. የእድሜህ ዘመን ስንት ነው ?
. የሚሰራበት ቀንና ስለ ማይሰራበት ሌሊት አውቀዋልን?
የመግቢያ ጥቅሶች
''....ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ልፈጽም ይገባኛል፡፡ ማንም የማይሰራባት ሌሊት ትመጣለችና፡፡'' ዮሐ.9፤4
''.....አንተ እንድሰራው የሰጠኸኝን ስራ ፈጽሜ በምድር አከበርኩህ ፡፡'' ዮሐ.17፤4
እነዚህ ሁለት ጥቅሶች የሚያስረዱት የመጀመሪያው የተሰጠንን ተልዕኮ እና ዓላማ በተሰጠን ቀን ቶሎ ልንፈጽመው እንደሚገባ እና በሌላ በኩል ደግሞ ቀኑ አልፎ ማንም ሊሰራባት የማይችልባት ሌሊት እንደምትመጣ ነው፡፡ ከተፈጥሮ እንደምንረዳው ቀን የሚባልና ሌሊት የሚባሉ ጊዜዎች አሉ፡፡መንፈሳዊውም ልክ እንደዚሁ ነው፤ ከተፈጠርንበት ዓላማ ጋር የምንሰራበት ጊዜም አብሮ ይሰጣል፡፡ እርሱን በዋዛ፣ በፈዛዛ ካሳለፍነው ደግሞ ቢመኙም እንኩዋ ከብዙ ነገር አንጻር ምንም ማድረግ የማይቻልበት ጊዜ ይመጣል፡፡
ቀኖቻችን የተመቻቹ አጋጣሚዎቻችን ናቸው፡፡ጤናችን አፍላ ጉልበታችን፣ የተትረፈረፈ ሰዓታችን ሊሆን ይችላል፡፡ብዙ ነገሮችን በቀላል መንገድ መስራት የሚያስችሉን የዘመነኛው ቴክኖሎጂዎችም በተወሰነ መልኩ መልካም አጋጣሚዎቻችን ሊሆኑልን ይችላሉ፡፡ ምናልባት አንዳንድ ህጎች፣ፖሊሲዎች...ወዘተ ቀን እንደሆነልን ሊጠቁመሙን ይችላሉ፡፡ ምናልባት ዛሬ ክፍት የሆኑ ነገሮች ነገ ላይዘጉ ፤ ዛሬ እንደልብ ልናገኛቸው የምንችላቸው ነገሮች ነገ ላይወደዱ የሚችሉበት ምንም መተማመኛ ነገር የለም፡፡ የተትረፈረፈ ጊዜያችን ነገ ላይ በጭንቅም ላይገኝ ይችላል፡፡መጠቀም ዛሬን ነው፡፡ የምንችለውን ሁሉ አድርጎ ማለፍ !
ሁለተኛው ጥቅስ ደግሞ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ሳለ የተሰጠውን ተልዕኮ በተሰጠው ጊዜ ጨርሶ በሰማይ ወደ ነበረው ክብር እንደሚመለስ ያለውን ነገር ነው የሚያስረዳው፡፡ ተልዕኮን በአንድ በተሰጠ ጊዜ ጨርሶ ፈጸምኩ ማለት እንዴት ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው ?! ጳውሎስም ይህንኑ ነው ያለው .....ሩጫውን ጨርሼአለሁ ...........!
በሰው ህይወት ሁሉ የምንሰራበት ቀን እና የማንሰራባት ሌሊት አለች፡፡አሁን ቀን የሆነላችሁ ፡ ማለትም ከብዙ ነገር አንጻር ነገሮችን ለማድረግ ዕድሉ የተመቻቸላችሁ፣ በመንገዳችሁ ላይ የይለፍ አረንጉዋዴ መብራት የበራላችሁን......የሚወክል ሲሆን፤ለሌሎች ደግሞ ሌሊት ውስጥ ያላችሁ ትኖራላችሁ ፡፡ ማለትም ምንም ነገር ለማድረግ ነገሮች ያልተመቻቸላችሁ፣ ማድረግ ብትፈልጉም ማድረግ ያልቻላችሁ፣ የጊዜ እጥረት ያለባችሁ፣ በመንገዳችሁ ላይ ቀይ መብራት ስለበራ ማለፍ የማትችሉትን ጭምር ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ቀን ለሆነላችሁ በአግባቡ ጊዜውን እንድትጠቀሙበት ፣ ሌሊት የሆነባችሁ ደግሞ ተመልሶ በቸርነቱ ቀን እስኪያመጣላችሁ በጸሎት በመትጋትና በእምነት ጠንክራችሁ እንድትጠብቁ እመክራለሁ፡፡
ጊዜ ማለት ውድ ነገር ነው፡፡ የሚቆምበት እግር ያልተፈጠረለት ወፍ እንደማለት ነው ፡፡ ልናቆመውና እንዲጠብቀን ልናደርገው አንችልም፡፡ ለምሳሌ የትናንትናው ቀን ተመልሶ ሊመጣ ይችላልን ? አይችልም፡፡ ልክ ከአፋችን እንደወጣ ካርቦን ዳይኦክሳይድ /የተቃጠለ አየር/ ነው፡፡ ያስወጣነውን አየር መልሰን ልናስገባ አንችልም፡፡ ተቃጥለው ያለፉ ጊዜዎችም ልክ እንደዚህ ናቸው ፤ በነበራቸው ጊዜ አንዳች ሳይሰሩበት ከርመው በባነኑ ሰዐት ማጣፊያው ያጠራቸውና የቆጫቸው አያሌ ናቸው፡፡ የሌሊቱ ባህሪ ብዙ ጊዜ ጸጸትንና ቁጭትን ብቻ ነው የሚፈጥረው፡፡
በዘፍጥረት 47 ላይ ፈረኦን የያዕቆብን ዕድሜ ጠይቆት ነበረ፡፡ ‹‹..የእድሜህ ዘመን ስንት ነው? ለሚለው ጥያቄው የመለሰው ከቁጥር ጋር ክፉም ጥቂትም የሚሉ ቃላቶች ነበሩ፡፡እነዚህ ቃላት የሚያሳዩት በተለያየ ሁኔታ ስለ ተቃጠሉት ጊዜዎቹ ቁጭቱን ሲገልጽ ነው፡፡ ቢያንስ ሁለት ሰባት ዓመታቶች ሚስትን ለማግባት የተፈጁ እና ንጹህ ስድስት ዓመታት ደግሞ የግልን ንብረት ለማከማቸት ያለፈ ጊዜ ነው፡፡ በርከት ያሉ የመከራ ዓመታትንም ከስደት ጋር አሳልፉአል፡፡
እድሜህ ስንት ነው ?
'' የዘመኖቻችን ዕድሜ ሰባ ዓመት ቢበረታም ሰማንያ ዓመት ነው፤ ቢበዛ ግን ድካምና መከራ ነው፡፡ ከእኛ ቶሎ ያልፋልና ፡እኛም እንገሰጻለንና ፡፡''መዝ.90፤10
በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ በርካታ ክፍሎች ላይ ስለ እድሜያችን የተጠቀሱት ጥቅሶች የሚያስገነዝቡን ዕድሜያችን እምብዛም የሚያደላድል ና የሚያስፋፋ ነገር እንዳልሆነ ነው፡፡ በጣም ብዙ ዘመን እንደቀረው ሰው እንዳንኖር ትምህርት ይሰጠናል፡፡ ነገር ግን የሆነ ዓላማ ግን ፈጽመን ልናልፍበት እንችላለን፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ ዕድሜያችን ምን እንደተባለ ቀጥለን ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
- ዘመኖቻችን እንደ ሸረሪት ድር ይሆናሉ፡፡ መዝ.90፤9
- በከንቱ ይታወካል እንጂ በእውነት ሰው እንደ ጥላ ይመላለሳል፡፡ መዝ.39፤6
- ህይወታችሁ ምንድን ነው ? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ሁዋላ እንደሚጠፋ እንፉዋሎት ናችሁና፡፡ ያዕ.4፤1
- .....እንደ ተን.....መዝ.38....
- እንደ ሸማኔ መጠቅለያ፡፡ ኢሳ.38፡12
ሰዎችን ከማዳን ጎን ለጎን ግን ህጻናትን የማሳደግ፣ ድሆችን የመመገብ፣ አረጋውያንን የመንከባከብ፣ የአካባቢና የተፈጥሮ ጥበቃን የመሰለ፣ ሌላም ሌላም ህብረተሰብን የሚጠቅም በጎ ራዕይ ሰርቶ ማለፍ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በርካቶች ይህንን አድርገዋል፤ እያደረጉም ያሉ አሉ፡፡
በአንድ አገር ውስጥ የሰዎች ዕድሜ ላይ የሚያጠና አንድ ምሁር ሰዎች የምድር ዘመን ቆይታቸው ሰባ ዓመት ቢሆን በዋናነት ዕድሜያቸውን በምን ጉዳይ ፈጅተውት እንደሚያልፉ በጥናት ካሰፈረው ነገር ቀጥለን እናያለን፡-
- ለእንቅልፍ 23 ዓመት / 32% /
- ለስራ 16 ዓመት / 22% /
- የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመከታተል 8 ዓመት / 11% /
- በመመገብ 6 ዓመት / 8.6% /
- በመጉዋጉዋዝ 6 ዓመት / 8.6% /
- በመዝናናት 4.5 ዓመት / 6.5% /
- በተለያየ ህመም 4 ዓመት / 5.7% /
- በመልበስ 2 ዓመት / 2.8% /
- እንደ ጸሎት ያሉ የዓምልኮ ስርዐትን በመፈጸም 0.5 ዓመት / 0.9% /
ማስታወሻ፡- ውድ ጊዜያቸውን ለከበረ ዓላማ እንዲያውሉት ለሚሳሱላቸው ሰዎች ይህንን መልዕክት ያጋሩአቸው፡፡
benjabef@gmail.com
No comments:
Post a Comment