Wednesday, January 21, 2015

እግሬን አታጥብም !

                              እግሬን አታጥብም !

ዛሬ እንድንማር ልቤ ውስጥ የተቀመጠው መንፈሳዊ መርህ ጥቂት የሚባሉ ነገሮችን ባለማድረግ የሚቀርብን ታላላቅ ዕድሎችን ስለ ማወቅና በተቃራኒው ደግሞ ጥቂት መታዘዞችን በመፈጸም ትልልቅ ዕድሎችን ወደ ህይወታችን ማስለቀቅ እንዴት እንደሚቻል የሚያስረዳን ነው፡፡

 "...ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ እርሱም ጌታ  ሆይ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን?  አለው፤ኢየሱስም መልሶ እኔ የማደርገውን አንተ አሁን አታውቅም በሁዋላ ግን ታስተውለዋለህ፡፡ጴጥሮስም አንተ የእኔን እግር ለዘለዓለም አታጥብም አለው፡፡ኢየሱስም  ካላጠብኩህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም ብሎ መለሰለት፡፡....."ዮሐ.13፣6-10.

ጴጥሮስ ልክ ከላይ  እንደተገለጸው እግሬን አታጥበኝም አለ፡፡ነገሩ ከትህትና አንጻር የተደረገ ይመስላል፡፡ አንተ የእኛ መምህርና ጌታ ስትሆን እንዴት ዝቅ ብለህ የእኛን  አገልጋዮችህን እግር ታጥባለህ? አይነት ነው፡፡ነገር ግን በቀላሉ ደግሞ ሊስተው የነበረ ዘላላማዊ ሀሳብ ሲታይ በጣም  ከባድ  ነበር፡፡በቀላሉ አታጥበኝም! በማለቱ ካላጠብኩህ ዕድል ከእኔ ጋር የለህም ተባለ፡፡

ልክ እንደዚሁ የሚመስሉ ትናንሽ ነገሮችን መታዘዝ ስለሚያቅተን ይሆን፤፤ ብዙ ትልልቅ ነገሮችን የምናጣው? አንዳንድ ጥቃቅን የሚመስሉ ድርጊቶችና መታዘዞች ውስጥ የእኛ ዘላለማዊ ጉዳይ ተሰውሮበት እንደሆን ማን ያውቃል?

በብሉይ ኪዳን ንዕማን የተባለውን ሶሪያዊ አለቃን ከለምጽ ለመፈወስ እርሱ በጠበቀው የፈውስ መንገድ ሳይሆን በዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥ 7 ጊዜ ብቅ ጥልቅ እንዲል ታዞ ነበር፡፡እርሱ ግን መታዘዝን እንቢ አለ፡፡በሁዋላም አብረውት የመጡት ሰዎች ለምነውት ነው ወርዶ የታጠበው፤በቀላል ሁኔታ ግን ፈውሱን አጥቶ ነበር፡፡ አንዳንድ ፈውሶች እንደዚህ ባሉ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ውስጥ በጥቂት መታዘዝ የሚመጣ ይሆናል፡፡ወይም በጥቂት አለመታዘዝ ፈውስ ይዘገያል፡፡

ሮክ  ፌለር የሚባል የአለማችን ቁጥር አንድ ሐብታም የነበረ፤በአንድ ወቅት ከነበረበት ብርቱ የሆድ ህመም የተፈወሰው ፡ተስፋ ቆርጦ በቀሪው ዘመኑ ድሀ ህጻናትን በገንዘቡ በሚረዳበት ወቅት ነበር፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሊባርከን ሲል የሆነች ቀላል ፈተና ልትገጥመን ትችላለች፡፡ ለምሳሌ  የኢዮብን ሐብት በእጥፍ ለመመለስ እግዚአብሄር የቻለው ኢዮብ በቃላት ስለ ወጉትና ስላደሙት የቀድሞ ወዳጆቹ መጸለይ በመቻሉ ነው፡፡ ልክ ታዞ ሲጸልይ እግዚአብሄር ምርኮውን በእጥፍ መለሰለት ይላል፡፡ኢዮብ 42፣10.

የአንዳንድ ሰዎች በረከት እንዲህ ባለ መንገድ ተይዞ ቢሆን እግዚአብሔር ሰዎችን ይቅር እስክንል ድረስ ምርኮአችንን ሊይዝ ይችላል፡፡ልክ ሰዎችን ስንፈታ ና ለበደሉን መጸለይ ስንጀምር ነገሮች ባልጠበቅነው ሁኔታ እየተከናወኑ ይመጣሉ፡፡

አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እንደዚያች መበለት ሴት ለእርሱዋና ለልጁዋ የቀረውን ዱቄት- "ጋግረሽ በዘይት ለውሰሽ አምጪ" እንደማለት ያለ ትዕዛዝ ልንታዘዝ እንችላለን፡፡ አሁን በእውነት ይህች መበለት የሚወሰድባት ነች ወይስ የሚሰጣት? በመለኮታዊው ስሌት ግን የረሀቡን ዘመን በጥጋብ ለማለፍ ያላትን መስጠት ነበረባት ፡፡ ያንንም ታዛ አደረገች እግዚአብሔርም ባረካት፡፡

ስለዚህ አንዳንድ የማይጋጠሙ የሚመስሉ ትዕዛዞችን ብንፈጽም፣ ብንሸነፍ ፤ወይም ቶሎ ይቅር ብንል?....እግዚአብሄር ካዘገጋጀልን የተለያዩ ዕድሎች መጉደል አይሆንም፡፡እግዚአብሔር አምላካችን በዘላለማዊው ጸጋው ይርዳን ማስተዋልንም ይስጠን፡፡ አሜን፡፡

በርዕሳችን መሰረት ጴጥሮስ እግሬን አልታጠብም ቢልም ቅሉ፤ ነገሩ የእርሱን ከጌታ ጋር የመሆንና ያለመሆን ዕድል ፈንታ የሚያስወስን መሆኑን ሲረዳ  ጌታ ሆይ እግሬን ብቻ አይደለም ሰውነቴን ሁሉ እጠበኝ አስብሎታል፡፡ ጌታ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን  አሜን፡፡

አስተያየት ወይም ጥያቄ ካላችሁ በአድራሻው መጻፍ ይቻላል ፡፡ benjabef@gmail.com

No comments:

Post a Comment