Monday, March 2, 2015

አገልጋይና አገልግሎቱ

የዛሬው  ፅሑፍ እ.ኤ.አ. February, 2012 በአንድ አካባቢ ለተገኙ የአብያተ- ቤተክርስቲያናት  መሪዎችና አገልጋዮች ጉባኤ ላይ፡ ስለ አገልጋይና አገልግሎቱ  ለሚያነሱት ሰፊ ውይይት ለመነሻነት ባቀረብኩት ጽሁፍ  ላይ መጠነኛ ነገር ተጨምሮበት የቀረበ ነው፡፡

የንባብ ክፍል ገላቲያ 2፤1-10
    '' ከዚያ ወዲያ ከአስራ አራት ዓመት በሁዋላ ከበርናባስ ጋር ቲቶን ደግሞ ይዤ ወደ ኢየሩሳሌም ሁለተኛ ወጣሁ፤እንደ ተገለጠልኝም ወጣሁ፤ምናልባትም በከንቱ እንዳልሮጥ ወይም በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን በአህዛብ መካከል የምሰብከውን ወንጌል አስታወቅኩዋቸው፤ዋኖች ግን መስለው ለሚታዩ ለብቻቸው አስታወቅኩዋቸው፡፡ ''

በክፍሉ ላይ እንደ ተመለከተው ሐዋርያው ጳውሎስ እራሱንና አገልግሎቱን ያስፈተሸበት ታሪክ ነው፡፡ ከዳነ  ከ14  ዓመታት በሁዋላ ወሳኝ የሚባሉ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ጠይቁዋል፡፡

1ኛ-በከንቱ ሮጬ እንዳልሆን ? የሚልና

2ኛ-ደግሞ ምናልባት በከንቱ እንዳልሮጥ

 የመጀመሪያው አሳብ ለዓመታት የሄደበትን፣ የደከመበትን ሩጫና አገልግሎት ማስገምገሙ ሲሆን ፣ሁለተኛው ግን ያለፉት የአገልግሎት ሩጫዎች በከንቱ የነበሩ እንኩዋ ከሆነ ፤ቀጣዩ ግን ትክክለኛና የሰመረ እንዲሆን ፣ እግዚአብሔርም የሚከብርበት እንዲሆን የታሰበ ነው፡፡ ስለዚህም እስከዛሬ ድረስ የሚሰብከውን ወንጌል ለዋነኞቹ ሐዋርያት በዝርዝር በማቅረብ ትክክል እንደሆነና እንዳልሆነ አስገምግሞአል፡፡

  ለመሆኑ ሐዋርያትስ ምን አሉት? እነርሱማ ነገሩን በመንፈስ ከመዘኑት በሁዋላ በአገልግሎቱ ውስጥ የተሳሳተ ወይም  ከእውነት ጋር የተቃረነ ነገር ስላላገኙበት፡ በርታ ፣ቀጥል ብለው ቀኝ እጃቸውን ሰጥተውታል፡፡በብዙ አስገራሚ መንፈሳዊ ልምምዶች ውስጥ የከረመና መለኮታዊ ሚስጥራትን  በመግለጥ የሚታወቀው ፣ለበርካታ አብያተክርስቲያናት መተከል ፣መታነጽ ና ማደግ ምክንያት የሆነው፤ከዚህም ሌላ ከ13 የማያንሱ ፡ከግማሽ በላይ የአዲስ ኪዳን መጻህፍቶችን የጻፈ ሐዋርያ፣ እራሱንና አገልግሎቱን  አቅርቦ ካስገመገመ፣ ቆም ብሎ ከጠየቀ? እኛማ ይልቁን እንዴት አብዝተን ማድረግ ይጠበቅብን ይሆን?

አገልግሎትን ስናስብ በ1ኛ ጢሞቲዎስ ም.3 ቁ.1 ላይ ያለው ቃል ትዝ ሊለን ይችላል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካም ስራን ይመኛል፡፡'' ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ አዋቂዎች እንደሚናገሩት የዚያን ጊዜ የነበረው አገልግሎት አገልጋይነትን የሚያስመኝ ዓይነት አልነበረም ይላሉ፡፡ ስለዚህም በዚያ የጠበበ በር ሾልኮ ለመግባትና እነዚያን የማይመቹ ሁኔታዎች አልፎ ለማገልገል የሚመኝ ካለ ፡መልካም እንዳደረገ ለመግለጽ ነው፡፡ ቃሉ የሚመኝ ስላለ ብቻ አገልግሎት በምኞት የምንገባበት ነው ማለት አይደለም፡፡ የተመኘም ሁሉ የሚከናወንበትም አይደለም፡፡ አገልግሎት የጥሪ ፣ የሸክም ጉዳይ ነው፡፡ የተጠሪው ብቻ ሳይሆን የጠሪውም ሙሉ ፈቃድ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

አገልጋይነት  ሌሎች ለኛ እንዲኖሩ ፣ ሌሎች ለኛ እንዲሰሩ የምናዝበት ሳይሆን፤ከስሙ እንደምንረዳው ሌሎችን ማገልገል ማለት ነው፡፡ ለሌሎች መዳን ፣ጥቅምና ትርፍ መድከምን ያሳያል፡፡ ጌታችን እንደ ተናገረው '' የሰው ልጅ ሊያገለግልና ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ  ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም፡፡'' ብሎአል ማር.10፤45፡፡ ደግሞ በሉቃስ ወንጌል ም.22 ቁ.27 ላይ '' ..እኔ ግን በመካከላችሁ እንደሚያገለግል ነኝ ፡፡ '' ብሎ ተናግሩዋል፡፡ እነዚህ ጥቅሶች የአገልጋይነትን ትክክለኛ ትርጉም የሚያስረዱ ናቸው፡፡ ነፍስን ቤዛ ማድረግ  እንኩዋ ቢቀር ባለን ጸጋ፣ ሙያ፣ ክህሎት ሁሉ ለብዙዎች ቤዛ መሆን እና  ክብርና ሙገሳን ሳይፈልጉ በሰዎች መካከል እንደ አገልጋይ መኖርን ግን ያካትታል፡፡

 ከዚህ ቀጥለን አንዳንድ መንፈሳዊ ሰዎች ስለ አገልግሎት የተናገሩትን ነገር እንመለከታለን፡-
  • አንድ ምሁር ስለ አገልጋይነት የተናገረው እንዲህ ነበር '' አገልጋይ ማለት ሰዎች ሊሰሩ የማይፈልጉትን ነገር እንዲሰሩ ማድረግና ፣የሚሰሩትንም ነገር እንዲወዱት የማድረግ ችሎታ ነው '' ብሎአል፡፡
  • አንድ ሌላ ዶክተርም እውነተኛ አገልጋይ ማለት መንገዱን የሚያውቅ ፣ከመንገዱ ሳይዛነፍ ወደ ፊት የሚገሰግስ ና ከሁዋላ  ያሉትንም ሰዎች ወደ ፊት የሚስብ ነው ብሎአል፡፡
  •  ሞንት ጎመሪ የተባለ የጦር አዛዥ የነበረ ሰው እንደ ጻፈውም '' ሰዎችን የመማረክ  ችሎታ የሚወሰነው ፡ሰውየው ባለው መልካም ባህሪያት መጠን ይሆናል፡፡ የማነቃቃት ፣የማበረታታትና ሰዎችን የመሳብ ችሎታ ካለው  ሰዎችን ይማርካል'' ብሎአል፡፡ ሌሎችም በርካታዎች ስለ አገልጋይና አገልግሎት የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ጽፈዋል ፡ተናግረዋልም፡፡

  እንዲያው ለመሆኑ አገልጋይ እና አገልግሎቱ  ስንል የቱን ማለታችን ነው? የተባለ እንደሆነ፤የቃሉን ሰባኪና አስተማሪ ማለታችን ነው፤ ህዝቡን የሚመግቡ መጋቢዎችንና የቤተክርስቲያን ሽማግሌዎችን ማለታችን ነው፤ ደግሞ የጋብቻ ና የተለያዩ መንፈሳዊ ጉዳይ  አማካሪዎችን ማለታችን ነው፤ የውስጥ ና የውጪ የሙሉ ጊዜ እና የትርፍ ጊዜ አገልጋዮችን ማለታችን ነው፡፡ሌሎችንም እንደ ድቁንና፣ የጸሎት፣ ዝማሬ፣ የህጻናት አገልጋዮችንና የመሳሰሉትን ይጨምራል፡፡
እንግዲህ እነዚህን ነገሮች ስናነሳ ለዛሬ ትኩረታችን ወደ ሆነው ወደ ሌላው ተከታዩ ሐሳብ እናመራለን፡፡ብዙዎች እንደሚስማሙት አገልግሎትም ሆነ አገልጋዮች ላይ ከፊት ይልቅ ጠንከር ያለ ተግዳሮት በዝቶባቸዋል፡፡ ብዙ ጥያቄዎች አሉ፣ ብዙ ግራ የሚያጋቡ ነገሮችም አሉ፡፡ እንደውም አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች  እንደሚናገሩት ፡ አንድ የሆነ ሪቫይቫል ካልመጣ ወይም በሆነ መንገድ መለኮታዊው ጣልቃ ገብነት ካልተከሰተ በቀር፡ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ ሊያሽቆለቁሉ ይችላሉ ብለው ይፈራሉ፡፡

   መድረኮቻችን፣ የጊዜ አጠቃቀማችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እውቀታችን ውስንነት፣ የንባብ ፣የጸሎት ህይወታችንና ልምምዳችን አጠቃላይ ከዕለት ዕለት እየቀነሱ እና በሌሎች ጊዜን በሚወስዱ እንደ ፌስቡክ፣ ድራማ፣ ፊልም፣ ሌሎች መዝናኛዎች እየተፈተኑ እንዳለ በርካታ ክርስቲያኖች ስለራሳቸው ጭምር ይናገራሉ፡፡ የ '' መድረኮቻችን በመጽሐፍ ቅዱስ ዕይታ '' ፀሐፊም በመጽሐፋቸው ውስጥ ሊጠቁሙን የሞከሩት ይህንኑ ሀቅ ነው፡፡ ከቃሉ ውጪ የሆነ አደራረግ ና ልምምድ በዝቶአል፤ የሚያምነውም የማያምነውም  አላማኝ  ስለ አገልጋዮችም ሆነ ስለ አገልግሎቱም ሁኔታ አጥብቆ እየጠየቀ ነው ብለዋል፡፡ እንዲያው ባጠቃላይ የት እንደምንገኝና ሁኔታዎች ምን እንደሚመስሉ ለመጠቆም ያህል ጥቂት ጥያቄዎችን መጠየቅ አግባብ ይሆናል፡

  •  አሁን ያለው አገልጋይ ወደ ፊት ልጁ  /ለልጆቹ/ እንደ እርሱ አገልጋይ እንዲሆን  ይፈልጋል ወይም ይመኛልን?
  •  የተሻለ የሚባልና የሚያማልል ነገር ከዓለም ቢያገኝ ጥሪዬ፣ አገልግሎቴ ይበልጥብኛል ብሎ የቀረበለትን መደለያ  እምቢ ለማለት አቅም አለው ወይ?
  •  ህይወት እንደገና እንዲጀምር ቢደረግ ስንት አገልጋይ መልሶ አገልጋይነትን ይመርጣል?
  •  በአሁኑ ጊዜ ወላጆች ልጆቻቸውን ለአገልጋይ ይድራሉ ወይ? በዚህስ ክብር ይሰማቸዋል ወይ?
  •  የቤተ ክርስቲያን አመራርና ሽማግሌዎችን ቁጣ በመፍራት ወይም የደሞዝ መቆረጥ ስጋት ሳይሆን በጥሪና በሸክም የሚያገለግል፣ያልዳኑ ሰዎች ጉዳይ፣ደቀ መዝሙር ያልተደረጉ ምዕመናን ሰዎች ጉዳይ ፣ የተለያዩ  እንቆቅልሻቸው ያልተፈታ ሰዎች ጉዳይ ዘንድሮም ከልቡ አሳስቦት የሚጸለይ እና ርምጃ የሚወስድ፣ የሚተጋ ስንት ነው?
  • ዘንድሮ በራሱ ተነሳሽነት የተሰጠውን ሀላፊነት ሁሉ በትጋት የሚወጣ ና ጌታን ሰምቶ ነገሮችን በቅን ልብ  የሚያደርግ አገልጋይ ስንት ነው?
እነዚህ  ነገሮች የሚመለከታቸው በትክክል ጥሪና ሸክም  እንዳላቸው ተፈትሾ ቤተክርስቲያን ለአገልግሎት ያሰማራቻቸውን ሲሆን፤ አንዳንድ የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደሚናገሩት በትክክል ጥሪው መጥቶላቸው ሳይሆን ፡እንዲሁ ያለ እውነተኛ ሸክም ገብተው በቤተክርስቲያን ውስጥ የሚያገለግሉም እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡ 

 መቼም ለየትኛውም የሙያ ስራና አገልግሎት ለሚታጩ ሰዎች የየራሳቸው መመዘኛዎች አሉዋቸው፡፡ አንዳንድ መመዘኛዎች ወደ ሰዎቹ ወደ ራሳቸው ጥቅም የሚያደላ  ሆኖ ተገኝቶአል፤ ለእግዚአብሔር ቤት በትክክል የሚያደሉና ስራው በትክክል እንዲሰራ የሚናፍቃቸው እውነተኞችም አሉ፡፡ ለሁሉም መመዘኛ መኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ከነገ  ወቀሳ  ያተርፋል፡፡ ችግሩ መመዘኛችን እውነተኛና ከጥሩ ሞቲቭ መመንጨታቸው ላይ ነው፡፡ በመቀጠል ምናልባት ይጠቅም እንደሆነ ፡አንድ  ዶክተር የተማሪዎቹን ክህሎት ይመዝንበት የነበሩ ወደ ዘጠኝ ያህል ጥያቄዎች  ቀርበዋል  / ከአንድ መጽሐፍ ላይ የተወሰዱ ናቸው፡፡/ ተጠቀሙበት!

  1. ትናንሽ የሆኑ ነገሮችን ደህና አድርጎ ይሰራልን?
  2. ቅድሚያ መስጠት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ተረድቶአልን?
  3.  የዕረፍት ጊዜውን በአገግባቡ ይጠቀምበታልን?
  4.  ሥራውን በንቃት መንፈስ ይሰራልን?
  5.  የዕድገት ዝንባሌ የሚታይባቸውን ሥራዎች መርጦ ሊጠቀምባቸው ይችላልን?
  6. የማደግ  ዝንባሌ ይታይበታልን?
  7.  ተስፋ  የሚያስቆርጡ ነገሮች ሲገጥሙት እንዴት ነው?
  8.  አስቸጋሪ ነገሮችን እንዴት ይፈታቸዋል?
  9.  ድክመቶቹን ያውቃቸዋል?  ከዚያስ ምን ያደርጋል?
 እኛስ እንደ አገልጋይ ለዋና ነገራችን ፣ለጥሪ ቦታ ከመስጠት አንጻር ፣ከመታዘዝ  ህይወት፣ጊዜን በአግባብ ከመጠቀም አንጻር ፣ ለማደግ ከመፈለግ፣ በመከራዎችና በፈተናዎች ከመጽናት አንጻር ፣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በብቃት ከመወጣትና ትግሎችን በመልካም ከማሸነፍ አንጻር  እንዴት ነን?
  ነገሮቻችን ከላይ በተገለጸው መሰረት ነጥረው እንዳልወጡ የሚያሳብቁብን አንዳንድ ጉዳዮች  አሉ፡፡ ዓለም በድህረ ዘመናዊነት፣ በዘመናዊነትና በረቀቀ ዓለማዊነት በምትታመስበት ወቅት ይህም አንዳንድ ጊዜ ሾልኮ በቤተክርስቲያንም ጭምር እየታየ ባለበት ወቅት፡ የቤት ስራችንን በጊዜ ለመስራት ካልተነሳን ወደ ፊት የሚጠብቀን ተግዳሮት ቀላል አይሆንም፡፡ የእኛ ይህንን ለመመከት ዝግጅት አለማድረግ እና በነገሮች ላይ ነቅቶ ቶሎ እርምጃዎችን ያለመውሰድ፡ ነገሮች ከድጡ ወደ ማጡ እንዳይሄዱ ያሰጋል፡፡

 የምንፈራውና የምንሰጋበት ነገር እንዲብስ ያደረገው፡ በተለይ አሁን ላለው ትውልድ የቀረበለት ምርጫ በርካታ መሆኑ ሲሆን፤አብዛኞቹ ምርጫዎች እንኩዋን በህይወት ሊያኖሩት ቀርቶ፤ ተመልሶ የእውነት እና የቤተክርስቲያን ጠላት እንዲሆን ሊያደርጉት ስለሚችሉ ነው፡፡ ተጠናክሮ በመጣ መንፈሳዊ መሰልና ባልሆነ ጎርፍ ትውልዱ እንዳይወሰድ ምን ማድረግ ይገባናል? ብለን ማቀድ አለብን፡፡ ቢያንስ ሁሉም የቤተክርስቲያን አባል የሆነ ሁሉ በትንሹ አስርቱ ትዕዛዛትን ፣ ወንጌላትን በቅጡ እንዲያውቅ ፣ የጥምቀት ስርዐት ፣ የጌታ እራት ስርዐት ምን እንደሆነ፤ ስለ አምልኮ፣ ስለ ጸሎት፣ ስለ ጾምና ጥሞና የምናሳውቅበት መንገድ  ማመቻቸት የሚጠበቅብን ይመስለኛል፡፡

  በአሁን ሰዐት በተለይ ወጣቱ  በአውሮፓ እግር ኩዋስ ተጫዋቾች ፍቅር የተያዘ ወይም በሆሊ ውድ አክተሮች ፍቅር የተነደፈ ነው፡፡ ስለ እነርሱ ማንነት ፣ሁኔታ ፣ደሞዛቸውን ፣ዝውውራቸውን እየተከታተለ ፡ ደግሞ ለሌሎች አንዳች ሳያዛንፍ እያብራራ ነው ያለው፡፡ ስለ ወንጌል እና ከላይ ስለ ጠቀስናቸው፣ ህይወቱን ስለሚጠቅሙት ጉዳይ፡ ምንም መሰረታዊ ዕውቀት አልያዘም፡፡ በእርግጥ ሁሉም የቤተክርስቲያን ችግር ብቻ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ አንዳንዱ የቀረበላቸውን ማዕድ በመግፋት ነው ለዚህ የተዳረጉት፡፡ ምናልባት አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የቀረበበት መንገድም ብዙ የሚስብ ና ትውልዱን በሚማርክ መንገድ  ስላልሆነ  ነው የሚሉም አሉ፡፡  ብቻ ለሁሉም ቢያንስ መሰረታዊውን የደህንነት ዕውቀት ፣ ጌታ ለምን እንደመጣ? ፣ለምን እንደተሰቀለ?፣ ስለ ሞቱና ስለ ትንሳኤው እንዳያውቅ፤ ስለ ሚከተለው እምነት ምንነት እና ምክንያት ለሌሎች የሚያስረዳበትን ዕውቀት እንዳይጨብጥ ችግር የሆነበትን ምክንያት ማወቅ አለብን፡፡ ምናልባት ቤተክርስቲያን በመጽሀፍ ቅዱስ ዕውቀት የደረጁ አስተማሪዎች የላት ይሆን? ወይስ አሁን ያሉ መሪዎች ይህ ጉዳይ ብዙም የሚያሳስባቸው ስላልሆነና በሌላ ነገር ባተሌ ሆነው ይሆን ? ወይስ ሌላ ተጠያቂ  የሚሆን /ምክንያት/ ይኖር ይሆን ? እሺ ችግራችን ምንም ይሁን!  ከእንግዲህ ምን እናድርግ ? ቢያንስ ጥቂት መፍትሔዎችን ቀጥሎ  ፈንጠቅ ለማድረግ ተሞክሩዋል፡፡

  • አገልግሎት እየሰለቸን ሳይሆን ደስ እያለን ከሌሎች ጋር የምንሰራበትን ሁኔታዎች ቢመቻች
  •  የቤተክርስቲያን አገልጋዮች እና የዘርፍ መሪዎች በሁሉም መንገድ ብቃት እንዲኖራቸው የሚያድጉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ፤ለምሳሌ በስልጠና ፣ ስነ መለኮት ትምህርት ቤት በመላክ ፣ እርስ በርስ የልምድ ልውውጦችን በማድረግ፤
  •  ለመሪዎችና ለአገልጋዮች ስለ አገልግሎታቸው ብቻ ሳይሆን ስለ ኑሮአቸውም ማሰበ፤
  • በቤተክርስቲያን ምስባክ ላይ እየቀረቡ ያሉ መልዕክቶች  ሁሉ አቀፍና የተመጣጠኑ ስለ መሆናቸው ፤ ደግሞ ጠቃሚነታቸውን በየተወሰነ ጊዜ መገምገም፤
  •  የተሰማሩ ግን ጥሪና ሸክም የሌላቸውን ለይቶ ማወቅ፣ ጥሪው ያላቸውን ደግሞ ያልተሰማሩትን በተቻለ መጠን ማሰማራት የሚሉት ከብዙ በጥቂቱ  ናቸው፡፡
ማስታወሻ፡- ማናቸውም የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ለሆኑ ሁሉ እንዲጠቀሙበት ሊልኩላቸው ይችላሉ፡፡ እግዚአብሔር ይባርክዎ!

                                                                                 benjabef@gmail.com

No comments:

Post a Comment