Monday, May 18, 2015

ራዕይ እንዴት ይጀመራል...?

እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ?

" ኢየሱስም ዓይኖቹን አንስቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊሊጶስን ፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? አለው፡፡ ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ፡ ሊፈትነው ይህንን ተናገረ፡፡ '' ዮሐ.6፤5ና 6፡፡

 በዚህ ትምህርት ብዙዎቻችሁ  የተቀበላችሁትን ራዕይ  ከየት እና እንዴት እንደምትጀምሩ መርህን የምትማሩበት ፡፡ ወይም ደግሞ በህይወቴ አንድ ነገር ሰርቼ ማለፍ እፈልጋለሁ ፤ግን ከየት እና ከምን እንደምጀምር አላውቅም ለምትሉ መንገድ መንገዱን ጠቁዋሚ ትምህርት ነው ብዬ አምናለሁ ፡፡

   ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ መካከል ጥያቄ ሲጠይቃቸው እንመለከታለን፡፡ ‹ህዝቡን ለማብላት እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?› በመሰረቱ እየመጣ የነበረው ህዝብ፡ ወንዶች ብቻ ተቆጥረው 5ሺህ ህዝብ ነበሩ፡፡ ሴቶችና ህጻናት ሲቆጠሩ 13 ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገሩን እነዚህን ሁሉ የመመገብ የራዕይ ጅማሬ ብለን ልናስበው እንችላለን፡፡ ረዕዩ ሲታይ በጣም ሰፊ እና ገና በሐሳብ ደረጃ ያለ ነገር ነው፡፡እነርሱም ማሰብ ጀመሩ ፤ ከየት ነው የሚጀመረው? ሰዎች አንድን ራዕይ ለመጀመር ከሐሳብ ቀጥሎ የሚያነሱት ጥያቄ አላቸው፡፡እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሙዋሉ ድረስ ምንም ነገር መጀመር ሊከብዳቸው ይችላል፡፡ የሚጠይቁዋቸው ወሳኝ የሆኑ ሁለት መሰረታዊ ጥያቄዎችን ፊሊጶስና እንድርያስ ጠይቀውልናል፤ ወይም በራዕይ ጅማሬ ላይ ሊነሱ የሚገባቸውን ቁልፍ ሁለት ሐሳቦችን አንስተውልናል ፡፡ ቀጥለን  እንዳስሳቸዋለን፡፡

                ሀ. ለራዕዩ የሚያስፈልግ ነገር ሲሙዋላ መጀመር...?
ፊሊጶስ፡- '' ፊሊጶስም እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኩዋ እንዲቀበሉ የ 200 ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት፡፡ ቁ.7፡፡ በዚያን ጊዜ ከጌታ የተሰጣቸውን አንድ ፕሮጀክት ወይም ራዕይ ለመጀመር የሚያስፈልገውን መነሻ ካፒታል ነው አስልቶ የተናገረው፡፡ 200 ዲናር በጊዜው በጣም ብዙ ብር ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ለመረዳት ያህል፡ ጌታ ኢየሱስን አሳልፎ ለጠላቶቹ ለመስጠት ይሁዳ ከካህናት አለቆች ጋር የተደራደረበት ብር 30 ብር ነው፡፡ በዚህ ብር በዚያን ጊዜ እንጀራ ቀርቶ መሬት እንኩዋ የሚገዛበት ብር እንደነበረ  ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ጌታውን የሸጠበትን ገንዘብ በቤተ መቅደስ ሄዶ በተነ፤ ነገር ግን መሬት ገዙበት፤ ቦታውም አኬልዳማ ተባለ ፤የተባለው ነገር ነው፡፡ እንግዲህ 30 ብር በጊዜው እንዲህ ትልቅ ከነበረ፡ 200 ብር ምን ያህል ይሆናል? የፊሊጶስ ሒሳብ ለሰው አዕምሮ ትክክል ይመስላል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለመመገብ ይህን የሚያክል በጀት አስፈላጊ ነው ማለቱ፡፡
                      ለ. ራዕዩን በእጅ ላይ በተገኘው ነገር መጀመር......?
እንድርያስ፡-''..አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሳ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል፡፡ '' ቁ.9 ፡፡ ይህ  ሁለተኛው የአማራጭ ሐሳብ ነው፡፡ ፈንድ ተፈላልጎ፡  አልያም በሆነ መንገድ ከሚገኝ ካፒታል መጀመር የማይቻል ከሆነ፡ ምናልባት እጃችን ካለው ጥቂት ነገር መጀመር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም ካልሆነስ ነው ጥያቄው? ፐሮጀክቱ ያቀፈው ህዝብ በሺህ የሚቆጠር ፡ በእጃቸው ያለው መነሻ ካፒታል ደግሞ ለአንድ ለሁለት ሰው ብቻ የሚበቃ፡፡ 'ይህ ምን ይሆናል ? ' አለ እንድርያስ !

   በነገራችን ላይ በርካታ ራዕዮችና ውጥኖች ሳይሰራባቸው ተቀምጠው ያሉት፡ በነዚሁ ሁለት ግዙፍ ጥያቄዎች  ውስጥ ወድቀው ነው፡፡ መነሻ ካፒታል ሲታሰብ ፣ ለመነሻ የሚሆን ብር ሲጠበቅ አይሞላም፡፡ ስለዚህም ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡ ቤሳ ቤስቲ የሌላቸው ሰዎች ከመሬት ተነስቶ 200 ዲናር ከየት ያመጣሉ? ሌላው ደግሞ እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም የማይበቃ መሆኑ ነው ፡፡ በተለይም ከታሰበው ራዕይ ጋር ሲነጻጸር ማለቴ ነው፡፡ ጀምሩት ቢባል እየቆረሱ ድንገት ቢያልቅስ ? ፣ ጀምሮ መዋረድ አይሆንም ? አዕምሮ ያለው ሰው ይህንን ሊያደርግ ይችላልን ?  ስለዚህም ነው በሁለቱም ጎራ የተነሱት ሐሳቦች ብዙዎቻችንን ይወክላሉ ብዬ የማምነው፡፡ ሁለቱም ነገሮች ከባባዶች ናቸው፡፡ ሙሉ የፐሮጀክቱን መነሻ ካፒታል ማግኘትም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ካላችሁ ነገር ጀምሩ ማለትም በሁዋላ ላይ የሚመጣውን መዘዝ በማሰብ የሚያንቀሳቅስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ የጌታ ሐሳብ ለመሆኑ ምንድን ነው?

     የጌታ ሐሳብ ‹ ከየትን እንጂ በምንን አታስብ ! ›
 ታስታውሱ እንደሆነ  ሲጀመርም የጌታ ጥያቄ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? ነው እንጂ በምን እንገዛለን? የሚል አልነበረም፡፡ ለጌታ በምን? የሚለው አያስጨንቀውም፡፡ ስለዚህም ነው በምን? ን ትቶ ከየት? የሚለውን የጠየቀው፡፡ ሰው ደግሞ በምን? የሚለው ሳይመለስለት ከየት? ወደሚለው ቀጣይ ነገር ውስጥ መግባት አይፈልግም፡፡ ስለ ዚህም ነው ሳይጠየቁ ሒሳብ መስራት የጀመሩት ፡፡ ለተሰጠ ራዕይ ሁሉ የሰው አስተሳሰብ ይኸው ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲመለስለት የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ካልተመለሰለት በቀር መጀመር ይፈራል፡፡ ጌታ ደግሞ እርሱን ለእኔ ተወውና ከየት እንደሚገዛ ንገረኝ ይላል፡፡ በተለይ '' እራሱ ሊያደርገው ያለውን ነገር አውቆ ይህን አለ፡፡'' የሚለው ቃል አስደናቂ ነው፡፡ ምንም ወደ ሌላቸው ሰዎች ትልልቅ ራዕይ ሲያመጣ እርሱ አዋቂ ነው፡፡ እርሱ ሊያደርግ ያለውን ነገር ስለሚያውቅ ነው ፡፡ በቅድሚያ በጀቱን ሰጥቶ ሂዱና ህዝቡን  አብሉ!፤ ይህንና ይህን ስሩ! ቢለን መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደዚያ አይሆንም፡፡

  ለመሆኑ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገሮች ፡ማለትም ፊሊጶስ ካቀረበውና፡ እንድርያስ ካቀረበው ሐሳብ፡ ጌታ የትኛውን መረጠ ? ወይም ምን አደረገ ? የሚለውን ነገር ከቃሉ ላይ አብረን እንመልከት፡፡ '' ኢየሱስም ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ አለ፤በዚያም ስፍራ ብዙ ሳር ነበረበት፡፡ወንዶችም ተቀመጡ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር፡፡ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ ፡አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፤ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡዋቸው፡፡ ''ቁ.11-12
  እንዳነበብነው እጃቸው ላይ ያለውን ያውም የራሳቸው ያልሆነ ግን በመካከላቸው የተገኘ የአንድ ብላቴና እራትን ተጠቀመበት፡፡ አመስግኖ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፡፡ በአዕምሮአችን ውስጥ መሀል ላይ ቢያልቅስ? ፣ ባይዳረስስ? ....ወዘተ የሚሉ አሳቦች ይኖራሉ ፡፡ ነገር ግን እነርሱን  እንተዋቸው፡፡ ዝም ብለን ባለን ነገር እንጀምር፡፡ አርሱ አያሳፍረንም፡፡ በጣም መጠንቀቅ ያለብን ፡ መነሻ ላይ ማነው የተናገረኝ? የሚለው ላይ ብቻ ነው፡፡ራዕዩ የትኛውንም ያህል ትልቅ ይሁን  እግዚአብሔር ተናግሮን ከሆነ መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለህዝቡ ቆርሰው ማደል ጀመሩ ፤ አይናቸው እያየ ሁሉ እንደሚፈልገው መጠን ወስዶ ፣ጠግቦ ፣ የተረፈውን ቁርስራሽ 12 መሶብ ሞሉ፡፡ የኛ ጌታ እንደዚህ ነው ፡፡ የመጨረሻውን ውጤት ከመነሻህ ጋር ማመሳከር እስኪያዳግት ድረስ የሚባርክ አምላክ ነው፡፡

  በጣም ትልልቅ ነገር የሰራባቸውን ሰዎች ምስክርነት መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ዎርልድ ቪዥን ዛሬ ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ከመድረሱ በፊት፡ መነሻ ካፒታሉ ቦብ ፒየርስ የሚባል የድርጅቱ መስራች  በወንጌል ምክንያት የተሰደደችን አንዲት ብላቴና በጊዜው ከረዳበት አምስት /5/ የአሜሪካን ዶላር እንደተጀመረ ጋሽ በቀለ ስለ ዎርልድ ቪዥን በጻፈው መጽሐፉ ላይ ታሪኩን አስፍሩዋል፡፡
 ከብዙዎች ንግግር እንደተረዳሁት ሁሉም ክርስቲያኖች ማለት ይቻላል፡ በተለይ ከሆነ ጊዜ በሁዋላ በህይወታቸው አንዳች ነገር ሰርቶ የማለፍ ጥማት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ግን ከየት? እና እንዴት? እንደሚጀምሩት አያውቁም፡፡ ለምሳሌ ብዙ ህጻናትን የማሳደግ እና አዛውንቶችን የመንከባከብ አልያም ሌሎች በጎ የልማት ስራዎችን ስለ መስራት አስበው ከሆነ ፡ ቢያንስ ከአንድ ህጻን ወይም አንድ አዛውንትን ከመርዳት መጀመር ሊኖርባቸው ይችላል፡፡ ከቆይታ በሁዋላ ስራው /ራዕዩ/ እየሰፋ ይሄድና ለብዙዎች ጥላ ለመሆን ይበቃል፡፡ ራዕዩ ከጌታ ይሰጠን እንጂ፡ ያለንን ጥቂት ነገር  ባርኮ መጀመር ብቻ ነው ፡፡

  ጥርት ያለ ራዕይ ተቀብለው : ለመጀመር  ሚሊዮን ብሮችን ሲጠብቁ ሲጠብቁ ፡ ራዕያቸው አጀንዳቸው ላይ ብቻ የቀረባቸው አያሌዎች ናቸው፡፡የምንፈልጋቸው ውጤቶች ስንጠብቃቸው ሳይሆን እየሰራን እያለ የሚመጡ ነገሮች ናቸው፡፡ ከመጠበቅ መንፈስ ወጥተን ፡ባለን ነገር እንቅስቃሴ ውስጥ እንግባ፡፡ ነገሮች እንደ መብረቅ ድንገት ላይከሰቱ ይችላሉ፡፡ ትልልቅ ነገሮችን እጃችን ባለው ትንሽ  ነገር እንጀምራቸው ፡፡ ነገ ትልቅ የማይሆኑበት ምክንያት የለም፡፡ አንዳንዶቻችን ይህ እውቀት ጎድሎን ነው ነገራችንን ያዘገየነው፤ አንዳንዴም  ያበላሸነው፡፡ እስኪ ዛሬ እንደገና ለመነሳት እንሞክር ፤ ዓላማችንን አንስተን በእምነት እንጀምር፡  መክሊታችንን ሳንነግድበት ጌታ ድንገት እንዳይመጣብን  እፈራለሁ፡፡ ነገ ዛሬ ሳንል ስንፍና መጥቶ እንደ ወንበዴ ሳይከበን፣ ምክንያቶቻችንን ሁሉ ጥለን፡ ራዕያችንን ለመፈጸም  እንነሳ፡፡ ቢያንስ እኮ አንድ  ለወንጌል ልቡ የሚቃጠልበትን የገጠር ወንጌላዊ መርዳት፣ አንድ ወይም ሁለት ልጆችን አስተምሮ ለቁም ነገር ለማብቃት መነሳት፣ ወይም በተለያየ ጊዜ ከቡና ቤት በወንጌል አምነው የወጡትን ሌላ  ስራ እስኪይዙ ድረስ  ኑሮአቸውን ማገዝ፣ ወይም አንድን ድሀ ቤተሰብ ፈልጎ መርዳት፣ ወይም ትራክቶችን ማሳተም....ወዘተ ማድረግ ይቻላል፡፡ እንዲህ ያሉ  በጣም ብዙ ብዙ በጎ ራዕዮች አሉ፡፡ እባካችሁ እንፍጠን!!!

ማስታወሻ፡- አስተያየት ካላችሁ በአድራሻው /ከታች ባለው ኢሜይል/ ሐሳባችሁን መጻፍ ትችላላችሁ፡፡ ሳንሰበሰብ በፊት ራዕያችንን እንድንፈጽመው ጌታ በቀሪ ዘመናችን በነገር ሁሉ ይርዳን፡፡ አሜን!

                                                                                                       benjabef@gmail.com

No comments:

Post a Comment