Friday, February 6, 2015

አስቸኩዋይ መልዕክት

     "ኢየሱስ ይሰብክ ወይበል፡ተነስሑ እስመ ቀርበት መንግስተ ሰማያት!" ወንጌል ዘማቴዎስ 4፤17           /ኢየሱስም መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ እያለ ይሰብክ ጀመረ /

                     ለምወዳችሁ  ቤተሰቦቼና ወዳጆቼ

በቅድሚያ የፍቅርና የከበረ ሰላምታዬን  በእግዚአብሔር ስም አቀርብላችሁዋለሁ፡፡ የጌታ ሰላምም ይብዛላችሁ፡፡

ዛሬ ይህንን አጭር መልዕክት ልጽፍላችሁ ያነሳሳኝ ምክንያት ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደሰማችሁት በክርስቶስ የማያምኑ ሁሉ የዘላለም ፍርድ ይጠብቃቸዋል ፤ያመኑት ግን የዘላለም ህይወትን አግኝተው መንግስቱን ይወርሳሉ፡፡ስለሆነም ይህንን እውነት ለምወዳቸው ሁሉ አስረግጦ መናገር በዚህ  የመጨረሻ መጨረሻ ጊዜ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ሁሉ ሐጢያት ሞተ፣ተቀበረ፣በሶስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሳ፤ሞትንም ድል አድርጎ በተነሳ  በ40ኛው ቀን ወደ ሰማይ አረገ፣በአባቱም ቀኝ ተቀመጠ፡፡አሁን በቅርብ ተመልሶ ለፍርድ ይመጣል ፡፡ያን ጊዜም የዓለም መጨረሻው ይሆናል፡፡ ማንም ሰው ይህንን እውነት ቢያምንና ቢቀበል ከዘላለም ፍርድ ያመልጣል፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን  ''ወይቤሉ ኢየሱስ አነ ውእቱ ፍናትኂ ወጽድቅ ወህይወት ወአልቦ ዘይመጽእ ኀበ አብ ዘእበለ እንተ ኃቤየ "  / ኢየሱስም እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፡፡በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም::/ ብሉዋል፡፡ የዮሐንስ ወንጌል 14፤6፡፡ ይህም የሰው ልጆች ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊመጡ የሚችሉበት እውነተኛና ብቸኛ መንገድ ክርስቶስ እንደሆነ በግልጥ ተቀምጡዋል፡፡

እንዲሁም በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 3 ቁጥር 16-18  " በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ  ዓለሙን እንዲሁ ወዱዋልና፤ ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አላከውምና፤በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሐር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡" ተብሎ ተጽፉዋል፡፡

ዋና ዋና ነጥቦቹ ፡-  1ኛ- ለሰው ልጆች ሁሉ መዳን እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጥቱዋል፡፡

             2ኛ- ክርስቶስ የመጣው ዓለምን ሁሉ ለማዳን ነው፡፡

             3ኛ- በክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ አይፈረድባቸውም፡፡

             4ኛ- በክርስቶስ አምነው ያልዳኑ ሁሉ ፍርድ ይጠብቃቸዋል፡፡ ስለሆነም ከልጅነት እስከ ዕውቀት በማናቸውም ሁኔታ የሰራነውን ሐጢያትና በደል ለእርሱ እየተናዘዝን ለሐጢያታችን የከፈለልንን ዋጋ ማመን አለብን፡፡ 1ዮሐ.1፤9 ሲናገር  "ኀጢያታችንን ብንናዘዝ ኀጢያታችንን ይቅር ሊለን ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡"

እንግዲህ አንድ ሰው በተሰጠው የዕድሜ ዘመን ሁሉ አንድ ቀንም ይህንን ሳይቀበል፣ኀጢያቱንም ለክርስቶስ ዘርዝሮ ሳይናገርና ምህረትን ሳይቀበል፣ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለይ፤ ወይም ክርስቶስ በዳግም ምጽአቱ  ድንገት ቢመጣ ፤የዘላለም ሞት ነው የሚፈረድበት፡፡ የዮሐንስ ራዕይ 20፤15

እናንተም ወዳጆቼ ከዚህ የዘላለም ጥፋትና ስቃይ እንድትድኑ ይህንን የመዳን ወንጌል ቸል ልትሉት አይገባም፡፡

እስኪ ከዚህ በታች ያለውን የንስሐ ጸሎት ከልባችሁ ሆናችሁ ጸልዩ፡- " ጌታ ሆይ እኛ ኃጢያተኞች ነን፤ከልጅነት ጀምሮ እስከዚህ ቀን ድረስ ባለማወቅና በድፍረት የሰራነውን ኃጢያት ሁሉ

 ይቅር በለን፡፡ጌታ ኢየሱስ  ሆይ  ስለ እኛ ሐጢያት መከራን እንደተቀበልክ ፣ደምህን እንዳፈሰስክ ና
 
እንደሞትክልን እናምናለን፡፡ ስለ ሐጢያታችን በፈሰሰው ደምህ ከበደላችን ሁሉ አንጻን ፤ልጆችህም

 አድርገን፡፡ ከዛሬዋ ዕለት ጀምረን አንተን  የህይወታችን ጌታና አዳኝ አድርገን 

ተቀብለንሐል፡፡በልባችንም ላይ ንገስ! ስማችንንም በህይወት መዝገብ ላይ ፃፍልን በኢየሱስ 

ክርስቶስ  ስም አሜን፡፡"

       ይህንን ታላቅ የንስሐ ጸሎት ከጸለያችሁ በሁዋላ ባደረጋችሁት ውሳኔ ፅኑ! በእምነታችሁም እንዳትደክሙ መፅሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ አንብቡ፤ ዘውትርም ጸልዩ፡፡ ህይወታችሁን የሰጣችሁት ጌታ በነገር ሁሉ ከእናንተ ጋር ይሆናል፤ይረዳችሁማል፡፡አሜን፡፡

ማስታወሻ፡- እባክዎ እርሶ የተጠቀሙበትን መልዕክት ቢያንስ ለ10 ወዳጆችዎ ይላኩ!!!

 በወንጌል እንደተባለው  " ወቀርበ ኢየሱስ ወተናገርሙ እንዘ ይብል ተውህበ ሊተ ኩሉ ኩነኔ ሰማይ ወምድር ሑሩ መህሩ ኩሉ አሕዛብ እንዘ ታጠምቅዎሙ በስመ አብ ፡ወወልድ ፡ወመንፈስ ቅዱስ ወመሀርወሙ ኩሉ ያዕቀቡ ዘአዘዝኩክሙ፡ወናሁ አነ ምስሌክሙ በኩሉ መዋዕል እስከ ኀልቀተ ዓለም "  /ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው ስልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ ፡፡እንግዲህ ሂዱና አህዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችሁአቸው ያዘዝሁዋችሁን እንዲጠብቁ  እያስተማራችሁአቸው ደቀ መዛሙርት አድርጉዋቸው ፤እነሆም እኔ እስከ ኣለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ፡፡/  ማቴዎስ 28፤18-20

No comments:

Post a Comment