ዝም ብሎ ሊያልፍ የሚችልም ነገር እንደሆነ ጭምር ነው፡፡ እግዚአብሔር እድሜን የሰጠን በአቅማችን ሰርተን ማለፍ ካለብን ዓላማ ጋር ነው፡፡ በተለይ ሰዎችን ከዘላለም ሞት ከማዳን ዓላማ ጋር የተያያዘው ደግሞ የላቀው ነው፡፡አለዚያ ዘመናችን ውስን በሆኑና እዚህ ግቡ በማይባሉ አልባሌ ነገሮች ሊያልቁ ይችላሉ፡፡ ስንት ነገር መስራት የሚችል አዕምሮ በዋል ፈሰስ የቀረበት፣ የተፈጠሩበትን ዓላማ ሳያሳኩ ጊዜ ያለፈባቸው፣ ኸረ እንደውም የቀበርናቸው ስንት ናቸው፡፡ ከሚያሳሳው ጉልበታቸው ጋር፣ ችሎታና ብቃታቸው ጋር ያለፉትን ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ግን አሁንም ያልረፈደብን በርካቶች አለን፡፡ ቃሉ እንደሚል '' ደስ አያሰኙም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፡ ብርሐን ወደ ጨለማ ሳይቀየር...ስጋም ወደ አፈሩ ሳይመለስ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ፡፡'' መክ. 12፤1-8፡፡

ሰዎችን ከማዳን ጎን ለጎን  ግን ህጻናትን የማሳደግ፣  ድሆችን የመመገብ፣ አረጋውያንን የመንከባከብ፣ የአካባቢና የተፈጥሮ ጥበቃን የመሰለ፣ ሌላም ሌላም ህብረተሰብን የሚጠቅም በጎ ራዕይ ሰርቶ ማለፍ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በርካቶች ይህንን አድርገዋል፤ እያደረጉም ያሉ አሉ፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የሰዎች ዕድሜ ላይ የሚያጠና አንድ ምሁር ሰዎች  የምድር ዘመን ቆይታቸው ሰባ ዓመት ቢሆን በዋናነት ዕድሜያቸውን በምን ጉዳይ ፈጅተውት እንደሚያልፉ በጥናት ካሰፈረው ነገር  ቀጥለን እናያለን፡-
  • ለእንቅልፍ 23  ዓመት / 32% /
  •  ለስራ 16  ዓመት  / 22% /
  •  የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመከታተል 8 ዓመት / 11%  /
  •  በመመገብ 6 ዓመት / 8.6% /
  •  በመጉዋጉዋዝ 6 ዓመት / 8.6%  /
  •  በመዝናናት 4.5 ዓመት / 6.5% /
  •  በተለያየ ህመም 4 ዓመት / 5.7%  /
  •  በመልበስ  2 ዓመት / 2.8% /
  • እንደ ጸሎት ያሉ የዓምልኮ ስርዐትን በመፈጸም 0.5 ዓመት / 0.9% /
      በእርግጥ አንዳንዶቹ እንደየ አካባቢው ሁኔታና እንደየ ህብረተሰቡ ዓይነት ሊለያዩ የሚችሉ ነገሮች ቢሆኑም፤አብዛኞቹ  ግን በብዙዎቻችን ህይወት ያጋጠሙና እያጋጠሙ ያሉ ነገሮች ናቸው፡፡ ከዚህም ውጪ ጊዜዎቻችንን በደንብ አድርገው እየጎመዱ ያሉ ነገሮች አይጠቀሱ እንጂ እንዳሉ እሙን ነው፡፡ እስኪ ጥቂት ጊዜ ወስደው የእርሶን ጊዜ በአብዛኛው እየፈጀ ያለ ጉዳይ ምን እንደሆነ ያስቡና ፡ በዓመት ያስሉት ፤ ከዚያ ወደ ሰባ ዓመት ይቀይሩት፡፡ በእርግጠኝነት  አንድ ነገር ይማሩበታል፡፡ በቀን የሚጸልዩትን ሰዐት ወደ ወር ፣ ደግሞ ወደ ዓመት ቢቀይሩም በጌታ ፊት ምን ያህል ጊዜ በዘመንዎ እንዳጠፉ ማወቅ አይቸግርዎትም፡፡  የተፈጠርንበትን ዓላማ በተሰጠን ዕድሜ በትክክል ፈጽመን እንድናልፍ እግዚአብሔር ይርዳን ! ጊዜያችን በከንቱ ያለቀብንና ዕድሜያችን የገፋም ካለን ፡ ምንም የማየይሳነው ጌታ ተምችና ኩብኩባ የበላብንን ዓመት እንዲ መልስልን ብንማጸነው ፣ ወይም እንደሶምሶን አንድጊዜ እንዲያስበንና የመጨረሻ ስራ ሰርተን እንድናልፍ ብንጠይቀው መልካም ነው፡፡ በእግር ኩዋስ ዓለም ያለ ምንም ግብ 90 ውን ደቂቃ ከጨረሱ በሁዋላ፡ በባከነ ሰዐት ግብ አስቆጥረው ፣ ድል  አድርገው እንደሚወጡት ቡድኖች  ሊሆን ይችላል፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በነገር ሁሉ ያግዘን ፡፡ አሜን፡፡

ማስታወሻ፡-  ውድ ጊዜያቸውን ለከበረ ዓላማ እንዲያውሉት ለሚሳሱላቸው ሰዎች ይህንን  መልዕክት ያጋሩአቸው፡፡
                                                                                                     
                                                                                                benjabef@gmail.com

New Ethiopian Orthodox Preaching by Memhir Asegid- ነፍሴ የወደደችዉን አገኘሁት

Friday, March 6, 2015

የጻድቃን ምልጃ

ስለ ጻድቃን እና መላዕክት  ምልጃ  ......
/ከአማላጅነት ክፍል አንድ ላይ የተወሰደ፡፡ ሙሉውን ከዚያ ላይ ያንብቡት!/

ጻድቃን በምድር ሳሉ በምድር ላይ ገና በህይወት ላሉት ሰዎች ሊጸልዩ ና ሊያማልዱ ይችላሉ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያምም አማልዳለች፡፡የሰዎችን ጉዳይ ለልጁዋ ነግራለች ከዚህም በላይ ከበጉ ሐዋርያት ጋር አብራ ጸልያለች፡፡ምናልባት ወንጌል ገና ስላልደረሰበት የአለም ክፍሎች አሳስበው ይሆን?  ሌላም ብዙ የሰዎችን የተወሳሰበ ጉዳየ ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ቀርበው ይሆናል፡፡ምን እንደ ጸለዩ ነው እንጂ የማናውቀው መጸለያቸውን እናውቃለን፡፡ሐዋ. ስራ 1፤14፡፡

አለምን ሁሉ ከአብ ጋር የማስታረቅና የማዳን ስራ ግን የተሰራው በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራ በመሆኑ፤ ጻድቃንም ሆኑ ሰማዕታት ሰዎችን የማዳንም ሆነ መንግስተ ሰማይ የማስገባት ስልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ የዘላለም ህይወት ጉዳይ እንዲህ ቀላል ነገር ቢሆንማ ኖሮ  ክርስቶስ መጥቶ ባልተሰቀለ፤ያን ሁሉ ዋጋ ባልከፈለ ነበር፡፡ እርሱ በስጋ ሳይወለድ እኮ ነብያት፣ አባቶች፣ ነበሩ፡፡ግን መዳን በእነርሱ በኩል ሊፈጸም የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ ነው የጌታችን መምጣት የግድ የሆነው፡፡

ከመዳን ጉዳይ ባሻገር ለተለያዩ ጉዳዮችም ቢሆን የሞቱ ቅዱሳን በህይወት ስላሉት ሊለምኑና የሰዎችን ጸሎት ሁሉ ሊሰሙ  እንዴት ይችላሉ? በመጀመሪያ ከፈጣሪ በስተቀር ሁሉ ፍጡራን  ናቸው፡፡ምድራዊ እናትና አባት ኖሮአቸው የተወለዱ በጊዜና በስፍራ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው መሞታቸው፡፡ ከላይ ሆነው ሁሉን ማየት እንደ እግዚአብሔር ከቻሉ እኮ: መለኮት ሆነዋል ማለት ነው ፤ግን እንደዛ አይደለም፡፡

              መላዕክት

በዚሀም ላይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ እልፍ አዕላፋት የሆኑት፤ አንድ መልዐክ ሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘት ስለማይችልና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መስማት ስለማይችል ነው፡፡ለምሳሌ አብሳሪውን የጌታ ታማኝ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤልን እንውሰድ ዕለተ ቀኑ በሚባለው 19 ምናልባት ታህሳስ 19  ንግስ ተብሎ በሚነገረው ቀን ፤ካሉት በርካታ በስሙ የተሰየሙ አብያተክርስቲያናት መካከል መርጦ የሚገኘው የትኛው ክልል ነው? የትኛውስ ቤተክርስቲያን ነው? ምክንያቱም አንድ ነው ብለናል፡፡ ሁሉን መቻል / Omnipotent /፣ ሁሉን ማወቅ / Omniscience  /፣ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት / Omnipresent    / የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ባህሪ ነው፡፡ሁሉም ጻድቃን፤ መላዕክት ሁሉን ማወቅ፤በሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘትና የሁሉን ሰው ጸሎት ማድመጥ የሚችሉ ከሆነ እግዚአብሔር የሚባለው አምላክ ምን ልዩነት አለው ታዲያ?  ነገር ግን እውነቱ እነዚህ ባህርያት ማንንም ያላጋራበት የስላሴ ብቻ የሆነ ነው፡፡ ስላሴን የተለየ የሚያደርጋቸውም ይህ ባህሪ ነው፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ገብርኤል የኢየሱስን እናት ማርያምን ሊያበስራት የመጣ ጊዜ እርሱን ሌላ ቦታ ማግኘት አይቻልም፡፡ ምናልባት በዚያ ጊዜ አጣዳፊ ጉዳይ ካለ እንኩዋ ሌላ መልአክ ነው የሚላከው:: ምክንያቱም አንድ መልዐክ መገኘት የሚችለው በአንድ ቦታ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ወደ ዳንኤል መልስ ይዞ  እየበረረ ይመጣ የነበረውን መልዐክ  /አንዳንድ ሰዎች ገብርኤል  እንደሆነ ይላሉ/  የፋርስ አለቃ  (የፋርስ መንግስት አገር  ላይ በአየሩ ላይ አለቃ የነበረ አጋንንት) እንዳያልፍ ከልክሎት እንደነበር፤ ለ 21 ቀናትም ተቸግሮ እንደነበር ማወቁ ጥሩ ነው፡፡በሁዋላም ወደ ዳንኤል መምጣት የቻለው የመላዕከት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው ስለመጣ ነበር /ዳን.10፤13-20/፡፡ መላዕክት ሲላኩ በቦታ በስፍራ የሚወሰኑ መሆናቸውን ተመለከታችሁ? እንዳይመጣ ተከልክሎስ እንደ ነበረ አያችሁ?

መላዕክቶችም ሆኑ ቅዱሳን ወደ ጠሩአቸው ሁሉ የመሄድ፣ እንደወደዱ የማድረግ ማንነት አይደለም ያላቸው፡፡ መላዕክትነታቸው ለእግዚአብሔር ነውና እርሱ ወደ ላካቸው ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ እርሱ ያዘዛቸውንም ይፈጽማሉ፡፡ ይህን እውነት ማወቅና መናገር እነርሱን ማዋረድ ማለት አይደለም፡፡ በፍጹም እነርሱን ዝቅ ማድረግም አይደለም፡፡ እውነት አርነት ያወጣል፡፡አብርሐም ቤት የመጡት መላዕክት አብርሀም ቤት ጉዳያቸውን ሲፈጽሙ ነው  ሎጥ ዘንድ ሰዶም የሄዱት፡፡

ከመጀመሪያው ግን ከዘላለም  ሞት እንዲያድኑንና እንዲያስታርቁን ተሹመው በነበረ ፡አለመታዘዛችን ነበር ሀጢያት የሚሆን፡፡እነርሱም ብዙ በታዘቡን ነበር፡፡ አሁን ግን ከገረማቸው እንኩዋ  ሊገርማቸው  የሚችለው እነርሱ  ለእረኞች ያበሰሩትን ጉዳይ ያለመታዘዛችንን ሲያዩ ነው  /ሉቃ.2፤9-14/፡፡ የፃድቃንም አግራሞት ለእነርሱም መደሀኒት ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ አለማተኮራችን ነው፡፡ ቅድስት  ማርያምም ከገረማት እንኩዋ የሚገርማት ‹አርሱን ሰሙት›  ያለችውን፣ መድሀኒቴ አምላኬ ባለችው ልጁዋ አለማመናችን ነው፡፡ስለ ሁሉም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በመስቀል ላይ ስለ ከፈልክልኝ ዋጋ አመሰግንሀለሁ፡፡በቀራንዮ መስቀል በፈሰሰው ደምህ ሀጢያቴን እጠብልኝ ከበደሌም አንጻኝ፤ወደ ልቤም ገብተህ አብረኸኝ ኑር በማለት ከልባችን  ንስሀ  እየገባን በመጸለይ   ራሳችንን ለመንግስተ ሰማይ እናዘጋጅ፡፡የጌታችን ዳግም ምፅዐት ቀን ተቃርቡዋል፡፡ ከእግዚአብሔር በኩል ያለው ነገር ሁሉ ተሰርቶ አልቁዋል፤ ከእኛ በኩል የቀረውን እናድርግ!! ሰምተን እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡

አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ ከስር አስተያየት መስጫ ሣጥኑን  / COMMENT   / ተጭነው ይጻፉ፡፡






Monday, March 2, 2015

አገልጋይና አገልግሎቱ

የዛሬው  ፅሑፍ እ.ኤ.አ. February, 2012 በአንድ አካባቢ ለተገኙ የአብያተ- ቤተክርስቲያናት  መሪዎችና አገልጋዮች ጉባኤ ላይ፡ ስለ አገልጋይና አገልግሎቱ  ለሚያነሱት ሰፊ ውይይት ለመነሻነት ባቀረብኩት ጽሁፍ  ላይ መጠነኛ ነገር ተጨምሮበት የቀረበ ነው፡፡

የንባብ ክፍል ገላቲያ 2፤1-10
    '' ከዚያ ወዲያ ከአስራ አራት ዓመት በሁዋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአህዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኩዋቸው፤ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኩዋቸው፡፡ ''

በክፍሉ ላይ እንደ ተመለከተው ሐዋርያው ጳውሎስ እራሱንና አገልግሎቱን ያስፈተሸበት ታሪክ ነው፡፡ ከዳነ  ከ14  ዓመታት በሁዋላ ወሳኝ የሚባሉ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ጠይቁዋል፡፡

1ኛ-በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን ? የሚልና

2ኛ-ደግሞ ምናልባት በከንቱ እንዳልሮጥ

 የመጀመሪያው አሳብ ለዓመታት የሄደበትን፣ የደከመበትን ሩጫና አገልግሎት ማስገምገሙ ሲሆን ፣ሁለተኛው ግን ያለፉት የአገልግሎት ሩጫዎች በከንቱ የነበሩ እንኩዋ ከሆነ ፤ቀጣዩ ግን ትክክለኛና የሰመረ እንዲሆን ፣ እግዚአብሔርም የሚከብርበት እንዲሆን የታሰበ ነው፡፡ ስለዚህም እስከዛሬ ድረስ የሚሰብከውን ወንጌል ለዋነኞቹ ሐዋርያት በዝርዝር በማቅረብ ትክክል እንደሆነና እንዳልሆነ አስገምግሞአል፡፡

  ለመሆኑ ሐዋርያትስ ምን አሉት? እነርሱማ ነገሩን በመንፈስ ከመዘኑት በሁዋላ በአገልግሎቱ ውስጥ የተሳሳተ ወይም  ከእውነት ጋር የተቃረነ ነገር ስላላገኙበት፡ በርታ ፣ቀጥል ብለው ቀኝ እጃቸውን ሰጥተውታል፡፡በብዙ አስገራሚ መንፈሳዊ ልምምዶች ውስጥ የከረመና መለኮታዊ ሚስጥራትን  በመግለጥ የሚታወቀው ፣ለበርካታ አብያተክርስቲያናት መተከል ፣መታነጽ ና ማደግ ምክንያት የሆነው፤ከዚህም ሌላ ከ13 የማያንሱ ፡ከግማሽ በላይ የአዲስ ኪዳን መጻህፍቶችን የጻፈ ሐዋርያ፣ እራሱንና አገልግሎቱን  አቅርቦ ካስገመገመ፣ ቆም ብሎ ከጠየቀ? እኛማ ይልቁን እንዴት አብዝተን ማድረግ ይጠበቅብን ይሆን?

አገልግሎትን ስናስብ በ1ኛ ጢሞቲዎስ ም.3 ቁ.1 ላይ ያለው ቃል ትዝ ሊለን ይችላል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካም ስራን ይመኛል፡፡'' ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚናገሩት የዚያን ጊዜ የነበረው አገልግሎት አገልጋይነትን የሚያስመኝ ዓይነት አልነበረም ይላሉ፡፡ ስለዚህም በዚያ የጠበበ በር ሾልኮ ለመግባትና እነዚያን የማይመቹ ሁኔታዎች አልፎ ለማገልገል የሚመኝ ካለ ፡መልካም እንዳደረገ ለመግለጽ ነው፡፡ ቃሉ የሚመኝ ስላለ ብቻ አገልግሎት በምኞት የምንገባበት ነው ማለት አይደለም፡፡ የተመኘም ሁሉ የሚከናወንበትም አይደለም፡፡ አገልግሎት የጥሪ ፣ የሸክም ጉዳይ ነው፡፡ የተጠሪው ብቻ ሳይሆን የጠሪውም ሙሉ ፈቃድ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

አገልጋይነት  ሌሎች ለኛ እንዲኖሩ ፣ ሌሎች ለኛ እንዲሰሩ የምናዝበት ሳይሆን፤ከስሙ እንደምንረዳው ሌሎችን ማገልገል ማለት ነው፡፡ ለሌሎች መዳን ፣ጥቅምና ትርፍ መድከምን ያሳያል፡፡ ጌታችን እንደ ተናገረው '' የሰው ልጅ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ  ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም፡፡'' ብሎአል ማር.10፤45፡፡ ደግሞ በሉቃስ ወንጌል ም.22 ቁ.27 ላይ '' ..እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ ፡፡ '' ብሎ ተናግሩዋል፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የአገልጋይነትን ትክክለኛ ትርጉም የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ነፍስን ቤዛ ማድረግ  እንኩዋ ቢቀር ባለን ጸጋ፣ ሙያ፣ ክህሎት ሁሉ ለብዙዎች ቤዛ መሆን እና  ክብርና ሙገሳን ሳይፈልጉ በሰዎች መካከል እንደ አገልጋይ መኖርን ግን ያካትታል፡፡

 ከዚህ ቀጥለን አንዳንድ መንፈሳዊ ሰዎች ስለ አገልግሎት የተናገሩትን ነገር እንመለከታለን፡-
  • አንድ ምሁር ስለ አገልጋይነት የተናገረው እንዲህ ነበር '' አገልጋይ ማለት ሰዎች ሊሰሩ የማይፈልጉትን ነገር እንዲሰሩ ማድረግና ፣የሚሰሩትንም ነገር እንዲወዱት የማድረግ ችሎታ ነው '' ብሎአል፡፡
  • አንድ ሌላ ዶክተርም እውነተኛ አገልጋይ ማለት መንገዱን የሚያውቅ ፣ከመንገዱ ሳይዛነፍ ወደ ፊት የሚገሰግስ ና ከሁዋላ  ያሉትንም ሰዎች ወደ ፊት የሚስብ ነው ብሎአል፡፡
  •  ሞንት ጎመሪ የተባለ የጦር አዛዥ የነበረ ሰው እንደ ጻፈውም '' ሰዎችን የመማረክ  ችሎታ የሚወሰነው ፡ሰውየው ባለው መልካም ባህሪያት መጠን ይሆናል፡፡ የማነቃቃት ፣የማበረታታትና ሰዎችን የመሳብ ችሎታ ካለው  ሰዎችን ይማርካል'' ብሎአል፡፡ ሌሎችም በርካታዎች ስለ አገልጋይና አገልግሎት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጽፈዋል ፡ተናግረዋልም፡፡

  እንዲያው ለመሆኑ አገልጋይ እና አገልግሎቱ  ስንል የቱን ማለታችን ነው? የተባለ እንደሆነ፤የቃሉን ሰባኪና አስተማሪ ማለታችን ነው፤ ህዝቡን የሚመግቡ መጋቢዎችንና የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን ማለታችን ነው፤ ደግሞ የጋብቻ ና የተለያዩ መንፈሳዊ ጉዳይ  አማካሪዎችን ማለታችን ነው፤ የውስጥ ና የውጪ የሙሉ ጊዜ እና የትርፍ ጊዜ አገልጋዮችን ማለታችን ነው፡፡ሌሎችንም እንደ ድቁንና፣ የጸሎት፣ ዝማሬ፣ የህጻናት አገልጋዮችንና የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡
እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ስናነሳ ለዛሬ ትኩረታችን ወደ ሆነው ወደ ሌላው ተከታዩ ሐሳብ እናመራለን፡፡ብዙዎች እንደሚስማሙት አገልግሎትም ሆነ አገልጋዮች ላይ ከፊት ይልቅ ጠንከር ያለ ተግዳሮት በዝቶባቸዋል፡፡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፣ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችም አሉ፡፡ እንደውም አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች  እንደሚናገሩት ፡ አንድ የሆነ ሪቫይቫል ካልመጣ ወይም በሆነ መንገድ መለኮታዊው ጣልቃ ገብነት ካልተከሰተ በቀር፡ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ ሊያሽቆለቁሉ ይችላሉ ብለው ይፈራሉ፡፡

   መድረኮቻችን፣ የጊዜ አጠቃቀማችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውቀታችን ውስንነት፣ የንባብ ፣የጸሎት ህይወታችንና ልምምዳችን አጠቃላይ ከዕለት ዕለት እየቀነሱ እና በሌሎች ጊዜን በሚወስዱ እንደ ፌስቡክ፣ ድራማ፣ ፊልም፣ ሌሎች መዝናኛዎች እየተፈተኑ እንዳለ በርካታ ክርስቲያኖች ስለራሳቸው ጭምር ይናገራሉ፡፡ የ '' መድረኮቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ '' ፀሐፊም በመጽሐፋቸው ውስጥ ሊጠቁሙን የሞከሩት ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ከቃሉ ውጪ የሆነ አደራረግ ና ልምምድ በዝቶአል፤ የሚያምነውም የማያምነውም  አላማኝ  ስለ አገልጋዮችም ሆነ ስለ አገልግሎቱም ሁኔታ አጥብቆ እየጠየቀ ነው ብለዋል፡፡ እንዲያው ባጠቃላይ የት እንደምንገኝና ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ ለመጠቆም ያህል ጥቂት ጥያቄዎችን መጠየቅ አግባብ ይሆናል፡

  •  አሁን ያለው አገልጋይ ወደ ፊት ልጁ  /ለልጆቹ/ እንደ እርሱ አገልጋይ እንዲሆን  ይፈልጋል ወይም ይመኛልን?
  •  የተሻለ የሚባልና የሚያማልል ነገር ከዓለም ቢያገኝ ጥሪዬ፣ አገልግሎቴ ይበልጥብኛል ብሎ የቀረበለትን መደለያ  እምቢ ለማለት አቅም አለው ወይ?
  •  ህይወት እንደገና እንዲጀምር ቢደረግ ስንት አገልጋይ መልሶ አገልጋይነትን ይመርጣል?
  •  በአሁኑ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ለአገልጋይ ይድራሉ ወይ? በዚህስ ክብር ይሰማቸዋል ወይ?
  •  የቤተ ክርስቲያን አመራርና ሽማግሌዎችን ቁጣ በመፍራት ወይም የደሞዝ መቆረጥ ስጋት ሳይሆን በጥሪና በሸክም የሚያገለግል፣ያልዳኑ ሰዎች ጉዳይ፣ደቀ መዝሙር ያልተደረጉ ምዕመናን ሰዎች ጉዳይ ፣ የተለያዩ  እንቆቅልሻቸው ያልተፈታ ሰዎች ጉዳይ ዘንድሮም ከልቡ አሳስቦት የሚጸለይ እና ርምጃ የሚወስድ፣ የሚተጋ ስንት ነው?
  • ዘንድሮ በራሱ ተነሳሽነት የተሰጠውን ሀላፊነት ሁሉ በትጋት የሚወጣ ና ጌታን ሰምቶ ነገሮችን በቅን ልብ  የሚያደርግ አገልጋይ ስንት ነው?
እነዚህ  ነገሮች የሚመለከታቸው በትክክል ጥሪና ሸክም  እንዳላቸው ተፈትሾ ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት ያሰማራቻቸውን ሲሆን፤ አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደሚናገሩት በትክክል ጥሪው መጥቶላቸው ሳይሆን ፡እንዲሁ ያለ እውነተኛ ሸክም ገብተው በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ 

 መቼም ለየትኛውም የሙያ ስራና አገልግሎት ለሚታጩ ሰዎች የየራሳቸው መመዘኛዎች አሉዋቸው፡፡ አንዳንድ መመዘኛዎች ወደ ሰዎቹ ወደ ራሳቸው ጥቅም የሚያደላ  ሆኖ ተገኝቶአል፤ ለእግዚአብሔር ቤት በትክክል የሚያደሉና ስራው በትክክል እንዲሰራ የሚናፍቃቸው እውነተኞችም አሉ፡፡ ለሁሉም መመዘኛ መኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ከነገ  ወቀሳ  ያተርፋል፡፡ ችግሩ መመዘኛችን እውነተኛና ከጥሩ ሞቲቭ መመንጨታቸው ላይ ነው፡፡ በመቀጠል ምናልባት ይጠቅም እንደሆነ ፡አንድ  ዶክተር የተማሪዎቹን ክህሎት ይመዝንበት የነበሩ ወደ ዘጠኝ ያህል ጥያቄዎች  ቀርበዋል  / ከአንድ መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ ናቸው፡፡/ ተጠቀሙበት!

  1. ትናንሽ የሆኑ ነገሮችን ደህና አድርጎ ይሰራልን?
  2. ቅድሚያ መስጠት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረድቶአልን?
  3.  የዕረፍት ጊዜውን በአገግባቡ ይጠቀምበታልን?
  4.  ሥራውን በንቃት መንፈስ ይሰራልን?
  5.  የዕድገት ዝንባሌ የሚታይባቸውን ሥራዎች መርጦ ሊጠቀምባቸው ይችላልን?
  6. የማደግ  ዝንባሌ ይታይበታልን?
  7.  ተስፋ  የሚያስቆርጡ ነገሮች ሲገጥሙት እንዴት ነው?
  8.  አስቸጋሪ ነገሮችን እንዴት ይፈታቸዋል?
  9.  ድክመቶቹን ያውቃቸዋል?  ከዚያስ ምን ያደርጋል?
 እኛስ እንደ አገልጋይ ለዋና ነገራችን ፣ለጥሪ ቦታ ከመስጠት አንጻር ፣ከመታዘዝ  ህይወት፣ጊዜን በአግባብ ከመጠቀም አንጻር ፣ ለማደግ ከመፈለግ፣ በመከራዎችና በፈተናዎች ከመጽናት አንጻር ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በብቃት ከመወጣትና ትግሎችን በመልካም ከማሸነፍ አንጻር  እንዴት ነን?
  ነገሮቻችን ከላይ በተገለጸው መሰረት ነጥረው እንዳልወጡ የሚያሳብቁብን አንዳንድ ጉዳዮች  አሉ፡፡ ዓለም በድህረ ዘመናዊነት፣ በዘመናዊነትና በረቀቀ ዓለማዊነት በምትታመስበት ወቅት ይህም አንዳንድ ጊዜ ሾልኮ በቤተክርስቲያንም ጭምር እየታየ ባለበት ወቅት፡ የቤት ስራችንን በጊዜ ለመስራት ካልተነሳን ወደ ፊት የሚጠብቀን ተግዳሮት ቀላል አይሆንም፡፡ የእኛ ይህንን ለመመከት ዝግጅት አለማድረግ እና በነገሮች ላይ ነቅቶ ቶሎ እርምጃዎችን ያለመውሰድ፡ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሄዱ ያሰጋል፡፡

 የምንፈራውና የምንሰጋበት ነገር እንዲብስ ያደረገው፡ በተለይ አሁን ላለው ትውልድ የቀረበለት ምርጫ በርካታ መሆኑ ሲሆን፤አብዛኞቹ ምርጫዎች እንኩዋን በህይወት ሊያኖሩት ቀርቶ፤ ተመልሶ የእውነት እና የቤተክርስቲያን ጠላት እንዲሆን ሊያደርጉት ስለሚችሉ ነው፡፡ ተጠናክሮ በመጣ መንፈሳዊ መሰልና ባልሆነ ጎርፍ ትውልዱ እንዳይወሰድ ምን ማድረግ ይገባናል? ብለን ማቀድ አለብን፡፡ ቢያንስ ሁሉም የቤተክርስቲያን አባል የሆነ ሁሉ በትንሹ አስርቱ ትዕዛዛትን ፣ ወንጌላትን በቅጡ እንዲያውቅ ፣ የጥምቀት ስርዐት ፣ የጌታ እራት ስርዐት ምን እንደሆነ፤ ስለ አምልኮ፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ ጾምና ጥሞና የምናሳውቅበት መንገድ  ማመቻቸት የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡

  በአሁን ሰዐት በተለይ ወጣቱ  በአውሮፓ እግር ኩዋስ ተጫዋቾች ፍቅር የተያዘ ወይም በሆሊ ውድ አክተሮች ፍቅር የተነደፈ ነው፡፡ ስለ እነርሱ ማንነት ፣ሁኔታ ፣ደሞዛቸውን ፣ዝውውራቸውን እየተከታተለ ፡ ደግሞ ለሌሎች አንዳች ሳያዛንፍ እያብራራ ነው ያለው፡፡ ስለ ወንጌል እና ከላይ ስለ ጠቀስናቸው፣ ህይወቱን ስለሚጠቅሙት ጉዳይ፡ ምንም መሰረታዊ ዕውቀት አልያዘም፡፡ በእርግጥ ሁሉም የቤተክርስቲያን ችግር ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንዱ የቀረበላቸውን ማዕድ በመግፋት ነው ለዚህ የተዳረጉት፡፡ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የቀረበበት መንገድም ብዙ የሚስብ ና ትውልዱን በሚማርክ መንገድ  ስላልሆነ  ነው የሚሉም አሉ፡፡  ብቻ ለሁሉም ቢያንስ መሰረታዊውን የደህንነት ዕውቀት ፣ ጌታ ለምን እንደመጣ? ፣ለምን እንደተሰቀለ?፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሳኤው እንዳያውቅ፤ ስለ ሚከተለው እምነት ምንነት እና ምክንያት ለሌሎች የሚያስረዳበትን ዕውቀት እንዳይጨብጥ ችግር የሆነበትን ምክንያት ማወቅ አለብን፡፡ ምናልባት ቤተክርስቲያን በመጽሀፍ ቅዱስ ዕውቀት የደረጁ አስተማሪዎች የላት ይሆን? ወይስ አሁን ያሉ መሪዎች ይህ ጉዳይ ብዙም የሚያሳስባቸው ስላልሆነና በሌላ ነገር ባተሌ ሆነው ይሆን ? ወይስ ሌላ ተጠያቂ  የሚሆን /ምክንያት/ ይኖር ይሆን ? እሺ ችግራችን ምንም ይሁን!  ከእንግዲህ ምን እናድርግ ? ቢያንስ ጥቂት መፍትሔዎችን ቀጥሎ  ፈንጠቅ ለማድረግ ተሞክሩዋል፡፡

  • አገልግሎት እየሰለቸን ሳይሆን ደስ እያለን ከሌሎች ጋር የምንሰራበትን ሁኔታዎች ቢመቻች
  •  የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና የዘርፍ መሪዎች በሁሉም መንገድ ብቃት እንዲኖራቸው የሚያድጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ፤ለምሳሌ በስልጠና ፣ ስነ መለኮት ትምህርት ቤት በመላክ ፣ እርስ በርስ የልምድ ልውውጦችን በማድረግ፤
  •  ለመሪዎችና ለአገልጋዮች ስለ አገልግሎታቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ኑሮአቸውም ማሰበ፤
  • በቤተክርስቲያን ምስባክ ላይ እየቀረቡ ያሉ መልዕክቶች  ሁሉ አቀፍና የተመጣጠኑ ስለ መሆናቸው ፤ ደግሞ ጠቃሚነታቸውን በየተወሰነ ጊዜ መገምገም፤
  •  የተሰማሩ ግን ጥሪና ሸክም የሌላቸውን ለይቶ ማወቅ፣ ጥሪው ያላቸውን ደግሞ ያልተሰማሩትን በተቻለ መጠን ማሰማራት የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ  ናቸው፡፡
ማስታወሻ፡- ማናቸውም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ለሆኑ ሁሉ እንዲጠቀሙበት ሊልኩላቸው ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ይባርክዎ!

                                                                                 benjabef@gmail.com