Tuesday, November 27, 2018

ኢጆሌ! ..ኢጆሌ..ነምኒ ኢንጅሩ?

ኢጆሌ! ..ኢጆሌ..ነምኒ ኢንጅሩ?
/ልጆች!..ልጆች!..ማንም የለም?/
      ♠♠♠♠♠♠
ሰሞኑን ከምስራቅ ወለጋ አካባቢ ሚድያዎችን ጭምር እያነጋገረ ስላለ ጉዳይ ሰምተዋል?አቶ ሂርጳ ነገሮ ይባላሉ ፤ አባወራ ናቸው ፤ከታመሙ ዓመታት ሞላቸው። አንዴ በንቀምት ከፍ ሲልም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጭምር ለመታከም ሞክረዋል። እምብርታቸው አካባቢ ነው የሚያማቸው፤ ምናልባት የጉበት በሽታ ይሆናል ብለው ይጠራጠራሉ። እንደውም የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ  ...ቀዶ ህክምና አድርገውም ነበር። መፍትሄ ግን አልመጣም። እናም ህመሙ ጸንቶባቸው ባለፈው ማክሰኞን ዕለትን  መሻገር ሳይችሉ ቀርተው ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ ነፍሳቸው ከስጋቸው ተለያየች። ገናዣቸው አቶ ኢታና ይህንን እውነታ አረጋግጠው ሬሳውን ገንዘው፣ ራሳቸው ባመጡት ሳጥን ውስጥ ከተቷቸው፤ ሳጥኑ ታሸገ! ከዚያም ቀድሞ በአካባቢው እንዳለው ልምድ ጥሩንባ ተለፈፈ፣ ግቢ ውስጥ ድንኳን ተጣለ ፤ ብዙ ጊዜ ወንዶች ይህን ሲያደርጉ ፣ ሴቶች ደግሞ በፊናቸው ለንፍሮ የሚሆን ስንዴና ሽንብራ ያዘጋጃሉ፤ ምስር ይለቅማሉ..ሌላም ሌላም...፤

የሰማ ሰው ሁሉ እየመጣ ከወዳጅ ዘመድ ጋር ያለቅሳል...ከሞቱ 4 ሰዐታት ቆይታ በኋላ ከሳጥን ውስጥ ኢጆሌ! ኢጆሌ...የሚል ድምጽ ይሰማል! በቅርበት የነበሩ የሟች እናትና ባለቤታቸው ፈርጥጠው ወደ ውጭ  ወጡ! ...ገሚሱም በድንጋጤ አካባቢውን ጥለው ፈረጠጡ፤ ከገናዡ ከአቶ ኢታንል በቀር መጠጋት የቻለ አልነበረም። << ኢጆሌ! ኢጆሌ! ነምኒ እንጅሩ!>> ደጋግመው ይናገራሉ፤ በኋላም ሳጥኑን ፈንቅለው ወጡ! ሁሉን ግርምት ሞላ! ..አመሻሽ ላይ ሚሪንዳ ቀማመሱና አቅማቸው ተመለሰ...የተሰበሰበ ብዙ ህዝብ ነበረና..ግማሹ እልልታ ያሰማል! ገሚሱ ያለቅሳል! አቶ ሂርጳ ጆሯቸው መስማት ጀመረ! ምንድን ነው? ብለው ጠየቁ፤ ተነገራቸው! ...ከሰዓትልት በፊት ሞተው ነበር እኮ አሏቸው፤..ለዚህም ነው ድንኳኑ፣ ለቅሶው...

የአማርኛ ጣቢያ ቢቢሲ ሞተው የተነሱትን አቶ ሂርጳንና አረጋግጠውና አስተክልክለው ገንዘው ሳጥን ውስጥ የከተቷቸውን አቶ ኢታናን ቃለ መጠይቅ አርጒልልቸዋል። በዚህ ክፍል ውስጥ ለአቶ ሂርጳ የቀረበው ጥያቄና መልሳቸው ተካቷል።  

፨ ቢቢሲ፡- አቶ ሂርጳ ከሞቱ በኃላ ምን ተመለከቱ? አቶ ሂርጳ ሲመልሱ:- ብዙ ነገር እንዲህ ነው ብዬ መግለጥ አልችልም። አንዳንዱ ተዘንግቶኛል...አሁን የማየው ያህል የሚታየኝ ግን ብዙ ነገር አለ!  ለምሳሌ አንድ በብረት ሰንሰለት የታጠረ የሚመስል፤ በርካታ ሰዎች የተሰበሰቡበት ግቢ አይቻለሁ..በሩ የሳንቃ ይሁን የብረት ትዝ አይላቸውም፤ እዚያ ውስጥ ከነበሩት ሰዎች ውስጥ ሶስቱን ብቻ ነው የማውቃቸው፤  አንደኛው የራሴ ወላጅ አባት ሲሆኑ፡ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ነው የሞቱት፤ ሁለተኛው ሰው አማቻቸው፤ ሦስተኛውም ሰው አጎታቸው ናቸው፤ እነዚህ ደግሞ ከሞቱ በርከት ያሉ ዓመታት አልፈዋቸዋል። ...ሰዎቹ ተከተለን ብለዋቸው ነበርና ሲከተሉ ሊደርሱባቸው እንዳልቻሉ ይናገራሉ እንደ ህልም ጉዞ አይነት ሆነ። ከዚህ ውጭ ግን እርስ በርስ ምን እንዳወጉ ትዝ አይላቸውም።

፨ ሌላው የማይረሱት ነገር ነጭ ልብስ የለበሰውን መልዐክ ነው..ኢየሱስን ይመስላል ይላሉ። ቢቢሲ አስረግጦ ለማወቅ ያዩት መልዐክ ጥቁር ነው? ቀይ? አላቸው፤ አቶ ሂርጳ ሲመልሱ  ቀይ መልዐክ ነው ፤ ነጭ ልብስ ግን ለብሶ ነበር አሉ።

፨ ቢቢሲ፡- ፊቱስ ምን ይመስል ነበር? የሰው ወይስ የመልዐክ? አላቸው።
አቶ ሂርጳ:-በእርግጥ ፊቱን በደንብ አላየሁትም። እኔ ውጭ ነበርኩ፤ እርሱ ደግሞ በውስጥ በኩል ቆሞ ነበር...ሰዎችንም ወደ ውስጥ አስገባና ይዟቸው ሄደ!

፨ ቢቢሲ ቀጠለና ሌላ መልዐክ አጠገቡ አልነበረም? አቶ ሂርጳ መለሱ አላየሁም! እርሱን ብቻ ነው ያየሁት።
ምን አለዎት?
አቶ ሂርጳ "አንተ የት ትሃልዳለህ? ተመለስ አለኝ።
በምን ቋንቋ አናገረዎት? በኦሮምኛ ነዋ!
አልፈሩም? በፍጹም! ክልከላውን/ኬላውን አልፌ መሄድ አምሮኝ ነበር ..ነገር ግን ውስጥ አልፎ ለመግባት አቅም አልነበረኝም!

፨ ቢቢሲ ወደ ምድር በመመለስዎ ቆጨዎት እንዴ?
አቶ ሂርጳ:- እዚያው ብሆን ደስ ይለኝ ነበር። አሁንም ግን ከቤተሰቤ ጋር ተመልሼ ስለተቀላቀልኩ ቅር አላለኝም።

፨ ቢቢሲ:- ከዚህ በኋላ በቀሪው ዘመንዎ ምን ማድረግ ያስባሉ?
አቶ ሂርጳ:- ከዚህ በኋላ የኃይማኖት ትምህርት በመስጠትና ሰዎችን በማስታረቅ ጉዳይ ላይ ተግተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
(ምንጭ:- BBC Amharic  Nov.23 2018)

♥ ከሞት በኋላ ህይወት እንዳለ እሙን ነው። ሰዎች ወይ የዘላለምን ህይወት፤ አልያም የዘላለምን ሞት ሊወርሱ የሚችሉበት ሁለት ዕድሎች አሏቸው፤ ሲኦልም ሆነ መንግስተ ሰማይ ዘላለማዊ ቦታዎች ናቸው። አማኞች (ሁላችንም) የክርስቶስን ወንጌል ለሰዎች ሁሉ በመመስከር፡ ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ንስሐ እንዲገቡና ከወዲሁ ምርጫቸውን እንዲያስተካክሉ እንድንተጋ አደራ እላለሁ። አቶ ሂርጳ ብቻ ሳይሆኑ እኛ ሁላችንም ወንጌልን እናስተምር! የተጣሉትን እናስታርቅ!!
------------
" እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ።
እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።"
                           2ኛ ቆሮ.5 ቁ 19ና 20

                 ♠♠♠♠♠♠♠
<< LET US BE WITNESSES FOR CHRIST! >> 

No comments:

Post a Comment