Friday, May 1, 2015

ለቤተክርስቲያን መሪዎች!

                            ክፍል ሁለት
 ወንጌልን መመስከር ከልባችን ተነክተን እንድናደርገው፡ ነፍሳትን የመታደግ ቅንዓት እንዲጨምርብን አስቀድመን ብንጸልይ መልካም ነው፡፡ ፍሬያማ ና ውጤታማ እንድንሆን ያግዛልና፡፡ ብንጸልይ ሊሰጠን እንደሚችል ከተጻፈልን ተስፋ ቃሎች ውስጥ ሁለቱን እንመልከት፡-

1-  ማቴዎስ  ወንጌል 7፤7-8 '' ለምኑ ይሰጣችሁአል፤ፈልጉ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኩዋኩ  ይከፈትላችሁዋል፡፡ የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፣ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኩዋካ ይከፈትለታል፡፡'' እንደሚል፤ ከልባችን እየፈለግን እንለምን፡፡ በሩን እስኪከፍትና እስኪሰጠን  ድረስ  ደጋግመን በሩን እንቆርቁር፡፡ በተስፋ ቃሉ መሰረት በሩን ይከፍትልናል፡፡ ሌሎችን የምናተርፍበትም የወንጌል ቅንዐት ከብዙ ጥበብ ጋር ወደ ልባችን ይገባል፡፡

2-  ሁለተኛው የያዕቆብ መልዕክት 1፤17 ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲህ ይላል፡-'' በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው ፤መለወጥም በእርሱ ዘንድ ከሌለ በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ ከሌለ ከብርሃናት አባት ይወርዳሉ፡፡''  ለወንጌል  የመቅናት ስጦታ በጎም ፍጹምም ነው፡፡ ይህን በረከት ከጌታ ልንቀበል እንደምንችል ቃሉ ያሳያል፡፡

ፀሎት፡- ጌታ ሆይ  የወንጌልን ቅናት እንድትሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እለምንሀለሁ!! 
       
               አሁን ለኛ ቀን ነው ሌሊት?
'' ቀን ሳለ የላከኝን ስራ ላደርግ  ይገባኛል፡፡ማንም ሊሰራ   የማይችልባት ሌሊት ትመጣለች፡፡'' ዮሐ.9፤4፡፡
    በሰው ህይወት ውስጥ ቀንም ሌሊትም አለ፡፡ ይህ ሁሉን ሰው ሲያጋጥም የኖረ፣ የሚኖር ጉዳይ ነው፡፡የምንሰራበት ምቹ ጊዜና ሁኔታ ይሰጠናል ፤ደግሞ ሌላ ጊዜ መስራት ብንፈልግና ጊዜ ቢኖረን እንኩዋ የወደድነውን ማድረግ የማንችልበት ሌሊት ደግሞ ይመጣል፡፡የተመቻቸው ቀን ላይ ያልሰራ፣ያልተጋ ሰው የማይሰራበት ሌሊት ሲመጣበት ይቆጨዋል፡፡
     ከወንጌል መስበክ አኩዋያ እነዚህን ሁለት ሁነቶች በምድራችን ላይ እንኩዋ ማሰብ ይቻላል፡፡ አንዱ  ወንጌልን በነጻነት መስበክና ማስተማር የማይቻልበት  ጊዜ ነበር፡፡ ምናልባት ደግሞ አሁን በአንጻራዊ  ሁኔታ ቤተክርስቲያን በድብብቆሽ  ከምትሰበሰብበትና ከምትሰራበት ሁኔታ ወጥታ ወንጌልን በትልልቅ  አዳራሾች ና በአደባባይ መስበክ ችላለች፡፡ ይህ ሲባል ግን መቼም ዘመን ቢሆን ወንጌልን ከመስበክ ጎን ለጎን ከሚገጥሙ ትንሽም፣ ትልቅም  ተግዳሮቶች ጋር ማለት ነው፡፡
  ይሁንና ይህንን ነጻነት ተጠቅመን የማንሰብክበት፣ የማንመሰክርበት ከሆነ ነገ ደግሞ ሌሊት ሊመጣብን ይችላል፡፡ ቀጥሎ ምን እንደሚከሰት አይታወቅም፤ የወንጌል ተቃዋሚዎች በዓለም ላይ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አይለው ተነስተዋል ጌታም ለጊዜው ስለ ፈቀደላቸው ይመስለኛል፡ አንዳንድ በጸሎት መከልከል የማንችላቸውን ድርጊቶች ሁሉ እያደረጉ ያሉበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ ነገ በእኛ አካባቢ ምን ሊከሰት ይችላል?  ከህግ ፣ከዲሞክራሲ አንጻር የሰው መብት አትንካ ፣የራስህን አመለካከት ሰው ላይ መጫን አትችልም፤ የስብከት ፍቃድ፣ የአገልጋይነት ፍቃድ....ወዘተ የሚሉ ነገሮች ከአሁኑ በራችንን እያነኩዋኩ ነው፡፡ ለምሳሌ  የኤርትራ ወንድሞችና በዚያም ያለች ቤተክርስቲያን ሌሊት ውስጥ ናቸው ያሉት፡፡ እንደሚሰማው መስበክ ና መናገር አይቻልም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር ምናልባት በቅርብ ጊዜ ምቹ ቀን ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚህ ሀዘናቸውም ይጽናናሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ይሁንና እኛ ግን ከእንደነዚህ  አይነት ሁኔታዎች መማር አለብን እላለሁ፡፡
   
            ወንጌልን በራሳችን ዘመን ...!
" ዳዊት በራሱ  ዘመን  የእግዚአብሔርን  ሐሳብ  ካገለገለ  በሁዋላ  አንቀላፋ፡፡" ሥራ.13፤35
 ዳዊት በተሰጠው በራሱ ዘመን እንዲሰራው የተቀመጠለትን ነገር አድርጎ ማለፉን ነው ቅዱስ ሉቃስ የዘገበልን፡፡አሁን እኛ በእኛ ዘመን እንድንሰራው የሚፈለግ ታላቅ የእግዚአብሔር ዓላማ፡ በዋነኛነት ምን ሊሆን ይችላል?  ይህንን ጥያቄ  ለመመለስ  በሚደረጉ ጥረቶች ብዙ ሰዎች የተለያየ በጎም የሚመስሉ፣  በጎም ያልሆኑ አመለካከቶች ውስጥ ገብተዋል፡፡ ፊት ለፊት የተቀመጠላቸውን የእግዚአብሔርን አጀንዳ ችላ ብለው ሲመራመሩ ፡አላስፈላጊ ወደ  ሆኑና ከእግዚአብሔር የልብ ትርታ ጋር ግንኙነት ወደሌላቸው ፣ ከአንድነት ይልቅ መከፋፈልን፣ ከትህትና ይልቅ ትዕቢትን ፣ለሌላው ከማሰብ ይልቅ ለራስ ብቻ በሚያደላ አፍቅሮ ነዋይ እየተሳቡ ገብተው ሲለፉና ሲሰቃዩ ማየት የተለመደ ነገር  ሆኑዋል፡፡ሁሉም ድርጊቶች የሚፈጸሙት የእግዚአብሔር የዘመኑ አሳብ ፣ ራዕይ ና ጥሪ ስም ነው፡፡ በተለይም  ቤተክርስቲያን  ዋና ነገሩዋን ስትስት ከማየት በላይ የሚያም ምን ነገር አለ? እግዚአብሔር ግን በዚህ ዘመን ማድረግ የፈለገውን አሳቡን በግልጽ ተናግሩዋል '' በክርስቶስ ለማድረግ እንደወደደ እንደ አሳቡ የፍቃዱን ሚስጥር አስታውቆናልና፡፡'' በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን በክርስቶስ ለመጠቀቅለል ነው''  ኤፌ.1፤10፡፡ ሁሉም በኢየሱስ ክርስቶስ ውስጥ እንዲሆንና ለእርሱም እንዲሆን ባለ የመለኮት አጀንዳ ውስጥ ተሳታፊ መሆን  ምን ያህል ታላቅ ዕድል ነው?! ሰዎችን ሁሉ በክርስቶስ  የምናደርግበት መንገዱ ደግሞ ወንጌልና ወንጌል ብቻ ነው፡፡ ለሰው  የሞኝነት መንገድ የሚመስል በእግዚአብሔር ዘንድ ግን አስቀድሞ የታሰበ ዘዴ ፣ጥበብ ፣ ብልሀት ነው፡፡ '' ....ያለ ሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ፣ ካልሰሙስ እንዴት ያምናሉ? ''----የተባለበት ሚስጥር፡፡
               
             ቤተክርስቲያን ሆይ ንቂ !
  ጾምና ጸሎት ይዘን በወንጌል ሳይሆን በተለያዩ ዘመነኛ ሃጢያቶች ና ሱሶች ቀስ በቀስ እየተወረሰ  ያለውን ህብረተሰብና አካባቢ እንዲሰጠን መጸለይ ብንጀምርስ ? ክፉ በብዙ እየተጋ ነው፡፡ ከቤተክርስቲያን በሰበብ አስባብ የጸሎት ቀናት ፣ሰዐታት እያስቀነሰ ፣የማለዳ  ጸሎቶች ፣ አዳር ጸሎቶችን እያስተወ፡ ያለምንም ውጊያ እየሰራ ያለ ይመስላል፡፡ መሳሪያዎቹዋን ቀስ በቀስ የተዘረፈችዋ ቤተክርስቲያን በአሁኑ ሰዐት መንቃት ይጠበቅባታል፡፡ ሙሽራው ሊመጣ በደጅ ነው !እያልን ሙሽሪት ተገቢውን ልብስ  ሳታደርግ ፣ ሳትዘጋጅ እንዴት ይሆናል?
  ቤተክርስቲያን ትውልዱን እየተናጠቀች  ካልጸለየች ሌላ የተጋ ይወስዳቸዋል፡፡ ዲያቢሎስ ለራሱ አጀንዳ እንደሚጸልይ  የእግዚአብሔር ቃል ይናገራል፡፡ እንዲህ ይላል፡- '' ሰይጣን እንደ  ስንዴ  ሊያበጠጥራችሁ ለመነ" ሉቃ.22፤31 ፡፡ የሰይጣን ልመና ትውልድን የማበጠር፣ የማድከምና የመበተን ሲሆን : ጌታ ግን ስለ ጴጥሮስ '' እኔ ግን እምነትህ እንዳይጠፋ ስለ አንተ አማለድሁ '' ይላል፡፡ምንም እንኩዋ ጴጥሮስ በፈተናው ተሸንፎ ክዶ ሄዶ የነበረ ቢሆንም ቆይቶ በንስሀ ተመልሱዋል፡፡ ለመመለሱ ምክንያት የነበረው ግን ጌታ ስለ እርሱ ስለ ማለደለት ነው፡፡/ቁ.32/
     ቤተክርስቲያን ዕቅድ ያላወጣችበትን ህዝብ እና ስፍራ ጠላት እያቀደበት ነው ፡፡ ሰሞኑን አይ ኤስ የተባለው እስላማዊ ድርጅት ምን እየደረገ እንደሆነ ለማንም ጆሮ ባዳ አይደለም፡፡ የደከሙ መንግስታትን እያሰሰ ይቆጣጠራል ፣ ይደራጃል፤ ለምሳሌ ጋዳፊ የወደቁበት ሊቢያ፣ ሳዳም ሁሴን የወደቁበት ኢራቅ፣ በብዙ ጦርነት የደቀቀችውን ሶሪያ....እንደ የመን ያሉ ሌሎችንም አገሮች፡፡ በትንሽ ተዋረድ ደግሞ ወንጌል ለመስበክ ያላሰብንባቸው አካባቢዎች ና ጠንካራ ጸሎት የማይደረግባቸው ልል ቦታዎች ልክ ጠንካራ መንግስት እንደሌለባቸው አገሮች ለክፉው ስራ የተጋለጡ  ይሆናሉ፡፡ ለምሳሌ ምን ምን ያልነበረባቸው አንዳንድ አካባቢዎች  እንደ ወረርሽኝ የጫትና የተለያዩ አደንዛዥ ዕጾች ማከፋፈያ እና መጠቀሚያ ሆነው ሲታዩ ፤የዝሙት ማስፋፊያ፣ የመጠጥ ንግድ ቤቶች ፣ዳንኪራ ቤቶች እንደ ሰደድ እሳት በየቦታው በፍጥነት ሲስፋፉ፡ ከሁዋላ  ደጀን የሆናቸው ና ዕቅድ አውጪው  ማን ነው?  በዚህ ሁሉ ቤተክርስቲያን የት ነች? ለትውልዱ ምን እያሰበች ነው?

በዚህና  በዚያ ተወጥሮ  ያለውን  ወጣት ትውልድ  ከጠላት  መንጋጋ  ለማላቀቅ  ተግቶ  እየጸለየ ያለ ማን ነው? የትውልድ  ሸክም ያለበት የዘመኑ  የወንጌል ሰው ማን ነው? ቀድማ አይታ  የተነሳች ፣ እንደ ሰራዊት  እየጸለየች ያለች  የዘመንዋ  ቤተክርስቲያን  የቱዋ ነች?  ለሚከፈቱ  አጥቢያዎች አጀንዳ  ያላት፣ ለወንጌል በጀት ያላለቀባት፣ የጌታ  ዋነኛ  አሳብ  የገባት  አጥቢያ  የት ናት? ሲመስለኝ ሰይጣን የቤት ስራ ሰጥቶን ፡እርሱ የራሱን ስራ እየሰራ ነው፡፡ አንገብጋቢና ዋና  ባልሆኑ ነገሮች ላይ ጊዜ እንድንፈጅ ፣ እርስ በርስ እንድንለያይ፣ ወንድም ወንድሙን እንዲጠላ ፣ቤተክርስቲያን  ከቤተክርስቲያን ፣መሪዎች ከመሪዎች  እንዲራራቁና እንዳይግባቡ ተደርገናል፡፡ እንደ ጥንቱዋ ቤተክርስቲያን መሪዎች ስለ ተሐድሶ ወይም ስለ ሪቫይቫል ሊያስቡ በሚገባበት ጊዜ ላይ '' የማርያም አይን ጥቁር ነው ቡናማ ?''፣ '' በአንድ መርፌ ላይ ስንት መላዕክት ይቆማሉ?''፣ '' ቅዱስ ቁርባን ውስጥ ዝንብ ብትገባ ዝንቡዋ ትቀደሳለች ወይስ ቁርባኑ ይረክሳል ? '' በሚሉ ጭቅጭቆች ተወጥረው፣  በሐሳብ ተለያይተው፡ ውድ ጊዜያቸውን እንዳቃጠሉ ፤ ሰይጣንም ኑፋቄዎችን በቤተክርስቲያን አሾልኮ ለማስገባት ዕድል እንዳገኘ፡ ዘንድሮም ታሪክ ራሱን እንዳይደግም ብናስተውል መልካም ነው፡፡
   ሩቅ የመሰሉን ነውሮች ቤተክርስቲያን ደጅ ላይ፣ ብቻ አይደለም ምስባኩ ላይ ከወጡ ቆዩ፤ የጺዮንን በር የተዳፈሩ ጆሮን ጭው የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች  እየሆኑ ነው ፡፡ እኛስ እንደ ዳነ ሰው ፣ እንደ ቤተክርስቲያን  ምን እያሰብን ነው?

በመጨረሻ፡- ቢቻል የቤተክርስቲያን መሪዎች እና የሚመለከታቸው ሁሉ ተሰብስበው ዘመኑንና ትውልዱን ያማከለ አዳዲስ  የወንጌል ምስክርነት ዕቅድ ቢያወጡ ፣
                  -ጥቂት በእግዚአብሔር ፊት ጊዜ እንዲወስዱና እንዲሰሙት ቢሆን መልካም ነው፡፡
                - በማንኛውም የወንጌል ዕቅዶች ላይ ለመመካከር ከፈለጉ  በሚከተለው አድራሻ  ይጻፉ E-mail ‹ benjabef@gmail.com ›

ማሳሰቢያ ፡- ይህንን መልዕክት የቤተክርስቲያን መሪዎች ለሆኑ ሁሉ እንዲደርስ ያድርጉ!!! ሃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ!!!

                                                                                          benjabef@gmail.com                                       

No comments:

Post a Comment