Friday, March 6, 2015

የጻድቃን ምልጃ

ስለ ጻድቃን እና መላዕክት  ምልጃ  ......
/ከአማላጅነት ክፍል አንድ ላይ የተወሰደ፡፡ ሙሉውን ከዚያ ላይ ያንብቡት!/

ጻድቃን በምድር ሳሉ በምድር ላይ ገና በህይወት ላሉት ሰዎች ሊጸልዩ ና ሊያማልዱ ይችላሉ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያምም አማልዳለች፡፡የሰዎችን ጉዳይ ለልጁዋ ነግራለች ከዚህም በላይ ከበጉ ሐዋርያት ጋር አብራ ጸልያለች፡፡ምናልባት ወንጌል ገና ስላልደረሰበት የአለም ክፍሎች አሳስበው ይሆን?  ሌላም ብዙ የሰዎችን የተወሳሰበ ጉዳየ ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ቀርበው ይሆናል፡፡ምን እንደ ጸለዩ ነው እንጂ የማናውቀው መጸለያቸውን እናውቃለን፡፡ሐዋ. ስራ 1፤14፡፡

አለምን ሁሉ ከአብ ጋር የማስታረቅና የማዳን ስራ ግን የተሰራው በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራ በመሆኑ፤ ጻድቃንም ሆኑ ሰማዕታት ሰዎችን የማዳንም ሆነ መንግስተ ሰማይ የማስገባት ስልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ የዘላለም ህይወት ጉዳይ እንዲህ ቀላል ነገር ቢሆንማ ኖሮ  ክርስቶስ መጥቶ ባልተሰቀለ፤ያን ሁሉ ዋጋ ባልከፈለ ነበር፡፡ እርሱ በስጋ ሳይወለድ እኮ ነብያት፣ አባቶች፣ ነበሩ፡፡ግን መዳን በእነርሱ በኩል ሊፈጸም የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ ነው የጌታችን መምጣት የግድ የሆነው፡፡

ከመዳን ጉዳይ ባሻገር ለተለያዩ ጉዳዮችም ቢሆን የሞቱ ቅዱሳን በህይወት ስላሉት ሊለምኑና የሰዎችን ጸሎት ሁሉ ሊሰሙ  እንዴት ይችላሉ? በመጀመሪያ ከፈጣሪ በስተቀር ሁሉ ፍጡራን  ናቸው፡፡ምድራዊ እናትና አባት ኖሮአቸው የተወለዱ በጊዜና በስፍራ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው መሞታቸው፡፡ ከላይ ሆነው ሁሉን ማየት እንደ እግዚአብሔር ከቻሉ እኮ: መለኮት ሆነዋል ማለት ነው ፤ግን እንደዛ አይደለም፡፡

              መላዕክት

በዚሀም ላይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ እልፍ አዕላፋት የሆኑት፤ አንድ መልዐክ ሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘት ስለማይችልና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መስማት ስለማይችል ነው፡፡ለምሳሌ አብሳሪውን የጌታ ታማኝ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤልን እንውሰድ ዕለተ ቀኑ በሚባለው 19 ምናልባት ታህሳስ 19  ንግስ ተብሎ በሚነገረው ቀን ፤ካሉት በርካታ በስሙ የተሰየሙ አብያተክርስቲያናት መካከል መርጦ የሚገኘው የትኛው ክልል ነው? የትኛውስ ቤተክርስቲያን ነው? ምክንያቱም አንድ ነው ብለናል፡፡ ሁሉን መቻል / Omnipotent /፣ ሁሉን ማወቅ / Omniscience  /፣ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት / Omnipresent    / የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ባህሪ ነው፡፡ሁሉም ጻድቃን፤ መላዕክት ሁሉን ማወቅ፤በሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘትና የሁሉን ሰው ጸሎት ማድመጥ የሚችሉ ከሆነ እግዚአብሔር የሚባለው አምላክ ምን ልዩነት አለው ታዲያ?  ነገር ግን እውነቱ እነዚህ ባህርያት ማንንም ያላጋራበት የስላሴ ብቻ የሆነ ነው፡፡ ስላሴን የተለየ የሚያደርጋቸውም ይህ ባህሪ ነው፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ገብርኤል የኢየሱስን እናት ማርያምን ሊያበስራት የመጣ ጊዜ እርሱን ሌላ ቦታ ማግኘት አይቻልም፡፡ ምናልባት በዚያ ጊዜ አጣዳፊ ጉዳይ ካለ እንኩዋ ሌላ መልአክ ነው የሚላከው:: ምክንያቱም አንድ መልዐክ መገኘት የሚችለው በአንድ ቦታ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ወደ ዳንኤል መልስ ይዞ  እየበረረ ይመጣ የነበረውን መልዐክ  /አንዳንድ ሰዎች ገብርኤል  እንደሆነ ይላሉ/  የፋርስ አለቃ  (የፋርስ መንግስት አገር  ላይ በአየሩ ላይ አለቃ የነበረ አጋንንት) እንዳያልፍ ከልክሎት እንደነበር፤ ለ 21 ቀናትም ተቸግሮ እንደነበር ማወቁ ጥሩ ነው፡፡በሁዋላም ወደ ዳንኤል መምጣት የቻለው የመላዕከት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው ስለመጣ ነበር /ዳን.10፤13-20/፡፡ መላዕክት ሲላኩ በቦታ በስፍራ የሚወሰኑ መሆናቸውን ተመለከታችሁ? እንዳይመጣ ተከልክሎስ እንደ ነበረ አያችሁ?

መላዕክቶችም ሆኑ ቅዱሳን ወደ ጠሩአቸው ሁሉ የመሄድ፣ እንደወደዱ የማድረግ ማንነት አይደለም ያላቸው፡፡ መላዕክትነታቸው ለእግዚአብሔር ነውና እርሱ ወደ ላካቸው ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ እርሱ ያዘዛቸውንም ይፈጽማሉ፡፡ ይህን እውነት ማወቅና መናገር እነርሱን ማዋረድ ማለት አይደለም፡፡ በፍጹም እነርሱን ዝቅ ማድረግም አይደለም፡፡ እውነት አርነት ያወጣል፡፡አብርሐም ቤት የመጡት መላዕክት አብርሀም ቤት ጉዳያቸውን ሲፈጽሙ ነው  ሎጥ ዘንድ ሰዶም የሄዱት፡፡

ከመጀመሪያው ግን ከዘላለም  ሞት እንዲያድኑንና እንዲያስታርቁን ተሹመው በነበረ ፡አለመታዘዛችን ነበር ሀጢያት የሚሆን፡፡እነርሱም ብዙ በታዘቡን ነበር፡፡ አሁን ግን ከገረማቸው እንኩዋ  ሊገርማቸው  የሚችለው እነርሱ  ለእረኞች ያበሰሩትን ጉዳይ ያለመታዘዛችንን ሲያዩ ነው  /ሉቃ.2፤9-14/፡፡ የፃድቃንም አግራሞት ለእነርሱም መደሀኒት ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ አለማተኮራችን ነው፡፡ ቅድስት  ማርያምም ከገረማት እንኩዋ የሚገርማት ‹አርሱን ሰሙት›  ያለችውን፣ መድሀኒቴ አምላኬ ባለችው ልጁዋ አለማመናችን ነው፡፡ስለ ሁሉም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በመስቀል ላይ ስለ ከፈልክልኝ ዋጋ አመሰግንሀለሁ፡፡በቀራንዮ መስቀል በፈሰሰው ደምህ ሀጢያቴን እጠብልኝ ከበደሌም አንጻኝ፤ወደ ልቤም ገብተህ አብረኸኝ ኑር በማለት ከልባችን  ንስሀ  እየገባን በመጸለይ   ራሳችንን ለመንግስተ ሰማይ እናዘጋጅ፡፡የጌታችን ዳግም ምፅዐት ቀን ተቃርቡዋል፡፡ ከእግዚአብሔር በኩል ያለው ነገር ሁሉ ተሰርቶ አልቁዋል፤ ከእኛ በኩል የቀረውን እናድርግ!! ሰምተን እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡

አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ ከስር አስተያየት መስጫ ሣጥኑን  / COMMENT   / ተጭነው ይጻፉ፡፡






No comments:

Post a Comment