Friday, February 20, 2015

አማላጅነት-2

             ክፍል -2

በዚህ በክፍል ሁለት ትምህርት ውስጥ ካለፈው የቀጠለውንና ከዚህ ሐሳብ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች እናነሳለን፡፡
  • ሐጢያትን  ለካህን  መናዘዝ  ተገቢ  ነውን ?
  • የአዲስ ኪዳን  ዘመን  ካህናት  እና ሊቀ  ካህን  ማን ነው?
  •  በጻድቃን  ስም  ቀዝቃዛ  ውሀ  ማጠጣት  ያጸድቃል?
  •  ዝክር  መዘከርና  ምጽዋት  ማድረግ  ለጽድቅ  ይጠቅማል?
  • የሙታን  ተስካር  ወይም  /ፑርጋቶሪ/ ምንድን  ነው?
                  የአዲስ ኪዳን  ካህናት እነማን ናቸው?
        ስለ ካህናት ስናነሳ በቅድሚያ መታወቅ ያለበት ጉዳይ፡ ካህናት በብሉይ ኪዳን የነበራቸው ሚና እና የአዲስ ኪዳን ክህነት ምን እንደሆነ ነው፡፡ የብሉይ ኪዳን ካህናት የሚመረጡት ከሌዊ ነገድ ሲሆን ምግባራቸውም የቤተ መቅደሱን መንፈሳዊ ስርዐት መምራት ነው፡፡ በተለይም ለኀጢያት ስርየት የሚቀርቡ መባ ና መስዋዕቶችን ህዝቡን ወክለው በእግዚአብሄር ፊት የሚያቀርቡት እነርሱ ነበሩ፡፡ የብሉይ ኪዳን ህዝብ ሐጢያቱን የሚናዘዘው የሚሰዋው በግ ወይም ጠቦት ላይ ሲሆን ሊቀ ካህኑም ደሙን ይዞ በአመት አንድ ጊዜ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይገባል፡፡/ ዕብ.9፤6-7 /

  በአዲስ ኪዳን ዘመን ለሐጢያት ተብሎ የሚቀርብ መስዋዕት ወይም ደም የለም፡፡ሊቀ ካህናችን የሆነው ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የገዛ ደሙን ይዞ ወደ እውነተኛው የሰማይ መቅደስ እንደገባ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡/ዕብ.10፤11-18/ በአሁኑ ሰዐት እስራኤላውያን፣ ካህናቱ ሌዋውያንን ጨምሮ በተወሰነ መንገድ ስርዐቱን የሚከተሉ ቢሆንም የእውነተኛውን አዳኝ የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሳኤ ና ጌትነት ግን አልተቀበሉም፡፡

               የማሰርና የመፍታት ስልጣን...!
        የማሰርና የመፍታት ስልጣን የተሰጣቸው ካህናት እነማን ናቸው? በማቴዎስ ወንጌል ም.18 ቁ.18 ላይ እንደተጠቀሰው "...እውነት እላችሁዋለሁ በምድር የምታስሩት ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤በምድርም የምትፈቱት ሁሉ በሰማይ የተፈታ ይሆናል፡፡":: በሌላም ስፍራ  ጌታ ለጴጥሮስ እንደተናገረው " የመንግስተ ሰማያትንም መክፈቻዎች እሰጥሀለሁ በምድር የምታስረው ሁሉ በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤በምድርም የምትፈታው ሁሉ በሰማያት የተፈታ ይሆናል" ማቴ.16፤18፡ አንባቢ  እንደሚረዳው እነዚህ ቃላት የተነገሩት የመጀመሪያው ጥቅስ የጌታችን ደቀመዛሙርት ለነበሩት ለመጀመሪያዎቹ የበጉ ሐዋርያት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ለሊቀ ሐዋርያው ለጴጥሮስ የተነገረ ነው፡፡መሰረታዊውን ታሪክ ለማስታወስ ብዬ ነው እንጂ፤ በሌላ ዘመን ለሌሎች ክርስቲያኖች ቃሉ አይሰራም ለማለት አይደለም፡፡ ሁሉም የአዲስ ኪዳን ሰዎች ናቸው፤ በክርሰቶስ በመሲሁ አዳኝነት ያመኑ እስራኤላውያን ናቸው፤ ደግሞ የክርስቶስ ሞቱና ትንሳኤው ምስክር ለመሆን የተመረጡ ወንጌል ሰባኪዎች  ናቸው፡፡ ለእነርሱ ግን የተለየ ልብስ እና የተለየ ጥምጥም አልነበራቸውም፡፡
     ሁለቱም ሐሳብ የብሉይ ኪዳንን ስርዐት ስለሚከተሉ ካህናት አይናገርም፡፡ ለእነርሱ እንዲህ ያለ ስልጣን የላቸውም፡፡ እንደዚህ ለመሆን አስቀድሞ በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ነበረባቸው፡፡
     ከዚህ ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ያንን ለምጻም ከፈወሰ በሁዋላ " ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ !" ሉቃ.5፤14 ያለውስ ጉዳይ ? ብለን ብናነሳ፡ በቅድሚያ ጌታችን መድሐኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመጣበት ጊዜ በምድር ላይ የነበረው ስርዐት የአይሁድ ስርዐት እንደመሆኑ ሙሉ ለሙሉ ስራውን ፈጽሞ አዲስ ኪዳንን እስኪተካ ድረስ የሙሴን  ህግ በመታዘዝ ነው ይህንን ያደረገው፡፡ አንደኛ ህግን ልሽር ሳይሆን ልፈጽም ነው የመጣሁት ስላለ ማቴ. 5፤17፡፡ ሁለተኛው በዘመኑ የነበሩ ፈሪሳውያን ሙሴን ህግ ይሽራል የሚል ተደጋጋሚ ክስ ቢያነሱም፡ እርሱ ግን ያንን አለማድረጉን ካሳየበት አንዱ ማሳያ ይህ ታሪክ ነው፡፡በሙሴ ህግ እንደተቀመጠው ሰው በለምጹ ከሰፈር ከተወገደ በሁዋላ ሌላ ጊዜ በሆነው መንገድ ቢፈወስ ወደ ህብረተሰቡ ከመቀላቀሉ በፊት ራሱን ለዘመኑ ካህናት ማሳየት ነበረበት፡፡ካህኑም መንጻቱን አረጋግጦ ወደ ሰፈር ይቀላቅለው ነበር፡ ዘሌዋውያን 14፤2-32፡፡ ስለዚህም ጌታ የፈወሰውን ያንን ለምጻም በህጉ መሰረት በካህናቱ እንዲታይ ነው የሰደደው፡፡ ያንንም ያደረገው በትህትናና በታዛዥነቱ ነው፡፡ በዚህም ላይ የነጻን ለምጽ ሄዶ ለካህናት ማስፈተሸ ሐጢያትን ለእነርሱ ከመናዘዝ ጋር ምን ግንኙነት አለው? በዘመኑ የብሉይ ኪዳን ካህናት ከለምጹ የነጻን ሰው የሚፈትሹት እነርሱ ነበሩና ያንን አደረገ፡፡ከህጉ በላይ የሚቀኑለትን ወግና ስርዐታቸውን ግን አጥብቆ ይኮነንን ነበር፡ /ማር.7፤14-21/
     የአዲስ ኪዳን ዘመን ህዝብ ሐጢያቱን መናዘዝ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በኩል  በቀጥታ ለእግዚአብሔር ነው፡፡ የአዲስ ኪዳን ሊቀ ካህንና መካከለኛ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ዕብ.9፤15፡፡ በእርሱ የሚያምኑ ሁሉ ደግሞ ካህናት ተብለው ተጠርተዋል፡፡!1ጴጥ.2፡9 ፡፡በዚ መሰረት አንዱ ስለ አንዱ እርስ በእርስ ሊጸልይ ይችላል እንጂ፤ ለብቻው የተለየ ልብስ የለበሰ እና ለእርሱ ብቻ የሚገባ የጸሎት መጽሐፍ እያነበበ ንስሐ የሚያድል እና የህዝብን ሐጢያት የሚያስተሰርይ ሰዋዊ የክህነት ስርዐት የለም፡፡እግዚአብሔር  ሁሉንም ሰው በአንድ ጊዜ መስማት ስለሚችል፤ በፊቱ ንስሀ የሚገቡትን ሁሉ በክርስቶስ ይቅር ይላቸዋል፡፡ 1ዮሐ.1፡4-9፣ሥራ.10፤48፡፡

             በጻድቅ ስም ውሀ  የሚያጠጣ .. !?
" እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል፡፡ ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፤ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቅን ዋጋ ይወስዳል፡፡ማንም  ከእነዚህ  ከታናናሾቹ ለአንዱ  ቀዝቃዛ  ጽዋ ውሀ  ብቻ  በደቀ መዝሙሩ ስም የሚያጠጣ አውነት እላችሁአለሁ ዋጋው አይጠፋበትም፡፡ " ማቴ.10፤40-42፡፡
 በጥሞና አንድ ጥያቄ እናንሳ የነቢያትና የጻድቃን ዋጋቸው ምንድን ነው?  ነቢይ እግዚአብሄርን ሰምቶ ላመጣው መልዕክት፡ ዋጋው ሰው ሲመለስ ፣ንስሀ ሲገባ ማየት ፣ከመቅሰፍት ከዕልቂት አምልጦ በፈንታው ለእግዚአብሔር እየተገዛ ሲኖር ማየት ነው፡፡ ጻድቅም አመጻን ጠልቶ  በጽድቅ ለኖረበት ኑሮ ጌታ የሚከፍለው መንፈሳዊና ስጋዊ በረከት ነው፡፡ ስለ መንግስተ ሰማይ ስለ መግባት ጉዳይማ ቢሆን ማንም ቢሆን በህግ እና በስራ አይድንም /ኤፌ.2፤8-9/፡፡ ከዚህ ጋር ሌላው ዋና ነገር  " እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል " የሚለው ቃል ነው፡፡ ጻድቃንን ስንቀበል የምንቀበለው እነርሱ የሚሰብኩትን መድሐኒታችንን ኢየሱስን ነው፡፡ እርሱ እነርሱን ያዳነና ያጸደቀ በመሆኑ ልክ እነርሱን ተቀብለን ስናስተናግድ፣ ስንሰማቸው ፡ስበኩ ብሎ የላካቸውን ጌታ እንቀበላለን፡፡ ጻድቃንን የተቀበላችሁ ወገኖቼ  መስክሩ ብሎ የላካቸውን ኢየሱስንስ ተቀብላችሁዋል?? እርሱ እናንተን  የሚቀበል እኔን ይቀበላል ብሎአልና፡፡  በደቀ መዝሙሩ ስም ቀዝቃዛ ውሀ  የሚያጠጡ ሰዎችም ዋጋቸው አይጠፋም! ነው  እንጂ  የሚለው  አጸድቃቸዋለሁ አይደለም፡፡ ዋጋው /ክፍያው/ ብዙ ዓይነት ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ለዘላለም ህይወት መንገዱ ግን አንድ ብቻ ነው፡፡ እርሱም ሰው በሆነው በክርስቶስ አምኖ ንስሐ መግባት ነው፡፡/ዮሐ.14፤6/፡፡

  አያይዘን ዝክርን፣ ምጽዋትን፣ ሌሎች ለጽድቅ ተብለው የሚደረጉትን ነገሮች ሁሉ ብንመለከት እንዴት መንግስተ ሰማይ ለመግባት ሊጠቅሙን ይችላሉ?  በእንደዚህ ሁኔታ መዳን ቢቻል ኖሮ ለምን መድኀኒዓለም መጥቶ ዋጋ  ከፈለልን ? ለምን ተገረፈ ?፣ ተሰቀለ ?፣ ሞተ ?፣ ተቀበረ ? ለምን ?? ቃሉ የሚለን  " ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን አንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ስራ እንዳይሆን ስጋን የለበሰ ሁሉ በህግ ስራ ስለ ማይጸድቅ እኛ ራሳችን...እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል፡፡ ገላ.2፤16፡፡ በሐዋርያት ሥራ 4 ቁ.12 ላይ እንደተገለጠውም ወአልቦ፡ ካልእ፡ ሕይወት፡ ወአልቦ፡ ካልእ፡ ስም፡ በታሕተ፡ ሰማይ፡ ዘይትወሀብ፡ ለእጉዋለ፡ እመሕያው፡ በዘ፡ የሐዩ፡፡ /መዳን በሌላ በማንም የለም፡እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ  ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና፡፡"

   ቆርነሌዎስ የሚባለው ሰው / በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ 10፤1-48 ላይ የምናገኘው/ ፡ ለጽድቅ ብሎ ብዙ ነገሮችን ይፈጽም ነበር፤ ለምሳሌ ይጾም ነበር፣ ከቤተሰዎቹ ጋር እግዚአብሔርን የሚፈራና የሚያመልክ ነበር፣ ለድሆች እጅግ ምጽዋት ያደርግ  ነበር፡፡ ምንም እንኩዋ ድርጊቱ ደስ የሚያሰኝና እግዚአብሔር ዘንድ የደረሰም ቢሆን ለመጽደቅ ግን ዋነኞች ጉዳይ ስላልነበሩ፡ መልዐክ  ወደ እርሱ ዘንድ ተልኮ ስለ ክርስቶስ ወንጌል የሚነግረው፣ እንዲያምን የሚረዳውና የሚያስተምረው ደቀመዝሙር ጠቁሞት ልኮ አስመጥቶታል፡፡ ያደረገው ነገር ሁሉ ለመዳኑ በቂ  ከነበረ  ጴጥሮስ ለምን ወንጌል እንዲነግረው ታዘዘ ?  መልካም ስራዎች ሁሉ በጌታ ያመኑና የጸደቁ ሰዎች ሊያደርጉት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በመልካም ስራቸው ጌታቸውን ማስመሰገንና መግለጥ ስላለባቸው፡፡ በጎ ስራ መስራት ዝክር፣ ጾምና ጸሎት፣ ምጽዋት ማድረግ ግን ብቻውን አያጸድቅም፡፡

              የሙታን ተስካር
  ለሞቱ ሰዎች መጸለይ ይገባል! የሚሉ ሰዎች መነሻ ጥቅሳቸው 2ኛ መቃቢያን 12፡41-46 / ከ66ቱ መጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ባለ አዋልድ መጽሐፍ ላይ የሚገኝ/ ሲሆን፤ በእርገግጥ በጥንት ጊዜ ጀምሮ በቻይናውያን እምነትም ዘንድ እንደ ቡዲዝም ባሉት እምነቶች ሙታንን ወክለው መስዋዕት ማቅረብ የተለመደ ነገር ነው፡፡
 ለሙታን መጸለይ /ፑርጋቶሪ/ አንድ ሰው ከሞተ በሁዋላ ነፍሱ ሲኦል ትገባለች፤ ነገር ግን ቤተሰቦቹና ዘመድ አዝማድ ከሞተበት ዕለት ጀምሮ እስከ ሰባት ዓመት ድረስ በየተወሰነው ጊዜ በስሙ ዝክር ቢያወጡለት ቀስ በቀስ ከሲኦል እየወጣ ይመጣና በሂደት ገነት ይገባል የሚል የኑፋቄ ትምህርት ነው፡፡ ምናልባት ወደፊት የምናነሳቸው የገድላት መጽሐፍት ለዚህ ትምህርት አስተዋጽኦ አድርገዋል ብዬ አስባለሁ፡፡

  1.   ነገር ግን ሉቃስ 16 ቁ.19-31 ከቀረበውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው ምሳሌ እውነቱን  መማር እንችላለን፡ አንድ ሰው የሆነውን ሆኖ ከሞተ ወዲያ ሰማይ ላይ ሔዶ የሚያስቀይረው ሐሳብ የለም፡፡ በጻድቃን ሰማዕታት ምልጃና ልመናም መዳን አይችልም፡፡ ክፍሉ ላይ እንደተመለከተው ሐብታሙ ሰው ከሲኦል ሆኖ ምንም አብርሐምን በእሳት እየተንገበገበ ቢለምንም '' በዚህ ያሉ ማለትም በአብርሐም እቅፍ ውስጥ በእረፍት ያሉ ወደ ስቃዩ ስፍራ መሄድና ማዳን እንዳይችሉ በመካከል ታላቅ ገደብ ተደርጎአል:: '' ነው ያለው፡፡ / በገነት ያሉ ወደ ሲኦል ፤በሲኦል ያሉ ወደ ገነት መምጣት አይችሉም ! / ፡፡ ከዚያ በሁኣላ በምድር ላይ አባቱ  ቤት ስላሉ 5ት ወንድሞቹ  ነው የተጨነቀው፡፡ ወደዚህ ስቃይ ስፍራ እንዳይመጡ ሰው ከሞት ተነስቶ ይመስክርላቸው ብሎ ተማጸነ፡፡ ምናልባት እንደርሱ ሰማይ ስንሔድ ጻድቃን ሰማዕታት አሉልን! ብለው ተዘናግተው ከሆነ እንኩዋ፤እውነቱ ያ እንዳልሆነ ስለተረዳ ይሆን ?  ለማንኛውም ለዚህም ጥያቄ ቢሆን እዛው ምድር ላይ ያሉትን መስካሪዎች /ሙሴና ኤልያስ አሉላቸው / እነርሱን  ይስሙ ነው የተባለው፡፡ ተመለከታችሁ በሰማይ ምንም አይነት ቀልድ እንደሌለ? ሐጢያተኛ ሰው ከሞተ ወዲያ፡ ፍርድ ብቻ ነው የሚጠብቀው፤ አንድ  ጊዜ  በፍርድ  ሲኦል  የገባን   ነፍስ  ተከራክሮ ፣ ውሳኔ  አስቀይሮ  ወደ ገነት ሊያመጣ  የሚችል  አንድም  መልዐክ  ወይም  ጻድቅ  የለም!!!   ወገኖቼ አንሞኝ ዛሬውኑ ፡ቀን ሳለልን ፣ትንፋሻችን ሳይቆም በክርስቶስ አምነን እንዳን ! አውነተኛ ንስሐም እንግባ፡፡ ጌታ ሆይ ሐጢያቴን ይቅር በለኝ ልጅህን ኢየሱስን የህይወቴ አዳኝ አድርጌ እቀበላለሁ እንበል፡፡ አሁኑኑ ባሉበት ቦታ ሆነው ንስሐ ሊገቡ ይችላሉ፡፡

ማስታወሻ፡- በተጨማሪ አማላጅነት ክፍል- 1ን  ያንብቡ፣ ለዘመዶችዎ እና ለወዳጆችዎ ሁሉ ይላኩላቸው! ይጸልዩላቸው!  

                                                                  benjabef@gmail.com


No comments:

Post a Comment