Monday, February 16, 2015

ንገስባት!

                                           ከፍል-1

 በመጽሐፍ ቅዱስ  ላይ ስለ ሐጢያት በርካታ ቦታዎች ላይ ተጠቅሱአል፡፡ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎች በብርታትም ፣በድካምም አልፈዋል፡፡ ሁሉም ነገር ለትምህርታችን የተጻፈ ነው፡፡ ዛሬ በዚህ ርዕስ ስር የተወሰኑትን በማንሳት በሐጢያት ላይ መንገስ መጽሐፍ  እንዴት እንደሚያስተምረን እናያለን፡፡

        ሐጢያት ምንድን ነው?

1-  የመጀመሪያው ሐጢያት ያለመታዘዝ ነው፡፡ ዘፍ .3፤11
2-  ሐጢያት ቶሎ የሚከብ ነገር ነው፡፡ ዕብ.12፤2
3-  በደጅ /በልብ/ የሚያደባ ነገር ነው፡፡ ዘፍ.4፤7
4- ዕድል ካገኘ በስጋ ላይ መንገስ የሚችል ነው፡፡ሮሜ 8፤12

ሐጢያትን ልክ እንደ ኮምፒውተር ቫይረስ ውሰዱትና፤ ቫይረስ እንዴት በስርዐት የተቀመጡትን ፕሮግራሞች እንደሚያዛባ፤መረጃዎችን እንዴት እንደሚያጠፋ፤እንዲሁም የተለመደውን ስራ እንዳይሰራ እንዴት እንደሚያስተጉዋጉል መመልከት ይቻላል፡፡ሐጢያትም  ልክ እንደዚሁ በሰው ውስጥ ያሉትን በጎ ራዕይና ዓላማዎች እንዳይሳኩ የሚያደናቅፍ ፣ ሰውን ከአምላኩ የሚለይ፣ከራሱ የተፈጥሮ ሁኔታ አስወጥቶ ሌላ ፍጡር የሚያስመስል፤ እንዲሁም ሰዎች ለሰዎች  ካላቸው  የተቀደሰ ህብረትና ግንኙነት የሚለይና የማበላሸት አቅምን የሚጨምር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ክርስቶስን ከዙፋን አስወርዶ ወደ ምድር ያመጣውን፣ ታላቅም የህይወት ዋጋን ያስከፈለው ሐጢያት እንደቀላል በማየት በህይወታቸው ዕቃቃ የሚጫወቱ ብዙዎች ናቸው፡፡ለኀጢያት ዝቅተኛ ግምት የሚሰጥ ክርስቲያን ኀጢያት ምን እንዳስከፈለ በትክክል አልተረዳም እንደ ማለት ነው፡፡

ቫይረስ በአንቲ ቫይረስ እንዲጠፋ እንዲሁ የሐጢያት ማስወገጃው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ክቡር ደሙ ነው፡፡ምክንያቱም የፈሰሰው በትክክል ለሐጢያታችን ማስተሰርያ በመሆኑ ነው፡፡ምናልባት አንቲ ቫይረሶች እንደየ ሁኔታው ሊለያዩ ቢችሉም፡ አንዳንድ ጊዜ አንዱ አንዱን ማጥፋት ላይችል ይችላል፡፡ ዓለም ላይ ለተሰራው ማንኛውም ሐጢያት በሙሉ ግን መንጻት የሚቻለው በክርስቶስ ደም ብቻ ነው፡፡ለሐጢያት ሌላ ተስተካካይ ክፍያ የለውም ወይም የትኛውም ሀይማኖታዊ ና በጎ ተግባራት ለበደል መቀነሻነት /ማስተሰረያነት/ ሊውሉ አይችሉም፡፡ይህ የክርስቶስን ደም ማቃለል ነው የሚሆነው፡፡

ታዲያ በሀጢያት ላይ መንገስ የምንችለው እንዴት ነው? ከዚህ በፊት እሰቲ የሐጢያት ምንጩ ከየት እንደሆነ እንመልከት......ማርቆስ ወንጌል ም.7 ቁ.20 እስከ 23 ላይ ሲናገር  እንዲህ ይላል " ከሰው የሚወጣው ሰውን የሚያረክስ ያ ነው፡፡ከውስጥ ከሰው ልብ የሚወጣ ክፉ ሐሳብ፣ዝሙት፣ መስረቅ፣መግደል፣ ምንዝርነት፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ተንኮል፣ መዳራት፣ ምቀኝነት፣ ስድብ፣ ትዕቢት፣ ስንፍና ናቸው፤ይህ ክፉው ሁሉ ከውስጥ ይወጣል፡ ሰውንም ያረክሰዋል፡፡" በዚህ መሰረት ሐጢያት ከውጪ የሚመጣ ነገር ሳይሆን ከውስጥ ያለ ግፊት ነው ማለት ነው፡፡ ልክ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው ከመስረቁ ወይም ዝሙትን ከመፈጸሙ በፊት ልቡ ውስጥ ያስባል፡፡ዝሙትና ስርቆቱ ድርጊቶቹ እና ፍጻሜዎቹ ናቸው፤ እንጂ ቀድሞም ቢሆን በልብ ፣በሐሳብ ሳይጨረስ ወደ ድርጊት አይገባም፡፡አንድ ሰው ሰኞ ላይ ሆኖ ቅዳሜ ስለሚፈጽመው ሐጢያት ሊያስብ ይችላል፡፡ ሐጠጢየያተቱ ሰኘኞ ጀምሮአል እንጂ ገና ቅዳሜ አይደለም የሚጀምረው፡፡አሁን ርብርቦሹ የተደረጉ ሐጢያቶች ላይ ሆኑዋል፡፡ ነገር ግን ጥራትና ጽዳት የሚያስፈልገው ምቹ ቀናትና ሁኔታን እየጠበቀ ያለ ውስጣዊ ሐጢያት ላይ ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ታዲያ የሰይጣን ተሳትፎው ምንድን ነው? ካልን ክፉ ሐሳብ መላክ፣ ሁኔታዎችን ማመቻቸት..ወዘተ ነው ፡፡እንጂ የማንንም እጅ ይዞ ና ጠምዝዞ ሐጢያት አያሰራም፡፡ ሔዋንንም ቢሆን በቃልና በሐሳብ ነው የማረካት ድርጊቱን ያደረገችው እርስዋ ነች፡፡

          የሐሳብ መበላሸት

   ለሰው ልጆች ሁሉ ውድቀት ሰበብ  የሆነው  የህይዋን  ስህተት የመጣው ሰይጣን ሐሳቡዋን አበላሽቶት ነው፡፡ 2ቆሮ.11፤3 ፡፡ ሐሳቡ የተበለላሸበት ሰው ወደ ድርጊቱ ለመግባት ቀላል ይሆንለታል፤ ልክ እንደ ቃየን ሁሉ የዳዊት ልጅ አቤሴሎምም ወንድሙን አምኖንን ከመግደሉ በፊት ረጅምና የቆየ የግድያ ሐሳብ አርግዞ ነበር፡፡ ጊዜውና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ደግሞ አስገደለው፡፡ 2ሳሙ.13፤2፡፡

   አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሐሳብ ያድርና ድርጊቱ ሊቆይ ይችላል፤ ይህን ጊዜ መንቃት ነው፡፡ ምንም እስካላደረኩ ድረስ ንጹህ ነኝ  ማለት አይቻልም፡፡ ቀን የሚጠብቅ ክፉ ምኞት ላይ መንገስ ያስፈልጋል፡፤ እግዚአብሔር ቃኤልን ቀድሞ ያስጠነቀቀው ለዚያ ነው፡፡ ደጅህ ላይ ሐጢያት እያደባች ነው ንገስባት አለው፡፡ አለዚያ እርሱዋ  ትነግስብሃለች፡፡ ያን ጊዜ ፍቃዱዋን ታደርጋለች፡፡እግዚአብሄር ወደ ቃየን መጥቶ ከነገረው ነገር የምንማረው ኀጢያት ላይ እኛ መንገስ ካልቻልን ኀጢያት በእኛ ላይ መንገስ ይጀምራል፡/ ዘፍ.4፤7/የሚለውን ነው፡፡

   ያዕቆብ 1፤15 ላይ ሲናገር '' ምኞት  ጸንሳ  ሐጢያትን  ትወልዳለች ፡ሐጢያትም  ጸንሳ  ሞትን ትወልዳለች፡፡ " ሞት የሚባለው /ውድቀት ሊሆን ይችላል/፤ ከመከሰቱ በፊት ውስጥን ይዞ  የሚከርመው ሐሳብ  /ምኞት/ ነው፡፡ ምኞት ዝም ከተባለ ቆይቶ ቆይቶ  ሀጢያትን ይወልዳል፡፤ ከዚያም ወደ ሞት ያመጣል፤ ሁሉም ሂደት ነው ማለት ነው፡፡ ሐጢያትን፣ሞትንና ውድቀትን በህይወቱ ማየት የማይፈልግ ሰው ራሱን ማንጻት ያለበት ከውስጥ ነው፡፡ ምን አርግዣለሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ እንዲሰጥ በቅድሚያ ሐሳብ ነው የመጣበት፡፡ '' ዲያቢሎስም ሐሳብ ካስገባ በሁአላ ''ይላል፡ ምናልባት ዲያቢሎስ ወደ አዕምሮው የላከበትን ሐሳብ መቃወም ይችል ነበር ፡፡ ምናልባትም ወደ ሌሎች ደቀመዛሙርትም ሐሳብ ቀርቦም ይሆናል፡፡ ምናልባትም እነርሱ ተቃውመውት ይሆናል፡፡ ይሁዳ ግን ሐሳቡን አስተናገደ፤ ወደ ቀጣዩ ና ከባዱ ነገርም አለፈ፡፡ ሮሜ 6፤12 ''...ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ስጋችሁ ሐጢያት አይንገስ '' ስጋችን ላይ ሐጢያት ሲነግስ  እንደ ስጋ ፈቃድ ለመኖር የስጋን ነገር አዘውትረን እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ /ሮሜ.8፤5/

   ውስጡ የተሸነፈን ሰው ወደተገዛለት ነገር በቀላሉ መጎተት ይቻላል፡፡ ብዙ የሚያቅተው ከነገሮች ውስጥ መውጣት ሳይሆን ነገሮችን ከውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስራኤላውያን በእግራቸው ከግብጽ ውስጥ ወጥተው ነበር፡ ነገር ግን በቆይታ እንደታየው ግብጽ ውስጣቸው ነበረ፡፡ ስለዚህም በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ ይለናል፡፡/ሥራ.7፤39/፡፡ ከዓለም ወጥተን ግን ዓለም ውስጣችን ካለች  እየዘመርን ፣ እየጸለይን ፣ ቤተክርስቲያን እየሄድን የሐጢያት ተጠቂዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ከሁሉ ነገር ተገልለው አንድፊቱኑ ገዳም ለገቡ መነኮሳት እንኩዋ ትልቁ  ትግል የውሰጥ ነው፡፡ ከግብጽ ወጥተህ ግብጽ ግን ከልብህ ካልወጣ ችግር ነው፡፡የሎጥ ሚስት  ከሶዶም በእግሩዋ ወጥታለች ነገር ግን ሶዶም ከውስጥዋ አልወጣም ነበርና እንቅፋት ሆነባት፡፡ መቀየር ፣መለወጥ  ከውስጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በአዕምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ......" የሚለን፡፡ ከየ ዕለቱ ኑሮአችን እንኩዋ ብንመለከት አንድ ሰው ወተት ወይም ጎመን የሚጠላ ቢሆን፡ ከፈለገ  ቦታ ቢመጣም ወይም ነጻም ቢሆን አይነካውም፡፡ ሐጢያትን ከውስጥ ስንጠላ አዩኝ አላዩኝ ከሚል መሳቀቅ እንወጣለን፡፡ በዚህም ላይ ውስጣችንን ቦርቡሮ በጊዜ ሒደት ከሚጥለን ነገር እንገላገላለን፡፡ ልክ እንደ ጎመኑ ና ወተቱ  የትም ብንሆን ፣መቼም ቢሆን አንነካውም፡፡

አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር ውስጡ ችግር ያለበት  ሰው ያማረ  ህንጻ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ውስጥ ቢገባ  ችግሩ አያቆምም ብሎአል፡፡ የገባበት ቦታ ነገሩን ሊለውጥ ስለማይችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት አንድ በጣም ወፍራምና ዕድሜ ጠገብ ዋርካ አውቃለሁ፡፡ነገር ግን በሆነ ወቅት እምብዛም ነፋስ ባልነበረበት ጊዜ ነው ሌሊት ላይ ወድቆ የተገኘው ፤በጊዜው ሁኔታው ሲጠና ዛፉ በከፍተኛ ሁኔታ ውስጡ በብል ተቦርቡሮ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ቅርፊት ተሸፍኖ ያለ እየመሰለ ኖረ፤ነገር ግን ባልታሰበ ቀን ወድቆ ተገኘ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደዚያ ይመስሉኛል ተሸፍነን ጠንካራ ሰዎች እንመስላለን፣ አስተማማኝ እና የመላዕክት ህይወት ያላቸው እንመስላለን፤ ምናልባት ውስጣችን ግን በብዙ እየተገዘገዘ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን በየ አደባባዩ ላይ የሚሰሙት ውድቀቶቻችንም የዚህ ውጤት ይሆናል፡፡እስቲ  ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ ና ነጻ እንውጣ ፡፡ ውድቀትን ብዙ ሰው ሊያየው ፣ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ያለን የውስጥ መቦርቦርና ትናንሽ ልምምዶች ግን እምብዛም አይታይም፡፡እኛው ከጌታ ጋር እንፍታው፡፡ልምምዱ ከፍ ያለ ደረጃ እንኩዋ የደረሰ ቢሆን በጾም ጸሎት በፊቱ ብንሆን የማይለወጥ ነገር ምንም የለም፡፡ ጌታ ሁሉን ይችላልና፡፡

ውስጣችን ያለውን፣ የምንቸገርበትን ነገር  በምን እንደምናውቅና ፣ የውስጥን ትግል እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል በክፍል ሁለት ትምህርታችን እንቀጥላለን፡፡

ማስታወሻ:- ይህን ትምህርት ቅዱሳን እንዲጠቀሙበት ያድርጉ፡፡

                                                                        benjabef@gmail.com

No comments:

Post a Comment