Saturday, January 31, 2015

አማላጅነት!

                                      አማላጅነት

                                    /ክፍል- 1 /

ክርስቶስ ፈራጅ ነው /አማላጅ  ?

የጻድቃን አማላጀነት ያስፈልጋል ወይ ?

የመላዕክት ድርሻስ ምንድን ነው ? የሚሉትን ነገሮች በስፋት እንዳስሳለን፡፡

በቅድሚያ ጻድቅ የሚባለው ማን ነው?  ምን ያደረገ ነው?  የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ መጽሀፍ ቅዱስ ላይ ተመስርተን እንመልስ፡ ጻድቅ ማለት በእግዚአብሔር ፊት ትክክል የሆነ ፣ተቀባይነትን ያገኘ ማለት ሲሆን፡፡ ህግጋትን በመፈጸምና አንድም ሀጢያት ባለመፈጸም የታወቀው ብቸኛ ሰው የሆነው ደግሞ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሌሎች ሰዎች ሁሉ በደልን እንደሰሩ ቃሉ እንዲህ ይላል፡ ‹‹ልዩነት የለምና ሰዎች ሁሉ ኃጢያትን ሰርተዋል የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሎአቸዋል በክርስቶስ በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ  ››  ሮሜ.3፤20-23 ይላል፡፡ 'ልዩነት የለም'  የሚለው ቃል ጻድቅ  እንደሌለ እና በራሱ ተቀባይነትን በእግዚአብሔር ፊት ያገኘ አንድም እንደሌለ ነው የሚያሳየው፡፡ ስለሆነም በክርስቶስ በኩል በእምነት የሆነው የእግዚአብሔር ጽድቅ ወደ ሰዎች መጣ  /ሮሜ.5፤1/፡፡

       ‹‹እንግዲህ በአንድ በደል ምክንያት ፍርድ ለኩነኔ ወደ

         ሰው ሁሉ እንደ መጣ እንዲሁም በአንድ ጽድቅ

         ምክንያት ስጦታው ህይወትን ለማጽደቅ  ወደ ሰው

         ሁሉ መጣ፡፡በአንዱ ሰው አለመታዘዝ  ብዙዎች ኀጢያተኞች

         እንደሆኑ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች

         ጻድቃን ይሆናሉ፡፡›› ሮሜ.5፡18 ና 19

እግዚአብሔር ያዘጋጀው ጽድቅ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የሚገኝ ጽድቅ ነው፡፡ እንጂ ህግን በመፈጸም ና በጎ ተግባራትን በመከወን  አይደለም /ሮሜ.3፡28/፡፡ በአዲስ ኪዳን ዘመን ጻድቅ ማለት በጌታችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ  አምኖ የዳነ፣ በደሙም ኀጢያቱን የታጠበ እና በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ታርቆ በጽድቅ እየኖረ ያለ ሰው ነው፡፡

ክርስቶስ ለተወሰነ ህብረተሰብ ክፍል አይደለም የሞተው ::ለዓለም ሁሉ እንጂ፡፡ስለዚህም ነው መድኀኒዓለም ብለን የምንጠራው፡፡የእርሱ ስቅለትና ሞቱ እኛን ለማዳን በቂ ነው፡፡ለኀጢያታችን የከፈለው ዋጋ፣የፈሰሰው ደም፣የተሰቃየው ስቃይ የሁላችንን እርግማን ለመሻር ና ዕዳችንን ለመክፈል በቂ፣ ከበቂም በላይ ነው፡፡አባቱ በቂ አይደለም! ብሎት በነበረ ኖሮ ሌሎች ተጨማሪ የመዳን ስራዎችን በሰራን ነበር፡፡ነገር ግን እኛን ለማዳን ያነሰ ና የቀረ ነገር አልነበረም የመስቀሉ ስራ አብን አርክቶታል፡፡ ተፈጸመ ብሎኣል፡፡ ስለዚህ ጽድቅ  የማግኛው መንገድ ክርስቶስ ብቻ እንደሆነ ዮሐንስ በወንጌሉ ላይ ምዕራፍ 14 ቁጥር 6  እንዲ ይላል፡-" እኔ መንገድና እውነት ህይወትም ነኝ፡፡በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም፡፡"  'በእኔ በቀር'  የሚለው ከጌታችን ኢየሱስ  በስተቀር ማንም ማዳን እንደማይችል ያሳያል፡፡

አማላጅነት የሚለው ቃልና ሀሳብ ብዙ የተሳሳቱ ትርጉም ሲሰጣቸው ይስተዋላል፡፡ማማለድ ማለት ማስታረቅ፣ማስማማት ማለት ነው:: ይህን ነገር በሁለት ሊስማሙ በሚገባቸው መሀል ገብቶ የሚፈጽመው ሰው አማላጅ /አስታራቂ / ይባላል፡፡ለምሳሌ በዚህ ዘመን እንደሚታወቀው አንድ አገር ከሌላ አገር ጋር ሲጣሉ ሊሸመግሉ የሚገቡት ከተጣሉት አገራት በብዙ ነገራቸው የሚበልጡና ከፍ ያሉ አገራት ናቸው፡፡ለምሳሌ ሁለቱ ሱዳን አገራትን እያስማሙ ያሉት አገራት ፕሬዝዳቶችን ብናይ በፍጹም ከተጣሉት ያነሱ አይደሉም እንደውም ብዙ ጊዜ ከበድ ያለ ሰው ሲመጣ ሽምግልናው ይሳካል፡፡በቤተሰብ ደረጃም ብንሔድ ልጅ ከአባቱ ወይም ከእናቱ ጋር ቢጣላ ወደ ወላጆቹ ለዕረቅ የሚላከው ሰው እናትና አባት ሊሰሙትና ሊያከብሩት የሚችሉት ሰው መሆን አለበት፡፡ይህን ሁሉ የምንለው ማማለድ ማለት የማነስ ምልክት አይደለም ለማለት ነው፡፡

ታዲያ ሰውና እግዚአብሄርንም ለማስታረቅ ከሰውም ሰው የሆነ: ከእግዚአብሔር ጋርም እኩያ የሆነ አስፈላጊ ነበር፡፡ ክርስቶስ ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እኩል የሆነ አምላክ በመሆኑ የማማለድን ስራ ሰራ፡፡ እርቁ ግን ከአብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱም ጋር ነበር፡፡

ይማልዳል / ያስታርቃል/ ሲባል ተንበርክኮ ይለምናል ፣ዝቅ ብሎ ይለማመጣል ማለት አይደለም፡፡እንኩዋን እርሱ ከላይ የጠቀስናቸው የአገራት ሽማግሌዎች  ተደፍተው አይለምኑም፡፡ነገር ግን ለሰው ልጆች ሁሉ ቤዛ የሆነበት ደሙ በአብ ፊት ዘውትር ይታያል ማለት እንጂ፡፡ስለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ ሲጠቅስ ''እርሱ ግን ስለ ኀጢያት አንድን መስዋዕት ለዘላለም አቅርቦ በእግዚአብሔር ቀኝ  ተቀመጠ፡'' የሚለን፡፡ ዕብ. 10፤12  በተጨማሪ  9፤28ን ያንብቡ፡፡

አሁን በሰማይ እገሌንም ይቅር በለው እገሊትንም ይቅር በላት እያለ የሚለመንበት ዓይነት የምልጃ ስርዐት  ይኖራል ብለን አንጠብቅም፡፡ በክርስቶስ በኩል የቀረቡትን ሁሉ  ከሐጢያትና ከበደል ነጻ የሚያደርግ ቅዱስ  ደም ግን አለ፡፡ ደሙ ስለ ሁላችን ሐጢያት ማስተሰርያ እንዲሆን የፈሰሰ ነው፡፡

ክርስቶስ ስለ እኛ ይማልዳል! የሚለውም ቃል /ሮሜ 8፤34/ ከላይ በተገለጠው አግባብ ካልተፈታ በቀር ሌላ ነገር እንድንረዳ ሊያደርገን ይችላል፡፡አምላክ ሆኖ እንዴት ዝቅ ይላል እንዴት ይማልዳል ? ክርስቶስ ፈራጅ ነው አማላጅ?  የሚሉ ጥያቄዎች/ አሳቦች/ በስፋት  ይነሳሉ ፡፡ለነገሩ አምላክ ሆኖ እንዴት ያማልዳል? ከሚለው ነገር ይልቅ አምላክ ሆኖ እንዴት ይሞታል? የሚለው ነው ከባድ መሆን የነበረበት፡፡ነገር ግን አምላክ የሆነው ኢየሱስ  መከራን ተቀብሎአል፣ ተገርፎአል፣ ተሰቅሎአል፣ ሞቶኣል፡፡የማዳን ስራውም ተፈጽሞአል፡፡ ወደ እርሱ የሚቀርቡ ማናቸውም ሰዎች በደሙ ነጽተው ይጸድቃሉ፡፡እርሱ በስጋው ወራት የከፈለው የሀጢያት ክፍያና ከብርቱ ጩኸት ጋር ያቀረበው ምልጃ፣ አጠቃላይ የመስቀል ስራው ህያው ሆኖ ወደ እርሱ ለሚቀርቡት ሁሉ ይታይላቸዋል፡፡ክፍያው ስለ ሰው ልጅ ሁሉ  ነውና፡፡

የጻድቃን ምልጃ

ጻድቃን በምድር ሳሉ በምድር ላይ ገና በህይወት ላሉት ሰዎች ሊጸልዩ ና ሊያማልዱ ይችላሉ፡፡ የጌታችን የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያምም አማልዳለች፡፡የሰዎችን ጉዳይ ለልጁዋ ነግራለች ከዚህም በላይ ከበጉ ሐዋርያት ጋር አብራ ጸልያለች፡፡ምናልባት ወንጌል ገና ስላልደረሰበት የአለም ክፍሎች አሳስበው ይሆን?  ሌላም ብዙ የሰዎችን የተወሳሰበ ጉዳየ ይዘው በእግዚአብሔር ፊት በጸሎት ቀርበው ይሆናል፡፡ምን እንደ ጸለዩ ነው እንጂ የማናውቀው መጸለያቸውን እናውቃለን፡፡ሐዋ. ስራ 1፤14፡፡

አለምን ሁሉ ከአብ ጋር የማስታረቅና የማዳን ስራ ግን የተሰራው በጌታችንና በመድሐኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ስራ በመሆኑ፤ ጻድቃንም ሆኑ ሰማዕታት ሰዎችን የማዳንም ሆነ መንግስተ ሰማይ የማስገባት ስልጣን አልተሰጣቸውም፡፡ የዘላለም ህይወት ጉዳይ እንዲህ ቀላል ነገር ቢሆንማ ኖሮ  ክርስቶስ መጥቶ ባልተሰቀለ፤ያን ሁሉ ዋጋ ባልከፈለ ነበር፡፡ እርሱ በስጋ ሳይወለድ እኮ ነብያት፣ አባቶች፣ ነበሩ፡፡ግን መዳን በእነርሱ በኩል ሊፈጸም የሚችል ጉዳይ ባለመሆኑ ነው የጌታችን መምጣት የግድ የሆነው፡፡

ከመዳን ጉዳይ ባሻገር ለተለያዩ ጉዳዮችም ቢሆን የሞቱ ቅዱሳን በህይወት ስላሉት ሊለምኑና የሰዎችን ጸሎት ሁሉ ሊሰሙ  እንዴት ይችላሉ? በመጀመሪያ ከፈጣሪ በስተቀር ሁሉ ፍጡራን  ናቸው፡፡ምድራዊ እናትና አባት ኖሮአቸው የተወለዱ በጊዜና በስፍራ የተወሰኑ ናቸው፡፡ ስለዚህም ነው መሞታቸው፡፡ ከላይ ሆነው ሁሉን ማየት እንደ እግዚአብሔር ከቻሉ እኮ: መለኮት ሆነዋል ማለት ነው ፤ግን እንደዛ አይደለም፡፡

              መላዕክት

በዚሀም ላይ መላዕክት እንኩዋ ቢሆኑ እልፍ አዕላፋት የሆኑት፤ አንድ መልዐክ ሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘት ስለማይችልና ሁሉንም በአንድ ጊዜ መስማት ስለማይችል ነው፡፡ለምሳሌ አብሳሪውን የጌታ ታማኝ መልዐክ ቅዱስ ገብርኤልን እንውሰድ ዕለተ ቀኑ በሚባለው 19 ምናልባት ታህሳስ 19  ንግስ ተብሎ በሚነገረው ቀን ፤ካሉት በርካታ በስሙ የተሰየሙ አብያተክርስቲያናት መካከል መርጦ የሚገኘው የትኛው ክልል ነው? የትኛውስ ቤተክርስቲያን ነው? ምክንያቱም አንድ ነው ብለናል፡፡ ሁሉን መቻል / Omnipotent /፣ ሁሉን ማወቅ / Omniscience  /፣ በአንድ ጊዜ በሁሉም ስፍራ መገኘት / Omnipresent    / የእግዚአብሔር ብቻ የሆነ ባህሪ ነው፡፡ሁሉም ጻድቃን፤ መላዕክት ሁሉን ማወቅ፤በሁሉ ቦታ በአንድ ጊዜ መገኘትና የሁሉን ሰው ጸሎት ማድመጥ የሚችሉ ከሆነ እግዚአብሔር የሚባለው አምላክ ምን ልዩነት አለው ታዲያ?  ነገር ግን እውነቱ እነዚህ ባህርያት ማንንም ያላጋራበት የስላሴ ብቻ የሆነ ነው፡፡ ስላሴን የተለየ የሚያደርጋቸውም ይህ ባህሪ ነው፡፡

ለምሳሌ ቅዱስ ገብርኤል የኢየሱስን እናት ማርያምን ሊያበስራት የመጣ ጊዜ እርሱን ሌላ ቦታ ማግኘት አይቻልም፡፡ ምናልባት በዚያ ጊዜ አጣዳፊ ጉዳይ ካለ እንኩዋ ሌላ መልአክ ነው የሚላከው:: ምክንያቱም አንድ መልዐክ መገኘት የሚችለው በአንድ ቦታ ብቻ ስለሆነ ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ወደ ዳንኤል መልስ ይዞ  እየበረረ ይመጣ የነበረውን መልዐክ  /አንዳንድ ሰዎች ገብርኤል  እንደሆነ ይላሉ/  የፋርስ አለቃ  (የፋርስ መንግስት አገር  ላይ በአየሩ ላይ አለቃ የነበረ አጋንንት) እንዳያልፍ ከልክሎት እንደነበር፤ ለ 21 ቀናትም ተቸግሮ እንደነበር ማወቁ ጥሩ ነው፡፡በሁዋላም ወደ ዳንኤል መምጣት የቻለው የመላዕከት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ሊረዳው ስለመጣ ነበር /ዳን.10፤13-20/፡፡ መላዕክት ሲላኩ በቦታ በስፍራ የሚወሰኑ መሆናቸውን ተመለከታችሁ? እንዳይመጣ ተከልክሎስ እንደ ነበረ አያችሁ?

መላዕክቶችም ሆኑ ቅዱሳን ወደ ጠሩአቸው ሁሉ የመሄድ፣ እንደወደዱ የማድረግ ማንነት አይደለም ያላቸው፡፡ መላዕክትነታቸው ለእግዚአብሔር ነውና እርሱ ወደ ላካቸው ሁሉ ይሄዳሉ፡፡ እርሱ ያዘዛቸውንም ይፈጽማሉ፡፡ ይህን እውነት ማወቅና መናገር እነርሱን ማዋረድ ማለት አይደለም፡፡ በፍጹም እነርሱን ዝቅ ማድረግም አይደለም፡፡ እውነት አርነት ያወጣል፡፡አብርሐም ቤት የመጡት መላዕክት አብርሀም ቤት ጉዳያቸውን ሲፈጽሙ ነው  ሎጥ ዘንድ ሰዶም የሄዱት፡፡

ከመጀመሪያው ግን ከዘላለም  ሞት እንዲያድኑንና እንዲያስታርቁን ተሹመው በነበረ ፡አለመታዘዛችን ነበር ሀጢያት የሚሆን፡፡እነርሱም ብዙ በታዘቡን ነበር፡፡ አሁን ግን ከገረማቸው እንኩዋ  ሊገርማቸው  የሚችለው እነርሱ  ለእረኞች ያበሰሩትን ጉዳይ ያለመታዘዛችንን ሲያዩ ነው  /ሉቃ.2፤9-14/፡፡ የፃድቃንም አግራሞት ለእነርሱም መደሀኒት ወደ ሆነው ወደ ክርስቶስ አለማተኮራችን ነው፡፡ ቅድስት  ማርያምም ከገረማት እንኩዋ የሚገርማት ‹አርሱን ሰሙት›  ያለችውን፣ መድሀኒቴ አምላኬ ባለችው ልጁዋ አለማመናችን ነው፡፡ስለ ሁሉም ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት በመስቀል ላይ ስለ ከፈልክልኝ ዋጋ አመሰግንሀለሁ፡፡በቀራንዮ መስቀል በፈሰሰው ደምህ ሀጢያቴን እጠብልኝ ከበደሌም አንጻኝ፤ወደ ልቤም ገብተህ አብረኸኝ ኑር በማለት ከልባችን  ንስሀ  እየገባን በመጸለይ   ራሳችንን ለመንግስተ ሰማይ እናዘጋጅ፡፡የጌታችን ዳግም ምፅዐት ቀን ተቃርቡዋል፡፡ ከእግዚአብሔር በኩል ያለው ነገር ሁሉ ተሰርቶ አልቁዋል፤ ከእኛ በኩል የቀረውን እናድርግ!! ሰምተን እንድንታዘዝ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡አሜን፡፡

አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ ከስር አስተያየት መስጫ ሣጥኑን  / COMMENT   / ተጭነው ይጻፉ፡፡




Wednesday, January 28, 2015

ሰጥቶም ነስቶም...!

                               ሰጥቶም ነስቶም ሲያየን?!

ብዙ ጊዜ በህይወታችን የምናልፋቸው ሁለት ነገሮች አሉ፡፡አንደኛው ማግኘት ሲሆን ሁለተኛው ማጣት ይሆናል ፡፡ይህ  ምናልባት ገንዘብ ነክ በሆነ ጉዳይ ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡አንዳንድ ጊዜ ደስ የሚሉ ቀኖች በህይወታችን ይከሰታሉ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ መኖርንና መፈጠርን እስኪያስጠላ ድረስ ሊኮን ይችላል፡፡ደግነቱ የመከራና የችግር ዘላለማዊ ማህተም ማንም ላይ ስላልታተመ፤ ደግሞ ከደረሰብን ጉዳትና ከገጠሙን ችግሮች በጸጋው አገግመን ሌላ ደስታና ሰላም ውስጥ ስለምንገባ እግዚአብሔር ይመስገን ፡፡

 ለዛሬው ርዕሳችን የኢዮብን ህይወት በመጠኑ ብንዳስስ አሰብኩ፡-ኢዮብ  ትልቅ የሚባል መከራ ውስጥ የነበረ ጻድቅ ሰው ነበር ፡፡ ለምን ያን ሁሉ መከራ ደረሰበት ?  የነበረውን ያን ሁሉ ሐብት እንዴት በአንድ ጊዜ አጣ ?  የሚስቱ መኮብለል፡የልጆቹ መሞት፣የወዳጆቹን ማጣት፣ከዚህ ሁሉ ጋር የእርሱ በቁስል መመታት ...ለኢዮብ ምን ያህል አስከፊ ወቅት እንደነበር መገንዘብ አያዳግትም፡፡ይህ  ሁሉ ለምን እንደ ደረሰበት ኢዮብ በጊዜው የገባው ነገር ባይኖርም ለእኛ ለአንባቢዎች ግን የተገለጠ ነገር አለ፡፡ቃሉ እንደዚህ ይላል፡-

‹‹....እግዚአብሄርም ሰይጣንን  በውኑ  ባሪያዬን ኢዮብን ተመለከትከውን?  እንደሱ ፍጹምና ቅን  እግዚአብሄርን የሚፈራ ከክፋትም የራቀ ሰው የለም ሰይጣንም ለእግዚአብሔር እንዲ ብሎ መለሰለት በውኑ ኢዮብ እግዚአብሔርን የሚፈራ በከንቱ ነውን ? እርሱንና ቤቱን በዙሪያውም ያሉትን ሁሉ አላጠርህለትምን?.... ነገር ግን እጅህን ዘርግተህ ያለውን ሁሉ ዳስስ በእውነት በፊትህ ይሰድብሀል፡፡እግዚአብሔርም ሰይጣንን እነሆ ለእርሱ ያለው ሁሉ በእጅህ ነው ነገር ግን በእርሱ ላይ እጅህን አትዘርጋ አለው፡፡›› ኢዮብ 1፤6-12



ከላይ እንደተገለጸው ሰይጣን የኢዮብን መስግድ፣የሰርክ መስዋዕት ለእግዚአብሔር ማቅረብ ና ማምለኩን፤ ከበዛለት ጥበቃና ከተደረገለት አንጻር ብቻ እንደሆነ ነው  እያስረዳ የነበረው፡፡ ነገሩ እንካ በእንካ አይነት ነው፡፡ እግዚአብሔር ደግሞ የኢዮብ መሰጠትና አምልኮ  ከሁኔታዎች ጋር የተያያዘ አይደለም አለ፡፡በኢዮብ ላይም ከነበረው ጽኑ መተማመን አንጻር ሲሆንለት፣ ሲበዛለት ያመልካል፡፡ ከነጠከው ና ከነሳኸው ግን በፊትህ ይሰድብሀል፡ ተብሎ እየተከሰሰ ያለውን ሰው ሒድና አረጋግጥ፣ ያለውን ሁሉ ጉዳበት፡ እርሱን ግን ተው ብሎ ፈቀደለት፡፡

ጌታ እንዲህ ሊተማመንብን ይችል ይሆን? ብዙ የተደረገላቸው እና አላቸው የሚባሉ ሰዎች ቢነሳቸው በቤቱ ይቀጥላሉ ወይ?  በተቃራኒው ምንም የለሌላቸው ሰዎች ሲሆንላቸውና ሲሳካላቸው  የድሮውን ፍርሀትና አምልኮ ይቀጥላሉ ወይ?  ከችግር፣ ድህነታቸው ከተላቀቁ በሁዋላ  ጸባያቸው የተቀየረ የድሮውን እግዚአብሔርን መፍራታቸውን ትተው፣የሰርክ፤የማለዳ  ጸሎታቸውን ትተው በመዝናናት የተኩ ስንት ናቸው?  የሰጣቸው ነገር ከሰጪው ያራቃቸው ስንት ናቸው?  ከቤተ ክርስቲያን ፣ከተለያዩ መንፈሳዊ ህብረቶች እርቀው ያሉ ስንት ናቸው?

እግዚብሔር ግን ስለ ኢዮብ በድፍረት ተናገረ፡፡ ባይኖረውም ያመልከኛል፡፡የእርሱ ከእኔ ጋር መሆን ነገሮች አይደሉም ምክንያቱ ...እርሱ እኔን እንጂ  ያለኝን ብቻ ፈላጊ አየይደለም!  እንደማለት ነው፡፡

በዚህ ጉዳይ ኢዮብ ተፈትኖ ያለፈ ይመስላል፡፡ ለአብነት ያህል ሚስቱ እግዚአብሔርን ስደብና ሙት ብላ ከተናገረችው በሁዋላ  ኢዮብ ከመለሰው ክፍል እንኩዋ ብናይ ኢዮብን  በቀለላሉ መረዳት ይቻላል፡‹‹..በዚህ ሁሉ ኢዮብ በከንፈሩ አልበደለም፡፡›› ም.2፤9-10 :: ኖሮት በድሎት  ያመለከውን ጌታ አጥቶ ነጥቶም እርሱ ጻድቅ ነው ብሎ መስክሩአል፡፡  እግዚአብሄርም ስለ እርሱ የተናገረው ለሶስቱ ሰዎች "እንደ ባሪያዬ ኢዮብ ስለ እኔ ቅንን ነገር አልተናገራችሁም" ኢዮብ 42፤8--፡፡

ምናልባት በቅዱሳን ህይወት የተለያዩ ፈተናዎች ሊገጥሙ ይችላሉ፡፡ለምሳሌ የሚወዱዋችሁ ሰዎች ቢጠሉዋችሁ፣ በቤተሰብ አካባቢ ያልታሰበ ነገር ቢገጥማችሁ፣ በዙሪያችሁ ያሉ ደስ የሚሉ ነገሮች ድንገት ቢቀየሩ፣ የተማመናችሁበትን ስራ ብትለቁ፣ምናልባት ኑሮ እንደ በፊቱ ባይሆንላችሁ፣ ብርቱ ወዳጆቻችሁ / ያመናችሁት ሰው / ቢከዳችሁ፣ነገሮች እንደምትፈልጉት ሳይሆኑ ሲቀሩ....ወዘተ እንደ ድሮአችሁ አምልኮአችሁን ትቀጥላላችሁ ወይ ? ነው ፈተናው፡፡

ከድህነትና ባለጠግነት ጋር በተያያዘ ጠቢቡ ሰለሞን የተናገረው አንድ ነገር አለ ‹‹ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን  እንጀራ ስጠኝ: እንዳልጠግብ እንዳልክድህም  እግዚአብሔር ማን ነው? እንዳልል ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል. ››  /ምሳ 30፤8-9/  ከቃሉ አንጻር የድሀ ፈተናው ከማጣቱ የተነሳ በእግዚአብሄር ስም ሀሰት እንዳይናገር ሲሆን ፤ የባለጠግነት የጎንዮሽ ችግር ደግሞ: እግዚአብሔር ማን ነው? የማለት፤ ‹ገነንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ.› እስካለኝ ድረስ ማንም ምንም ሊያደርገኝ አይችልም!! የሚል አጉል ትዕቢት ውስጥ መግባት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ልከኛ የሆነ ኑሮን ለራሱ የተመኘው፡፡ለነገሩ በሁለቱም ጎን /ሳይዶች/  ችግሮቹ እየታዩ ነው፡፡ አንዳንድ የአፍሪካ ድሆች  ለምን አፍሪካዊ ሆንን? ለምን ጠቆርን? ለምን ይሄ ና ይሄ የለንም ?  የሚሉ ጥያቄዎችን አንግበው የክህደት አቅጣጫ ሲይዙ:: ባለጠጋዎቹ ደግሞ ሌሎችን በመናቅ፣ለራሳቸው የተለየ ስፍራን በመስጠት ተነጥለው ይኖራሉ፡፡

       ሰዎች የተለያየ በረከት ሲሰጣቸው እና ስኬት ውስጥ ሲገቡ ሊያስቡዋቸው የሚገቡ ጥቂት ቁም ነገሮች አሉ፡፡ምናልባትም ለክፉ ነገር እንዳንነሳሳ እንደ ማርከሻ ልንጠቀምበት እንችላለን፡፡ ከዚያም  በችግር ወቅት ምን ማሰብ እንዳለብን  ጥቂት እናያለን፡፡

1- ትናንትናን/መነሻችንን/ አለመርሳት

 ‹‹ዛሬ  አንተን የማዘውን ትዕዛዙንና ፍርዱን ስርዓቱን ባለመጠበቅ አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ ተጠንቀቅ፤ከበላህና ከጠገብክ በሁዋላ ፣መልካምም ቤት ሰርተህ  ከተቀመጥክ በሁዋላ ፣የላምና የበግ መንጋ ከበዛልህ በሁዋላ .፣ ብርህና ወርቅህ ያለህም ከበዛልህ በሁዋላ ፣ልብህ እንዳይጉዋደድ.....አምላክህን እግዚአብሔርን እንዳትረሳ፤ በልብህም ጉልበቴ የእጄም ብርታት ይህን ሀብት አመጣልኝ እንዳትል፡፡›› ዘዳግም 8፤11-18

2- የተሰጠኝ ነገር በጎ ስራ እንድሰራበት ነው በሚል ዕቅዶችን ማውጣትና ሌሎችን በመርዳት ጉዳይ መንቀሳቀስ

 ‹‹ በአሁን ዘመን ባለጠጎች የሆኑት የትዕቢትን ነገር እንዳያስቡ ደስም እንዲለን ሁሉን አትርፎ በሚሰጠን በህያው እግዚአብሔር እንጂ በሚያልፍ ባለጠግነት  ተስፋ እንዳያደርጉ እዘዛቸው ፡፡እውነተኛውን ህይወት ይይዙ ዘንድ ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሰረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ስራ ባለጠጎች እንዲሆኑ ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው፡፡  ›› 1ጢሞ.6፤17-19

ብዙዎች በአሁን ጊዜ ከረሀብና ከጥጋብ የትኛው ያስቸግራል ? ብለው ይጠይቃሉ፡፡አንዳንዶች እንደ ዳዊት በችግር /በስደት/  ዘመን ታማኝ ሆነው ኖረው ፤ሲነግሱ ሲያልፍላቸው የሚበድሉ አሉ፡፡ዳዊት ከነገሰ በሁዋላ ነው አስከፊ በደሎችን የሰራው ፤በሰራዊቱ ልቡ የታበየው፤ የታማኝ ወታደሩን የኦርዮንን ሚስት የደፈረው፡፡ሌሎች ደግሞ በችግር ወቅት የጣሉት ብዙ መንፈሳዊ ነገር  አለ፡፡ ለምሳሌ ኤሳው ውድ የሆነ ብኩርናውን ለሚጠፋ መብል የለወጠው በራበው ጊዜ ነው፡፡

3-  በጊዜውም አለጊዜውም መጽናት.........ቃሉ በህይወት የሚገጥሙ ሁለቱን ገጽታዎችን ነው የሚጠቁመን፡፡በጊዜው የሚለው የሚመችና ደስ የሚለውን ቀናት ሲሆን፤ያለ ጊዜው የሚለውz ደግሞ ደስ አይሉም የምንላቸውን የማይመቹ ክፉ ቀናትን ነው፡፡

ምናልባት በዚህ ጊዜ በማይመች ሁኔታ ውስጥ ያላችሁ ይህ ዘመን አልፎ ሌላ የበረከት ሁኔታ ውስጥ ትገባላችሁ ብዬ በጌታ ታምኜ እነግራችሁዋለሁ፤ ነገር ግን ሁሌም የማይለወጥና ያው የሆነ ህይወት እስከመጨረሻ እንድንይዝ  አስቀድመን ልንጸልይ ይገባል፡፡በተደላደለ ሁኔታ ያላችሁም ሰዎች ምንም ማድረግ የማትችሉበት ክፉ ቀን ሲመጣባችሁ ታማኝነታችሁ ሳይጎድል ጌታን መጠበቅ እንድትችሉ ተግቶ መጸለይ ያሻል፡፡

በመጨረሻ ሰጥቶም ነስቶም ቢያየን ያው አምላኩን የሚፈራና የሚያመልክ አውነተኛ ክርስቲያን ሆነን አንዲያገኘን ጌታ በዘላለማዊ ጸጋው ይርዳን በማለት በሮሜ 8 ላይ የተጠቀሰውን ሐሳብ ወስጄ ትምህርቴን አጠቃልላለሁ ፤ጳውሎስ እንደጠቀሰው ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየኛል ? ይልና ሁለቱን ዓይነት ገጽታዎች ያስቀምጣል ፡፡ በተለይ " ከፍታም -ዝቅታም" የሚለው ቃል ውስጤን ይስበዋል፡፡ በህይወታችን በተለያየ መንገድ ከፍታ ሲመጣም ፣ ደግሞ ዝቅታዎች ሲገጥሙን ዘላለማዊው ፍቅሩ ያለመናወጥ ውስጣችን ይደር አሜን፡፡.

አስተያየት ና ጥያቄ ደግሞ የጸሎት ርዕስ ካለዎት በአድራሻው ይጻፉ፡፡  benjabef@gmail.com


Friday, January 23, 2015

ራሱን ካላዳነ...!

               ለዛሬ ደግሞ የህይወትን ሌላ አቅጣጫ የምናይበት ግጥም ቀርቦአል፤  ታስታውሱ እንደሆነ ጌታችን በተሰቀለበት ጊዜ ከጎንና ጎኑ አብረው የተሰቀሉ ወንበዴዎች ነበሩ፡፡ አንደኛው እንደዚህ ብሎት ነበር ፡-" አንተስ ክርስቶስ አይደለህምን ? ራስህንም  እኛንም አድን ብሎ ሰደበው !"/ ሉቃ.23፤39/ ይህ  ሰው ያሰበው ራሱን ካዳነ ለእኛም አያቅተውም የሚል ዓይነት ነው፡፡ ግን መለኮታዊው መርህ  ምን ነበር ? ግጥሙን  ደጋግማችሁ በማንበብ ትምህርት እንደምታገኙበት አልጠራጠርም፡፡ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን፡፡በተለይም በመሸነፍ ውስጥ ማሸነፍ እንዳለ ላልተመለከታችሁ የመለኮትን አሰራር እና አደራረግ ትረዱበታላችሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡እሰቲ መሸነፍና ሞኝነት በሚመስል መንገድ ውስጥ እግዚአብሔር የሚሰጠንን ድል እንለማመድ!!



                                ራሱን ካላዳነ !

                   የመከራዋ ቀን ዘግናኝቱ ሌሊት

                   ልብን ከሚሰነቅሩ ብዙ ቃላት

                   በተለይ በተለይ ራስህን አድን የሚለው

                   ራሱን ካዳነ ይሆን የሚያድነው?

                    በራሱ ሲያሳይ ነው በሰው ሚታመነው?

                    እንዲህ ይሆን ወጉ ያገር ፍልስፍናው?

                    ለራሱ ካልሆነ ለእኛ በምኑ ነው!

                    ግን እኮ ራሱን ካዳነ በዚህች ዕለት

                    መከራ ካልነካው ጂራፍ ካልገረፈው

                    ውሀ  ጥም ካልጠማው ደም ላብ  ካላላበው

                    ሰራዊቶች  መጥተው ከሰማይ ከረዱት

                    ደመኞቹን  መጥተው ከተበቀሉለት

                    ወታደር  ከወታደር ጋር ተጋጭቶ

                    ከሰማይ የመጣው የምድሩን ረትቶ

                    ያለ እስራት ፣ያለ ችንካር ፣ያለ ውርደት

                    በሰው አጠባበቅ እንዲ ነው ጀግንነት::

                    ራሱን ካዳነ ለእኛ ምን ሊያቅተው?

                    ለእኛም ያደርገዋል ለእሱ  እንዳደረገው::

                    ነገር ግን እውነቱ  ያንድዬ ብልሀቱ

                     ድነትን ሲቀምር በአዋቂነቱ

                     ካላዳነ ራሱን መድሐኒት ተገኘ

                     በራሱ ሳያሳይ በእኛ ዝናው ናኘ::

                      እርሱ ተገረፈ እኛ ተፈወስን

                      እርሱ ተሰቃየ እኛ ድል አገኘን::

                      ራሱን ካላዳነ ነበር የሚያድነው

                     መለኮት እንደዚህ ድነትን ቀመረው፡፡

                                                                                                    benjabef@gmail.com

Wednesday, January 21, 2015

እግሬን አታጥብም !

                              እግሬን አታጥብም !

ዛሬ እንድንማር ልቤ ውስጥ የተቀመጠው መንፈሳዊ መርህ ጥቂት የሚባሉ ነገሮችን ባለማድረግ የሚቀርብን ታላላቅ ዕድሎችን ስለ ማወቅና በተቃራኒው ደግሞ ጥቂት መታዘዞችን በመፈጸም ትልልቅ ዕድሎችን ወደ ህይወታችን ማስለቀቅ እንዴት እንደሚቻል የሚያስረዳን ነው፡፡

 "...ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ እርሱም ጌታ  ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?  አለው፤ኢየሱስም መልሶ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም በሁዋላ ግን ታስተውለዋለህ፡፡ጴጥሮስም አንተ የእኔን እግር ለዘለዓለም አታጥብም አለው፡፡ኢየሱስም  ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት፡፡....."ዮሐ.13፣6-10.

ጴጥሮስ ልክ ከላይ  እንደተገለጸው እግሬን አታጥበኝም አለ፡፡ነገሩ ከትህትና አንጻር የተደረገ ይመስላል፡፡ አንተ የእኛ መምህርና ጌታ ስትሆን እንዴት ዝቅ ብለህ የእኛን  አገልጋዮችህን እግር ታጥባለህ? አይነት ነው፡፡ነገር ግን በቀላሉ ደግሞ ሊስተው የነበረ ዘላላማዊ ሀሳብ ሲታይ በጣም  ከባድ  ነበር፡፡በቀላሉ አታጥበኝም! በማለቱ ካላጠብኩህ ዕድል ከእኔ ጋር የለህም ተባለ፡፡

ልክ እንደዚሁ የሚመስሉ ትናንሽ ነገሮችን መታዘዝ ስለሚያቅተን ይሆን፤፤ ብዙ ትልልቅ ነገሮችን የምናጣው? አንዳንድ ጥቃቅን የሚመስሉ ድርጊቶችና መታዘዞች ውስጥ የእኛ ዘላለማዊ ጉዳይ ተሰውሮበት እንደሆን ማን ያውቃል?

በብሉይ ኪዳን ንዕማን የተባለውን ሶሪያዊ አለቃን ከለምጽ ለመፈወስ እርሱ በጠበቀው የፈውስ መንገድ ሳይሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ 7 ጊዜ ብቅ ጥልቅ እንዲል ታዞ ነበር፡፡እርሱ ግን መታዘዝን እንቢ አለ፡፡በሁዋላም አብረውት የመጡት ሰዎች ለምነውት ነው ወርዶ የታጠበው፤በቀላል ሁኔታ ግን ፈውሱን አጥቶ ነበር፡፡ አንዳንድ ፈውሶች እንደዚህ ባሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ውስጥ በጥቂት መታዘዝ የሚመጣ ይሆናል፡፡ወይም በጥቂት አለመታዘዝ ፈውስ ይዘገያል፡፡

ሮክ  ፌለር የሚባል የአለማችን ቁጥር አንድ ሐብታም የነበረ፤በአንድ ወቅት ከነበረበት ብርቱ የሆድ ህመም የተፈወሰው ፡ተስፋ ቆርጦ በቀሪው ዘመኑ ድሀ ህጻናትን በገንዘቡ በሚረዳበት ወቅት ነበር፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሊባርከን ሲል የሆነች ቀላል ፈተና ልትገጥመን ትችላለች፡፡ ለምሳሌ  የኢዮብን ሐብት በእጥፍ ለመመለስ እግዚአብሄር የቻለው ኢዮብ በቃላት ስለ ወጉትና ስላደሙት የቀድሞ ወዳጆቹ መጸለይ በመቻሉ ነው፡፡ ልክ ታዞ ሲጸልይ እግዚአብሄር ምርኮውን በእጥፍ መለሰለት ይላል፡፡ኢዮብ 42፣10.

የአንዳንድ ሰዎች በረከት እንዲህ ባለ መንገድ ተይዞ ቢሆን እግዚአብሔር ሰዎችን ይቅር እስክንል ድረስ ምርኮአችንን ሊይዝ ይችላል፡፡ልክ ሰዎችን ስንፈታ ና ለበደሉን መጸለይ ስንጀምር ነገሮች ባልጠበቅነው ሁኔታ እየተከናወኑ ይመጣሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደዚያች መበለት ሴት ለእርሱዋና ለልጁዋ የቀረውን ዱቄት- "ጋግረሽ በዘይት ለውሰሽ አምጪ" እንደማለት ያለ ትዕዛዝ ልንታዘዝ እንችላለን፡፡ አሁን በእውነት ይህች መበለት የሚወሰድባት ነች ወይስ የሚሰጣት? በመለኮታዊው ስሌት ግን የረሀቡን ዘመን በጥጋብ ለማለፍ ያላትን መስጠት ነበረባት ፡፡ ያንንም ታዛ አደረገች እግዚአብሔርም ባረካት፡፡

ስለዚህ አንዳንድ የማይጋጠሙ የሚመስሉ ትዕዛዞችን ብንፈጽም፣ ብንሸነፍ ፤ወይም ቶሎ ይቅር ብንል?....እግዚአብሄር ካዘገጋጀልን የተለያዩ ዕድሎች መጉደል አይሆንም፡፡እግዚአብሔር አምላካችን በዘላለማዊው ጸጋው ይርዳን ማስተዋልንም ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

በርዕሳችን መሰረት ጴጥሮስ እግሬን አልታጠብም ቢልም ቅሉ፤ ነገሩ የእርሱን ከጌታ ጋር የመሆንና ያለመሆን ዕድል ፈንታ የሚያስወስን መሆኑን ሲረዳ  ጌታ ሆይ እግሬን ብቻ አይደለም ሰውነቴን ሁሉ እጠበኝ አስብሎታል፡፡ ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን  አሜን፡፡

አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ በአድራሻው መጻፍ ይቻላል ፡፡ benjabef@gmail.com

Friday, January 2, 2015

የጌታችን ልደት /ገና/

                                 የክርስቶስ  ልደት   /ገና/

አስቀድሜ እንኩዋን ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዐል በሰላም አደረሳችሁ እላለሁ፡፡

      ''እነሆ ለህዝቡ ሁሉ የሚሆን ታላቅ ደስታ የምስራች      እነግራችሁዋለሁና አትፍሩ ዛሬ በዳዊት  ከተማ  መድሐሀኒት  እርሱም  ክርስቶስ  ጌታ  የሆነ ተወልዶላችኃልና.....''ሉቃ.2፤11

የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ዜና ነው፡፡እርሱ የዓለምን ሁሉኀጢይት ለማስወገድ ተወለደ፡፡መለዐኩ ቅዱስ ገብርኤል ለቅድስት ማርያም እንዳበሰረው ''....ስሙን  ኢየሱስ ትዬዋለሽ እርሱም  ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል.." የሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 2 ቀ. 32  ፡፡

ምናልባት ብዙ ጊዜ በተለምዶ ብቻ ገናን ማክበር እየተስፋፋ የሄደ ጉዳይ ነው፡፡ ፈረንጆቹ  በልደቱ  ቀን ስጦታን መለዋወጠ፤ዛፎችን በደመቀ መብራት ማሸብረቅ፤መብላት እና መጠጣት የመሳሰሉትን ጉዳዮች በመፈጸም ቀኑን ያሳልፋሉ፡፡ከበዛ ደግሞ ሳንታ ክሎስ ብለው ከሰየሙት የገና አባት ጋር ፎቶ መነሳት ህጻናቶችን  ማስደሰት....የመሳሰሉትን ያደርጋሉ፡፡እንደውም አሁን አሁን ገና ማለት የልጆች ጊዜ ለማድረግ ትንሽ የቀረው ይመስላል፡፡ይህ ማለት ከዋናው ጉዳይ ጋር እየተለያየን ነው ማለት ነው፡፡

በአገራችንም ከዚህ ባልተናነሰ ሁኔታ ባህላዊ ምግቦችን በማዘጋጀት እና የገና ዛፎችን በማስጌጥ ሲዘፈን ሲጨፈር መዋል የተለመደ ነገር ሆኑዋል፡፡ብቻ በሁሉም ጎን ማለት ይቻላል ፈር የለቀቀ ጉዳይ ይስተዋላል፡፡ማለትም ከዋናው ጉዳይ ጋር ያለተገናኙ ነገሮች የበዐሉ ዋና ነገር ሆነው ቀርበዋልና፡፡

ከርስቶስን  ከውልደቱ ጀምሮ ሊገድለው ሲፈልግ የነበረ ሰይጣን፤ በሁዋላም ከሞት መነሳቱን በውሸት ዜና ተክቶ አልተነሳም ብለው እንዲናገሩ ሲጥር የነበረው ሰይጣን፤ አሁን ደግሞ ስልቱን ቀይሮ ሰዎች የገናን ትክክለኛ ነገር እንዳይረዱ በማድረግ በሚችለው ሁሉ እየሰራ ይገኛል፡፡በተወሰነ መልኩ የተሳካለትም ይመስላል፡፡

የልደቱን ባለቤት በቅጡ ያልተረዳ ህዝብ ገናን ቢያከብር ለሰይጣን የራስ ምታት አይደለም ፡፡ ብዙዎች ክርስቶስን ለሌላ ሀይማኖት እየሰጡ: ከልብና ከቤት አስወጥቶ  ፤ደግሞ  ሌሎች ምናልባት ያልተቀበሉትን የኢየሱስን ልደት ለማክበር ደፋ ቀና ማለት ምን ያህል ያለማስተዋል ይሆን ? ምዕመናን  ሆይ  ልብ ልንል የሚገባው ዋና ነገር የተወለደው ክርስቶስ በእኛ ልብ ስለመኖሩ እና የተወለደበት፣የተሰቀለበት፣የሞተበትንና፣የተነሳበት ትክክለኛ ዓላማ ገብቶናል ወይ የሚለው ቁም ነገር ነው፡፡


ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ከሐጢያት ለማዳን ተወለደ፤በእርሱ የሐጢያታችንን ስርየት እናገኛለን /የሐዋርያት ሥራ.10፤43/፤ መጽሐፍ በእርሱ የሚያምን ሁሉ አያፍርም ይላል፡፡ ሮሜ 10፤11

እርሱ  የህይወታችንም  የክርስትናችንም መሰረት ነው፡፡ ያውም በልደቱ  ቀን እርሱን ደስ የማያሰኘውን ጉዳይ  እየፈጸምን እርሱን አስወጥተን ወይም ቸል ብለን ድግሱ ላይ ብቻ የምናተኩር ከሆንን ምኑ ላይ ነው ክርስትናው?  ያስብላል፤

እህቶቼና ወንድሞቼ አባቶቼና እናቶቼ ምንም እንኩዋ ብዙ ዓመታት ሳይገባን ያደረግን ቢሆን አሁን ግን ወደ እውነት እንመለስና ትክክለኛውን ልደት እናክብር ንስሐ እንግባ፣በደሙም ፊቱ በመቅረብ እንቀደስ፡፡

ልብዎ ፈቃደኛ  ከሆነ ቀጥሎ ያለውን ጸሎት ይጸልዩ፡-እግዚአብሄር ሆይ አንድያ ልጅህን ወደ ዓለም ልከህ ስለ እኔና ስለ ዓለም ሐጢያት እንዲወለድ ስላደረግህ አመሰግንሀለሁ፡ከልጅነት እስከ ዕውቀት የሰራሁትን መተላለፍና ሐጢያት ይቅር በለኝ፡፡ጌታ  ሆይ ወደ ልቤ እንድትገባ እፈቅድልሀለሁ ሁለጊዜ አንተን በማመን ጸንቼ እንድኖር እርዳኝ በጌታችን በመድሀኒታችን በኢየሱስ ክርሰቶስ ስም አሜን፡፡

                                                                                                             benjabef@gmail.com

Thursday, January 1, 2015

አራቱ ጨረቃዎች / ክፍል -3 /

ክፍል 3

በባለፉት ተከታታይ ጊዜያት ስለ አራቱ ጨረቃ ደም ለብስው በ 2014 እና 2015 ስለሚወጡበት ሁኔታና መጽኀፍ ቅዱሳዊ ትንታኔ በመጠኑ በመስጠት ነበር ያለፉት ጽሁፍ ላይ የተቀመጠው አነሆ ዛሬ ደግሞ የመጨረሻው ዘመንን በተመለከተ ከእነዚህ ክስተቶች ጋር በማየያያዝ እንቀጥላለን፤

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በርካታ ቦታዎች ላይ የመጨረሻውን ዘመን በተመለከተ ብዙ የተጻፈ ቢሆንም በተለይ ሊታዩ ከሚችሉ ምልክቶች አንጻር የተጠቀሱትን በተወሰነ መልኩ ባለፈው ክፍል ሁለት ጽሁፍ ላይ ማነሳታችን ይታወሳል፡፡ስለሆነም ከብዙ ምክንያቶች አንጻር አሁን ያለንበት ዘመን የመጨረሻ መጨረሻ ዘመን እንደሆነ አመላካች ነገሮች አሉ፡ ከነዚህም ውስጥ በምድር ላይ ያለው ብርቱ ጦርነት፤ሽብር መስፋፋቱ፤ረሀብና ቸነፈር፤የተፈጥሮ መናጋትና መዛባት.....ለሌሎች ብዙ መከራዎችነን ማንሳት ይቻላል፡፡

ታዲያ በዚህ ወቅት እኛ ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?

1-ክርስቶስ ዋጋ የከፈለለትን ውድ ሕይወታችንን በዓለም ጉድፍ ሳናሳድፍ ልንጠብቅ ይገባል፡፡በአሁኑ ጊዜ ሁሉ ነገር አይኑን አፍጥጦ የመጣበት ጊዜ ነው፡፡ድሮ በስውር የነበሩ ነገሮች አሁን አሁን ድብቅ መሆናቸው ቀርቶ የአደባባይ ሆነዋል፡፡ምንም በብዙዎች የሳቱ ቢኆንም ቅሉ እውነተኛ ክርሰቲያኖች ግን ራሳችንን ከዓለም ነውር መጠበቅ አለብን፡፡

2- ዕለት ዕለት ራሳችንን በእግ ዚአብሔር ፊት ማቅረብ ደግሞ ሌላው ጉዳይ ነው፡፡ የእግዚአብሄር ቃል ሳታቁዋርጡ ዘውትር ጸልዩ ይላልና ፤   1ተሰሎንቄ 5፤16፤ ይህም እየተገለጠ ባለ ስህተት እንዳንወሰድ ይጠብቀናል፡፡ከዚሁ ጋር በንስሀ ፊቱ መውደቅና በፍጹም መንፈሳዊነት ህይወታችንን ጠብቀን መኖር አስፈላጊ ነው፡፡

3-ለጠፉ ወንድሞቻችን እና እህቶ ቻችን ወንጌልን መመስከርም ሌላው የቤት ስራችን ነው፡፡ሰው አንድ ጊዜ ከሞተ ሌላ የንስሀ ዕድል አይኖረውም ፤ወገኖቻችን ለዘላለም ወደሚፈረድበት እና ዳግመኛ ዕድል ወደ ሌለበት ቦታ ከመሄዳቸው በፊት ዓለምን ሊያድን ከመጣው ክርስቶስ ጋር መታረቅ አለባቸው፤ሐጢያታቸውም በክርስቶስ ደም መታጠብ አለበት፡በሐጢያታችን ምትክ ሆኖ ተሰቅሎ የሞተውን በሶስተኛውም ቀን የተነሳውን በ40ኛው ቀንም ወደ ሰማይ ያረገውን ክርስቶስን ማመን እንዲችሉ ልንረዳቸው ይገባል፡፡

ክርስቶስ በቅርብ  ዳግም ወደ ዓለም ይመጣል ያን ጊዜም የዓለም መጨረሻው ይሆናል፡፡ ነቅተን እንድንጠብቀው ጌታ ይርዳን፡፡

                                                                                                 benjabef@gmail.com