Friday, May 1, 2015

ለቤተክርስቲያን መሪዎች!

                      ክፍል አንድ
ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ ፡ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፡፡
 /ወይቤሎሙ፡ ሑሩ፡ ውስተኩሉ፡ ዓለም፡ ወሰብኩ፡ ወንጌል፡ ለኩሉ፡ ፍጥረት፡፡ / ማርቆስ 16፤15፡፡

ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ እንዲሰበክ ትዕዛዝ የሰጠን ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ወንጌል መስበክ የአንድ ወቅት ስራ አይደለም፡፡ እኛ ወደ ጌታ እስከምንሔድ ወይም ጌታ በዳግም ምፅዓት እስኪመለስ ድረስ የምንከውነው ታላቅ የሆነ ሰዎችን የማዳን ተገግባር ነው፡፡

አንዳንድ ጊዜ ይኸው ወንጌልን የማሰራጨት ተልዕኮ ለጥቂቶች ብቻ የተተወ  ይመስላል፡፡ ሌሎቹ  ምንም የማይመለከታቸው ነውን? አንዳንድ ጊዜም በዘመቻ ይጀመርና በዘመቻ ሲተውም ይታያል፡፡ በእኔ እምነት አንድ ቤተክርስቲያን ወንጌል መስበኩዋን ማቆም ያለባት በዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ ድነው ካበቁ እና የዓለም ፍጻሜ ደርሶ ጌታ ዳግመኛ ሲመጣ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ወንጌልን መስበክ ማቆምና እንደፈለግን አጀንዳውን መቀያየር የምንችል አይመስለኝም ፡፡ ቤተክርስቲያንን የመሰረታት እና ራስ የሆነላት ጌታ እስኪመለስ ድረስ አድርጉ ብሎ ያዘዘውን ተልዕኮ መፈጸም ይኖርብናል፡፡ ተቁዋሙ የእርሱ ነውና፤ በቤቱ የእርሱ ትዕዛዝ ሊተገበር እንደሚገባ አስባለሁ ፡፡

 መሰረታዊው  ነገር ይህ ሆኖ ሳለ፡ በሌላ በኩል ደግሞ ወንጌልን በግድ ፣በፍርሀትና በመጨነቅ እንዳንሰብክ ደግሞ ያስፈልጋል፡፡ ታዲያ እንዴት እንስበክ ?... ከውስጥ በሆነ ፍቅር! በጋለ ስሜት! ነፍሳት እንዲድኑ ባለ እውነተኛ ቅንዐት  / passion   /፡፡ በነገራችን ላይ ለወንጌል ብቻ ሳይሆን፡ ሰለ ሌላውም  ስለምናደርገው ነገር አስቀድሞ ፍቅርና መነሳሳት ቢኖረን ጥሩ ነው፡፡ ቶዘር የሚባል አንድ መንፈሳዊ ሰው እንደተነናገረው '' አንድን ነገር ከመስራት በፊት ለዚያ ነገር ፍቅርና መነሳሳት ያሻል፡፡ በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ትልቁ ነገር፡ ከሌሎች ነገሮች ይልቅ እግዚአብሔርን መውደድ ነው፡፡ የውስጥ መነሳሳት፣ ለነፍሳት የሚኖረን ፍቅር ፣ ተልዕኮና አገልግሎት ሁሉ የሚገኘው ወይም የሚገነባው ለክርስቶስ ኢየሱስ ባለን ጥልቅ ፍቅር ላይ ተመስርቶ ነው '' ብሎአል፡፡

            ከውስጥ የሆነ ፍላጎት /passion/ እንዴት ይመጣል?
ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ለምሳሌ የነህምያን ታሪክ ብንመለከት፡ ከጦቢያና ሰንበላጥ  የመጣበትን ዛቻ ና ማስፈራሪያ ሳይበግረው ህዝቡን አስተባብሮ የኢየሩሳሌምን ቅጥር በ 52 ቀናት  ሰርቶ የጨረሰ ታላቅ ባለ ራዕይ ነው፡፡ የትልቅ ነገር ባለ ራዕይና ባለ ገድል ከመሆኑ በፊት ግን፡ እስራኤላውያን፡ ተግዘው በሄዱበት በስደት ምድር - በባቢሎን ቤተመንግስት ውስጥ በጠጅ አሳላፊነት ሙያ ተቀጥሮ ኑሮውን ሲገፋ የነበረ ሰው ነው፡፡አንድ ቀን ግን አናኒ የሚባል ወንድሙ ስለ ኢየሩሳሌም ጉዳይ ወሬ ይዞ መጣ፡፡ ያንን ወሬ ሌሎችም  የእስራኤል ሰዎች ሳይሰሙ አይቀርም፡፡ ከሰማው ነገር ተነስቶ አንድ ነገር ለማድረግ የወሰነ ግን አናይም፡፡ ነህምያ ግን የኢየሩሳሌም ቅጥር መፍረስና ፣የአባቶቹ መቃብር ያለበት ከተማ በር መቃጠሉን ሲሰማ  ልቡ ተነካ፤ አያሌ ቀን ተቀምጦ  አለቀሰ፡፡/ነህ.1፤3-4/፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡ በሰማይ አምላክ ፊት እያዘነ ይጾምና ይጸልይ ነበር፡፡ በዚህ መልክ ውስጡ ሲነካ ነው ፡ወደ ቀጣዩ እንቅስቃሴ የተራመደው፡፡ ከሞቀ ስራው አስፈቅዶ ወጥቶ የሄደው፤ ሌሎችን ሁሉ አስተባብሮ ቅጥሩን ሰርቶ የጨረሰው፡፡

ልክ እንደዚህ የሆነ ነገር ስንሰማ፣ ስንሰበክ፣ ስንማር ወይም  ስናነብ፣ ቅዱስ ቅንዓት ውስጣችን ሊገባ ይችላል፡፡ የወንጌል ቅንዓትም ወይ በዚህ መልኩ አልያም በሌላ መንገድ ውስጣችን ይመጣል፡፡ ለምሳሌ በሉቃስ ወንጌል 15 ላይ የምናገኘውና ክርስቶስ የተናገረውን ምሳሌ እንመልከት፡፡ታሪኩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፤ አንድ ሰው መቶ በጎች ነበሩት ፤ከመቶዎቹ መካከል አንደኛው በግ ወደ በረሀ ኮበለለ፡፡ ወዲያውም ሰውዬው የነበሩትን ዘጠና ዘጠኙን በመተው የጠፋውን አንዱን ሊፈልግ እንደሄደ ይገልጻል፡፡ያሉትን ዘጠና ዘጠኙን ይባርክልኝ ብሎ እንደ መቀመጥ ፡እንዴት ስለ አንድ በግ  ብሎ ፍለጋ ወጣ  ? ብንል፤ መልሱ ሊሆን የሚችለው ስለ አንድ ግድ የሚያሰኝ ጥልቅ ፍቅር ገብቶበት ነው! በጉ ጠፍቶ መተኛት አይችልም፡፡ ቀጥሎም ነገሩን ከልቡ ሆኖ እንደሚያደርገው የሚያሳየን  '' እስኪያገኘው ድረስ  አጥብቆ መፈለጉ ነው፡፡'' ቁ.4 ፡፡ ካገኘው በሁዋላ ደግሞ፡ ደስታውን የገለጠበት መንገድ በተጨማሪ ልቡንና ቅንዐቱን ያሳየናል፡፡ በጫንቃው ተሸክሞ ወደ ቤት አምጥቶ፣ ጎረቤቶቹን ጠርቶ፣ ደስታውን ገለጸ ይላል፡፡ ካደረጉስ ማድረግ እንዲህ ነው፤ እስኪያገኙ ድረስ አጥብቆ መፈለግ !

     ዛሬ በኛ ዘመን ስንት በግ ጠፍቶብን ነው የተቀመጥነው?

እ.ኤ.አ. ሚያዚያ ወር 2012  ላይ ስለ ዓለም ህዝብ ቁጥር  አንድ አለም አቀፍ ሪፖርት ወጥቶ ነበር ፡፡ሪፖርቱ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ሰዐት የዓለም ህዝብ ቁጥር 7 ቢሊዮን ገደማ ይሆናል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህ ውስጥ 750 ሚሊዮን ወይም 11% የሚሆነው ህዝብ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት  የሚያምን፣ 2.6 ቢሊዮን የዓለም ህዝብ ወይም  38%  ገደማ የሚሆነው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሰማ ነገር ግን ያልተቀበለ  / ሌሎች አዳኞች አሉ ብለው የሚያምኑ/ ፣ የተቀረውና ሰፊው ህዝብ ማለትም 3.5 ቢሊዮን ወይም  50% ገደማ የሚሆነው ምንም የወንጌል መልዕክት ያልሰማና የክርስቶስን አዳኝነት ያልተቀበለ ነው፡፡
   ከነበሩት መቶ  በጎች  አንዱ ቢጠፋ አክንፎ ያስኬደው ፍቅር ተጽፎልን ፡ከሶስት  ቢሊዮን በላይ የዓለም ህዝብ ጠፍቶ ምንም ሳይመስለን ተረጋግተን መቀመጣችን  ምን ያህል አዚም ቢደረግብን ነው ? ማን ነው ይህን ታላቅ ቅንዐት ከውስጣችን የዘረፈብን ? እርግጥ ነው በዚህ የተቀደሰ ተግባር ላይ የተሰለፉ ተግዳሮቶች በርካታ ናቸው፡፡ ውስብስብም ናቸው፡፡ ነገር ግን ጌታ ተልዕኮውን በሰጠበት ጊዜ " አይዞአችሁ እኔ  እሰከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ብሎናል '' ማቴ.28፤20፤

ነፍሳትን ከሲኦል የመታደግ አገልግሎት በእግዚአብሔር መንግስት ካሉት አገልግሎቶች ሁሉ ላቅ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ደግሞ ከላይ እንደተገለጸው ትልቅ ውጊያ ያለበት አገልግሎት ነው፡፡ በስጦታ ካልሆነ በቀር ብዙዎች በምርጫ ደረጃ ላይመርጡት ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም ብዙ መስዋዕትነትን የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ይሁንና ታላቅ የነፍስ እርካታ የሚገኘውም ፡ የነፍስ ማዳን ርብርቦሽ ውስጥ እንደሆነስ  ያውቃሉ? ሰው  ከሲኦል ሲያመልጥ ያለ እርካታ!

 ወንጌልን መመስከር ከልባችን ተነክተን እንድናደርገው፡ ነፍሳትን የመታደግ ቅንዓት እንዲጨምርብን አስቀድመን ብንጸልይ መልካም ነው፡፡ ፍሬያማ ና ውጤታማ እንድንሆን ያግዛልና፡፡ ብንጸልይ ሊሰጠን እንደሚችል ከተጻፈልን ተስፋ ቃሎች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት፡-
.........................ይቀጥላል..................!

No comments:

Post a Comment