Wednesday, May 27, 2015

የሐሳብ መበላሸት!

      የሐሳብ መበላሸት

   ለሰው ልጆች ሁሉ ውድቀት ሰበብ  የሆነው  የህይዋን  ስህተት የመጣው ሰይጣን ሐሳቡዋን አበላሽቶት ነው፡፡ 2ቆሮ.11፤3 ፡፡ ሐሳቡ የተበላሸበት ሰው ወደ ድርጊቱ ለመግባት ቀላል ይሆንለታል፤ ልክ እንደ ቃየን ሁሉ የዳዊት ልጅ አቤሴሎምም ወንድሙን አምኖንን ከመግደሉ በፊት ረጅምና የቆየ የግድያ ሐሳብ አርግዞ ነበር፡፡ ጊዜውና ሁኔታዎች ሲመቻቹለት ደግሞ አስገደለው፡፡ 2ሳሙ.13፤2፡፡

   አንዳንድ ጊዜ ክፉ ሐሳብ ያድርና ድርጊቱ ሊቆይ ይችላል፤ ይህን ጊዜ መንቃት ነው፡፡ ምንም እስካላደረኩ ድረስ ንጹህ ነኝ  ማለት አይቻልም፡፡ ቀን የሚጠብቅ ክፉ ምኞት ላይ መንገስ ያስፈልጋል፡፤ እግዚአብሔር ቃኤልን ቀድሞ ያስጠነቀቀው ለዚያ ነው፡፡ ደጅህ ላይ ሐጢያት እያደባች ነው ንገስባት አለው፡፡ አለዚያ እርሱዋ  ትነግስብሃለች፡፡ ያን ጊዜ ፍቃዱዋን ታደርጋለች፡፡እግዚአብሄር ወደ ቃየን መጥቶ ከነገረው ነገር የምንማረው ኀጢያት ላይ እኛ መንገስ ካልቻልን ኀጢያት በእኛ ላይ መንገስ ይጀምራል፡/ ዘፍ.4፤7/የሚለውን ነው፡፡

   ያዕቆብ 1፤15 ላይ ሲናገር '' ምኞት  ጸንሳ  ሐጢያትን  ትወልዳለች ፡ሐጢያትም  ጸንሳ  ሞትን ትወልዳለች፡፡ " ሞት የሚባለው /ውድቀት ሊሆን ይችላል/፤ ከመከሰቱ በፊት ውስጥን ይዞ  የሚከርመው ሐሳብ  /ምኞት/ ነው፡፡ ምኞት ዝም ከተባለ ቆይቶ ቆይቶ  ሀጢያትን ይወልዳል፡፤ ከዚያም ወደ ሞት ያመጣል፤ ሁሉም ሂደት ነው ማለት ነው፡፡ ሐጢያትን፣ሞትንና ውድቀትን በህይወቱ ማየት የማይፈልግ ሰው ራሱን ማንጻት ያለበት ከውስጥ ነው፡፡ ምን አርግዣለሁ? ብሎ ራስን መጠየቅ፡፡ የአስቆሮቱ ይሁዳ ጌታን አሳልፎ እንዲሰጥ በቅድሚያ ሐሳብ ነው የመጣበት፡፡ '' ዲያቢሎስም ሐሳብ ካስገባ በሁአላ ''ይላል፡ ምናልባት ዲያቢሎስ ወደ አዕምሮው የላከበትን ሐሳብ መቃወም ይችል ነበር ፡፡ ምናልባትም ወደ ሌሎች ደቀመዛሙርትም ሐሳብ ቀርቦም ይሆናል፡፡ ምናልባትም እነርሱ ተቃውመውት ይሆናል፡፡ ይሁዳ ግን ሐሳቡን አስተናገደ፤ ወደ ቀጣዩ ና ከባዱ ነገርም አለፈ፡፡ ሮሜ 6፤12 ''...ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ስጋችሁ ሐጢያት አይንገስ '' ስጋችን ላይ ሐጢያት ሲነግስ  እንደ ስጋ ፈቃድ ለመኖር የስጋን ነገር አዘውትረን እንድናስብ እንገደዳለን፡፡ /ሮሜ.8፤5/

   ውስጡ የተሸነፈን ሰው ወደተገዛለት ነገር በቀላሉ መጎተት ይቻላል፡፡ ብዙ የሚያቅተው ከነገሮች ውስጥ መውጣት ሳይሆን ነገሮችን ከውስጥ ማስወጣት ነው፡፡ እስራኤላውያን በእግራቸው ከግብጽ ውስጥ ወጥተው ነበር፡ ነገር ግን በቆይታ እንደታየው ግብጽ ውስጣቸው ነበረ፡፡ ስለዚህም በልባቸው ወደ ግብጽ ተመለሱ ይለናል፡፡/ሥራ.7፤39/፡፡ ከዓለም ወጥተን ግን ዓለም ውስጣችን ካለች  እየዘመርን ፣ እየጸለይን ፣ ቤተክርስቲያን እየሄድን የሐጢያት ተጠቂዎች ልንሆን እንችላለን፡፡ ከሁሉ ነገር ተገልለው አንድፊቱኑ ገዳም ለገቡ መነኮሳት እንኩዋ ትልቁ  ትግል የውሰጥ ነው፡፡ ከግብጽ ወጥተህ ግብጽ ግን ከልብህ ካልወጣ ችግር ነው፡፡የሎጥ ሚስት  ከሶዶም በእግሩዋ ወጥታለች ነገር ግን ሶዶም ከውስጥዋ አልወጣም ነበርና እንቅፋት ሆነባት፡፡ መቀየር ፣መለወጥ  ከውስጥ ነው፡፡ ለዚህም ነው የእግዚአብሔር ቃል በአዕምሮአችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ......" የሚለን፡፡ ከየ ዕለቱ ኑሮአችን እንኩዋ ብንመለከት አንድ ሰው ወተት ወይም ጎመን የሚጠላ ቢሆን፡ ከፈለገ  ቦታ ቢመጣም ወይም ነጻም ቢሆን አይነካውም፡፡ ሐጢያትን ከውስጥ ስንጠላ አዩኝ አላዩኝ ከሚል መሳቀቅ እንወጣለን፡፡ በዚህም ላይ ውስጣችንን ቦርቡሮ በጊዜ ሒደት ከሚጥለን ነገር እንገላገላለን፡፡ ልክ እንደ ጎመኑ ና ወተቱ  የትም ብንሆን ፣መቼም ቢሆን አንነካውም፡፡

     አንድ የእግዚአብሔር ሰው ሲናገር ውስጡ ችግር ያለበት  ሰው ያማረ  ህንጻ ውስጥ ወይም አውሮፕላን ውስጥ ቢገባ  ችግሩ አያቆምም ብሎአል፡፡ የገባበት ቦታ ነገሩን ሊለውጥ ስለማይችል ነው፡፡ ከዚህ በፊት አንድ በጣም ወፍራምና ዕድሜ ጠገብ ዋርካ አውቃለሁ፡፡ነገር ግን በሆነ ወቅት እምብዛም ነፋስ ባልነበረበት ጊዜ ነው ሌሊት ላይ ወድቆ የተገኘው ፤በጊዜው ሁኔታው ሲጠና ዛፉ በከፍተኛ ሁኔታ ውስጡ በብል ተቦርቡሮ ነበር፡፡ ለረጅም ጊዜ ቅርፊት ተሸፍኖ ያለ እየመሰለ ኖረ፤ነገር ግን ባልታሰበ ቀን ወድቆ ተገኘ፡፡ ብዙ ነገሮች እንደዚያ ይመስሉኛል ተሸፍነን ጠንካራ ሰዎች እንመስላለን፣ አስተማማኝ እና የመላዕክት ህይወት ያላቸው እንመስላለን፤ ምናልባት ውስጣችን ግን በብዙ እየተገዘገዘ ይሆናል፡፡ አሁን አሁን በየ አደባባዩ ላይ የሚሰሙት ውድቀቶቻችንም የዚህ ውጤት ይሆናል፡፡እስቲ  ሁላችንም ውስጣችንን እንፈትሽ ና ነጻ እንውጣ ፡፡ ውድቀትን ብዙ ሰው ሊያየው ፣ ሊሰማው ይችላል፡፡ ከዚያ በፊት ያለን የውስጥ መቦርቦርና ትናንሽ ልምምዶች ግን እምብዛም አይታይም፡፡እኛው ከጌታ ጋር እንፍታው፡፡ልምምዱ ከፍ ያለ ደረጃ እንኩዋ የደረሰ ቢሆን በጾም ጸሎት በፊቱ ብንሆን የማይለወጥ ነገር ምንም የለም፡፡ ጌታ ሁሉን ይችላልና፡፡
  • የዚህን ሙሉ ትምህርት ‹ ንገስባት › ከሚለው ሊንክ ርዕስ ስር ማየት ይችላሉ፡፡

ማስታወሻ:- ይህን ትምህርት ቅዱሳን እንዲጠቀሙበት ያድርጉ፡፡

                                                                        benjabef@gmail.com

No comments:

Post a Comment