Tuesday, November 27, 2018

በቤሩት-ሊባኖን የተፈጸመ!

በቤሩት-ሊባኖን የተፈጸመ!
    ******************
  የእግዚአብሔር ቃል "ወደ ዓለም ሁሉ ሂዱ፤ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ፤" ማር.16፡15 እንደሚል፤  የዳነችበትንና የገባትን ወንጌል በዓረብ አገር ላገኘቻቸው አንድ ቤተሰብ ስትመሰክር ስለገጠማት አስደናቂ ነገር እህታችን ነጻነት ተከታዩን ታሪክ አጫውታኛለች:-

እ.ኤ.አ. 1997  በኤጀንሲዎች በኩል ተቀጥሬ ለሥር ወደ አረብ አገር ለመሄድ ተነሳሁ። ለመብረር ሁለት ቀን ሲቀረኝ ...አንድ አገልጋይ አገኝኝና ሲጸልይልኝ  እንዲህ የሚል መልዕክት ተናገረኝ " እህቴ ሆይ የምትሄጅው ለወንጌል አገልግሎት ነው! በዚያ ለስሜ ትመሰክሪያለሽ! ይልሻል፤" የሚል ነበር፤ አገሩ ቤሩት -ሊባኖን ይባላል፤ የተቀጠርኩበት ቤተሰብ በቁጥር 7ት ያህል ሲሆኑ ከእነዚህ ውስጥ 4ቱ ልጆች ፣ እናትና አባትን ጨምሮ አያታቸው (የሰውየው እናትም) አንድ ላይ ነበሩ። ከ4ቱ ልጆች 3ቱ ዩንቨርስቲ የተመረቁ ሲሆኑ አንድ ልጅ ብቻ ገና በትምህርት ላይ ነበረ።

ቤተሰቡ የካቶሊክ አማኝ ቢሆኑም ያን የሚያህል አጥባቂ አይደሉም፤ እንደውም በቤታቸው ፊት ለፊት አንድ ወፍራም ዛፍ አለ፤ አጠገቡም  በመስታወት የተከበበ ሻርቤል ተብሎ የሚጠራ ጣኦት ፤ በየጊዜውም ልዩ ልዩ ስጦታዎች የሚቀርቡለት  ነበር። ....እንደሄድኩ ሰሞን በር እየቆለፉብኝ ተቸግሬ ነበር፤ ስለዚህም በጥንቃቄ ነበር የምኖረው፤ እኔ እንደገባኝ ስጋታቸው  ጠፍታ ሌላ ቦታ ትሄድብናለች ! የሚል ጥርጣሬ ነው፤ ወደ ዓረብ አገር እንደዚህ  ተቀጥረው የሚሄዱ ሰራተኞች ባልተመቻቸው በማንኛውም ሰዓት ጠፍተው ይወጡና  በሌላ ደላላ ሌሎች ቦታዎች ላይ የመቀጠር ልማድ አለ። እኔ ትንሽ ተስፋ ልሰጣቸው ሞከርኩ! ...አይዞአችሁ እኔ ክርስቲያን ነኝ! የትም  ሄጄ አልጠፋባችሁም፤ ብዬ ላረጋጋቸው ሞከርኩ፤ ማዳም አለፍ አለፍ ብላ ጥያቄ ትጠይቀኝ ነበር ...ስለላ ቢጤ  መሰለኝ! ስለ እኔ ማንነት የበለጠ ለማወቅ ትፈልጋለች፤ ይሁንና በደፈናው ክርስቲያን ነኝ! ከማለት ውጪ ስለ አማኝነቴ በዚህ ፍጥነት ለማስታወቅ አልፈለኩም ነበር። ስራዬን በትክክል እሰራለሁ፣ ጌታን በሕይወቴ ለማሳየት እጥራለሁ፤ በቃ ከዚያ ጌታ የፈቀደው ይሆናል፤...  አየሩንም ሆነ የቤተሰቡን ሁኔታ በተወሰነ መልክ እየተላመድኩ መጣሁ፤ ... እስትንፋሴ እስካለች ድረስ መቼም ቢሆን የትም፣ ከምንም ነገር በላይ ማስረዳትና  መናገር የምፈልገው አንድ ብርቱ ዜና አለ! ይኽውም የዳንኩበት የጌታዬ የኢየሱስ ክርስቶስ የወንጌል ጉዳይ ነው። እናም እግዚአብሔር ዕድሉን ሰጠኝና ወንጌልን በዓረብ አገር ሁሉ ተዘዋውሬ ባልሰብክ እንኳ፤ ቢያንስ ባለሁበት ቤት ውስጥ ግን ምስክርነቴን መጀመር እንዳለብኝ ገብቶኝ የአቅሜን አድርጌያለሁ።

የዳንክበትን ወንጌል የትስ ቢሆን እንዴት ልትደብቅ ትችላለህ?... አንድ ቀን ቤቱን እያስተካከልኩ ሳለ የአረብኛ መጽሐፍ ቅዱስ አየሁ፤ እርሱን መነሻ አድርጌ ውስጤ የታፈነውን ምስክርነት የምጀምርበት  ሆነኝ! ልጆቹን ይሄ ምንድን ነው? አልኳቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ነው! ብለው መለሱልኝ፤ ታዲያ ለምንድን ነው? ስታነብቡት የማላያችሁ? ብታንነቡት እኮ መልካም ነው! ማንም አንዳች አልመለሱልኝም። ጥቂት ግፊት ማድረግ ጀመርኩና ማታ ማታ አብረን ማንበብ ጀመርን፤ እነርሱ አረብኛውን ማንበብ ይችላሉ፤ እኔ ደግሞ አማርኛውንና እንግሊዘኛውን ቨርዥን እያፈራረቅኩ አነባለሁ፤ በንባባችን እየገፋንበት መጣን፤ በተለይም አንደኛዋ ልጅ በደንብ እየወደደችው መጣች። የልጅቷ ስም ሞንያ ነው።

  ሁለተኛ ጊዜ ለቤተሰቡ ስለ ወንጌል የምናገርበት  ሌላ ዕድል ተፈጠረ፤ ነገሩ እንደዚህ ነው፤ ማዳም አንድ ቀን ጠዋት የጣኦት ቤቱን ሄጄ አዋራውን እንዳጸዳ ትዕዛዝ ሰጠችኝ፤ እኔም ውስጤ በኃይል ተቆጥቶ አላደርገውም! አልኳት፤ ማዳምም ለምንድን ነው? የምልሽን የማትታዘዢኝ? አለችኝ። በዚያ ጊዜ ልትመታኝ ትችል ነበር፤ እኔም በወቅቱ ይህን ግምት ውስጥ አላስገባሁም ነበር።  እናም መለስኩላት  መጽሐፍ ቅዱስ አምጥቼ ዘዳግም 5 ላይ ያለውን ቃል አነበብኩላት ፤ እርሷ የተማረች ነርስ ናት፤ ቢሆንም የመንፈሳዊ እውቀት ግን አልነበራትም።  ቃሉን አምጥቼ አነበብኩላት እንዲህ ይላል "በላይ በሰማይ ካለው በታችም በምድር ካለው ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ ፤...አትስገድላቸው! አታምልካቸውም።" ዘዳ.5:8-10። ስለዚህ  እግዚአብሔር ጣኦትን ይጠላል! አልኳት። ለጊዜው መልስ አልሰጠችኝም። ሞንያ ግን ይህ ያነበብሽው እኮ የድሮ /የብሉይ ኪዳን/ ህግ ነው! አሁን ሊሰራ አይችልም! አለችኝ። እኔም" ዓይን ስለ ዓይን ፣ ጥርስም ስለ ጥርስ " (ምናልባት ጥርስህን ለሚያወልቅህ ጥርሱን አውልቀው! እንደማለት ነው) የሚለው ነው ተሽሮ አንድ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሌላኛውን አዙርለት፣...አንድ ምዕራፍ ለሚጠይቅህ ሁለት ምዕራፍ አድርግለት፣..(ማቴ.5፡38-42) ፤ ...እንዲህም ስለሚመስል ነገር እንጂ ከእኔ በቀር ሌላ አምላክ አታምልክ፤ ወይም አትስረቅ፣ አታመንዝር! የሚሉት ትዕዛዛት  ለዘላለም የማይሻሩ ናቸው! ብዬ አስረዳኋት። አሃ..! አለችና ጭንቅላቷን ነቅንቃ ጥቂት ዝም አለች ፤ ሲመስለኝ ቃሉን እየተረዳች ነው፤ እግዚአብሔርም በልጅቷ ህይወት ውስጥ አንድ የሆነ ዓላማ ያለውም ይመስለኛል ። ብዙ ጊዜ ስራዬን በጊዜ ጨራርሼ መጽሐፍ ቅዱስን እንድናነብ የበለጠ ፍላጎት ስላሳየችኝ ይህንን ለማድረግ ተጋሁ። ...በተለይ ወንጌልን በደንብ አድርጋ ነው የተማረችው፤ ጥቅስ አወጥተን እናነባለን ፤...እያንዳንዱ ታሪክ ይመስጣል፣ ህይወት ሰጪው ቃል በየማታው በውስጧ ይንቆረቆራል።

  ነገሩ በእንደዚህ ሁኔታ እየቀጠለ ሳለ አንድ ቀን ቤተሰቧ ከካናዳ የመጣ ባል አዘጋጅተውላት ነበረና ከመቅጽበት እቤት ውስጥ ወሬው ሁሉ እርሱ ሆነ፤ እኔ በጣም ተጨነቅኩ! ጠላት ይህን ሰበብ ፈጥሮ ከኔ ሊለያት ነው አልኩ፤ እስካሁን የለፋሁበትም ገደል ሊገባ ነው ? ብዬ መጸለይ ጀመርኩ፤ ሰውየው ሃብታም ቢጤ ነው ሲባል ስምቻለሁ፤ ያው ደግሞ ዘመዳቸው ነው፤ በባህላቸው መሠረት ሊባኖናውያን ከአክስትና ከአጎት ልጅ ጭምር ጋር እርስ በርስ ጋብቻሞች መሆን ይችላሉ መሰለኝ። ሰውየው አንድ ምሽት ላይ ጠቅላላ ቤተሰቡን እራት ሊጋብዝ ነው ተብሎ ተለቅ ወዳለ ስመጥር ሆቴል ለመሄድ ሲዘጋጁ ሳለ እኔም   እንድዘጋጅና አብሬያቸው እንድሄድ ተነገረኝ። እኔ ግን እራሴን አሞኛል! በሚል ሰበብ እንደማልሄድ ገለጥኩላቸው። ለነገሩስ የሞንያ ነገር ስላሳዘነኝ ጌታ ጣልቃ እንዲገባ ለመጸለይ አስቤ እንጂ አሞኝ አልነበረም የቀረሁት። ሞንያ ወደ እራት ስፍራ ከመሄዷ በፊት ወደ እኔ መጥታ <..ግን ምን ይመስልሻል?> አለችኝ። ውሳኔው የራስሽ ቢሆንም በፍጹም የማያምን ሰው ጋር  መጋባት ግን አለብሽ ብዬ አላምንም! አንቺ ማግባት ያለብሽ እንዳንቺ ክርስቶስን የሚያምን ክርስቲያንን ነው...።  ሁሉም ተከታትለው ሲሄዱ እኔ ተንበርክኬ መጸለይ ጀመርኩ፤ ከሰዓታት በኋላ ሞንያ ብቻዋን በመኪናዋ ወደ ቤቷ መጣች፤ ..ብዙ ነገር አላስደሰታትም መሠለኝ! እራት ብቻ በልታ፥ ጭፈራ ስትጋበዝ አምልጣ ነው የመጣችው፤ ቤተሰቡ ገና አልመጣም። ሰውየው ተናዷል አሉ! ቤተሰቦቿም በልጃቸው ድርጊት ተበሳጭተው ፊታቸው ፍም መስሎ ነው የተመለሱት። በቃ እልወደደችውም! ጌታ ጣልቃ የገባ ነው የሚመስለኝ! ትላለች ነጻነት።

እነ ሞንያ ቤት ከገባሁበት ጊዜ አንስቶ የሚረብሸኝ ሌላው ነገር ቅጥ የሌለው የዘፈን ድምጽ ነው፤ ሞንያ በጣም ነበር ዘፈን የምትወደው፤ ስትዘፍን፣ ስትደንስ" ነፍሷንም አታውቅ" ነበር። ዛሬ አልጨፍርም! ብላ ንቃ መጣች! እቤት ውስጥም ቢሆን ጸጥታ ሰፍኗል። ይህ ጉዳይ ደግሞ ቤተሰቡን አሳስቦታል። ይህች ልጅ ምን ሆና ነው የተቀየረችው? ይባባላሉ፤ በማናቸውም ሰዓት ያን ለብዙ ጊዜ ዝም ብሎ የተቀመጠ መጽሐፍ ስታንብ ነው የምትታየው። <ከነጻነትና ከዚህ መጽሐፍ ራስ ላይ አንወርድም!> የተባባሉ ይመስላል። ምክንያቱም እኔ ላይ ፊታቸውም ሆነ ቃላታቸው ተለውጧል። ትንሽ መፍራት ጀመርኩ!  ከአገራቸው  እንኳ ሊያስባርሩኝ ይችላሉ ብዬ ሰጋሁ። በተለይ በተለይ ግን በዚህ ሁኔታ ከሞንያ ጋር እንዳያለያዩን ነው ዋናው ስጋቴ። ሁሉም ሰው ልጅቷን ያበላሸችው ነጻነት ነች! ሲባል እየሰማሁ ነበር። ወይ ዓለም! ዘፈን፣ ጭፈራ፣ ስካር፣ ዝሙት ..መተውን <መበላሸት!> ብለው ነው የሚገልጹት፤ የሚጠቀሙበት ዲክሽነሪ ምን ዓይነት ነበር..?! ይገርማል!

የሆነ ቀን ቤተሰቡ አንድ ከባድ ውሳኔ ወሰነ፤ ውሳኔው ሞንያና እኔ በምንም መንገድ  አብረን እንዳንገናኝ ነበር ። አንዳንድ ጊዜ <ኪችን> ስንገናኝ ከቤተሰቡ መካከል አንዳቸው ይመጣሉ፤ በመሃላችን ይገቡና ይለያዩናል፤ እርሷም ወደ ሌላ ክፍል ትሄዳለች። ስለዚህ ሞኒያ ዘዴ ዘየደች። ዘዴውም እንዲህ ነው፤ ሁሉም ከተኙ በኋላ በሌሊት ከክፍሏ ወጥታ ወደ እኔ ትንሽ ክፍል ትመጣለች፤ የተወሰነ ሰዓት የእኔን ጋቢ ትለብስና ታጣፊ አልጋዬ ጥግ ትንበረከክና አብረን እንጸልያለን። ጥቂት ጊዜ በዚህ ሁኔታ እያሳለፍን....፤ አንድ ቀን ልዩ ነገር ሆነ፤ ሞንያ በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች! በልሳን መናገር ጀመረች! እኔ ደስታዬ ወደር አልነበረውም፤ እርሷ ግን ምን ሆኜ ነው? ብላ ስትደነግጥ፤ ስለ መንፈስ ቅዱስ አሰራር ከቃሉ ላይ አስረዳኋትና ተደነቀች። ከዚያ በኋላ ባሰባት! በተገናኘን ቁጥር እንጸልይ ብቻ ነው የምትለው።

በ15 ቀን አንድ ጊዜ እረፍቴ በመሆኑ ከቤት ውጥቼ አንዳንድ ቦታ እሄድ ነበር። በእርግጥ ብዙ ጊዜ የምሄደውና የማልቀርበት ቦታ ቤተክርስቲያን ነው። የምታደርሰኝ ደግሞ ሞንያ ነች። ብዙ ጊዜ እኔን ቸርች አድርሳኝ እርሷ ትመለስ ነበር። አሁን ደግሞ ያ ቀርቶ፥ አብራኝ ገብታ በአበሾች መካከል ፥ ቋንቋው ባይገባትም በእማርኛ ዘምራ ፣ አምልካ መውጣት ጀመረች። ሌላ ጊዜ ደግሞ እየሆነ ያለውን ታሪክ ያጫወትኳት አንዲት አበሻ እህት ጥቂት የዳኑ አረቦች ተሰባስበው የሚጸልዩበትን ቦታ ጠቆመችንና ወደዚያ ሄድን። ...ይህማ ቋንቋዋ ነው፤ በአረብኛ ቃል ሰማች፤ ጌታን አመለከች....ደስ አላት፤ የአገሯን ሰዎች አገኘች። ከዚያ ስትመለስ እቤት ውስጥ በግልጽ መመስከር ጀመረች! ፍርሃት ቀረ!

የዚህ ሁሉ ምክንያት ነጻነት ነች! ተብዬ ቤተሰቡ የበለጠ ስለጠመደኝ፥ አትገናኙ የሚለው ህጋቸው እስካሁን አለ። ይሁንና ለቃል ረሃብተኛዋ ልጅ በኪሴ ጥቅስ እይዝና ወደ ማዕድ ቤት/Kitchen / እሄዳለሁ ፤ ቀስ ብላ ትመጣና ጥቅሱን እንቀባበላለን ፤ በዚህ ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስን እያነበበች ትውላለች፣ ታመሻለች። ከጊዜ በኋላ -ነገሩ በጣም እየከረረ ሲሄድ ከቤታቸው እንድወጣ ተፈረደብኝ። አንድ ቀን ቸርች ደርሼ ስመጣ ግቢው ውስጥ ጠቅላላው ቤተሰብና ጎረቤት ተሰባስበዋል፤ እንደገባሁ በይ! "ልብስሽን ያዢና ውልቅ በይ!" ተባልኩ። ያን ጊዜ የት እንደምሄድም አላውቅም፤ በመካከላቸው ሞንያን አላያትም፤ የት ሄዳ ይሆን? አልኩ በልቤ፤ በኋላ ስሰማ ክፍሏ ውስጥ ነበረች። እንዴት ወደ ውጭ  እንደወጣች አላውቅም፤ ከደቂቃዎች በኋላ ወደ ስብስቡ ቀረበች!...አለቀሰች! እኔ ሻንጣዬን ይዤ-- ፣ ታናሽ እህቴም አጠገቤ ነበርች፥ ልንወጣ ነው፤... <እኔን ለማን ትተሽ ነው የምትሄጂው? አለችኝ።> አንጀቴ ተላወሰ! ቢሆንም ቆፍጠን ብዬ አይዞሽ! ይህ ቤተሰብ ሁሉ ቆይተው ወደ ጌታ ይመጣሉ። ቃሉ" አንተ እመን ቤተሰብህም ይድናል!" ይላል አልኳት / በጊዜው የመጣልኝ ቃል ነው/፤ አንቺ ቤተሰብሽ ጋር አብረሽ ሁኚ! አልኴት። ...በነገሩ ብግን ብላ ነው መሰል፥ አክስቷ ተንደርድራ መጥታ አንድ ጊዜ አቀመሰችኝ! ንዴቷ ከፊቷ ላይ ይነበባል! ኽረ...በደንብ አድርጋ ነው ያቀመሰችኝ! የልቧ የደረስላት እንኳ አይመስለኝም፤ እኔ ደግሞ አንድ ጊዜ ጸጋውን አብዝቶልኝ የለ!? <ማዳም ሆይ እወድሻለሁ! /I love you!> አልኳት፤ <መበዴ!> አለች፤ በአረብኛ <አልፈልግም!> ማለቷ ነበር። ሞንያ ክፍሏ ገብታ ተንሰቅስቃ አለቀሰች፤ ወደ እናቷም መጣችና፥ ማማ ዛሬ የዚህን ቤት መብራት እንዳጠፋሽ እወቂው ? ብላት ገባች።...

ቤታቸው በኖርኩበት ጊዜ ያልመሰከርኩለት አባታቸውን ብቻ ነው፤ ስለ ሌሎቹ ምንም የሚቆጨኝ ነገር የለም። ከወጣሁ በኋላ እዛው አገር ሌላ ቦታ ስራ ጀመርኩ። ይሁንና የሞንያ ቤተሰቦች ሞንያን ወደ ጋና እንደላኳት ቆይቼ ሰማሁ። አባቷ ለስራ ጉዳይ ወደዚያ አገር ይሄድ ነበርና፤..ዶክመንቷን፣ ፓስፖርቷን ቀምተው ሰው አገር ወስደዋታል/አፍሪካ/። ትንሽ አዘንኩ! ግን ጌታ አዋቂ ነው።

እ.ኤ.አ.2000 ላይ ከሞንያ ጋር በደንብ ተለያየን። ጋና ምን ገጥሟት ይሆን? ህይወቷ እንዴት ሆኖ ይሆን? ...በልዑል እግዚአብሔር ፊት ከመጸለይ በቀር ምን ማድረግ እችላለሁ? እኔም ከጥቂት ዓመታት ቆይታ በኋላ አሜሪካን አገር ገባሁ፤ እርሱም የራሱ ታሪክ አለው፤ እህቴ ቀደም ብላ ወደ አሜሪካ መጥታ ነበር።

ከሞንያ ጋር ከተለያየን ድፍን 18 ዓመት ሞላን። አንድ ቀን ስልክ ተደወለ! ቁጥሩ የዱባይ ነው። ሠላም ለእናንተ ይሁን! ማን ልበል? የወንድ ድምጽ ይመስላል! መጋቢ በርናባስ እባላለሁ አለ! ...እሺ ምን ልታዘዝ? አኧይ.. አንድ ጓደኛሽ ነች ስልክሽን የሰጠችኝ! ለአገልግሎት ሊባኖን ሄጄ ሞንያ ከምትባል  ሴት ጋር በድንገት ተገናኘን፤ ..እንዴት ጌታን እንዳገኘች፤ የህይወት ምስክርነቷን ስታጫውተኝ ቆየን...በአንዲት አበሻ ሴት አማካኝነት ብላ በዋናነት ስለ አንቺ አነሳች፤... ወደ ጋና ሄዳ ስትመለስ አንቺን ማግኘት አልቻለችም ፤ አፈላልጋ፣ አፈላልጋ ደክሟት ሳለ፤ ከእኔ ጋር ሰሞኑን  ተገናኘን...አንቺን የሚያውቅሽ ሰው ሳጠያይቅ ነበር፤ በእግዚአብሔር ቸርነት የምታውቅሽን አንድ  እህት ዱባይ አገኘሁ እናም... ደወልኩልሽ። ቃላት ጠፋኝ....ዝቅ ብዬ መሬቱን ሳምኩት! ወደ ስልኩ ተመለስኩና...እባክህ ሞንያን አሁን እንዴት ማግኘት እችላልለሁ? ስል ጠይኩት፤ ይኽው ቁጥሯን ልሰጥሽ  አለኝ! ተቀበልኩት !

የሞንያ ቁጥር ላይ ደወልኩ፤ ስልኩ ተነሳ፥ በጌታ ልጄ፣ እህቴ ሞንያ... <ሄሎ!> አለች። ክብር ለጌታ ይሁን!!! ይህ የሚገርም አምላክ...አሁን ጉጉቴ 18 ዓመት ሙሉ እንዴት እንዳሳለፈች መስማት፤ ደግሞ አሁን  በምን ሁኔታ ላይ እንደምትገኝ  ማወቅ! በቃ ሌላ ጥማት የለኝም። ሞንያ የሆነባትንና የደረሰውን ሁሉ አንድ በአንድ ዘረዘረችልኝ፤ የዛሬሽ 18 ዓመት ወደ ጋና ከሄደች በኌላ....ሰዎችን አጠያይቃ ከተለያየ አገራት የመጡ ክርስቲያኖች በሳምንት አንዴ እየተሰባሰቡ የሚያመልኩበት ቦታ ጠቁመዋት ከእነርሱ ጋር ተገናኝች፤ አብራቸው የጌታን ጸጋ እየተካፈለች ከቆየች በኋላ ፤ እዚያው ቸርች በኳየር አገልግሎት ውስጥ መሳተፍ ጀመረች፤ ለሚስዮናዊ አገልግሎትም ወደ አውሮፓና ወደ ተለያዩ ቦታዎች ከሌሎች ጋር እየሄደች ታገለግል ነበር። በኋላም ሙሉ ለሙሉ ወደ ቤሩት ተመልሳ ከአበሻው ቸርች በመቀጠል ለመጀመሪያ ጊዜ በአረብኛ ጌታን ያመለከችበት ቤተክርስቲያን ውስጥ መጋቢ ሆና እንድታገለግል ተሹማ አገልግሎቷን ቀጥላለች!

መጋቢ ሞንያ በተወለደችበት ምድር ላይ ለብዙዎች አርዓያ በመሆን፣ ወንጌልን በድፍረት በመናገር አያሌዎችን ከሲኦል እያስመለጠች ሲሆን፤ ቤተሰቧ ሙሉ ለሙሉ ማለት እስኪቻል ድረስ ንስሐ ገብተው የክርስቶስ ተከታይ ሆነዋል። ነጻነትን በጥብቅ የምትጠላት  የሞንያ እህትማ በመንፈስ የተቃጠለች የወንጌል አማኝ ሆናለች፤ አባትና እናቷ አገልግሎቷን በአሁን ሰዓት በገንዘብ እየደግፉ ሲሆን፤ እህቶቿና የእህቶቿ ልጆች የቤተክርስቲያና አሸሮች፣ ሌሎቹም የህጻናት አስተማሪዎች ሆነዋል። በርካታዎች በየሳምንቱ ጌታን የሚቀበሉበት ቤ/ክ እንደሆነ መሰከረችላት፤ ከዚህ በተጨማሪ  በአሜሪካን ፣ በእንግሊዝ እንዲሁም በሌሎች አገሮች ላይ ተደጋጋሚ ጊዜ በመሄድ ወንጌልን ታገለግላለች። እህታችን ነጺ አብራን የጌታን ስራ የምትስራ የጌታ ሰው ናት። በቅርብ ጊዜ ወደ ቤሩት ሄዳ ጌታ እየሰራ ያለውን ነገር ለማየት ዕቅድ ስላላት ጸልዩላት። ክብር ሁሉ ለጌታ ይሁን!

አንዳንዶቻችን በጣም ትልልቅ የወንጌል ገድል ላንፈጽም እንችላለን፤ በርካታ የወንጌል ገድል የሚፈጽሙ እንደ ጳውሎስ፣ ፣ እንደ ቢሊግርሃም...ደግሞ እንደ ሞንያ ያሉትን የወንጌል ጀግኖች ግን ወደ ጌታ ልናመጣ እንችላለን!! ስለዚህ የምትመሰክሩለት ሰው ነገ ምን ሆኖ እንደሚገለጥ አታውቁምና ሳትታክቱ መስክሩ!** ከመሰከራችሁ በኋላ ጸልዩላቸው፣ ለመንፈስ ቅዱስም አሳልፋችሁ ስጧቸው። ሌላ ታሪክ ይቀጥላል....

<< LET US BE WITNESSES FOR CHRIST! >>

No comments:

Post a Comment