Monday, February 9, 2015

ምስጢረ ድነት




    ''ወይቤ፡ መጽሐፍ፡ ኩሉ፡ ዘየአምን፡ ቦቱ፡ የሐዩ " ሮሜ.10፡11
      

       በክርስትና ውስጥ ሊታወቁ የሚገባቸው ትክክለኛ የደህንነት /ድነት/ መሰረቶች እና ሊመለሱ የሚገባቸው ጥያቄዎች የሚከተሉት ናቸው፡-
 በቅድሚያ ድነት የምንለው የነፍስ ድነትን ነው፡፡ ይኸውም ሰው በሐጢያተኝነቱ ሊቀበለው ካለ ፍርድና ኩነኔ አምልጦ በክርስቶስ የዘላለም ህይወትን ስለ ሚወርስበት ጉዳይ ነው፡፡

1- ሁሉም ሰው ሐጢያትን ሰርቶአል?

" ልዩነት የለምና ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል፤በኢየሱስ  ክርስቶስ በሆነው ቤዛነት እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ፡፡"  በግዕዙ እንዲህ ይላል / ወኢፈለጣ፡ ወኢሌ ለየ፡፡እስመ፡ ኩሉሙ፡ አበሱ፡ወጌጋዩ፡ ወኀደጉ፡ ስብሐተ :እግዚአብሔር /   ሮሜ 3፤23       
 " ልዩነት የለም" የሚለው ቃል የሰውን ስጋ ለብሶ ከመጣው ከጌታችን በስተቀር ስጋን የለበሰን ሁሉ ሰው ማለት ነው፡፡ የሐጢያት መንስኤውም አንድም የአዳም አለመታዘዝ ሲሆን / ሮሜ .5፤19/ :ቀጥሎም ሰው ሁሉ በነፍስ ወከፍ ያደረገው ሐጢያት ነው፡፡

2- የሐጢያት ደሞዝ  ምንድን ነው?

" የኀጢያት ደሞዝ ሞት ነውና ::የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ህይወት ነው፡፡" ሮሜ.6፤20 : ጢይት ልክ  እንደማንኛውም ስራ የራሱ ደሞዝ አለው፡፡ ክፍያው ከበድ ያለ ስለሆነም ነው ንስሀ መግባት አስፈላጊ የሆነው፡፡ የኃጢያት ደሞዝ የዘላለም ሞት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ የዘላለም ሞት ሊታደገን  ፡እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ለእኛ ሰጠን /ዮሐ.3፤16/፡፡

3- ከሞት ፍርድ እንዴት  ማምለጥ ይቻላል?

የዮሐንስ ወንጌል ም.3 ቁ 16-18 ሲናገር " በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ  ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ፤ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አላከውምና፡ በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ  በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል፡፡ " ከላይ እንደተጠቀሰው  ከዘላለም ፍርድ ና ከዘላለም ሞት ለመዳን መንገዱ በክርስቶስ ማመን ነው፡፡ 

4- መዳን ወይም መጽደቅ  በእምነት ነው፡፡

 የእግዚአብሔር ቃል በሮሜ 10 ቁ.9 ሲናገር / እምከመ፡ ተአምን፡ በአፉከ፡ከመ፡ክርስቶስ፡ውእቱ፡እግዚእ፡ወተአምን፡ በልብከ፡ከመ፡አንሥኦ፡ እግዚአብሄር እምውታን፡ተሐዩ፡፡ወልብን፡ ዘየአምን፡ቦቱ፡ይጸድቅ፡ወአፍኒ፡ዘየአምን፡ቦቱ፡የሐዩ፡፡ " ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳነሳው በልብህ ብታምን ትድናለህና፤ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና፡፡ መጽሐፍ በእርሱ የሚያምን አያፍርም ይላልና፤" ሮሜ.10፤9-11፡፡ በቃሉ እንደተጠቀሰው የክርስቶስን ጌትነት በአፍ መመስከርና፣ ተሰቅሎ ለኃጢያት ስረየት የሚሆነውን ደሙን አፍስሶ፣ ሞቶ፣ ተቀብሮ፣ በሶስተኛው ቀን ከሙታን ተለይቶ እንደተነሳ ማመን ደግሞ ሁለተኛው ዋና ነገር ነው፡፡

5- ንስሐ መግባት!

 ኢየሱስም ራሱ " ተነስሑ እስመ ቀርበት መንግስተ ሰማያት"- /መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ፡፡/ ወንጌል ዘማቴዎስ 4፤17፡፡ በሌላም በኩል ማመንና ንስሐ መግባት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡ በ ሌላ አነጋገር ንስሐ መግባትና ማመን የማይነጣጠሉ ናቸው ማለት ነው፡፡ ታዲያ ንስሐ ስንገባ ኃጢያታችን ይቅር እንደሚባል ተስፋ ተሰጥቶናል፡፡ " በኃጢያታችን ብንናዘዝ  ኃጢያታችንን ይቅር ሊለን ከአመጻም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው፡፡ኃጢያትን አላደረግንም ብንል ሀሰተኛ እናደርገዋለን፡፡ቃሉም በእኛ ውስጥ የለም፡፡ " / 1ዮሐ.1፤9-10/፡፡ መናዘዝ ማለት በስውርና በግልጽ፤ በስህተትና በድፍረት የሰሩትን ሐጢያት ለእግዚአብሔር ዘርዝሮ መናገር ማለት ነው፡፡

6- ጌታን መቀበል ምንድን ነው?

 ጌታን መቀበል የሚለው ቃል የመጣው ከዮሐንስ  ወንጌል ም.1 ቁ.11-13 ባለው  መሰረት ነው፡፡ " ወለእለስ፡ ተወክፍዎ፡ወሀቦሙ፡ሥልጣን፡ውሉደ፡ እግዚአብሔር፡ ይኩኑ ለእለ፡አምኑ፡በስሙ፡፡ " /የእርሱ ወደ ሆነው መጣ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም ፡፡ለተቀበሉት ሁሉ ግን በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ስልጣንን ሰጣቸው፡/ ይላል፡፡ ጌታችን  መድሀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን የምንቀበለው  /የምናስተናግደው /  የልባችንን በር በመክፈት ሲሆን በህይወታችን ላይ እርሱን እንደ ሊቀ ካህን፣ እንደ ነቢይ  የዘላለም ጌታና  ንጉስ አድርጎ መሾም ነው፡፡ራዕይ 3፤20

7- ዳግም መወለድ ማለት ምንድን ነው?

   ከላይ የዘረዘርናቸውን መንፈሳዊ እውነቶች በህይወቱ  በመታዘዝ ያደረገ ሁሉ ዳግመኛ ተወለደ ማለት ይቻላል፡፡ በዮሐንስ  ወንጌል ም.3 ቁ.3 እንደሚናገረው  " ኢየሱስ ወይቤሉ፡አማን፡አማን፡እብለከ፡ዘኢተወልደ፡ዳገመ፡አይክል፡ርዕዮታ ለመንግሥተ፡ እግዚአብሔር፡፡" /...እውነት እውነት እልሀለሁ ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግስት ሊያይ አይችልም ! ማለት ነው ትርጉሙ::

ለምሳሌ በዚህ ታሪክ ላይ የምናገኘው ኒቆዲሞስ  ሽማግሌ ነበር፣ የአይሁድ አስተማሪ ነበር፣ ይህ ብቻ አይደለም አጥባቂ ፈሪሳዊ  ነበር፣ ደግሞ የአይሁድ አለቃ ነበር፡፡ ረጅም ዘመን ብሉይ ኪዳንን ያስተማረ እንኩዋ ቢሆን፣ ወይም አለቃና በእድሜው የበሰለ የሚባል ሰው ቢሆን?  ዳግመኛ  ካልተወለድክ፤ የእግዚአብሔርን መንግስት አታይም ነው የተባለው፡፡ ስለዚህ ዳግም ሳንወለድ የምናደርጋቸው የትኞቹም ኀይማኖታዊ  እንቅስቃሴዎች  ለመዳናችን  ፋይዳ  የላቸውም:: አንተ ወንድሜ፣ አንቺስ እህቴ  ዳግመኛ ተወልዳችሁአል?

7- ንስሐ  ለገቡ ፣ ዳግመኛ ለተወለዱ  የተዘጋጁ  በረከቶች:-

  •  የዘላለም ህይወት ያገኛሉ፡፡ ዮሐ.3፤18፣ 1ዮሐ.1፡13
  •  ስማቸው   በህይወት  መዝገብ  ላይ ይጻፋል፡፡ ሉቃ.10፤20 ና ራዕይ 20፤15
  •   ከድቅድቅ  ጨለማ ወደሚደነቅ  ብርሀን  ይወጣሉ፡፡1ጴጥ.2፤9
  •  
  •   የክርስቶስ  ክብር  ተካፋይ  ይሆናሉ፡፡2ተሰ.2፤1
  • አዲስ   ፍጥረት ይሆናሉ፡፡ 2ቆሮ.5፤17
  •   ይጸድቃሉ፤  ይድናሉ ፡፡ ሮሜ.10፤ 9፣ ዮሐ.3፤16-18
  •   የእግዚአብሄርም ቤተሰብ ይሆናሉ፡፡ ኤፌ.2፤19፣ 1ዮሐ.5፤1


                                                 benjabef@gmail.com    

No comments:

Post a Comment