Wednesday, June 24, 2015

የትንሹዋ ነገር ቀን !

  ገና ከዘፍጥረት ጀምሮ  የሰው ልጅ ምድርን እንዲጠብቃትና እንዲንከባከባት ተልዕኮ ሲሰጠው እንመለከታለን፡፡ ሰዎች አሁን አሁን ስራን በተለያየ መልክ ሊሰሩት ይችላሉ፡፡ ቅጥርን የሚፈልጉ ሌሎች በሚሰሩት ነገር ውስጥ በመግባት የተወሰነ ነገር በማድረግ ገቢን ለራሳቸው ያገኛሉ፡፡ ገሚሶች ደግሞ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ይሰራሉ፡፡ የራስን  ስራ ፈጥሮ በመስራት ዙሪያ ዛሬ የተወሰነ ነጥቦችን እንዳስሳለን፡፡

  ስራን ፈጥሮ አብሮ መስራት ከብዙ ነገር አንጻር ጥቅሙ ሰፊ ቢሆንም ፡ቅድመ ዝግጅቶች ከሌሉበት ግን በዕውቀት ማነስ የሚበላሸው ነገር ሊበዛ ይችላል፡፡ አብሮ ለመስራት ምን አይነት ዕውቀት ነው የሚያስፈልገን?

1. በቅድሚያ ራዕይ ሊኖረን ይገባል፡፡

 ራዕይ ከምንሰራው ነገር በፊት መኖሩ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ስራውን በጋራ የሚሰሩት በተመሳሳይ ራዕዩ ያላቸው ወይም በዚያ ራዕይ የሚስማሙ  ናቸው ፡፡ የቢዝነስ ጣምራም ያ ነው፡፡ ከስራው በፊት የጋራ ስምምነት ያወጣሉ፤ ራሳቸውን ጨምሮ ወደፊት ስራው ላይ የሚጨመሩት ሰዎች በሙሉ የሚተዳደሩበት እና የሚገዙለት ሕግ ይሆናል፡፡ ይህም ወደፊት የሚነሱ ችግሮችን ለመቀነስ ያስችላል፡፡ በስራው ውስጥ ቸልተኝነትን ለማጥፋት ፣ ብሎም የእርስ በርስ ቅራኔ እንዳይፈጠር ለማድረግ ሁሉም የስራ ድርሻ እንዲኖረው ማድረግ ፣ የተሰጠውን ሀላፊነት እያንዳንዱ በተገቢው ሁኔታ እንዲወጣ ማድረግ እና ባልተሰሩ ስራዎች ላይ ተጠያቂነትን መለማመድ ወሳኝ ነገሮች ከሚባሉት ውስጥ ናቸው፡፡

2. ትንሽ የሚመስሉ ጅማሬዎችን ማክበር፡፡

  የእግዚአብሔር ቃል  የጥቂቱዋን ነገር ቀን የናቀ ማን ነው? ዘካ.4፤10 እንደሚል፡ እጅግ የገዘፉ ራዕዮች እጅ ላይ ባሉ ጥቂት ነገሮች ሊጀመሩ ይችላሉ፡፡ እንደውም ብዙ ነገሮች በጅማሬ ጊዜ ላይሳኩ እና ላይስተካከሉ ቢችሉም፡  ዓላማው ትልቅ እስከሆነ ድረስ እና በነገሩ ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ እስካለበት ድረስ፡ መነሻ ካፒታሉ ትንሽ ቢሆንም ሊደንቀን አይገባም፡፡ ያለችውን ፣የተገኘችውን ይዞ መጀመር ከዚያም በትጋት መስራት ይገባል ፡፡

 3. ራዕይ ከየት እና እንዴት ይጀምራል?

 ሰዎች ሊሰሩ የሚያስቡትን ስራ ወይም አንድን ራዕይ ከሆነ ነገር ተነስተው ይጀምሩታል፡፡ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታ ሲሙዋሉላቸው ወይም  ለመነሻ ከሚሆን ጥቂት ነገር ተነስተው ፡፡ በዚህ ጉዳይ እሰኪ አንድ አንድ ነገሮችን ከዮሐንስ ወንጌል 6 ላይ እንመልከት፡፡ 
" ኢየሱስም ዓይኖቹን አንስቶ ብዙ ሕዝብ ወደ እርሱ ሲመጣ አየና ፊሊጶስን ፡- እነዚህ እንዲበሉ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? አለው፡፡ ራሱ ሊያደርግ ያለውን ያውቅ ነበርና ፡ ሊፈትነው ይህንን ተናገረ፡፡ '' ዮሐ.6፤ 5ና 6፡፡

   ከላይ እንደተጠቀሰው ጌታ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ጥያቄ ጠየቃቸው ፡፡ ‹ህዝቡን ለማብላት እንጀራ ከወዴት እንገዛለን?› በመሰረቱ እየመጣ የነበረው ህዝብ፡ ወንዶች ብቻ ተቆጥረው 5ሺህ ህዝብ ነበሩ፡፡ ሴቶችና ህጻናት ሲቆጠሩ 13 ሺህ ገደማ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል፡፡ ነገሩን እነዚህን ሁሉ የመመገብ የራዕይ ጅማሬ ብለን ልናስበው እንችላለን፡፡ ረዕዩ ሲታይ በጣም ሰፊ እና ገና በሐሳብ ደረጃ ያለ ነገር ነው፡፡  ሰዎች አንድን ራዕይ ለመጀመር ከሐሳብ ቀጥሎ የሚያነሱት ጥያቄ አላቸው፡፡ እነዚያ ቅድመ ሁኔታዎች እስካልተሙዋሉ ድረስ ምንም ነገር መጀመር ሊከብዳቸው ይችላል፡፡   ፊሊጶስና እንድርያስ በራዕይ ጅማሬ ላይ ሊነሱ የሚገባቸውን ሁለት ቁልፍ  ሐሳቦችን አንስተውልናል ፡፡

                ሀ. አንድን ነገር ለራዕዩ የሚያስፈልግ ነገር ሲሙዋላ መጀመር...? 

ፊሊጶስ፡- '' ፊሊጶስም እያንዳንዳቸው ትንሽ ትንሽ እንኩዋ እንዲቀበሉ የ 200 ዲናር እንጀራ አይበቃቸውም ብሎ መለሰለት፡፡ ቁ.7፡፡ በዚያን ጊዜ ከጌታ የተሰጣቸውን አንድ ፕሮጀክት ወይም ራዕይ ለመጀመር የሚያስፈልገውን መነሻ ካፒታል ነው አስልቶ የተናገረው፡፡ 200 ዲናር በጊዜው በጣም ብዙ ብር ነው፡፡ ነገሩን የበለጠ ለመረዳት ያህል፡ ጌታ ኢየሱስን አሳልፎ ለጠላቶቹ ለመስጠት ይሁዳ ከካህናት አለቆች ጋር የተደራደረበት ብር 30 ብር ነው፡፡ በዚህ ብር በዚያን ጊዜ እንጀራ ቀርቶ መሬት እንኩዋ የሚገዛበት ብር እንደነበረ  ከቃሉ መረዳት እንችላለን፡፡ጌታውን የሸጠበትን ገንዘብ በቤተ መቅደስ ሄዶ በተነ፤ ነገር ግን መሬት ገዙበት፤ ቦታውም አኬልዳማ ተባለ ፤የተባለው ነገር ነው፡፡ እንግዲህ 30 ብር በጊዜው እንዲህ ትልቅ ከነበረ፡ 200 ብር ምን ያህል ይሆናል? የፊሊጶስ ሒሳብ ለሰው አዕምሮ ትክክል ይመስላል፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩትን ለመመገብ ይህን የሚያክል በጀት አስፈላጊ ነው ማለቱ፡፡

                      ለ. ራዕዩን በእጅ ላይ በተገኘው ነገር መጀመር......?

እንድርያስ፡-''..አምስት የገብስ እንጀራ እና ሁለት ዓሳ የያዘ ብላቴና በዚህ አለ ፤ ነገር ግን እነዚህን ለሚያህሉ ሰዎች ይህ ምን ይሆናል፡፡ '' ቁ.9 ፡፡ ይህ  ሁለተኛው የአማራጭ ሐሳብ ነው፡፡ ፈንድ ተፈላልጎ፡  አልያም በሆነ መንገድ ከሚገኝ ካፒታል መጀመር የማይቻል ከሆነ፡ ምናልባት እጃችን ካለው ጥቂት ነገር መጀመር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ነገር ግን እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም ካልሆነስ ነው ጥያቄው? ፐሮጀክቱ ያቀፈው ህዝብ በሺህ የሚቆጠር ፡ በእጃቸው ያለው መነሻ ካፒታል ደግሞ ለአንድ ለሁለት ሰው ብቻ የሚበቃ፡፡ 'ይህ ምን ይሆናል ? ' አለ እንድርያስ !

   በነገራችን ላይ በርካታ ራዕዮችና ውጥኖች ሳይሰራባቸው ተቀምጠው ያሉት፡ በነዚሁ ሁለት ግዙፍ ጥያቄዎች  ውስጥ ወድቀው ነው፡፡ መነሻ ካፒታል ሲታሰብ ፣ ለመነሻ የሚሆን ብር ሲጠበቅ አይሞላም፡፡ ስለዚህም ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡ ቤሳ ቤስቲ የሌላቸው ሰዎች ከመሬት ተነስቶ 200 ዲናር ከየት ያመጣሉ? ሌላው ደግሞ እጃችን ላይ ያለው ነገር ለምንም የማይበቃ መሆኑ ነው ፡፡ በተለይም ከታሰበው ራዕይ ጋር ሲነጻጸር ማለቴ ነው፡፡ ጀምሩት ቢባል እየቆረሱ ድንገት ቢያልቅስ ? ፣ ጀምሮ መዋረድ አይሆንም ? አዕምሮ ያለው ሰው ይህንን ሊያደርግ ይችላልን ?  ስለዚህም ነው በሁለቱም ጎራ የተነሱት ሐሳቦች ብዙዎቻችንን ይወክላሉ ብዬ የማምነው፡፡ ሁለቱም ነገሮች ከባባዶች ናቸው፡፡ ሙሉ የፕሮጀክቱን መነሻ ካፒታል ማግኘትም ቀላል ነገር አይደለም፡፡ ካላችሁ ነገር ጀምሩ ማለትም በሁዋላ ላይ የሚመጣውን መዘዝ በማሰብ የሚያንቀሳቅስ አይደለም፡፡ በዚህ ሁሉ የጌታ ሐሳብ ለመሆኑ ምንድን ነው?

     የጌታ ሐሳብ - ‹ ከየትን እንጂ በምንን አታስብ ! ›

 ታስታውሱ እንደሆነ  ሲጀመርም የጌታ ጥያቄ እንጀራ ከወዴት እንገዛለን ? ነው እንጂ በምን እንገዛለን? የሚል አልነበረም፡፡ ለጌታ በምን? የሚለው አያስጨንቀውም፡፡ ስለዚህም ነው በምን? ን ትቶ ከየት? የሚለውን የጠየቀው፡፡ ሰው ደግሞ በምን? የሚለው ሳይመለስለት ከየት? ወደሚለው ቀጣይ ነገር ውስጥ መግባት አይፈልግም፡፡ ስለ ዚህም ነው ሳይጠየቁ ሒሳብ መስራት የጀመሩት ፡፡ ለተሰጠ ራዕይ ሁሉ የሰው አስተሳሰብ ይኸው ነው፡፡ በቅድሚያ እንዲመለስለት የሚፈልገው ነገር አለ፡፡ ካልተመለሰለት በቀር መጀመር ይፈራል፡፡ ጌታ ደግሞ እርሱን ለእኔ ተወውና ከየት እንደሚገዛ ንገረኝ ይላል፡፡ በተለይ '' እራሱ ሊያደርገው ያለውን ነገር አውቆ ይህን አለ፡፡'' የሚለው ቃል አስደናቂ ነው፡፡ ምንም ወደ ሌላቸው ሰዎች ትልልቅ ራዕይ ሲያመጣ እርሱ አዋቂ ነው፡፡ እርሱ ሊያደርግ ያለውን ነገር ስለሚያውቅ ነው ፡፡ በቅድሚያ በጀቱን ሰጥቶ ሂዱና ህዝቡን  አብሉ!፤ ይህንና ይህን ስሩ! ቢለን መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ ጊዜ እንደዚያ አይሆንም፡፡

  ለመሆኑ ከእነዚህ ከሁለቱ ነገሮች ፡ማለትም ፊሊጶስ ካቀረበውና፡ እንድርያስ ካቀረበው ሐሳብ፡ ጌታ የትኛውን መረጠ ? ወይም ምን አደረገ ? የሚለውን ነገር ከቃሉ ላይ አብረን እንመልከት፡፡ '' ኢየሱስም ሰዎቹ እንዲቀመጡ አድርጉ አለ፤በዚያም ስፍራ ብዙ ሳር ነበረበት፡፡ወንዶችም ተቀመጡ ቁጥራቸውም አምስት ሺህ የሚያህል ነበር፡፡ኢየሱስም እንጀራውን ያዘ ፡አመስግኖም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ ፤ደቀ መዛሙርቱም ለተቀመጡት ሰዎች ሰጡዋቸው፡፡ ''ቁ.11-12
  እንዳነበብነው እጃቸው ላይ ያለውን : ያውም የራሳቸው ያልሆነ ግን በመካከላቸው የተገኘ የአንድ ብላቴና እራትን ተጠቀመበት፡፡ አመስግኖ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፡፡ በአዕምሮአችን ውስጥ መሀል ላይ ቢያልቅስ? ፣ ባይዳረስስ? ....ወዘተ የሚሉ አሳቦች ይኖራሉ ፡፡ ነገር ግን እነርሱን  እንተዋቸው፡፡ ዝም ብለን ባለን ነገር እንጀምር፡፡ አርሱ አያሳፍረንም፡፡ በጣም መጠንቀቅ ያለብን ፡ መነሻ ላይ ማነው የተናገረኝ? የሚለው ላይ ብቻ ነው፡፡ራዕዩ የትኛውንም ያህል ትልቅ ይሁን  እግዚአብሔር ተናግሮን ከሆነ መፈጸሙ አይቀርም፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ለህዝቡ ቆርሰው ማደል ጀመሩ ፤ አይናቸው እያየ ሁሉ እንደሚፈልገው መጠን ወስዶ ፣ጠግቦ ፣ የተረፈውን ቁርስራሽ 12 መሶብ ሞሉ፡፡ የኛ ጌታ እንደዚህ ነው ፡፡ የመጨረሻውን ውጤት ከመነሻህ ጋር ማመሳከር እስኪያዳግት ድረስ የሚባርክ አምላክ ነው፡፡ በጣም ትልልቅ ነገር የሰራባቸውን ሰዎች ምስክርነት መመልከት እንችላለን፡፡ ለምሳሌ ዎርልድ ቪዥን ዛሬ ላይ በብዙ ሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ካፒታል ከመድረሱ በፊት፡ መነሻ ካፒታሉ ቦብ ፒየርስ የሚባል የድርጅቱ መስራች  በወንጌል ምክንያት የተሰደደችን አንዲት ብላቴና በጊዜው ከረዳበት አምስት /5/ የአሜሪካን ዶላር እንደተጀመረ ጋሽ በቀለ ስለ ዎርልድ ቪዥን በጻፈው መጽሐፉ ላይ ታሪኩን አስፍሩዋል፡፡

  የይስሐቅ ልጅ ያዕቆብ ድንገት በአንድ ወቅት የቆፈረው ጉድጉዋድ እርሱ ልጆቹ ከብቶቹ ጠጥተው ደግሞ ከ ብዙ ዘመን በሁዋላም  ሌላ ትውልድ ይጠጣው እንደነበረ በዮሐንስ 4 ላይ ካለው ታሪክ ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ ከራሳችን ያለፈ ነገር ማሰብ : ትውልድ የሚጠጣው ዘመን ተሻጋሪ ስራ መፍጠር ይቻላል፡፡ በርካቶች በራሳቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን የከፈቱት ቢዝነስ ህብረተሰቡን የሚለውጥ፣ አገርን እንኩዋ የሚጠቅም ሆኖ ተገኝቱአል፡፡ ከእነሱ አጥር ያለፈ አሳብ ስለነበራቸው ነው፡ ለውጥ ሊያመጡ የቻሉት፡፡የቆረቆሩት ትምህርት ቤት፣ የህጻናት ማሳደጊያ ፣ የአዛውንቶች መጦሪያ ወይም የህክምና ማዕከል ወይም የስራ ሙያ ማሰልጠኛ ማዕከሎችን ገንብተው የህዝብ ንብረት አድርገዋቸዋል፡፡ ኤሌክትሪክን ለዓለም አበርክቶ እንዳለፈው ሳይንቲስት ማለት ነው፡፡

  እኛ ክርስቲያኖች በእምነት የአብርሐም ልጅነታችንን እንቀበላለን፡፡ ከዚህ ጋር የአብርሐምን ሙሉ በረከት መቀበልም ሊያጉዋጉዋን ይገባል፡፡ የአብርሐም በረከት  እባርክሀለሁ ፡ ደግሞ ለበረከት ሁን፡፡ ዘፍ.12፡1-3 ፡፡ የሚል ሲሆን፡፡ ‹እባርክሃለሁ› ራስን በተመለከተ ቢሆንም ፡፡ ‹ለበረከት ሁን ›የሚለው ቃል ግን ለሌሎች መትረፍን የሚያመለክት ነው፡፡

    በስራ ጊዜ የሚገጥሙ እንቅፋቶች፡-

ሰዎች መንፈሳዊና ባለራዕይ ቢሆኑም ከችግር ነጻ  ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ምክንያቱም የአስተዳደግ ሁኔታ፣ የልምድ እጦት፣ ሰስጋዊነት ፣ የአካባቢ ወይም የዓለም ተጽዕኖ እና በሰይጣን የሚነሳ ውጊያ ስላለ ነው፡፡አብሮ በመስራት ጊዜ እነዚህ ችግሮች ብቅ ሊሉ ይችላሉ ፤ ችግሮች በተለያየ መልክ መቼም ጊዜ ሊነሱ ቢችሉም በወቅቱ ምን ና እንዴት ማድረግ ካላወቅንበት ይባባስና የት ሊደርስ የነበረ ስራ ይፈርሳል፡፡ ችግሮች በጥቂቱ ራስ ወዳድነት ፣ ግትርተኝነት /መሸነፍ ያለመፈለግ/ ፣የሌላውን ሐሳብ ያለመቀበል እና የንቀት ስሜት፣ ስንፍና፣ ለወጡ ህጎችና ስምምነቶች ያለመገዛት፤ነገሮችን አርቆ አለማሰብ-ችኩልነት፣ በሌላሰው ላይ አድቫንቴጅ ለመምታት ማሰብ፣ የፍክክር ስሜት....ወዘተ ናቸው፡፡ ዋናው ነገር ችግሮች ሲፈጠሩ ምን ማድረግ አለብን ? የሚለው ነው
  • ወንድሜ ከእኔ ይሻላል ማለትን ማሰብ ፊሊ.2
  •  አብርሐም ለሎጥ ቅድሚያ እንደሰጠ ለሌሎች ቅድሚያ መስጠት
  •  ቅንነትና ታማኝነትን ማዳበረ
  •  በስራው ላይ የባለቤትነት ሰሜት ሳይሆን ባለ አደራ እንደሆኑ ማወቅ
  •  በመነሻ ጊዜ የወጡትን ስምምነቶች ማክበር ፡ ሀላፊነትን ለመወጣትም ተግቶ መስራት ነው፡
  • መጽናት
  •  በእግዚአብሔር ፊት መጸለየ
  •  ብዙዎች ለተስማሙበት ነገር ተቃራኒ ያለመሆነ
  • ሌሎች ተሞክሮአቸውን በምክር መልክ እንዲለግሱ መፍቀድ 
ይህን ክፍል ለማጠቃለል ያህል ከመነሻው ጀምሮ ራዕይ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ከመፍትሔያቸው ጋር ለማቅረብ ተሞክሩዋል፡፡ እግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ እንበርታ፡፡ የተቀሩትን ነገሮች በሌላ ክፍል እንዳስሳቸዋለን፡፡

                                                                                       benjabef@gmail.com



No comments:

Post a Comment