Tuesday, November 27, 2018

መታነቂያ ገመድ የምገዛበት 60 ብር ብቻ..!

መታነቂያ ገመድ የምገዛበት 60 ብር ብቻ..!

" በቦሌም ብለህ በባሌ" እንደሚባል ተሳክቶላቸው ወደምዕራባውያኑ ምድር የመጡ ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል የቤተሰቦቻቸውን አልያም የጓደኞቻቸውን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ብርቱ ጥረት የሚያደርጉት በድሃ አገር ያለውን ችግር ስለሚረዱ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ካላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ ነው። ስለዚህም  ሁለትና ሶስት ስራ መስራት ለብዙዎች አዲስ ነገር አይደለም።

ክርስትና በቅጡ የገባቸው ወገኖች ደግሞ  ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብና ምድራዊ ቁስ ከመስጠት የላቀ ምኞትና ጥማት አላቸው። ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ውጭ አገር ለመኖር የመጣች የአንድ ክርስቲያን እናት ታሪክ ቀጥሎ ቀርቧል። እናኒ ሰሞኑን እንደውም  ለወገኖች ከሚላከው የቫይበር ላይ የምስክርነት ጽሁፍ ተነሳስታ ለዓመታት የሱስ እስረኛ ለሆነ፣ ህይወት አሰልቺ ለሆነበት የልጇ ባል ወንጌል መስክራ ወደ ቸርች አምጥታው  ኦክቶበር 21,2018 ጌታ ኢየሱስን እንደ ግል አዳኝ አድርጎ ተቀብሏል። ለሦስት ትናንሽ ልጆቹም ተጸልዩዋል።  በብዙ የህይወት ትግል ውስጥ ያለፈ፣ ዓለም የተጫወተችበት ሰው ነው፤ በወንጌል አምኖ ንስሐ ከገባ በኋላ  ደስታችን ወደር አልነበረውም። ሃሌ ሉያ!!  እናኒ ለቀሩትም ቤተስቦቿ ይህን  የሕይወት ዘመን ትልቅ ውሳኔ እንዲወስኑ የተቻላትን ሁሉ በማድረግ ላይ ነች። ቤተሰቦቿን እንኳን በራሷ የጸሎት ዝርዝር ውስጥ ቀርቶ እኛን እንኳ ስንት ጊዜ አደራ ብላ አሳስባናለች። ይህም ሰው እንዲጸና በያላችሁበት ጸልዩለት!

  እናኒ የሕይወት ውሳኔ አድርጋ ክርስቶስን ልትከተል የቻለችበት አስደናቂ ታሪክም አላት እነሆ፡-....
ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል የጀመረችው ህዳር 12,2000 ዓ.ም. ነው። ወደ ክርስቶስ እንድትመጣ ምክንያት የሆነው ነገር ደግሞ በተከታታይ ያጋጠማት ሐዘን ነበር። የልጅነት ባሏ በ1999 ዓ.ም. በመኪና አደጋ በድንገት ህይወቱን አጣ። ያን ጊዜ በድንጋጤ ወድቃ ግንባሯ አበጠ፤ ምልክቱ እስከዛሬ ድረስ ይታያል። በጣም ነበር የምንዋደደው፤የኑሯችን ብዙ ነገር እርሱ ላይ የተንጠለጠለ ስለ ነበር.. ጉዳቴን አከፋው ትላለች። የባለቤቴ ሃዘን ሳይለቀኝ ከ1ዓመት 4ወር በኋላ የምወዳት ሴት ልጄ ከቤሩት ወደ ቱርክ አገር እሻገራለሁ ብላ ከሌሎች ሰዎች ጋር በጀልባ በባህር ጉዞ ላይ እንዳሉ ሙሉ ለሙሉ ሰጥመው ውሃ በላቸው፤ የልጄ አስክሬንም ተፈልጎ ተላከልኝ፤ በጥቂት ጊዜ ልዩነት ውስጥ የምትወደውን ባል እና የደረሰች ሴት ልጇን ያጣች ምስኪን እናት ሆንኩኝ። ከዚያ በኋላ እዕምሮው እንደተነካበት ሰው ባዶ እግሬን ገዳም ለገዳም እየዞርኩ በባህላችንና- በዕምነታችን መሠረት የሙታን ተዝካር /ሙት ዓመት እያወጣሁ ገንዘቤን ቀስ በቀስ ጨረስኩ። በተለይ የልጄን 12 ካወጣሁ  በኋላ መሞት እንዳለብኝ ወሰንኩ! ..ሰይጣን አጠገቤ ቆሞ ብዙ ጊዜ የሚያዋራኝ ያህል ይሰማኝም ነበር ። አንቺ አሁን ሰው ነሽ?! እንዴት ቆመሽ ትሄጃለሽ? ሰው ምን ይልሻል? ...ለምን አትሞቺም?! ...እያለ ደጋግሞ ይወተውተኛል። ባሏንና ልጇን የምትወድ ብትሆን ኖሮ እንዴት እንደዚህ ቆማ ልትሄድ ቻለች? እያሉ ጎረቤቶች የሚያሙኝ ያስመስልብኝ ነበር። ጥቁር ልብሴም አልወለቀ! ሞራሌም ተሰባበረ፣ የልቤም ሆነ የኑሮዬ አቅም ወደቀ! ብቸኝነት ተሰማኝ፤ በተለይ ዓመታዊ በዐላት ሲመጡ ድሮ የለመድኩት በግና-ዶሮ ቀረ! ገና ያልጠነከሩ አንድ ወንድና ሌላ ሴት ልጄ ይከፉቸዋል ብዬ እጨነቃለሁ ። እነዚህ ሁሉ ነገሮች ተደራርበው ...መሞት እንዳለብኝ ወሰንኩ።

ባለቤቴ ሲሞት 300 ሺህ ብር ያህል ባንክ ውስጥ ተቀማጭ ነበረን፤ አሁን 60 ብር ብቻ ቀርቷል፤ እርሱ ደግሞ ገመድ መግዣ ይሆነኛል ብዬ ሌሊትና ቀን ከራሴ ጋር ሟውራት ጀምሬያለሁ። አንድ ቀን ልጄን ከቀበርኩ 12ኛው ቀን በኋላ በጠዋት 12 ሰዓት / 6AM/ ላይ ተነሳሁና ለልጆቼ እንጀራ ጋገርኩ፣ ወጥ ሰራሁ ፣ ልብሳቸውን አጣጠብኩና መታወቂያዬን፣ የእነርሱንም ፎቶ ይዤ ከእንቅልፍ ሳይነሱ የምታነቅበትን ገመድ ይዤ ከቤት ወጣሁ፤ መካኒሳ ሰፈር አካባቢ <አቦ ቤ/ክ> ጫካ ውስጥ ለመታነቅ ወስኛለሁ፤ አንድ ወፍራም የወይራ ግንድ ላይ ገመዱን ሸምቀቆ ሰርቼ፣ አስሬና አስተካክዬ ፡ ባሌና ልጄ ወደተቀበሩበት  ቦታ  መጣሁ (እዚያው አቅራቢያ ነበር)፤ ለሁለቱም ሟቾች ሻማ ለኩሼ ለደቂቃዎች አለቀስኩ ፤ "ልመጣላችሁ ነው!" እያልኩ ነበር የማለቅሰው፤ ውስጤ በኃይል ሲነድ ይሰማኛል፤ አስተኝቻቸው የመጣኋቸው ህጻናትም በአዕምሮዬ ይታወሱኛል፤ በሌላ አንጻር የሰይጣን ክስ   አለብኝ። እሞትና... መታወቂያዬንና የልጆቼን ፎቶ ያዩ እሬሳዬን አፈላልገው ለቤተሰቤ ይሰጡልኛል፤ በዚህ ላይ አባቴና ሌሎች ዘመዶቼ ለልጄ ለቅሶ ከጎንደር መጥተው አቅራቢያዬ ነው ያሉት፤ ለቀብሩም ሳይቸገሩ በዚሁ ይገላገላሉ!  እያልኩ ውሳኔዬን በአዕምሮዬ እያጠናከርኩ ነበር የማለቅሰው፤ ከዚያም ጨርሼ፡ ለመታነቅ ወዳዘጋጀሁት ስፍራ ስወርድ፤ መንገድ ላይ ከአንድ ሰው ጋር ተገናኘሁ፤ የቀብር ጉድጓድ በመቆፈር የታወቀ "መ??ይ" የሚባል የአካባቢዬ ሰው ነው። አንቺ ሴትዮ...! በሚል  ከፍ ባለ ድምጽ ንግግሩን ጀመረ፤...እንዚህን ህጻናት ትተሽ ጫካ ለጫካ ለምን ድነው የምትዞሪው? ለልጆሽ መኖር አይሻልሽም? ወይም ብትሞቺ ይሻልሻል!! ቀጠለ ንግግሩን...ወይም መፍትሄ የምትፈልጊ ከሆነ ደግሞ አሩሲ... አንድ አዋቂ ቤት አለ እዚያ ልውሰድሽ/ጥንቆላ ቤት መሆኑ ነው/፤ እዚያ ለሦስት ወር ቀጥ ብለሽ ካገለገልሻቸው ልጅሽንና ባለቤትሽን እንድታናግሪ በሙታን ጠሪ መንፈስ ያገናኙሻል...ወዘተረፈ አለ። እኔ ደግሞ በልጅነታችን ጠንቋይ ቤት እንዳንሄድ! ከቤተሰባችን መሃል የሚሄድ ካለ ርጉም ይሁን  ተብሎ ከተወሰነበት ቤተሰብ ነው ያደኩት! መሄድ አልወድም! ...በብዙ ሌላ ቃላት አባበለኝ፤..እስቲ ተመልከች! በቀደም ዕለት 15 ጉድጓድ እንድቆፍር ትዕዛዝ የሰጠኝ የኡሩሲው ጠንቋይ... ፤ ገና አንድም ሰው ሳይሞት 15 የቀብር ጉድጓዶች አስቆፈርኩ በዚያን ቀን 5ቱ ሞቱና ተቀበሩ፤ በተቀሩትም ጥቂት ቀናት 10ሩም ጉድጓዶች ውስጥ ሰው ተቀብሮበታል። ይታይሽ! አለኝ፤ ...ሰውየው የከብት እርባታ ያለው፣ መኪና  ያለው ሃብታም ቢጤ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡ ያን ሁሉ ንብረት ያፈራው  በጠንቋዩ እየተመራ ፣ጉድጓድ እየቆፈረ፤ ለ40ና 80 ተዝካር ለሟች ቤተሰቦች በሬ እየሸጠላቸው ነው።... ይህን ሁሉ ዝባዝንኬ ሲያወራ ቆሜ ሰማሁት፤ ነገር ግን አሁን እርሱ እያለ ታንቄ መሞት የለብኝም! ትንሽ ደቂቃ ወደ አስፋልቱ ልውጣና ሰውየውን ላሳልፈው፤ ብዬ ከጫካው ውስጥ ወጥቼ ወደ አስፋልቱ መንገድ ሄድኩ።

   እዚያ እንደ ደረስኩ ወዲህና ወዲህ ስል የባስ ፌርማታ አጠገብ ደረስኩ፤ አጠገቡ የቆመ ስልክ እንጨት አለ፡፡ እንጨቱ ላይ ደግሞ የተለጠፈ አንድ ጽሁፍ አየሁ፤ "ፖስተር"- የኮንፈረንስ ማስታወቂያ ነው። <<መዳን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው! ፤ ..እመን እንጂ አትፍራ!  ይላል >> እነዚህ መናፍቃን ናቸው! ብዬ ማሾፍ ጀመርኩ! ግን ጽሁፉ ውስጤ ቀረ! በአፌ" እነዚህ አታላዮች፣ ሌቦች... እላለሁ፤....ከልጅነቴ ጀምሮ ስለ ፕሮቴስታንቶች ያለኝ ስዕል የተበላሸ ነው፡፡ "ጨለማ ክፍል ውስጥ ገንዘብ በኮርኒስ ውስጥ የሚበትኑ..፤ የድመት ስጋ የሚያቆርቡ፣ በሰው 50 ብር እየተቀበሉ አዳዲስ ሰው የሚሰብኩ!"....."ድሮ ድሮ እንደውም የእናቴ ታላቅ ወንድም አማኝ ነበረ፤ እኛን ለመጠየቅ እቤታችን ሲመጣ እንኳ በእጁ አንጠልጥሎ የሚመጣውን ፍራፍሬ... ዘፍዝፈን፣ በብዙ ውሃ አጥበን ነበር የምንበላው ጴንጤ ስለሆነ ተጸይፈነው..። ስልክ እንጨቱን ይዤ እንዲህ አልኩ። <<እውነተኛው የድንግል ማርያም ልጅ ከሆንክ፣ አስቲ  ካዘጋጀሁት ከዚያ ገመድ አስጥለህ ለልጆቼ አኑረኝ! በዚህ እፈትንሃለሁ! አልኩት። ድንገት ሳላውቅ ፖስተሩ የተለጠፈበትን ስልክ እንጨት ተጠምጥሜ ይዣለሁ፤ አውሎ ነፋስ ከፊት ለፊቴ በኩል ሲነሳ አየዋለሁ..ብዙ ግሳንግስ ሰብስቦ ወደ እኔ ተጠጋ፤ አንዲት ድንቢጥ ወፍ ውስጡ ትታየኛለች፤ አይኔን ለታጠፋው ይመስላል እና እጄን እያወራጨሁ ተከላከልኳት፤ መሬት ላይ ወደቅኩ! ከደቂቃዎች በኋላ ስነሳ፡ በርካታ ሰዎች ከበውኝ ከንፈራቸውን ይመጣሉ። የተለኮሰ ክብሪት አጠገቤ አለ። የሚጥል በሽታ ነው ብለው አስበው ይህን እንዳደረጉ ገባኝ! የእኔን ትግል ማን አየ?!

ተነሳሁና ከበባውን ሰንጥቄ በመሄድ ፌርማታው ጋር የተቀመጠ አንድ ተለቅ ያለ  ሰው ጋር ተጠጋሁ፤ ይህ ማስታወቂያ ያለበትን ቤ/ክ ጠቁመኝ! አልኩት። ምነው አናቴ? አለኝ! መናፍቃን እኮ ናቸው፤ እዚያማ በፍጹም እንዳትሄጂ ! ይልቅስ  እዚህ ጋር ኪዳነብረት አለልሽ! እዚያ ጋርም ገብርኤል ቤ/ክ አለልሽ አለኝ በእጁ ምልክት እያሳየ! አአይ ለቅሶ ልደርስ ፈልጌ ነው ፤ ቦታው ደግሞ ቸርቹ ፊት ለፊት ነው፡ ስለው፤ ሰሞኑን አንድ ለቅሶ የነበረባት፥ ሴት ልጇ አረብ አገር የሞተችባት እና ባሏንም በሞት ያጣች ..ብሎ የእኔን ታሪክ ለራሴው ሳይጨርስ ተወው! እርሷን አውቃታለሁ፤ እርስዋ ሳትሆን ሌላ ሰው ነች! አልኩት። አደራ እንዳትጠጊያቸው! ብሎ ቦታውን በርቀት ጠቆመኝ። ወደዚያ አመራሁ FBI ቸርች ገና አዳራሹ እየተሰራ ዕቃዎች ብትንትን ብለው ይታያሉ፤ ተጠጋሁ ግን  በታች በኩል ነበር የሄድኩት፤ ዘበኛውን በአጥር ላይ አናገርኩት! ምን ፈልገሽ ነው? አለ ዘበኛው። " ወደ ወንዝ ልትገባ ያለችን ነፍስ የሚያድን! አልኩት" በደንብ ስላልገባውና እንደ ጤነኛም ስላልቆጠረኝ በላይኛው በር ዞሬ እንድመጣ ጠቆመኝ። ዞሬ መጣሁ፤ በዋናው በር ገብቼ የቅድሙን ቃል ደገምኩለት " ወደ ወንዝ ልትገባ ያለችን ነፍስ የሚታደግ ሰው ፈልጌ ነው! የመጣሁት፡፡" ወዲያው አንድ ወንጌላዊ ተጠራ፤ ወ/ዊ መንግስቴ ይባላል፤ አናገረኝና ይዞኝ ወደ ጸሎት ቤት አመራን ፤ እርሱ ከፊት ለፊት እየመራኝ እኔ እየተከተልኩት ነበር። ድንገት መሃል መንገድ ላይ ግን እኔ ቆምኩ በእውነት መንቀሳቀስ አልቻልኩም! የተከተልኩት መስሎት ነበር ፤ ሲያጣኝ ተመልሶ መጣ፤ ቆሜያለሁ። ምነው አለ? አልቻልኩም አልኩት! ገባውና መጸለይ ጀመረ፤ ሌሎች ሶስት አገልጋዮች መጡ.. እስኪያልባቸው ድረስ ጸለዩ ገሰጹ። ያ ቅድም ያየሁት አውሎ ነፋስ ያቺን ድንቢጥ ይዞ ዳግመኛ ሲመጣ ይታየኛል፤ እንደ ቅድሙ ግን አጠገቤ ሳይደርስ ተበትኖ ጠፋ! እግሬንም ለቀቀኝ ጸሎት ቤት ገብቼ ወንጌልን መሰከሩልኝ ክርስቶስን አዳኜና ጌታዬ አድርጌ ተቀበልኩ።

ወደ-ጫካው ተመልሰን ሄደን ገመዱን ፈታነው ፎቶዎቹንና ሌሎች እቃዎችን ይዘን መጣን። ከዚህ በፊት እዚያ ቦታ ቢያንስ አምስት ሰው ታንቆ እንደሞተ እስታውሳለሁ። በተለይ እኔ ገመድ ያንጠለጠልኩበት የወይራ ዛፍ ደግሞ አንድ ጎረቤቴ ታንቃ የሞተችበት ዛፍ ነው፤ ባሏንና ሁለት ልጆቿን በከባድ የመኪና አደጋ ካጣችበት ጊዜ ጀምሮ ባጋጠማት ሃዘን ምክንያት ነው፡ ይህን መጥፎ ውሳኔ የወሰነችው በህይወት የለችም። እኔን ግን ዛሬ  ኢየሱስ  ከሞት አድኖኛል። የሞቴን ገመድ በጥሶታል!!  ለ3 ቀናት ተመላልሼ የዳንኩበት ቤ/ክ ውስጥ የድነት ትምህርት ተማርኩ። በኋላም ጌታን መቀበሌን የሰሙ ክርስቲያን ጎረቤቶቼ ቀረቡኝ  አቅራቢያዬ ወደሚገኝ ቸርች አስፈቅጄ አብሬያቸው እንድመጣ ነገሩኝ፤ እኔም ለመጋቢዎች ነገርኳቸው ... የቀረኝን የድነት ትምህርት በሙሉ ወንጌል ቤ/ክ ውስጥ ተምሬ የውሐ ጥምቀት ወሰድኩ። የጥምቀት ስነስርዓቴ የሰርግ ያህል የደመቀ ነበር የእኔ ብትሉ የህዝቡ ደስታ ወደር አልነበረውም። ሃሌ ሉያ!!!
   እናኒ ከዚያም በኋላ መከራው በቅቷል አላለችኝም፤ ያው አንዳንድ ነገር አይጠፋም ፤ ለምሳሌ ድሮ ያውቋት የነበሩ ጎረቤቶች ከቸርች ስትመለስ ቆሻሻ ውሃ እየደፉባት  ቢያንስ 3ት ነጠላ ቀይሬያለሁ አለች! ልጆቿን እያሳደሙባትም የተወሰነ ጊዜ መከራ ቀምሳለች፤ ...እየመጡ እናታችን አዋረድሽን፣ አሸማቀቅሽን ይሏታል፤  ይህ አይነት መከራ ግን ስለ ስሙ ነው፤ ለኛ ክብር ነው! ጌታም በብዙ ሁኔታ አጽናናኝ አለች፤ በቀበሌያችን ውስጥ ከሚገኝ <ራሴድ >በሚባል ማህበር ውስጥ ታቅፌ፣ ስልጠና ወስጄ በአነስተኛና ጥቃቅን ንግድ ውስጥ ለመሰማራት 500 ብር ብድር ተሰጠኝ ፤ እየነገድኩ በወር 50 ብር አጠራቅም ነበር። ልጆቼን በግል ከፍዬ እስተማርኩ ዛሬ ሁለቱም ኮሌጅ ተመርቀዋል፤ ወንዱ ንግድ ላይ ተሰማርቷል፣ ሴቷ የማስተርስ ዲግሪ ቀጥላ እየተማረች ትገኛለች፤ እናኒ ወደ አሜሪካ ስትመጣ ከዚያች 500 ብር ተነስታ በአካውንቷ ውስጥ 60ሺህ ብር ተቀማጭ ነበራት፤ ዛሬ አብራን ጌታን እያከበረች ትገኛለች፤ መከራዋን ሁሉ ታሪክ አድርጎላታል፡፡

እናኒ ጌታ አብዝቶ ይባርክሽ! ክብር ሁሉ ለእግዚአብሔር ይሁን! እስከ ፍጻሜ ድረስም በቤቱ አጽንቶ ያቁምሽ! አሜን!

ወገኖች አሁንስ ቢሆን በየአካባቢያችን ስንት እናቶችና እህቶቻችን ገመድ ይዘው ለመሰቀል እየተንከራተቱ ይሆን?<< ወደ ወንዝ እየገባች ያለችን ነፍስ የሚታደግ ሰው አለ?>> ማንን ልላክ? ማንስ ይሄድልኛል? ይላል ዛሬም፤ ጌታ ሆይ እኔ አለሁልህ! እኔን ላከኝ! እንበል፤ ሌላ ታሪክ ይቀጥላል...

<<LET US BE WITNESSES FOR CHRIST>>

No comments:

Post a Comment